የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ደካማነት

“ደካማነት እውነት የሌለበትን ሰላም መፈለግ ፣ ቆይ እያለ ለነገ የችግር ፍም ማስቀመጥ ነው ።”

ሁላችንም የራሳችን ችግር ፣ የራሳችን ጉድለት ፣ የራሳችን ደካማ ጎን አለን ። የምንማረው ደካማ ጎናችንን ለማጽደቅ ሳይሆን ለመለወጥ ነው ። በትላንት አድራሻው የሚቀመጥ ድንጋይ እንጂ ሰው አይደለም ። ያ ማለት በየሳምንቱ የአቋም ለውጥ ማድረግ ሳይሆን በየዕለቱ የሕይወት ለውጥ ማድረግ ነው ። በየዕለቱ የምናስወግደው የቆየ ጠባይ አለ ፣ በየዕለቱ የምንሠራው መልካም ነገርም አለ ። የማንነቅልባትና የማንተክልባት ዛሬ አልተሰጠችንም ። ሰው ከራሱ ክፉ ጠባይ ጋር ሲታገል የሚኖር ፍጡር ነው ። በራሱ ላይ ድል ያገኘ አገር ከሚገዛ ይበልጣል ። በርግጥ በአንድ ጊዜ ወደዚህ ጠባይ አልገባንምና በቅጽበት ልንወጣ አንችልም ። እያንዳንዱ ቀን ግን የሚነቀለውን የምንነቅልበት ፣ የሚተከለውን የምንተክልበት ሊሆን ይገባዋል ። ትላንት የሞገተን ነገር ዛሬ ስንደግመው እየላላ ይመጣል ። ትላንት በእኛ ላይ የበላይ የመሰለን ነገር ዛሬ ከእኛ የበታች ይሆናል ። ከመቆም ዳዴ ማለት ፣ ልማድን ከማቀፍ ለመላቀቅ ትግል መጀመር መልካም ነው ። ሰማዕትነት እንደ ዘመኑ ነውና የዛሬው ዘመን ሰማዕትነት ፍላጎትን እንቢ ማለት ነው ።

ብዙ ደካማ ሰዎች በምድር ላይ አሉ ። እንደ እኛ ያለ ደካማ ግን የለም ብለን ማመን አለብን ። እንደ እኛ የሚደክም ፣ እንደ እግዚአብሔር የሚምር ማንም የለም ። ደካማነት ባለቤቱ ሳይቀር የሚጠላው ክፉ ጠባዩ ነው ። ደካማ ጠባያችን ድልን ያዘገይብናል ። ከእርሱ ለመላቀቅ ስንሞክር ከሕይወት ጥሪ እየዘገየን እንመጣለን ። ከምጠላው ከዚህ ማንነቴ አድነኝ እያልን እንጸልያለን ። ምናልባት ከምወደው ከዚህ ማንነቴ ገላግለኝ ማለት የተሻለ ይመስላል ። ደካማ ጠባያችን ካልተወገደ አብሮን የሚዞር ፣ አብሮን የሚኖር ነው ። የምናገኘው ማንኛውም ከፍታ ለደካማነታችን መገለጫ ይሆናል ። ከሥልጣን ከፍታ የሞራል ከፍታ የተሻለ ነው ። ደካማ ጠባያችን ራሳችንን ብቻ እያበሳጨ የሚቀር ሳይሆን ጎረቤትን ሲያልፍም አገርን ሊበክል ይችላል ። ትላንት ሰፈር ይቀራሉ ብለን የናቅናቸው ዛሬ አድማ የሚቀሰቅሱ ፣ የአገርና የቤተ ክርስቲያን ምሰሶ ተደርገው የሚታዩ ሆነዋል ። ሰው ቢጤውን ስለማያጣ ብዙ ደጋፊ አላቸው ። መምህር ኤስድሮስ እንዲህ ብለዋል፡- “ከመሃይም አትጣላ ፣ ደጋፊው ብዙ ነው ያሸንፍሃላ ።” አንድን ሰው ይሳደቡ የነበሩ ዛሬ ዘመን ባመጣው ቴክኖሎጂ ተደግፈው አንድን ሰው ለመላው ዓለም ያሙታል ። ሐሜተኛነታቸውንም ዓለም አቀፍ ያደርጉታል ። በደካማነታቸው የሚያዝኑ አሉ ፣ ይህ እንደ ንስሐ ይቆጠርላቸዋል ። በደካማነታቸው የሚኮሩ አሉ ። እነዚህን ሰዎች ለንስሐ ማቅረብ ከባድ ነው። እኔ አድማ ይሰምርልኛል ፣ የተሳደብኩት ስድብ አይለቅም ብለው የሚኮሩ ሰዎች አሉ ። ሰው ጽድቅን ሲሸሽ በኃጢአት እንደ ጽድቅ ይደሰታል ።

በፍርሃት የምንኖረው ፣ የማያስፈራው የሚያስፈራን ደካማ ስለሆንን ነው ። ለችግሮች መፍትሔ ከማበጀት መለያየትን የምንመርጠው ደካማ ስለሆንን ነው ። ሁሉንም ካልጨበጥሁ ምን እሆናለሁ ብለን የምንስገበገበው ደካማ ስለሆንን ነው ። ሃይማኖታችንን ለድርድር የምናቀርበው ፣ ሚስቴ ባሌ ደስ አላላቸውም እያልን ክርስትናን የካድነው ደካማ ስለሆንን ነው ። ደካማ ሰዎች ፍርሃታቸውን ይንከባከቡታል ። ፍርሃታቸውን እየፈሩት ይመጣሉ ። ፍርሃት የሚያዋራ ነውና የሚላቸውን ይሰሙታል ። ፈሪዎችንም እንደ ጴጥሮስ ይፈራሉ ። በብዙ ስጋት ውስጥ ይገባሉ ። ደካማነት ለፍርሃት አሳልፎ ይሰጣል ። ፈሪ ሰው የሁሉም መጫወቻ ይሆናል ።

ግጭት መልካም ባይሆንም አንዳንድ ጊዜ ወደ እውነተኛ ፍቅርና ሰላም ያደርሳል ። ድፍንፍን ያሉ ነገሮች ውስጣችንን እየበሉት ይመጣሉ ። ደካማነታችን ብንወያይ እንጋጫለን ብሎ ይፈራል ። በመነጋገር ውስጥ ግን የግምታችንን ሐሰተኛነት ፣ የሰዎቹንም የልብ አሳብ እናውቃለን ። መነጋገራችን የሚለያየን ከሆነ አለመነጋገራችን አንድ አያደርገንም ። በልብ ተለያይተን በአካል አንድ ላይ ብንኖር ይህ እውነተኛ አንድነት ሳይሆን ጊዜን ማቃጠል ነው ። በመኮራረፍ ውስጥ ፣ ባለመነጋገር ሰላም ያለ ይመስላል ። አዎ ኃይለ ቃላት ላይኖሩ ይችላሉ ። እየቆየ ሲመጣ ግን ውስጣችን እየታወከ ፣ መኖርን እየጠላን እንመጣለን ። ብንነጋገር ሁለት ነገር እንጂ ሦስት ነገር አይኖርም ። ወይ እኛ ወይ እነርሱ ጥፋተኛ ይሆናሉ ። እግዚአብሔር እንዳያልቅ አድርጎ የይቅርታን ውኃ ሰጥቶናልና በዚያ መንጻት ይቻላል ። ባለመነጋገር ውስጥ ያለውን ሰላም መሳይ ነገር የሚፈልገው ደካማነታችን ነው ። መነጋገር ሊደፈር ፣ አለመነጋገር ሊፈራ ይገባዋል ።

ቶሎ ውሳኔ አለመወሰን የደካማነት አንዱ መገለጫ ነው ። ዛሬ ያላስወገድነው ችግር ነገ ላይ ተራራ አህሎ ይመጣል ። ነገ የማንሸከመውን ዛሬ ማባበል ፣ ነገ የማንቀበለውን ዛሬ ላይ እየሳቁ መቀበል ተገቢ አይደለም ። ቶሎ እንዳንወስን የሚያደርገን ስንፍና ነው ። ዳግመኛም እነዚያን ሰዎች ላጣ እችላለሁ የሚል ፍርሃት ነው ። እኔን አልጎዱኝም ብሎ በእኔነት ሒሳብ ማሰብ ቶሎ እንዳንወስን ያደርጋል ። ውሳኔ በራሳችን መጥፎ ጠባይ ላይም ነው ። ሱስና አጉል ባልንጀርነትን ቶሎ መወሰን ያስፈልጋል ። ቶሎ ባለመወሰናችን የምንከፍለውን ዋጋ ቶሎ ብንወስን ኖሮ የማንከፍለው ዋጋ ነው ። በችግኙ ያልነቀልነውን ካደገና ግንድ ከሆነ በኋላ መንቀል ይከብደናል ። ባለበት የሚቆም ነገር የለም ። ክፉም ደጉም ራሱን ያሳድጋል ። ቶሎ መወሰን ግን ችግር በክብሪት እንዲቀር ያደርጋል ። ቶሎ ያልወሰኑት ነገ ላይ ፍም ሆኖ ያቃጥለናል ።

ብዙ ትዳሮችና ኅብረቶች ሰላም በሚመስል ዝምታ ውስጥ አሉ ። ከላይ የማይታይ ቍስል ውስጥ ውስጡን የሚጨርስ ነው ። እነዚህ ወገኖች የሚነቁት ሁሉም ነገር ካለቀ በኋላ ነው ። የላይ ቍስል ቶሎ የመታከም ዕድል አለው ። ማሬና ሆዴ በሚል ቃል የተሸፈነ ቍስል ግን መጨረሻው የማያምር ነው ። ደካማ የሆኑ የትዳር መሪዎች ፣ ደካማ የሆኑ የቤተ ክርስቲያንና የአገር መሪዎች ቶሎ ባለመወሰን ብዙ ዋጋ እንዲከፈል ምክንያት ይሆናሉ ። ደካማ ማለት አቅም የሌለው ሳይሆን አቅሙን በትክክለኛው መንገድና ሰዓት የማይጠቀም ነው ።

አቤቱ እኔም ያንተው ደካማ ነኝ አበርታኝ !

የብርሃን ጠብታ 4

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ