መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ድል ለነሣው » ድል ለነሣው / ክፍል 1

የትምህርቱ ርዕስ | ድል ለነሣው / ክፍል 1

መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚነግረን ከደስታዎች ሁሉ የሚልቀው ትልቁ የመኸርና የድል ደስታ ነው። ገበሬ በዝናብ በማጥ ዘርቶ፣ እቤት የተቀመጠውን ዘር ደጅ አውጥቶ በትኖ፣ የበረዶ፣ የአረም፣ የነቀዝ፣ የተምች፣ የዋግ፣ የአንበጣ፣ የወፍ ፈተናን አልፎ መኸሩ ሲደርስ ፍሬውን የሚሰበስበው በታላቅ ደስታ ነው። ከዚያ በኋላ ደስታና ሠርግ ያደርጋል፡ በአገራችን ሠርግ በጥር የሚደረገው መኸሩን ተከትሎ ነው። ከመኸር ቀጥሎ ሌላው ደስታ የድል ደስታ ነው። ተዋጊውን አሸንፎ የፈንጂውን ወረዳ ጥሶ፣ ግዛቱን አስከብሮ፣ ጠላት መሬት ላይ ባንዲራውን ተክሎ፣ ምርኮኛ ነድቶ፣ ምርኮ ተካፍሎ የሚገኘው ደስታ ከፍ ያለ ደስታ፣ በራስ ስም የማይጠራ በአገር ስም የሚጠራ ድል ነው። ከመኸር እንዲሁም ከድል ደስታ የሚበልጥ ደስታ እግዚአብሔር እንዳዘጋጀ ነቢዩ ኢሳይያስ ያውጃል። እርሱም የእግዚአብሔር ወልድ ሰው መሆን ነው /ኢሳ. 9፡3-7/።
የምንኖርበት ዓለም በትግል የተሞላ ዓለም ነው። የትግሉ መነሻዎች ብዙ ናቸው። አንዳንዴ መነሻቸው አይታወቅም። የተጣመመው ፍላጎታችን፣ መብረጃ የሌለው የክፉዎች ቁጣ፣ መልከ ቀና ግብረ ጠማማ የሆነችው ዓለም፣ አንድም ቀን ለእኛ በጎ የማይመኘው ሰይጣን የትግሉ መነሻዎች ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ ሁሉ ተግዳሮት ውስጥ ድል እንድንነሣ እግዚአብሔር ይፈልጋል።
ርእሳችን ያደረግነው ድል ለነሣው የሚለው ልብን የሚያነሣሣ ቃል በራእየ ዮሐንስ ምዕራፍ 2-3 ለሰባት ጊዜ ያህል ተጠቅሷል። ጠላት ውድቀታችንን ሲናፍቅ ጌታ ከመከራውና ከፈተናው ወደብ ላይ ሽልማት ይዞ ይጠብቀናል። እርሱ ሽልማት የሚሰጠን ዳኛ ብቻ ሳይሆን በትግሉ የሚያግዘን የበረሃው ጓድ ነው። በሕይወት ላይ እንደ መሸነፍ ልብን የሚያሳዝን ነገር የለም። እንደማሸነፍም የሚያረካ ነገር የለም። ድል ዋዜማው ጦርነት ቢሆንም ማግሥቱ ግን ምርኮ ነው። ድል የጠላት ድንበር ላይ የዓላማችንን ባንዲራ ማውለብለብ ነው።

በነቢዩ በዳዊት ዘመን አንድ የምርኮ ሕግ ወጥቷል። የተዋጋም ደጀን የሆነም እኩል ምርኮ እንዲካፈሉ የሚል ነው /1ሳሙ. 30፡24-25/። ደጀን ከሌለ ወታደር ስንቅና ትጥቅ ማግኘት፣ የድልን ደስታ መካፈል አይችልም። ስለዚህ በጦርነቱ የቅርብ ርቀት ላይ ሆነው ቁስለኛ የሚያክሙ፣ የደከመን የሚሸከሙ፣ የሠራዊቱን ዕቃ የሚጠብቁ ምርኮውን እኩል እንዲካፈሉ ዳዊት ደነገገ። ድል የጋራ ነው። በምክር የረዱን፣ በወኔ ቃል ያበረቱን፣ በጸሎት ያገዙን፣ ተስፋ ያደረጉን፣ ነገን በብሩህ ያዩልን፣ የእግዚአብሔርን ፍቅር ያወጁልን …የድሉ በረከት ይደርሳቸዋል። በመንፈሳዊ ትግላችን ለረዱን ሁሉ ሰላም ይጨመርላቸው!
ሰባቱ አብያተ ክርስቲያናት በእስያ አህጉር የሚገኙ እያንዳንዳቸው በሰማንያ ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ያሉ በክርስቶስ ስም ተጠሩ ማኅበረ ምእመናን ናቸው። እነዚህ ሰባት አብያተ ክርስቲያናት የኤፌሶን፣ የሰምርኔስ፣ የጴርጋሞን፣ የትያጥሮን፣ የሰርዴስ፣ የፊልድልፍያ፣ የሎዶቅያ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው።
የመልእክቱ ተቀባይ መልአኩ ተብሎ የተጠቀሰው የቤተ ክርስቲያኒቱ አስተዳዳሪ ወይም መንፈሳዊ መሪ ነው። ማኅበሩ በመበርታቱ ሲመሰገን፣ ማኅበሩ በመድከሙ ተወቅሷል። ይህ የሚያሳየን እግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያንን እንደ አንድ አካል እንደሚያውቃት ነው። ብርታታችንም ድካማችንም የጋራችን ነው። በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ግላዊ ሩጫ ካለ ቤተ ክርስቲያን የሚለው ጽንሰ አሳብ አደጋ ይገጥመዋል።
የመልእክቱ አወራረድ አራት ዓይነት ነው፡-
1-     ማበረታቻ
2-    ወቀሳ
3-    ማስጠንቀቂያና
4-   ሽልማት ናቸው።
መልእክቱን በቀጥታ የሚያስተላልፈው ሞቶ የነበረው ለዘላለም ሕያው የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው። እርሱ መልእክቱን በምስጋና እንጂ በመንቀፍ አይጀምርም። አሟልቶ የሚያነበን እንጂ እንከናችንን የሚፈልግብን አይደለም። ምክሩን አብያተ ክርስቲያናቱ ያላቸውን መልካም ነገር በመግለጥና በማበረታታት ይጀምራል። ቀጥሎ የጎደላቸውን በፍቅር ይጠቁማል። ሦስተኛ ያን ባያስተካክሉ የሚመጣውን ውጤት ይገልጣል። ያላቸውን ቢጠብቁና የጎደላቸውን ቢያሟሉ ድል ነሺዎች ናቸውና ሽልማት ያገኛሉ። ካለው መልካም ነገር የማይጀምር ማንኛውም ንግግር ወደ መግባባት አያደርስም። ሰው ክፉ ብቻ አይደለም፣ ሰይጣን ካልሆነ። ሰው መልካም ብቻም አይደለም፣ መልአክ ካልሆነ። እንደ ጌታ አካሄድ ከመልካሙ መጀመር ይገባል። በትዳር ውስጥ፣ በጓደኝነት፣ በአገራትና በማኅበራት ግንኙነት ፍቅርን የሚያነሣሣ ከመልካሙ የሚጀምረው ንግግር ነው።
ድል ለነሣው የሚለው ቃል በራእ. 2፡7፤11፤17፤26፤3፡5፤12፤21 ላይ ተጠቅሷል። ድል ለነሣው የተዘጋጀው ሽልማት ደስ የሚያሰኝ ነው። ደካማውን የሚያነቃቃ፣ ሰነፉን የሚያተጋ፣ ታጋዩን የሚያበረታ ነው።
  “ድል ለነሣው” የሚለው ልብን የሚያነሣሣ ቃል በራእየ ዮሐንስ ሁለት ምዕራፎች ውስጥ ሰባት ጊዜ ያህል ተጠቅሷል። ማንኛውም ነገር ወደ ራሱ ውጤት ያመራል። ደግነትም ክፋትም የራሱ ክፍያ አለው። “ድል ለነሣው” የሚለው ቃል ከትግሉ ወደብ ላይ ሽልማት ይዞ የሚጠብቀንን ጌታ ያሳያል። ክርስትና ነጻ ትግል ሳይሆን ዋጋ ያለው ጦርነት ነው። ሁለቱን ምዕራፎች በዝርዝር አንተርክም። ሰፊና ምጡቅ አሳብ ይዘዋል። ድል ስለምንነሣውና ስለተዘጋጀው ሽልማት ብቻ ለማየት እንሞክራለን። በአጭሩ ምእመናን ሰባት ነገሮችን ድል መንሣት ይገባቸዋል፡-
1-     መባረድን
2-    መከራን
3-    ገንዘብ መውደድን
4-   ባዕድ አምልኮን
5-   የስም ኩራትን
6-   ተቃዋሚዎችን
7-    ሚና የለሽነትን ድል መንሣት ይጠበቅባቸዋል።
ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም