የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ድል ለነሣው – መቀዝቀዝን ድል መንሣት / ክፍል 2

/ራእ. 2፡1-7/
 ለሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት ከተላከው መልእክት የመጀመሪያው ለኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የተላከው ደብዳቤ ነው። የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን በእስያ ከሚገኙት የታወቁ አብያተ ክርስቲያናት አንዷ ናት። ይህች ቤተ ክርስቲያን በጳውሎስ ሐዋርያዊ አገልግሎት የተመሠረተች ናት። ይህችን ቤተ ክርስቲያንም  ጳውሎስ፣ ጢሞቴዎስ፣ ዮሐንስ አስተዳድረዋታል። የኤፌሶን መልእክት የተጻፈው ለዚህች ቤተ ክርስቲያን ነው። የኤፌሶን ከተማ በሮም ግዛት ውስጥ ከነበሩት ትልልቅ ከተሞች አንዷ ናት። ኤፌሶን ከሮም ተነሥቶ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ በሚወስደው መንገድ ላይ የተመሠረተች ከተማ ናት። በከተማይቱም የአርጤምስ መቅደስ ይገኝ ነበር። ለጣኦት አምልኮ ይጠቀሙ ከነበረው መሥዋዕት አንዱ ዝሙት ስለነበር እንደ ስእለት ብዙዎች ዝሙትን ይፈጽሙ ነበር። ከተማይቱ በሥጋዊ ፈንጠዝያ የቆሸሽች ነበረች። የከተማይቱ ውበትና የባሕር ዳርቻ ላይ የተመሠረተች መሆኗ የበለጠ አድምቋት ነበር። ኤፌሶን የሚለው ቃል ትርጉም ማማር ወይም መጎምጀት ማለት ሲሆን ይህም የከተማይቱን ውበት የሚገልጥ ነው። የኤፌሶን መልእክት ሲጻፍ ከከተማዋ ባሻገር ያለውን የሰማይን ውበት እንዲያስቡ በሰማያዊ ስፍራ ስለ መቀመጥ ተጽፎላቸዋል። ይህች የኤፌሶን ከተማ ዛሬ የለችም። አሸዋ ተጭኗት የወደብ ዳርቻ ሆና ቀርታለች።
 የኤፌሶን መልእክት በግምት በ62 ዓ.ም ሲጻፍ በዮሐንስ ራእይ የመጣው መልእክት ደግሞ በ96 ዓ.ም. ተልኳል። ይህ መልእክትም ስለ ፍቅር መቀዝቀዝ ይናገራል። የቀዘቀዘው ለእግዚአብሔር ያላቸው ፍቅር ነው። የፍቅር ምንጩ እርሱ ነው። ለእርሱ ያላቸው ፍቅር ከቀዘቀዘ የወዳጅነት ፍቅራቸውም በዚያው መጠን ይቀንሳል። የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ድል እንድትነሣ የተጠየቀችው በዋናነት የፍቅርን መቀዝቀዝ ነው። “ዳሩ ግን የምነቅፍብህ ነገር አለኝ የቀደመውን ፍቅርህን ትተሃልና” የሚል መልእክት ደርሷታል።  እግዚአብሔር የመጀመሪያውን ቀን ፍቅር  እስከ መጨረሻው ይፈልገዋል። የፍቅር ዳርቻው ሰማይ እንጂ ሀብትና ዝና፣ ሥልጣንና ተፈላጊነት አይደለም። ፍቅር ግለቱ የሚጨምር የእግዚአብሔር ወንዝ እንጂ በተቀዳ ቁጥር የሚቀንስ የሰው ገንቦ አይደለም። ፍቅር እስከ የሚል ገደብ የለውም። የወዳጅ ፍቅር እስከ ሞት ሲሆን የጌታ ፍቅር ግን እስከ ሰማይ ነው።

 የእጮኝነት ፍቅር ትዳር ላይ መታየት ይገባዋል። ብዙዎች እጮኝነት ፍቅርን የሚካፈሉበት፣ ትዳር ደግሞ ገንዘብ የሚካፈሉበት አድርገው ይመለከቱታል። እጮኝነት ግን መጠናናት ሲሆን ትዳር ግን መተዋወቅ ነው። እጮኝነት ጊዜን የሚካፈሉበት ሲሆን ትዳር ግን ራሳቸውን የሚሰጡበት ነው። ስለዚህ ትዳር ላይ ፍቅር ሊጨምር እንጂ ሊቀንስ አይገባውም። የሚገዛን ያስቀመጥነው የጊዜ ገደብም ነው። የምማረው ለአንድ ወር ነው ያለ ተማሪ ሁለተኛውን ወር የሚከፍልለት ቢያገኝ እንኳ መማር ያቅተዋል። ፍቅር እስከ ትዳር ነው፣ ከዚያ በኋላ የኑሮ ግብግብ ነው ያለም ትዳር ላይ ሲገባ አቅም ሊያንሰው ይችላል። ትዳር ፍቅር የሌለበት የኑሮ ግብግብ ብቻ ተደርጎ መታየት የለበትም። በእጮኝነት ዘመን ዘመን ተቃቅፈው ይሄዱ የነበሩ ትዳር ውስጥ ሲገቡ ፊትና ኋላ መሄድ አይገባቸውም። በእጮኝነት ዘመን አንድ ኮት ለሁለት ለብሰው ይሄዱ የነበሩ ከተጋቡ በኋላ በረደኝ ስትል፡- “ይዘሽ አትወጪም ነበር?” የሚባልበት ሊሆን አይገባውም። ልክ እንደዚሁ ለእግዚአብሔር ያለን ፍቅር ሁለት ክፍል ያለው ሊሆን አይገባም። ሮጦ ሮጦ የደከመውን ክርስቲያን፣ የወረት ፍቅር ያጠቃውን ምእመን በብዛት ያዩ ታዛቢዎች፡- “አዲስ ክርስቲያን ከጳጳስ ይበልጣል” እያሉ ይተቻሉ። የክርስቲያን አሮጌ የለውም፣ ሁልጊዜ አዲስ ሆኖ መኖር ይገባዋል። እግዚአብሔር ፍቅርን ለኮንትራት ወይም ለመዳረሻ አልሰጠንም። ፍቅር የጊዜ ዳርቻ የሌለው ዘላቂ ነው። በሰማይ ስንደርስ እምነት በማየት ይተካል፣ ተስፋ በፍጻሜ ያበቃል፣ ፍቅር ግን ለዘላለም ይቀጥላል። ፍቅር ዘላለማዊ ነው።
እነዚህ የኤፌሶን ምእመናን ከሚያምኑት ይልቅ የሚያዩት እየማረካቸው ነበር። ፍቅራቸው ዓለም፣ እግራቸው ቤተ ክርስቲያን ቀርቶ ነበር። በአዳዲስ የዓለም ወሬ፣ በሚለዋወጠው ሥልጣኔ እንዲሁም የጣኦታውያንና የዘማውያን ግፊት የክርስትና ፍቅራቸውን ሸርሽሮት ነበር። መቀዝቀዝ የሞት ዋዜማ ነው። ሕይወት የሆነውን ክርስትና በልማድ ይዘውት፣ በመንፈስ ጀምረው በሥጋ እየጨረሱ ነበር። ለጌታ የነበራቸው የልጅነት ፍቅር ተባርዶ በሞትና በሕይወት መካከል ባለ ኑሮ ይኖሩ ነበር። ጸሎትና መንፈሳዊ ኅብረት ባለበት የማይቀሩ ነበሩ፣ አሁን ግን ለመጸለይና ኅብረት ለማድረግ ይለመኑ ነበር። የሚዘምሩት ለመርሐ ግብር ማማያ እንጂ ለአምልኮ አልነበረም። በእንባ ያመለኩበት ያ ዘመን፣ ስለ ስሙ የተሰደዱበት ያ ወራት ዛሬ በማሳደድ ተተክቶ፣ አካባቢው ተጭኖአቸው ነበር። ሰማይ ይደርሳሉ የተባሉ ምድር ቀርተዋል።
እምነት በልማድ፣ ክርስቶስ በዝና ተለውጧል። እንጀራዬ ክርስቶስ ነው ያለ ምእመን አሁን ደሞዜ እንጀራዬ ነው ይላል። ለነፍስ ጀምረው ለሥጋ ብለው ይኖሩ ነበር። ቃሉን በጥሞና ይሰሙ የነበሩ አሁን አቃቂር ማውጣት፣ ከሚበሉት የሚፈረፍሩት በዝቶ ነበር። የራሳቸውንም አስተማሪ የሚያከማቹበት እውነትን ለመስማት የሚጠሉበት ዘመን ላይ ደርሰው ነበር። ሕጻናት ወላጆቻቸውን ከቤት አላስወጣም ብለው ያለቅሱ ነበር። ካደጉ በኋላ ደግሞ የሚፈልጓቸው ወላጆቻቸው ናቸው። እግዚአብሔርን አልለቅም ያሉ ምእመናን ያን የልጅነት ፍቅር ትተው ጌታ ሲፈልጋቸው እንኳ አውቀው ተደብቀዋል፡፡ ይህ መባረድ ድል እንዲነሡ ጌታ መከራቸው። ድል ቢነሡ የሚያገኙት ሽልማትም ተገልጧል፡-
“ድል ለነሣው በእግዚአብሔር ገነት ካለው ከሕይወት ዛፍ እንዲበላ እሰጠዋለሁ” ይላል /ራእ. 2፡7/። በገነት የነበረው የሕይወት ዛፍ የእውቀት ዛፍም ይባላል። መባረዳቸውን ድል ቢነሡ የመኖር ልምላሜ የሆነ ሕይወትን፣ የብርሃን መገኛ የሆነውን እውቀትን ያገኛሉ። ክርስትናን ለመኖር የሚያስችል ኃይል እንዲሁም በመባረድ ውስጥ ያለውን ጉዳት የሚገነዘቡበት እውቀት ያገኛሉ። ሽልማቱ እውቀት ነው። በእውቀት ውስጥ እግዚአብሔር የመኖርን ኃይል ይሰጣል።
ዛሬስ አልተባረድንም ወይ? የኤፌሶን መልእክት እኛን አይመለከትም ወይ? ቃሉን ችላ እንድንል የሚያደርገን መባረድት ነው። እግዚአብሔርን በአገልጋይ እየመዘንን እንድንርቅ የሚያደርገን መባረድ ነው። ስንሰብክ የነበርነውን እንዲሰብኩን የሚያደርገን መባረድ ነው። የሰፋነውን መልሰን እንድንቀድ የሚያደርገን መባረድ ነው። የጸለይንላቸውን አገልጋዮች መልሰን እንድንወግር የሚያደርገን መባረድ ነው። የሚያሳስበን መብረዳችን ሳይሆን ለመብረዳችን ምክንያት የሆኑንን ነቅሰን ለማውጣት ወይም ለመክሰስ መሆኑ ይበልጥ ያሳዝናል። ቤተ ክርስቲያን በፊት በር እያስገባች በኋላ በር እያስወጣች ነው። አገልግሎት በቀዳዳ ከረጢት እንደ መሙላት እየሆነ ያለው ለዚህ ነው። ዛሬም የቀደመ ፍቅራችንን ትተናልና ወዴት እንደ ወደቅን ማሰብ አለብን። እግዚአብሔር ወደ ልጅነት ፍቅራችን ወደ ቀድሞው ደስታችን ይመልሰን።
  

ያጋሩ