የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ድል ለነሣው / ክፍል 7


 የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ እሑድ ሰኔ 7/2007 ዓ.ም

ጥላቻን ድል መንሣት
                                                         /ራእ. 3፡7-13/።

ፊልድልፍያ ማለት የወንድማማች ፍቅር ማለት ነው። ጌታ ለዚህች ቤተ ክርስቲያን የተገለጠበት የብርታቱ ጉልበት፡- “የዳዊት መክፈቻ ያለው፤ የሚከፍት የሚዘጋም የሌለ፤ የሚዘጋ የሚከፍትም የሌለ፤ ቅዱስና እውነተኛ የሆነ እንዲህ ይላል” በማለት ነው /ራእ. 3፡7/። የዳዊት መክፈቻ ሥልጣኑን ንግሥናውን የሚያመለክት ነው። እርሱ የዳዊት ልጅም ተብሎአል። የዳዊት ዘርና ተስፋውን ፈጻሚ ነውና። ሥልጣን ኃይልን ሁሉ የሚገዛ ነው። ሥልጣን ሁሉን የሚያዝ ነው። ኃይልን ሁሉ የሚገዛ፣ ሁሉን የሚያዝ ሥልጣን ያለው ጌታ ነው። በወንድማማች ፍቅር ውስጥ ስንሆን የእግዚአብሔርን ልብ እናሳርፋለን። ለአንድ አባት በደስታ ለመኖርም በደስታ ለመሞትም ጉልበቱ የልጆቹ ፍቅርና አንድነት ነው። የልጆች ፍቅር ሞትን በድፍረት እንዲቀበል ያደርገዋል። እግዚአብሔርም ከአባት የሚበልጥ አባት ነው። እርሱ ፈጣሪ አባታችን፣ ከመወለዳችን በፊት የሚያውቀን፣ ይህችን ቀን ያየልን ወዳጃችን ነው። እርሱ ከሚያስቡልን ይልቅ የሚያስብልን ነው። መንግሥተ ሰማያትን የሚመኝልን ሳይሆን የሚያወርሰን አባታችን ነው። ምድራዊ አባታችን መንግሥተ ሰማያትን ቢመኝልን ውለታው ከፍ ይልብናል። ጌታ ግን የሚያወርሰን ነው። ይህ አባት ደስታው ፍቅራችን ነው። ፍቅር ባለበት የሚቀር አቅም የለም። በወንድማማች ፍቅር ውስጥ ንጉሣዊ ኃይል አለ።

 ለፊልድልፍያ ቤተ ክርስቲያን የተገለጠላት ክርስቶስ የብርታቱ ገጽ ሉዓላዊ ሥልጣኑ ነው። እርሱ ከከፈተ የሚዘጋ የለም፤ እርሱ ከዘጋም የሚከፍት የለም። ይህን ማሰብና ማመን እንዴት ልብን ያሳርፍ ይሆን? እርሱ የሰጠንን ማንም አይነሣንም። እርሱ ከከለከለንም ማንም አይሰጠንም። እርሱ የከፈተውን የሚዘጋ ብርቱ የለም፣ እርሱ የዘጋውን የሚከፍት ደግ የለም። ጌታ ከሰዎች ደግነትና ኃይል በላይ ነው። ተማምነን የምንኖረው ጠላት ስለሌለብን ሳይሆን እግዚአብሔር የከፈተውን የሚዘጋው ስለሌለ ነው። አዎ ተወደን ልንሞት፣ ተጠልተን ልንኖር እንችላለን። ሥልጣን የጌታ ነው። በወንድማማች ፍቅር ውስጥ የተከፈተ በር ቢዘጋስ የሚያሰኝ ፍርሃት የለም። የተዘጋውም ጥያቄ አይሆንም። ፍቅር መልስ ነው። ጌታ እውነተኛና ቅዱስ ነው። እውነተኛ በመሆኑ ሰዎች እንዲያውቁን ጥረት አናደርግም። ቅዱስ በመሆኑ እንደሚቀድሰን እናምናለን። ቅዱስ ይቀድሳል፣ ርኩስ ያረክሳል።

ይህች ቤተ ክርስቲያን ብዛትዋ አነስተኛ፣ ኃይሏም የተመጠነ ነው። ነገር ግን የተወደደች ናት። ቤተ ክርስቲያን ከቁጥር ብዛትዋ ይልቅ የፍቅር ጽናቷ ኃይለኛ ያደርጋታል። የቤተ ክርስቲያን ኃይል የጌታ ደስታ ነው። የጌታ ደስታ ፍቅር ነው። በእውነተኛ ፍቅር ቢኖሩ አስመሳዮችን እንደሚማርኩ ተነግሯቸዋል። የማስመሰል ኑሮ የደከመው ብዙ ነው። እውነተኛ ፍቅር ሲኖረን ይህን ሁሉ መማረክ እንችላለን። ፍቅር ያጣው ዓለም ወደ እኛ የሚመጣው ፍቅር ሲኖረን ብቻ ነው። ይህች ቤተ ክርስቲያን የትዕግሥቱን ቃል ጠብቃለች። ፍቅር ትዕግሥትን ያመጣልና። ተራው እንዲህ ነው፡- ፍቅር ተስፋን፣ ተስፋም ትዕግሥትን፣ ትዕግሥትም ዋጋን ያስገኛል።
አክሊላቸውን ማንም እንዳይወስድባቸው ተነግሮአቸዋል። ይህች ቤተ ክርስቲያን የተመሰገነች ቤተ ክርስቲያን ናት። ጌታ ምን ያህል በቁ ነህ? አይለንም። ብቁ እንዳልሆንን ያውቀናል። ምን ያህል የፍቅር ልብ እንዳለን ግን ይጠይቀናል። ይህን አክሊል ማንም እንዳይወስድባቸው ተነግሮአቸዋል። ከፍቅር የበለጠ አክሊል የለም። አክሊል ድል ለነሡ የሚሰጥ ነው። ከሰማዕትነት ይልቅ አፍቃሪ መሆን ይበልጣል። ሰማዕትነት በሞት ማክበር ነው። ፍቅር ግን በኑሮ ማክበር ነው። ፍቅር የአክሊል ያህል ሊጠበቅ ይገባዋል። ብዙ ዝነኛ ሰዎች    

ተዘርፎ፣ ብዙ ንብረት ሲጠፋባቸው የሚቆጩት ሽልማታቸው በመሰረቁ ነው። አክሊል ልዩ ጥበቃ ያስፈልገዋል። ፍቅራችንን ጥበቃ ካላደረግንለት ይዘረፋል። ፍቅር የሚጠበቀው ከሐሜተኞች፣ ከጠላቶች፣ ከአስደንባሪዎች፣ ያሳለፍነውን ዘመንና የከፈልነውን ዋጋ ከማያውቁ ነው።

ይህን አክሊል ለሚጠብቁ የተሰጠው ተስፋ የድል ነሺዎች ሽልማት፣ አዲሲቱን ኢየሩሳሌም መውረስ ነው። መንግሥተ ሰማያት ከሞት በኋላ የምንጀምራት ሳይሆን ዛሬ የምንኖራት ናት። በሰማይ የሚጀምር የለም፣ የሚቀጥል ነው ያለው። መንግሥተ ሰማያት ፍቅር ናት። ከዛሬው ቁጥብ ፍቅር ወሰን ወደሌለው ፍቅር መጠቅለል ይህ ነው ሽልማቱ። ዛሬ ፍቅርን ያልተለማመደ በፍቅር ዓለም ለመኖር ይቸገራል።

                                                  በፍቅር እንድንኖር እግዚአብሔር ይርዳን።
                                                  

ያጋሩ