የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ድብብቆሹ

 ሁለት የአእምሮ ታማሚዎች በሚታከሙበት ስፍራ መንገዱ ላይ ሲተላለፉ ሁለቱም ተጋጩ ። አንደኛውም ተበሳጭቶ፡- “እያየህ አትሄድም?” ብሎ ዓይኑን አፈጠጠ ፣ እጁን ለቡጢ ጨበጠ ። ሁለተኛውም፡- “እርሱን ተወውና ይልቅስ ድብብቆሽ እንጫወት” አለው ። ያኛውም ተስማምቶ ድብብቆሽ ለመጫወት “እንጀምር” አለ ። ድብብቆሽ እንጫወት ያለውም እጁን ወደ ኋላ አደረገና፡- “በግራ እጄ ምን ይዣለሁ?” አለው ። መላሹም ፍርጥም ብሎ፡- “ሦስት ቍጥር አውቶብስ ነዋ!” ቢለው “እያየህ ነው እንዴ ?” ብሎ በጥፊ አጮለውና ተለያዩ ይባላል ። ሦስት ቍጥር አውቶብስ ከፒያሳ እስከ ሦስት ቍጥር ማዞሪያ ወይም ዘነበ ወርቅ ድረስ ትሄድ ነበር ። 

እየዩ መሄድ ግጭትን ባያስቀርም ይቀንሳል ። ሁለቱም የማያዩ ከሆነ ግን አደጋው ይከፋል ። በዚህ ዓለም ላይ እግዚአብሔርን የሚያሳዝነው እያዩ የማያዩ ሰዎች ናቸው ። ችግርን ቀምሰው ችግረኛን የማያዩ ፣ ስደት አገር ተቀምጠው ወገናቸውን የሚያፈናቅሉ ፣ ሀብት ማማ ላይ ተቀምጠው ትላንት የረዳቸውን ወገን የሚያሳድዱ ፣ በመዋጮ ደብተር ተምረው ያስተማራቸውን ሕዝብ ይጥፋ የሚሉ ፣ በድሀ አገር በጀት በልተው አገራቸውን ትውደም የሚሉ እያዩ የማያዩ ናቸውና በእነዚህ እግዚአብሔር ያዝናል ። ትምህርት በብዙ አገር ላይ ለለውጥ ረድቷል ይባላል ። ትምህርት ያፈረሳት አገር ግን የእኛ አገር ናት ። የራሳችንን ጥለን የሌሎችን ልንይዝ ስንል እርሱም አመለጠንና ባዶ እጃችንን የቀረን ሕዝቦች ሆንን ። ትምህርት ያለንን ነገር የሚያጠነክር እንጂ የሕይወት ለውጥ የሚሰጠን አይደለም ። ሕይወትን የሚለውጥ እውነትና ፍቅር ብቻ ነው ። ስስታም ሲማር ራሱን እንደ ሥነ ቁጠባ ባለሙያ ያያል ። ጨካኝም ሲማር ራሱን እንደ ጦር መሪ ይመለከታል ። መንገድ ላይ የቀሩ እውቀቶች ፣ በመስኩ ውጤት ያላመጡ ትምህርቶች ተስፋ የቆረጡ ሰዎችን ያመርታሉ ። ተስፋ መቍረጥም የጥላቻ ሰውና ዘረኛ ያደርጋል ። እነዚህ ሰዎች ብዙዎችን ከኋላቸው ማስከተት ይችላሉ ። ምክንያቱም የወደቀው የሰው ማንነት ከፍቅር ድምፅ ለጥላቻ ዋጋ ስለሚሰጥ ነው ። 

ሁለቱም አያዩም ፣ ሁለቱም ተጋጭተዋል ። አንዱ አንዱን ግን “እያየህ አትሄድም” ይለዋል ። እያየሁ ብሄድ አልጋጭም ነበር አይልም ። ለደረሰበት ነገር ሌላውን ተጠያቂ ያደርጋል እንጂ ኃላፊነት አይወስድም ። ማዶ ላይ ያለው ሰው ደጋግሞ ያየኛል ምን ፈልጎ ነው እንላለን ። ደጋግሞ እንደሚያየን ያወቅነው ግን ደጋግመን በማየታችን ነው ። እርሱም እንዲህ እያለን ነው ። በንዴት ሰዓት ቃላት ይጠፋሉ ፣ ተናደንም ግን የማይጠፋን ቃል፡- “እያየህ አትሄድም” የሚል ነው ። እያየሁ መሄድ አለብኝ ብሎ ራሱን የሚመክር የለም ። አገርንና ሕዝብን የሚጥል የትክክለኛነት ስሜት ነው ። ሕዝብ ራሱን እንዳያይ የሚደልሉት ብዙ ወገኖች አሉ ። ለሽልማት የሚያሞግሱ አዝማሪዎች ፣ ለቁራሽ የሚያወድሱ ባለቅኔዎች ፣ የአንተ ጎሣማ እያሉ ሥራን ሳይሆን ንቀትን የሚያስጠኑ ቤተ ዘመዶች ፣ የተበደልህ ነህ ፣ ደም መመለስ አለብህ የሚሉ ሽማግሌዎች ትውልድ ራሱን በማየት ካለበት ችግር እንዳይወጣ እንቅፋት ይሆናሉ ። የሌለንን እንዳለን አድርገው የሚናገሩ ነቢያት ነን ባዮች ፣ ጥፋት እየመጣ ሰላም ነው የሚሉ የአዎንታዊ ስብከት አደራጆች ፣ ዛሬ ላይ ትላንትን እንድንኖር የሚያደርጉ ጠብ አውራሾች ፣ ያልጨረሱትን ክፋት በልጆች ለመፈጸም የሚጥሩ ዕድሜ ያላስተማራቸው ምንዱባኖች አገርን ይጎዳሉ ፣ እየጎዱም እንደሆነ እናያለን ። አገር ተጎዳ ለማለት ያስቀምጥነው የሬሳ ኮታ ስንት ይሆን ? የምንቆጨው በስንት አንገት ይሆን ? ፍትሕን ለማስፈን የምንነሣው በስንት ሕፃናት መሰየፍ ይሆን ? ኮታው ስላልታወቀ ጥፋት ቀጣይ እየሆነ ነው ።

የሰለጠኑት ሕዝቦች አንድ ነገር በርቶላቸዋል ። መሳሳትን ተቀብለዋል ። በዚህም አድገዋል ። በየቀኑ የምንጠቀመው ቃል ያለንበትን ሁኔታ ያሳያል ። በሰለጠነው አገር ላይ “አመሰግናለሁ” እና “ይቅርታ” የሚሉት ንግግሮች ቀኑን በሙሉ ሥራ ላይ ናቸው ። “ከሞት የምትድኑት አመሰግናለሁና ይቅርታ የሚለውን ቃል ፈልጋችሁ ስታገኙ ነው” ብንባል ኢትዮጵያ ውስጥ ሞተን እንቀራለን ። አመሰግናለሁና ይቅርታ የሚሉ ቃላት በምድራችን ተጨቁነዋል ። አመሰግናለሁና ይቅርታ የሚሉት ንግግሮች ሥራ ፈትተው ዓመት ካመት ይኖራሉ ። ሰው የሠራውን ከማመስገን መርገም ፣ ቀና ያለውን ንቁ በብረት ዘነዘና መቅጨት ልማዳችን ሁኗል ። ይቅርታ የሚል ቃሉም ልቡም ስለሌለን የመቶ ዓመታት ቂም እንቆፍራለን ። ያላደግነው ምስጋናንና ይቅርታን ስለማናውቅ ነው ። 

በአገራችን ሁሉም ሰው ተበደልሁ ባይ ነው ። ሁሉም የተበደለ ከሆነ የበደለው ማን ነው ? ሁሉም ጭቆና ደርሶብኛል ባይ ነው ፤ ሁሉም ከተጨቆነ የጨቆነው ማነው ? ከብሶት ካልተላቀቅን እንዴት ማደግ እንችላለን ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ። የነገሥታቱንም ታሪክ ስናየው የሚጨቁን መደብ እንጂ ጨቋኝ ጎሣ የለም ። ዛሬም ጨቋኝ ጎሣ ለመፍጠር ብንጥርም ሁሉም ወገን አንድ ዓይነት ጨቋኝ መሆን አይችልም ። ከጎሣው አንዱ እናጥፋ ሲል አንዱ ተዉ ይላል ። ተጠቃሚ ጎሣም ጨቋኝ ነገድም ለመፍጠር ብንጥር እንኳ መልሶ ይጎዳናል እንጂ አይክሰንም ። 

ድብብቆሹ ከኋላ በተጠመለለው ግራ እጅ ላይ አውቶብስ ተቀምጧል በሚል መልስ ተጠናቋል ። የሚደንቀው ሁለቱም ማመናቸው ነው ። ይህም ታማሚ ያሰኛቸዋል ። አውቶብስን የሚያህል በግራ እጅ ላይ መቀመጡ ብቻ ሳይሆን ድብብቆሽ መሆኑ ገራሚ ነው ። የተደበቀው ተገለጠልኝ ባዩውም የተገለጠበትም ሁለቱም ተሳስተዋል ። የምናየውን ሳይሆን የምናስበውን ማየት እያዳበርነው የመጣ ጠባይ ነው ። እገሌ ይህን ያህል በላ እንላለን ፣ የገመትነው እንጂ እውነት ላይሆን ይችላል ። ያዘ የሚባለውም ሌብነትን እንደ ጀግንነት ቆጥሮ በልበ ሙሉነት ይቆማል ። በፍትሕና በእውነት ለመታማት የሚፈራው ወገን በትልልቅ ሌብነት ለመታማት ግን ይደፍራል ። የሌለው ነገር እየታየን ፣ በድፍረትም አየሁ የምንለውን ነገር እየተናገርን ነው ። ያላዩትን ነገር አዩ ብለንም ሌሎችንም በጥፊ እየመታን ነው ። በተሳሳተ ነገር እርግጠኛ የሆኑ ዱላዎችና ጥፋቶች ግን አሉ ። በአጭር ቃል ሁላችንም ታመናል ። 

ግመል ሰርቆ ተደብቆ መሄድ !

የራሳችንን አገር በጥብጠን የሌላውን አገር በሰልፍ ስንበጠብጥ መኖር ከጀመርን ይኸው አርባ ዓመት አለፈን ። የአገራችንን ውስጥ ልብስ መራቆታችንን ለሚወዱ ሕዝቦች ስንገልጥ ዓመታት ተቆጠሩ ። ብዙ ተጨቋኝ ሕዝቦች አሉ ። አገራቸውን ግን በኃያላኑ ፊት በየቀኑ የሚከስሱ ሕዝቦች አናይም ። በእንባ ፍቅራችንን የገለጥንላትን አገር በቀን የሻይ ሒሳባችንን አንድ ዶላር እንስጣት ሲባል ግን አልተገኘንም ። ኢትዮጵያን መውደድ በዘፈን እንጂ በተግባር አልታየም ። ለመቃወም ምክንያት አንፈልግም ፣ አንድ ብር ለመስጠት ግን ምክንያት እንፈልጋለን ። ብቻ ታመናል ። 

ምንም ባንቀበር ባንገባ መሬት ፣

አያሳፍረንም ሞተናል ማለት ።

ከድብብቆሹ ፣ ያልታየንን ተገለጠልኝ ከማለቱ ፣ የተስማማንበትን ውሸት እውነት ነው ከማለቱ እንውጣ ።

 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ