የስም ኩራትን ድል መንሣት
/ራእ. 3፡1-6/
የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ ግንቦት 25/2007 ዓ.ም.
ከሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት አምስተኛዋ ተወቃሽ ቤተ ክርስቲያን የሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን ናት። ወቀሳ የመንፈስ ቅዱስ ነው፣ ክስ የሰይጣን ነው። ይህች ቤተ ክርስቲያን ጌታ ገና የሚወዳት ቤተ ክርስቲያን በመሆኗ ይወቅሳታል። የሚወቅስ የሚቆረቆር ለመንፈሳዊ ውበታችን የሚጨነቅ ነው። የሚከስ በአደባባይ የሚያጋልጥ ነው፣ የሚወቅስ ግን በር ዘግቶ ይህ አይገባም የሚል ነው። የሚከስ ፍርድን የተጠማ ነው፣ የሚወቅስ ግን ማርልኝ እያለ የሚጸልይልን ነው። እንዲህ ያለ ወዳጅ በዛሬ ዘመን ማግኘት ውድ ቢሆንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን አለ። የሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን ገና በክርስቶስ እጅ ናት። ከበዱኝ ብሎ በማይለቀው፣ አቃተኝ ብሎ አሳልፎ በማይሰጠው በአማኑኤል እጅ ናት። “በሰርዴስ ወዳለው ወደ ቤተ ክርስቲያን መልአክ እንዲህ ብለህ ጻፍ፡- ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስትና ሰባቱ ከዋክብት ያሉት እንዲህ ይላል” በማለት ይጀምራል /ራእ. 3፡1/። ሰባቱ የእግዚአብሔር መናፍስት የተባሉት ሰባቱ የመንፈስ ቅዱስ ሀብታት ወይም ሰባቱ የመላእክት አለቆች ናቸው። ሰባቱ ሀብታት የሚባሉት በኢሳይያስ 11 ላይ የተጠቀሱት ጸጋዎች ናቸው። እነርሱም፡- ጥበብ፣ ማስተዋል፣ ምክር፣ ኃይል፣ እውቀት፣ እግዚአብሔርን መፍራት፣ በማየትና በመስማት አለመወሰን ናቸው። ሰባቱ መላእክት ናቸው ከተባለም /ራእ. 5፡6/ የአሳቡ ፈጻሚዎች የሆኑ የመላእክት አለቆች ናቸው። ሰባቱ ከዋክብት የተባሉት ግን የሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት መሪዎች ናቸው። የአገልጋዮች መጠሪያ እንዲህ የከበረ ነው።
ጌታ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን፡- “ሕያው እንደ መሆንህ ስም አለህ ሞተህማል” ይላታል። ስም የሕያው ነገር መገለጫ ብቻ ሳይሆን የግዑዝ ነገር መታወቂያ ነው። ላለ ነገር፣ ለተገኘ ነገር ስም ይሰጣል። ስም የመኖር የሕያውነት መገለጫ አይደለም፣ ስፍራ የያዘና በመኖሩ የታመነበት ነገር ሁሉ ስም አለው። ድንጋይም ስም አለው። የሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን በስም ብቻ የምትኮራ ነበረች። መልካም ስም የመልካም ኑሮ መግለጫ ላይሆን ይችላል። “መልከ ጥፉ በስም ይደግፉ” እንዲሉ። የሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን አለሁ እያለች ስም ብቻ ቀርቷት ነበር። ሰውዬው በሬን ሸጬ እከፍላለሁ እያለ ይበደራል፣ አሁንም ይበደራል። ብድሩ ከሽያጩ እያለፈ መጣ። አንድ ቀን ወደ ቤት ሲገባ በሬው ደጃፍ ላይ ተኝቶ አየውና፡- “አንተ በሬ ያለህ መስሎሃል ተበልተህ አልቀሃል” አለው ይባላል። የሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን ያለች መስሏት ተበልታ አልቃ ነበር። ከሕያውነት ይልቅ የትዝታን እሳት እየሞቀች የምትኖር ግን የበረዳት ቤተ ክርስቲያን ነበረች። የትዝታ እሳት አይሞቅምና። ነበር ብለው ሲናገሩት ደስ የሚለው ኃጢአትን፣ ሞትን ነው። አምልኮን፣ ዝማሬን፣ ሕይወትን በነበር መተረክ ከማስደሰት ያሳምማል። ስፍራ የያዘ ሁሉ ስም አለው፣ ስም አለኝ ብሎ መኩራት እንደማይገባ መልእክቱ ያብራራል። በእውነት ትልቅ ሞት ያሉ እየመሰሉ ማለቅ ነው። የሚመስል ነገር ለንስሐ የማያበቃ፣ ለበጎ ነገር የማያነሣሣ ማደንዘዣ ነው።
የሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን ክርስትናዋ ጎዶሎ ሆኖ ተገኝቷል። ክርስትናው አገም ጠቀም ያለበት ነበር። የጨከነ ክርስትና ወይ የጨከነ ክፋት በዚህች ቤተ ክርስቲያን አይታይም። ሁለት ቋንቋ እንደሚናገርና ለሁለት አገር እንደሚሰለፍ እንዲሁም ከሁለት አገር እንደሚጠቀም የድንበር ነዋሪ ሆናለች። ጎዶሎ ነገር ይንቦጫቦጫል። ይልቁንም ዳገት የሚወጣ ጎዶሎ ነገር ከያዘ ወደኋላ ይመልሰዋል። ጎዶሎ ነገር አደጋ አለው። ክርስትና በፈተና ውስጥ ሲያልፍ ጎዶሎ የተባለ ማመንታት፣ መላ ሕይወትን ለጌታ አለመስጠት ወደኋላ ሊመልስ ብሎም ሊያስክድ ይችላል። በደጉ ቀን ማምለክ ያልቻለ በክፉ ቀን ሊጸና እንደምን ይቻለዋል? ሁሉም ሰው ለጌታ ሰማዕት ቢሆን ይመኛል። እግዚአብሔር ግን ይበልጥ የሚከብረው በየዕለቱ ፍላጎታችንን እምቢ ብለን እርሱን በመከተላችን ነው። አንገትን መስጠት፣ በሰይፍ መከለል ለሁሉ የተሰጠ የሁልጊዜም ጥያቄ አይደለም። የሁልጊዜው ጥያቄ እንደ ቃሉ መኖር ነው።
በሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን ሊሞቱ ትንሽ የቀራቸው ጭል ጭል የሚሉ ነገሮች ተግኝተዋል። እንደ ዛሬው ፍቅር ይሆን? ዛሬም መተማመን በመጠባበቅ ተተክቷል። መግባባት በመገፋፋት ተለውጧል። ቸርነት የክብር መቸርቸሪያ እየሆነ ነው። ክብር ከቤተ ክርስቲያን ርቋል። የነውር ንግግሮችን አፋችንና ጆሮአችን ለምዷቸዋል። እየለመድናቸው ያሉ ክፉ ነገሮች ብዙ ናቸው። የሰይጣን ትልቅ ሥራው ጆሮአችንን ማስለመድ ነው።
የሰርዴስ ቤተ ክርስቲያን እንዴት እንደተቀበለችና እንደ ሰማች እንድታስብ ተነግሮአታል። በብዙ ዋጋ ወንጌልን ተቀብላለች። በዋጋ የተቀበለችውን ያለዋጋ እንዳትጥል ያስጠነቅቃታል። በዚህ ሁሉ ውስጥ ግን የስም ኩራቷን ድል እንድትነሣ ተነግሯታል።
ድል ብትነሣ ከትዝታ ወጥታ ሕያው ብትሆን ነጭ ልብስ እንደምትለብስ ተነግሮአታል። ነጭ ልብስ የክርስቶስ ጽድቅ ነው። ከኃጢአት የነጻ የይቅርታ ኑሮ ነው። ደግሞም በሕይወት መጽሐፍ እንደምትጻፍ ተነግሮአታል። ይህ በልበ ሥላሴ መታወቅ ነው።
እኛስ ክርስትና ትዝታ ሆኖብን ይሆን? የቀደመውን የብርታት ዘመን ብቻ እያሰብን በስም ተቀምጠን ይሆን? ከድንዛዜ ለመንቃት ጊዜው አሁን፣ መንቂያውም ንስሐ፣ መነሻውም መንፈስ ቅዱስ ነው። የስም ኩራትን ድል መንሣት ይሁንልን።
ይቀጥላል