የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ደህና ነው /3

ብዙ ሰው እግዚአብሔር ወደ ቤቴ ቢመጣ እቀበለዋለሁ ብሎ ያስባል ። እግዚአብሔር ግን በፍቅሩ ወደ ልቡ ፣ በአገልጋዮቹ ወደ ቤቱ ሲመጣ እየገፋ የሚኖር ነው ። በአገልጋዮቹ በኩል የልባችንና የቤታችንን ደጃፍ ሲፀፋ የከፈተ የለም ። አንዳንዱ ሃምሳ ዓመት ፣ ሌላውም ሃያ ዓመት እግዚአብሔርን በደጁ አቁሞታል ። ግን እግዚአብሔር መጥቶ እግዚአብሔርን ይጠብቃል ። እግዚአብሔር በክብሩ ቢመጣ እንኳን የእኛ ቤት የሰሎሞን መቅደስም አይችለውም ፣ እንኳን የሰሎሞን መቅደስ ሰማየ ሰማያትም አይችሉትም /1ነገሥ. 8 ፡ 27/ ። እግዚአብሔር ግርማዊ ሁኖ ሳይሆን በግፍ ባዘነ ሰው አምሳያ ይመጣል ። በእውነት ዳኛው ክርስቶስ ከፍትሕ ፈላጊው ጋር መጥቶ ፈርዶበታል ። ሐኪሙ ክርስቶስ እያቃሰተ በቸልታ አልፎታል ። እግዚአብሔር ወርቀ ዘቦ ግምጃ በሚነጠፍላቸው ሳይሆን የክረምቱ ብርድ ፣ የሌሊቱ ቁር በሚያሰቃያቸው ሰዎች መልክ ይመጣል ። ያቺ የሱነም ሴት እግዚአብሔር ከአገልጋዮቹ ጋር እንዳለ ፣ በሰማይ እንዲቀበላት እርስዋም በምድር ልትቀበለው እንዲገባት ተረድታለች ። ነቢይን መቀበል የነቢይን ዋጋ ማግኘት እንደሆነ አውቃለች ።

አንድ ቤት በአንድ ባለሙያ ብቻ አይሠራም ። ንድፍ ነዳፊ ፣ ቀያሽ ፣ ቆፋሪ ፣ ግንበኛ ፣ አናጢ ፣ ለሳኝ ፣ ቀለም ቀቢ ፣ የመብራትና የውኃ መስመር ዘርጊ ፣ የጽዳት ሠራተኛ ፣ የእንጨትና የብረት ባለሙያ ፣ የዕቃ ተሸካሚ … ትብብር አንድን ቤት ፣ ቤት ያሰኙታል ። የእግዚአብሔር ቤትም በአንድ አገልጋይ ምኞትና ጥረት ብቻ አይገነባም ። በሁሉም ትብብር የእግዚአብሔር ቤት ይታነጻል ።

ያቺ የሱነም ሴት ልቧ ባላጋራ ሁኖባት በልቧ አደባባይ ከሰሳት ። ልቧም ዳኛ ሁኖ ፈረደባት ። ልቧን ተጋፍታ ከልቧ ጋር መኖር እንደማትችል ገባት ። ያልተሠሩ ሥራዎች ፣ ያልተከወኑ በጎ አድራጎቶች ሁሉንም የሕይወት ክፍል ይዋጋሉ ። ስለዚህ ለእግዚአብሔር ሰው በቋሚነት የሚያርፍበት ቤት ለመሥራት ፣ ሙሉ ዕቃ ለማስገባት ወሰነች ። በዘመኑ ሁሉ ቀለብ ልትሰፍርለት በልቧ ቃል ገባች ። የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆነው ነቢይ ኤልሳዕ ደወል ሳይደወል የሚነቃ ፣ የሰዓት ፊርማ ሳይኖር የሚሠማራ ፣ የተከለለ ቦታ ሳይኖር መላውን አገር የሚያገለግል ነው ። ወደ ሥራ ለመሄድ አንዳንድ ሰው ደወል ያነቃዋል ፣ ሌላውንም ቤተሰቡ ይቀሰቅሰዋል ። አንዳንዱን የአለቃው ቍጣ ፣ የሰዓት ፊርማ ፣ ቀሪውን ቅጣት ያነቃዋል ። የእግዚአብሔር አገልጋዮች ግን የእርሱ ፍቅር ብቻ ያነቃቸዋል ። ይህች የሱነም ሴት ሰገነቷ ላይ ቆማ የእግዚአብሔርን ሰው ስትጠብቅ የዛሬ ሥራዋ አልተከናወነም ። ልብ በአሳብ ከተያዘ ሥራ መሥራት አይቻልም ። ለውጤታማ ሥራ ልብ መፈታት አለበት ። ሲመጣ እንዴት ወደ ቤቴ ግባ እለዋለሁ ብላ ናፍቆት ፣ ጉጉት ፣ ፍቅር ወጥሮ ይዟታል ። ርስትን እንደ ልጇ ልትሰጠው ፣ ቤት ሠርታ ልታሳርፈው ፣ ቀለብ ሠርታ ልትንከባከበው ወስናለች ። ይህን ውሳኔዋን የምታሳውቀው ዛሬ ነው ። ይህች ቀን እንዳለፉት ዘመናት በከንቱ አታልፍም ። የእግዚአብሔርን ቤት ለሚሠራው ቤት ልትሠራለት ቆርጣለች ።

ይህች የሱነም ሴት የአሳብ ልዕልናዋ የተደነቀላት ሴት ነች ። ሁሉም ዝም ብሎ እኔ ምን አገባኝ  የአገር ዕዳን ብቻዬን እንዴት እሸከማለሁ  ብላ ከራስዋ ጋር አልተማከረችም ። ከአመክንዮ እምነት እንደሚበልጥ አውቃለች ። ሌሎችንም ላስተባብር አላለችም ። ማስተባበር ብትጀምር እስከ ዛሬ አሳምና አትጨርስም ነበር ። ዛሬ በደረቁ የሚላጩ ፣ ሳያበሉ አገልጋዮች ላይ የረሀብ ሰይፍ የሚስሉ ፣ እኔ ጠልቻለሁ እናንተም ጥሉ ለማለት የሚተጉ ብዙዎች ናቸው ። ፍጻሜአቸው ግን ያማረ አይደለም ።

የእግዚአብሔር ሰው ኤልሳዕ ነገሮች እንደ ትላንቱ ቢሆኑም እግዚአብሔር ግን አዲስ ነው እያለ በሰማይ ዝማሬ ተመስጧል ። የሚያስደስት ነገር ሳይሆን ራሱ ደስታ ተቆጣጥሮታል ። እርሱ ተኝቶ የሚያስብለት እንዳለ ቢያምንም ዛሬ እንዲህ ይሆናል ብሎ አላሰበም ። ትላንት ቤት ጥሎ የወጣ ስለ እግዚአብሔር ቤት አልባ የሆነ ፣ ባለጠግነትን ትቶ በፈቃዱ ድሀ የሆነ ሰው ነው ። ነገሮች አልሳካ ስላሉት ሳይሆን ስኬትን ሠውቶ እግዚአብሔርን የሚያገለግል ነው ። ይህች ሴት መላውን ሱነምን ወክላ ተቀበለችው ። ሱነማውያን አልወከሏትም ። በእርስዋ ደግነት ግን አገሩም ሲወደስ ፣ ሲሰበክ ይኖራል ። በአንድ ቅዱስ አገር ይከበራል ። በሱነም አንዲት ታላቅ ሴት ነበረች ይላል ። /2ነገሥ. 4፡8 /። ታላቅነት ብዙ መስፈርቶች አሉት ። ይህች ሴት ግን በመንፈሳዊ መመዘኛ ትልቅ ሴት ነበረች ። የመጀመሪያው ትልቅነቷ በዚያ ምስኪን አገልጋይ ውስጥ ትልቁን እግዚአብሔር ማየቷ ነው ። ኤልሳዕ ወደ ቤቷ ደጃፍ ሲቃረብ በጎዳናው ላይ ወጥታ እንጀራ ይበላ ዘንድ ግድ አለችው ። ኤልሳዕ በብዙ ታገላት ፣ የሚጽናኑ ብዙ ሰዎች እየጠበቁኝ ነው ። መቸገራቸውን እንኳ የማያውቁ ሰዎች ከፊት ባለው መንደር አሉ ተይኝ ቢላት እርስዋ ግን እኔን ረግጠህ ሂድ እንጂ በጅ አልልህም አለችው ። ኤልሳዕ የምትናገረው በስሜት ፣ ደግሞም ለዝና ሳይሆን በእምነት መሆኑን አስተዋለ ። እንደ እግዚአብሔር ግብዣም ተቀበለው ። ሰው አልቋል ፣ ክብራችንም ቀርቷል የሚለውን መደምደሚያ እንደገና አሰበው ። ይህች ሴት እንጀራን ብቻ ሳይሆን ተስፋንም ዘርግታ የተቀበለችው ሴት ናት ። ገና ሰው አለ እንዲል ያደረገችው ፣ ሞቶ ከማገልገል የጠበቀችው ሴት ናት ። እግዚአብሔር አንዱን ላንዱ መጽናኛ አድርጎታል ። ይህች ሴት የብዙ ጥያቄዎች መልስ ናት ። ጥያቄ የሚፈጥሩ ሰዎች ባሉበት ዓለም መልስ ሆኖ መዘጋጀት እንዴት ድንቅ ነው ። ሰዎች ስለ እኛ እግዚአብሔርን ሲያመሰግኑ በረከታችን ፣ ተስፋቸውን ሲቀጥሉ ሕይወታችን ይለመልማል ።

ኤልሳዕን ቤት ልሥራልህ ብላ አልጀመረችም ። መጀመሪያ አክብሮቷን ገለጠች ። በአክብሮቷ ሲተማመን እንጀራ አቀረበች ። ይህች ሴት ግን በዚህ የምትረካ ሴት አልነበረችም ። ጥቂት ሰጥታ ብዙ የምታወራ ፣ አደረግሁ ለማለትም የምትቸር አልነበረችም ። ውዳሴ ከንቱ የተገረዘላት ፣ የእስራኤል አምላክ የሰጠኝን የምሰጥ ነኝ ብላ የምታምን ሴት ናት ። እግዚአብሔርን የማይፈራ ሰው ሲሰጥ ያሳቅቃል ። ሣንቲም ሰጥቶ ሰብእናን ይወስዳል ። ስጦታዋ እንደ እግዚአብሔር ወንዝ በቀስታ ፣ በውበት የሚወርድ ነበር ። ሆድ ሞልቶ ሕሊናን ማራቆት እንዳይኖር ትጠነቀቅ ነበር ።

የሱነም ሴት ለኤልሳዕ ያሰበችውን አሳብ መጀመሪያ ከባሏ ጋር መምከር ነበረባት ። በዚህም ትዳሯን ያሳመነች ፣ ባሏን በበጎ ተግባር ያሰለጠነች ናትና ትልቅነቷ የታወቀ ነው ። ባሏ የሚተማመንባት ፣ ምንም ብታደርግ ትክክል ናት ብሎ የሚያምናት ቢሆንም እርሱም ይባረክ ዘንድ አማከረችው ። “ይህ በእኛ ዘንድ ሁልጊዜ የሚያልፈው ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆነ አውቃለሁ ። ትንሽ ቤት በሰገነቱ ላይ እንሥራ በዚያም አልጋ ጠረጴዛ ወንበርና መቅረዝ እናኑርለት ወደ እኛም ሲመጣ ወደዚያ ይገባል አለችው ።” ይህች ሴት ጠልቃ የማየት አቅም የነበራት ሴት ናት ። ኤልሳዕ ቅዱስ ሰው መሆኑን ደግሞም ርካሽ ዓላማ የሌለው የእግዚአብሔር ሰው መሆኑን ተገንዝባለች ። ትልቅነቷ አርቃ ማየቷ ፣ ትልቅነቷ ለእግዚአብሔር ያደረውን ሰው መለየቷ ነው  ። ይህች ሴት የስጦታ ልቡ አላት ፣ አቅምም አላት ። አቅም ኖሯቸው ልቡ የሌላቸው ብዙዎች ናቸው ። ልቡ እያላቸው አቅም ያጠራቸውም አሉ ። ይህች ሴት ትልቅ ሴት ናትና ሰገነት ላይ ቤት ለመሥራት አሰበች ። ከፍ ያለ ቅዱስ ሰው ነውና ከፍ ያለ ቤት ተመኘች ። ታች ከሆነ በእኛ ድምፅ ይረበሻል ብላ አሰበች ። ቤታችን ብናስገባው በእኛ ላይደሰት ይችላል ፣ ሁከታችን ያውከዋል በማለት አጤነች ። በርግጥም ትልቅ ሰው ነበረች ። ዛሬ አንድ ሰገነት ላይ ትንሽ ቤት ለመግዛት በሚሊየን የሚቆጠር ብር ይፈስሳል ። ይህች ሴት ለእግዚአብሔር ሰው ለኤልሳዕ አሰበችለት ።

ቤት አልባ ብንሆንም ደህና ነው ። ቤት የሌለው ዜጋ ነኝ ማለት አይችልም የሚል ወሬ ቢወራም የማይፈርስ ቤት በሰማይ ይጠብቀናል ። እግዚአብሔርን ብቻ እንደ ተሰጠን ጸጋ ስናገለግል የእኛን ሸክም የሚሸከሙ ሰዎች ይዘጋጃሉ ። በእውነት ካለፈው የተሻለ ነው ። የዛሬም ቀን አዲስ ነው ። አዎ ደህና ነው ። ደህና ነው ስንል ማመስገናችን ነውና ይጨመርልናል ። በትንሹ ስንታመን በብዙ ይሰጠናል ። እኛ ብንተኛም እግዚአብሔር ለአገልጋዮቹ ይነቃል ። አዎ ደህና ነው ።

ይቀጥላል

ደህና ነው /3
ሰኔ 17 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ