የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ደህና ነው /5

ወረኞች ጥንትም ነበሩ ፣ ዛሬም አሉ ። ወረኞች ማለት የወሬ ጥማት ያላቸው ፣ ካላወሩ የሚሞቱ የሚስላቸው ፣ የሰሙትን ምሥጢር መቋቋም አቅቷቸው እንደ ወንፊት የሚያፈስሱ ፣ የጠባያቸው ቀላልነት የሰሙትን መሸከም አቅቷቸው ኧረ ልፈነዳ ነው ? የሚሉ ፣ እንደ ዝንብ በካይና በሽታ አምጪ ነገርን የሚያመላልሱ ፣ የሐሜት ፈረሶች ፣ የሰብቅ ሠረገላዎች ፣ የሰውን ንስሐ የማይቋጥሩ ፣ የሰሙትን ሽሽግ ነገር የሚያሰሙ ፣ እሺ – ይገርማል – ቀጥሎስ በሚሉ ቃላቶች ነዳጅ የሚሰጡ ፣ ነፋስ የሚያመርቱ ናቸው ። ወረኞች ብዙ ዓይነት ሲሆኑ ጥቂቶቹን ግን ማየት እንችላለን፡-

1- የስለላ ጓዶች፡-

የስለላ ሠራተኞች ያስወራሉ እንጂ አያወሩም ። እነዚህ ሰዎችም ሲመረጡ መጠጥና ዝሙት የማይወዱ መሆናቸው ተረጋግጦ ነው ። የስለላ ሠራተኞች አንድ አውርተው መቶ ይቀበላሉ   ። የሚመርጡት ሥራም ማንም ሰው ልብ የማይለውን ነው ። ሰው እንደ ቀላል የሚያያቸው ሰዎችና ቦታዎች ለስላላ ተመራጭ ናቸው ። እነዚህ ሰላዮች የሚከፈላቸው ወረኞች ናቸው ። አገራቸውንና መንግሥታቸውንም የሚጠብቁ ናቸው ። እነዚህ ወሬ ለቃሚዎች ፣ ነጭ ለባሾች ፣ ጆሮ ጠቢዎች የሚያዩትን ሰው ሁሉ አንድ መረጃ አያጣም ብለው ያስባሉ ። ወሬ በዚያ ዓለም መረጃ ይባላል ። የዳቦ ስም መሆኑ ነው ። ከየአቅጣጫው የሚቃረመው ወሬ የሚወቃበት ውድማ አለ ። እርሱም የደኅንነት ተቋም ነው ።

2- ሥራ ፈቶች፡-

ሥራ የሌላቸውና ሥራ ፈቶች ልዩነት አላቸው ። ሥራ የሌላቸው ዕድሉን ያላገኙ ፣ ሁሉም ስፍራ በዘመድ ተይዞ በር የተዘጋባቸው ምስኪኖች ናቸው ። “የሚበላና የሚወራ አይታጣም” እንዲሉ ለቀኑ የሚሆን አንድ ወሬ ካላገኙ የሚንቀዠቀዡ ፣ እገሌ ማለት እንጂ እኔ ማለት የማይችሉ ፣ የሐሜት ዕድር አቋቁመው ፣ እንደ እነርሱ የበታችነት ስሜት የሚያደቃቸውን ሰዎች ይዘው የሚሳደቡ ወረኞች ሥራ ፈቶች ናቸው ። እነዚህ ወረኞች በየትኛውም አገርና የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ናቸው ። ማሰብ የማይፈልጉት ነገር ያላቸውና ሥራ መሥራት የማይወዱ ናቸው ። ልጆችን በሥርዓት አለማሳደግ እገሌ ምን አለ ? እያሉ በልጅነታቸው ወሬ ለቃሚ ማድረግ ፤ አባትሽ ምን ሲሠራ ነበር ?  እናትሽ ምን ስታደርግ ነበር ? እያሉ በከረሜላ ጉቦ መጠየቅ የወሬ ሠራዊትን ማፍሪያ ነው ።

3- ሹመት ፈላጊዎች፡-

በአገራችን በሙያ ሳይሆን በፖለቲካ ተሳትፎ ሹመት ይቸረቸራል ። በዘር ተዋጽኦም መሾም የተለመደ ነው ። በድልድል ቀዶ ጥገና ላይ ሰው ባይመደብም ቀዶ ጥገና የሚሠራውን ሐኪም የሚያውኩ የፖለቲካ ሹመኞች ግን አሉ ። ባለሙያዎች ሙያ በሌላቸው ወረኞች እየታወኩ የሚኖሩባት ምድር ናት ። በአፍሪካ ሥልጣን ሕይወትና ሥራ ነው ። አንድን ሰው ሥልጣን ልቀቅ ማለት ሕይወትህን አስቀምጥ ፣ ሥራህን ተው እንደ ማለት ነው ። ስለዚህ ያለውን እሳት ሁሉ ያዘንባል ። ተናገር ብሎ ፈቅዶ ሲናገሩ ያኮላሻል ። ሥልጣን ቀናተኛ ባሎች በዝተውባት አንለቅሽም ፣ አብረን እንሞታለን ይሏታል ። በቤተ ክህነትም ምሥጢር መጋቢ እየተባሉ ወረኞች ይሾማሉ ። ባይማሩም ፣ ሙያ ባይኖራቸውም ከተማረውና ከባለሙያው በላይ የሚኖሩት ወረኞች ናቸው ። በዚህ ምክንያት አዛኝ መሳይ ፣ ያልቆሸሸ ቀሚስ የሚያራግፉ ፣ ለአንድ እንጀራ የሚልከሰከሱ ፣ ቀኑን በሙሉ እንደ ወፍ ወሬ ሲለቅሙ ውለው ለሚጠብቋቸው አባቶች የሚተነፍሱ አያሌ ናቸው ። እንዳይሳደቡ ተብለው ያለ ሥራ የሚከፈላቸው ፣ ተሳደቡልን ተብለውም የሚከፈላቸውን ሰዎች እያፈላን ነው ። የወረድንበት ዝቅጠት ከባድ ነው ።

4- የወሬ ተዋጊዎች፡-

ከቦታቸው ሳይነሡ ደረስን የሚሉ ፣ አንድ ጠመንጃ ይዘው ተዋጊ አውሮፕላን ይዘናል የሚሉ ፣ ከአደጋ ጣዮች በላይ ወሬ እየጣሉ አገር የሚያምሱ ብዙዎች ናቸው ።  ጦር ካስበረገገው ወሬ ያስበረገገው የሚባለው ለዚህ ነው ። “ከሺህ ጦረኛ አንድ ወረኛ” የሚባለውም በምክንያት ነው ። እነዚህ የፕሮፓጋንዳ ሠራዊት ሌላው ሲታወክ በሰላም የሚተኙ ናቸው ። ይህን ሙያ ብለው የሚሠሩ አሉ ። እንዲሁም ውስጣቸው እየጮኸባቸው የሚጮኹ ሰዎችም አሉ ። እነዚህ ወገኖች ሰው እንደ ጤነኛ ቆጥሯቸው ይሰማቸዋል ። ብዙ መታከም ያለባቸው ወረኞች አሉ ።

5- ተበቃይ ወረኞች፡-

ከበቀል መንገዶች አንዱ ወሬ ነው ። ያንን ሰው ከሰዎች ሕሊና እንዲወጣ ስለ እርሱ ክፉ መናገር አንዱ የበቀል መንገድ ነው ። ይህ መንገድ ግን የሚሰማው ሰው እንዲፈራንና እንዲሰጋን ያደርጋል ። ለእኔም እንዲህ ነው በማለት ሰው ሊሸሸን ይችላል ። “ውሻን በምን ይፈሩታል ቢሉ በአጥንት” ይባላል ።

6- ሱሰኛ ወረኞች፡-

እነዚህ ሰዎች የሚያነሡት ሰው ቢያጡ መድኃኔ ዓለምን እንቦጭቀው ሲሉ ይሰማሉ ። የሰውን ውስጥ ለማወቅ በጣም የሚጓጉ ፣ የማያውቁት ነገር ካለ የሚረበሹ ናቸው ። የሰው ቦርሳ ከፍቶ ማየት የሚወዱ ፣ ሰው ቤት ሂደው ድስት የሚከፍቱ በአስተዳደጋቸው ያልተገሩ ሰዎች አሉ ። ያለ ክፍያ የእገሌ ገቢ ስንት ነው ? ብለው ያጠናሉ ። ከፍለው ወሬን ያስሳሉ ። ስልኩና ዘመናዊ ዕቃው ሁሉ ሐሜት ማፍጠኛ ነው ። ድሮ አንድ ሐሜት ቢያንስ ሦስት ቀን ይፈጅበት ነበር ። አሁን በአንድ ደቂቃ ሐሜት ይሄዳል ።

7- አላውቅም ማለት የሚረብሻቸው፡-

አንድን ሰው ቶሎ ቀርበው ምሥጢሩን አውቀው ፣ ጉድለቱን ተረድተው ፣ ቶሎ የሚንቁት ፣ እንተዋወቃለን እኮ እያሉ የሚያስፈራሩ ፣ በአምስት ደቂቃ ውስጥ የአምስት ዓመት ምሥጢርን ፈልቅው የሚያወጡ ፣ የምስኪኖችን የዋህነት ተተግነው ወሬ የሚለቅሙ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች አንድ ነገር ሲፈጠር ስለ እገሌ እኔ አውቃለሁ ብለው የሚናገሩ እስከዚያው ግን የሚያደፍጡ ናቸው ። ወላጆች ምንም አያውቁም ወረኛ ልጆች ግን በደንብ ያውቃሉ ። መምህራን ስለዚያ ሰው የሚያውቁት ነገር ጥቂት ነው ። ደቀ መዛሙርቱ ግን ያ ሰውማ እንዲህ ነው በማለት ያጠኑትን ጥናት ያቀርባሉ ። ግያዝ ማለት እንዲህ ዓይነት ሰው ነበረ ።

ዛሬም የግያዝን አገልግሎት እንሰጣለን በማለት ነቢይና ፈዋሽ ነኝ ለሚሉ ምሥጢር ለቅመው ፣ የሰውን ጉድለት አጥንተው የሚያቀርቡ ፣ በደረሰው መረጃ መሠረትም እንዲህ የሆናችሁ እያለ የሚናገር ነቢይና ፈዋሽ ረዳት ሆነው የሚሠሩ አሉ ። 2ነገሥ . 4፡14ን ጠቅሰው ነቢዩ ኤልሳዕ የሱነም ሴት የጎደላትን ነገር አያውቅም ነበር ። ግያዝ ግን መረጃ ሰጠውና ሴቲቱ ወለደች ። እኛም የግያዝን አገልግሎት ማገልገል አለብን ብለው በድፍረት የሚናገሩ ፣ በኩራት የሚሠሩ እናውቃለን ።

ሰዎች ስለ እኛ ኑሮ ለማወቅ ቢጓጉም ፣ ትንሽ አይተው ብዙ ቢያወሩም ፣ ያላቸው መሣሪያ እርሱ ነውና የወሬ ጦር ቢወረውሩብንም ደህና ነው ። በሌላ ዓለም ርእስ ሁኖ የሚወራለትና የሚጻፍለት ትልቅ ሰው ነው ። ስለ እኛ ሲያወሩ የሚወሉ አክባሪዎቻችን ናቸውና ልንረበሽ አይገባንም ። ዋናው አለማማት ነው ፤ መታማት ግን ክብር ነው ። የሚያደርግ ሰው አያወራም ። ወረኞች ያላቸው አቅም ወሬ ብቻ ነው ፣ ያልተማረ ማኅበረሰብም የሰማውን ሁሉ ያምናል ። ቢሆንም መኖር በእግዚአብሔር ነውና ደህና ነው ። እርሱ በቃሉ መኖሪያህ የሰው ፍቅር ነው ሳይሆን የዘላለም አምላክ ነው ብሎናል ። ተሰባሪው ሰው መኖሪያችን አይደለም ። ክንዱ የማይዝለው እርሱ እግዚአብሔር መኖሪያችን ነውና ደህና ነው ።

ደህና ነው /5
ሰኔ 22 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ