የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ——- ማክሰኞ ታኅሳስ 1 / 2006 ዓ/ም
ይቅርታ በደልን ለመርሳት የሚደረግ ሙከራ፣ ወይም ሰውዬውን መርሳት አይደለም፡፡ ይቅርታ ለበደለኛው የማይገባውን መስጠት ማለት ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የታረቅንበት ምሥጢሩ ይህ የማይገባን ደግነት ነው፡፡ ለሰማያዊው አባት ያለንን ፍቅር ልንገልጥ የምንችለው እርሱ የፈጠራቸውን ሰዎች በመውደድ ነው፡፡ እግዚአብሔር ያሳየንን ፍቅር እኛም ለጎረቤታችን ማሳየት ይገባል፡፡ እግዚአብሔር የጠፋውን ዓለም በእኛ ውስጥ ሆኖ ሊወደው ይፈልጋል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ አስደናቂ ይቅርታ ስላሳዩ ሰዎች እናነባለን፡፡ ከእነርሱም ሦስቱን በዚህ ክፍል ለማየት መርጠናቸዋል፡፡ እነርሱም አዳም፣ ዮሴፍና የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች ናቸው፡፡
አዳም በሚወዳትና በሚያዳምጣት ሚስቱ አማካይነት በኃጢአት ወደቀ፡፡ ጸጋው ተገፈፈ፣ ነጻነት የሌለው ሰው ሆነ፣ ፍርሃትና ሽሽት ከማያመልጠው ማንነት ጋር ገጠመው፡፡ ምክንያትም ሳያስጥለው የዘላለም ሞት ተፈረደበት፡፡ በሥጋ ሞት ላይ የነፍስ ሞት፣ ወደ መቃብር በመውረድ ላይ ወደ ሲኦል መውረድ ተፈረደበት፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ እግዚአብሔር ተለየው፡፡ አዳም የሚስቱን ዓይን ላለማየት ቢወስን፣ ቢሸሻትና እርሷን ይቅር ለማለት ቢፈተን ማንም አይፈርድበትም፡፡ እርሱ ግን ፍጹም ይቅር ባይ ነበርና ያን የማይገባ ደግነት አሳያት፡፡ ሞትን ላመጣችበት ሴት «አዳምም ለሚስቱ ሔዋን ብሎ ስም አወጣ፣ የሕያዋን ሁሉ እናት ናትና» (ዘፍ3፡20)፡፡
ሔዋን አሁን ሕያው አይደለችም፡፡ ሙታንም ከእርሷ ይወጣሉ፡፡ ነገር ግን አዳም የአሁኑን ሳይሆን የተስፋዋን ፍጻሜ አየ፡፡ የሆነችውን ሳይሆን ልትሆን ያላትን አሰበ፡፡ ስለዚህ የሕያዋን እናት አላት፡፡ ለወደቁት ሰዎች የመነሣት ጉልበታቸው ዛሬም በእነርሱ ላይ ያለን እምነት ነው፡፡ ምን እንደሚሆኑ ያለን ተስፋ አንድ ቀን ራእያቸው ይሆናል፡፡ «የወደቁ ሰዎች የተዘረጉ እጆችን ይፈልጋሉ፡፡»
ጋብቻ እንደ አዳምና እንደ ሔዋን ነው፡፡ ውድቀት ያልፈታው ትዳር የእነዚህ ወገኖች ትዳር ነው፡፡ ዛሬ ብዙዎች ትዳራቸውን ይቅር ማለት አልቻሉም፡፡ ስለ ንብረታቸውና ስለ
ልጆቻቸው እያዘኑ ይኖራሉ፡፡ ዘይቱ እንዳለቀበት መቅረዝ ፍቅር አልቆባቸው ጨልመዋል፡፡ ተዋደው የገቡ ሳይሆን በፍርድ ቤት ትእዛዝ የተጣመሩ እስኪመስል መሸካከም አልቻሉም፡፡ ብዙ ጊዜም አንዳቸው በመንፈስ ጭንቀት ሲያዙ የጠባይ ለውጥ እየመሰለ ይበልጥ ይከፋፋሉ፡፡ የትዳር ጓደኛ መነጫነጭ፣አለመርካት፣ የትዳር ውሳኔውን መርገም፣ ልጆቹንና የትዳር ጓደኛውን ማየት ሲጠላ . . . የጠባይ ለውጥ ብቻ ላይሆን ይችላልና መመርመሩ መልካም ነው፡፡ በትዳር ውስጥ ትልቁ ጉዳትም ስህተትን የሚፈልግ ዓይን በመሆኑ ከዚህ መትረፍ ያስፈልጋል፡፡ በየዕለቱ ከምንሞላው ኃይል አንዱ ፍቅር ነውና ስንጎድልና ማፍቀር ሲያቅተን በጸጋው ዙፋን ፊት ወድቀን ሙላኝ ልንል ይገባል፡፡
ልጆቻቸው እያዘኑ ይኖራሉ፡፡ ዘይቱ እንዳለቀበት መቅረዝ ፍቅር አልቆባቸው ጨልመዋል፡፡ ተዋደው የገቡ ሳይሆን በፍርድ ቤት ትእዛዝ የተጣመሩ እስኪመስል መሸካከም አልቻሉም፡፡ ብዙ ጊዜም አንዳቸው በመንፈስ ጭንቀት ሲያዙ የጠባይ ለውጥ እየመሰለ ይበልጥ ይከፋፋሉ፡፡ የትዳር ጓደኛ መነጫነጭ፣አለመርካት፣ የትዳር ውሳኔውን መርገም፣ ልጆቹንና የትዳር ጓደኛውን ማየት ሲጠላ . . . የጠባይ ለውጥ ብቻ ላይሆን ይችላልና መመርመሩ መልካም ነው፡፡ በትዳር ውስጥ ትልቁ ጉዳትም ስህተትን የሚፈልግ ዓይን በመሆኑ ከዚህ መትረፍ ያስፈልጋል፡፡ በየዕለቱ ከምንሞላው ኃይል አንዱ ፍቅር ነውና ስንጎድልና ማፍቀር ሲያቅተን በጸጋው ዙፋን ፊት ወድቀን ሙላኝ ልንል ይገባል፡፡
ሌላው የተደነቀ የይቅርታ ሕይወት የሚታየው በዮሴፍ ላይ ነው፡፡ ዮሴፍ ከወንድሞቹ ይልቅ አባቱ ይወደው ነበር፡፡ ምንም ባይበድላቸው መወደድም የመጠላት ምክንያት ይሆናልና ወንድሞቹ ጠሉት (ዘፍ. 37፡4)፡፡ ዮሴፍ ሕልሙን በነገራቸው ጊዜ ደግሞ ወደፊት ይሆናል የሚሉትን ነገር ሲያስቡ በቅንዓት አበዱ፡፡ በበረሃ እየተቅበዘበዘ ሲፈልጋቸው እነርሱ ግን ሊገድሉት ተማክረው በጉድጓድ ጣሉት፡፡ የግብጽ ነጋዴዎች ሲያልፉ አይተውም በሃያ ብር ሸጡት፡፡ በጉስቁልና ከሕልሙ ያራቁት መስሏቸው ይበልጥ ወደ ሕልሙ ትርጓሜ ገፉት፡፡ «መገፋት ጥሩ ነው እምብዛም ሳይወድቁ፣ የተገፉት ቆመው የገፉት ወደቁ፤»
ዮሴፍም ገና በልጅነቱ ብርቱ መከራ ደረሰበት፣ በባዕድ አገር በአገልጋይነትና በእስር ተንገላታ፡፡ በኃጢአት አልተባበርም ማለት በዓለም ያስቀጣልና አሥራ ሦስት ዓመት ተቀጣ፡፡ ነገር ግን ይህ ጠባብ መንገድ ወደ ሰፊው ጎዳና የሚያወጣ ነበር፡፡ ዮሴፍ ከእግዚአብሔር የተሰጠውን ራእይ የጠላትነት ብዛት ሊያሸንፈው አልቻለም፡፡ እንደውም ጠላቶቹ ወደ ራእዩ እንዲደርስ ያቻኩሉት ነበር ፡፡ አንድ ሰው «እግዚአብሔር ታላቅ በረከት እንዳዘጋጀልኝ ቀድሞ የሚነግረኝ ሰይጣን ነው፡፡ ይተነኳኮለኛል» ብሏል፡፡
ዮሴፍ የግብፅ አገር ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነ፡፡ እግዚአብሔር ያለው አይቀርምና ወንድሞቹ ሰገዱለት፡፡ በከነዓን ምድር ረሃብ እያሯሯጠ ወደ ግብጽ አመጣቸው፡፡ ዮሴፍ አወቃቸው እነርሱ ግን አላወቁትም፡፡ ራሱን በገለጠላቸው ጊዜ በጭንቀት ተናጡ፡፡ በልባቸው ሌላውን ከመበደል ራስ መበደል ይሻላል ሳይሉ አልቀሩም፡፡ የዮሴፍን ፊቱን ማየት አልቻሉም፡፡ እርሱ ግን አልበደላቸውምና ፊታቸውን አየ፡፡ መልካምነት ሥልጣን ካልሆነን በቀር የማንንም ፊቱን ማየት አይቻለንም፡፡
ዮሴፍ አሁን ሊበቀላቸው ይችላል፡፡ እነርሱም ፈርተው ነበር፡፡ ዮሴፍ ግን እግዚአብሔር ክፉውን ለውጦ ለመልካም እንዳደረገው ስለተረዳ ይቅር አላቸው፡፡ ምንም ክፉ ቢያደርጉበትም ወደ ተስፋው እንዳቀረቡት ተረዳ፡፡ እግዚአብሔር አንዳንዴ እምነታችን እንዲያድግ በክፉ ሰዎች መካከል ያስቀምጠናል፡፡ እንድንጠነክር ታዝዘው መከራ ያደርሱብናል፡፡ ታዲያ ከንጉሡ ታዝዞ ሎሌው አርባ ቢገርፈን እንቀየመዋለን? ከሰዎች ጋር መታገል ከንቱ ነው፡፡
ዮሴፍ መበቀል እየቻለ አልተበቀላቸውም፡፡ በቀል የእግዚአብሔር፣ ይቅርታ የእርሱ መሆኑን ተረዳ (ዘፍ.50፣19-20)፡፡ ሕጋዊ መንግሥት ባለበት አገር የበደለንን ሰው ራሳችን ብንቀጣ መንግሥትን እንደካድን ይቆጠራል፡፡ እንዲሁም በጽድቅ የሚፈርድ አምላክ እያለ እኛ ተበቃይ ብንሆን እግዚአብሐርን ክደነዋል ማለት ነው (ሮሜ.12፣19-21)፡፡ አዎ የእግዚአብሔር ሰዎች በእግዚአብሔር ቦታ ሆነው የነገሮችን አካሄድ መለወጥ እንደማይችሉ ሲረዱ እግዚአብሔርም ለእነርሱ ነገሮችን ወደ በጎ የሚለውጥ መሆኑን ያምናሉ፡፡ ዮሴፍ ቢበቀል ኖሮ ከእግዚአብሔር ጋር በተጣላና ያን ክብር ባላገኘ ነበር፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ እግዚአብሔር የአገር መሪዎችና ባለሥልጣናት የይቅርታ ሰዎች እንዲሆኑለት ይፈልጋል፡፡ የበለጠ ኃላፊነትን ለመሸከም እግዚአብሔር ይቅር ባዮችን ያጫል፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ የምናየው ሦስተኛው የይቅርታ ሕይወት የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች ያደረጉት ነው፡፡ ወጣቱ ሰማዕት እስጢፋኖስ የሞተው በአሁኑ ጳውሎስና በግብረ አበሮቹ በድንጋይ ተወግሮ ነው፡፡ እስጢፋኖስ ግን «ጌታ ሆይ፡ ይህን ኃጢአት አትቊጠርባቸው» እያለ ጸለየላቸው፡፡ ይህንን ጸሎት የጸለየው «የእግዚአብሔርን ክብር ኢየሱስንም» ካየ በኋላ ነው (የሐዋ.ሥራ.7፣55-60)፡፡ ክርስቶስን ስናይ ብቻ ልባችን ለይቅርታ ይለዝባል፡፡ ከወጋሪዎቹ አንዱ ጳውሎስ የድሮው ሳውል ክርስቲያን ሆነ፡፡ ጳውሎስ የእስጢፋኖስ የይቅርታ ጸሎት ልቡን ነክቶታል፣ ወይም ልብን የሚነካ ጸጋ አምጥቶለታል፡፡
ይህ ጳውሎስ ያውም ለትምክሕት «የእስጢፋኖስንም ቤተ ሰዎች ደግሞ አጥምቄአለሁ ጨምሬ ሌላ አጥምቄ እንደሆነ አላውቅም» (1ቆሮ.1፣16) ማለቱ ያስገርመናል፡፡ እኛ ይቅር ብንል
እንኳ ቤተሰብ በቶሎ ይቅር አይልም፡፡ ቤተሰብ ስለልጅ መቀየም ጽድቅ ነው የሚመስለው፡፡ የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች ግን በልጃቸው ገዳይ በጳውሎስ እጅ መጠመቃቸው የይቅርታን ጽኑነት ያሳየናል፡፡
እንኳ ቤተሰብ በቶሎ ይቅር አይልም፡፡ ቤተሰብ ስለልጅ መቀየም ጽድቅ ነው የሚመስለው፡፡ የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች ግን በልጃቸው ገዳይ በጳውሎስ እጅ መጠመቃቸው የይቅርታን ጽኑነት ያሳየናል፡፡
እኛ ገንዘብ የካዱንን ይቅር ማለት ሲያቅተን አዳም ገነትንና እግዚአብሔርን ያሳጣችውን ሔዋንን ይቅር አላት፡፡ ዮሴፍ ልጅነቱን ለመከራ እቶን የዳረጉት ወንድሞቹን በበቀል ሳይሆን በይቅርታ አሸነፋቸው፡፡ የእስጢፋኖስ ቤተሰቦች ደም መላሽ ቢሆኑ ኖሮ ጳውሎስን በመልእክቱ ዛሬ አናገኘውም ነበር፡፡ ይቅርታ ለትውልድ የምናቆየው ውለታ ነው፡፡ በእርግጥም ይቅርታ የማይገባንን በሰጠን በእግዚአብሔር ፊት ሰውዬው የማይገባውን መስጠት ነው፡፡