ጋብቻ የእግዚአብሔር ሥርዓት ነው። እግዚአብሔር ጋብቻን ሲመሠርት ድርጅታዊ አድርጎ ሳይሆን አካላዊ አድርጎ ነው። ይኸውም ሔዋን ከአዳም ጎን መገኘቷ እንዲሁም ክርስቶስ የቤተ ክርስቲያን ራስ እንደሆነ ባልም የሚስቱ ራስ መሆኑን በመግለጥ ያብራራዋል /ዘፍ. 2፡21፣ኤፌ. 521-33/። ራስ የሌለው አካል ምሪት፣ አካል የሌለው ራስ ተግባር አይኖረውምና ራስና አካል መባል ተመጋጋቢነትን እንጂ ብልጫነትን አያሳይም። ጋብቻ ድርጅታዊ ሲሆንና አካላዊ ሲሆን ልዩነት አለው። ድርጅታዊ ግንኙነት መዋቅር እንጂ ሕይወት የለውም፣ አካል ግን የተዋቀረ ሕይወት ነው። ድርጅታዊ ግንኙት ጥቅም እስከ ሰጠ ድረስ የሚቀጥል ነው፣ አካላዊ ግንኙት ግን ደካማውን የሚሸከም ነው። ድርጅታዊ ግንኙነት ሁሉም የራሱን ድርሻ ብቻ የሚፈጽምበት ነው፣ አካላዊ ግንኙነት ግን የራስን ድርሻ ፈጽሞ የሌላውን ማከናወን ነው። ድርጅታዊ ግንኙነት በጀት እስካለ የሚኖር ነው፣ አካላዊ ግንኙነት ግን በችግር ዘመንም አብሮ የሚካፈል ነው። ድርጅታዊ ግንኙነት መገማገም ያለበት ነው፣ አካላዊ ግንኙነት ግን መመካከር ያለበት ነው። ድርጅታዊ ግንኙነት አንዱ ያንዱ ቁስል የማይሰማው ነው፣ አካላዊ ግንኙነት ግን ሕመም የጋራ ነው።
ድርጅታዊ ግንኙነት ሙያን መስጠት የሚጠይቅ ነው፣ አካላዊ ግንኙነት ግን ራስን መስጠት የሚጠይቅ ነው። ድርጅታዊ ግንኙነት ትክክለኛ የሀብት ክፍፍል ነው፣ አካላዊ ግንኙነት ግን ሀብትን የናቀ ነው። ድርጅታዊ ግንኙነት ምን አለው? ይላል፣ አካላዊ ግንኙነት ፍቅር አለ ይላል። ድርጅታዊ ግንኙነት በጉዳት፣ በጡረታ የሚያበቃ ነው፣ አካላዊ ግንኙነት ግን እስከ ሞት የሚዘልቅ ነው። ድርጅታዊ ግንኙነት ተጠያቂ ላለመሆን መጠንቀቅ ነው፣ አካላዊ ግንኙነት ግን በጋራ ማስተካከል ነው።
ጋብቻ ድርጅታዊ ሲሆን ጥቅምን ያሰላል፣ የፉክክር ኑሮ ይሆናል፣ በገንዘብ ላይ ይመሠረታል፣ መካሰስ ይበዛበታል፣ ጽንፍ ይይዛል፣ ስለ ሀብት ብቻ ያስባል፣ ምክንያት ፈላጊ ይሆናል። አካላዊ ሲሆን ደግሞ ምን አገኛለሁ? ሳይሆን ምን እሰጣለሁ? ይላል። የራሱን ድርሻ ፈጽሞ የሌላውን ክፍተት ይሞላል፣ ይሸፍናል፣ ምሥጢር ይጠብቃል፣ ይታዘዛል፣ አሳልፎ አይሰጥም፣ ስለ መብቱ አይሟገትም፣ ሀብቴ ፍቅር ነው ይላል፣ ከምክንያት በላይ በሆነ በአጋፔ ፍቅር ይዋደዳል፣ ጉድለትን አሟልቶ ያያል፣ የተሰበረውን ቃል ጠግኖ ይሰማል። እግዚአብሔር የመሠረተው ወዳጅነት፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ትዳር አካላዊ ነው። ሕይወትና ደስታ ያለው በአካል ውስጥ ነው። አካላዊ ግንኙነትን ይጨምርልን።
እኔ የክርስቶስ ባሪያ