የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ድንግል ሆይ !

እንኳን ለ2014 ዓ.ም. ለጾመ ማርያም በሰላም አደረሳችሁ !ሰማይ በጠቆረበት ፣ ምድር በኃጢአት የጋለ ናስ በሆነችበት ፣ ነቢያት ከተነሡ አራት መቶ ዓመታት ባለፈበት ፣ የነፍስ ገዥ ዲያብሎስ ፣ የሥጋ ገዥ ሮማውያን በሰለጠኑበት ፣ ሃይማኖት በአጥባቂ ፈሪሳውያን ፣ በለዘብተኛ ሰዱቃውያን ፣ በመናኝ ኤሴያውያን ቡድኖች በተከፈለበት ፣ ሊቀ ካህንነት መኰንን ፣ ካህን በገዛ ቤቱ ደመወዝተኛ በሆኑበት ፤ ዓለሙ በአንድ ልዕለ ኃያል አገር ሥር በወደቀበት ፣ የሰው ልጅ በጣዖት አምልኮ መንፈሱ ፣ በሄለናውያን የኑሮ ዘይቤ ኑሮው በተቃወሰበት ፣ ምዕራብና ምሥራቅ ገመድ በሚጓተቱበት ፣ ፈራጆች በዝተው ሁሉም “እኔ ከደሙ ንጹሕ ነኝ” እያለ እጁን በሚታጠብበት ፤ በዚያ ዘመነ ጽልመት ፣ ዓመተ ፍዳ ዓመተ ኩነኔ ፣ የጌታን ዓመት በሚጠባበቁበት ፣ ዓመተ ሰብእ መቼ ያበቃ ይሆን ? ተብሎ በሚናፈቅበት በአስጨናቂው ወራት …..ነቢይ ጠፍቶ ምክር ፣ ካህን ጠፍቶ ምሥጢር ጠባቂ ናዛዥ ፣ ንጉሥ ጠፍቶ መንጋ ሰብሳቢ ባልተገኘበት ፤ በዚያ የመርዶ ዘመን ጆሮዎችሽ የምሥራች ስለ ሰሙ ፣ ዓለሙ ሁሉ የሚሰማውን የምሥራች ያንቺ ጆሮዎች ሁሉን ወክለው ስለ ሰሙ ፣ ዓለሙ ሁሉ ወጥቶ ሊቀበለው የሚገባውን ጌታ በማኅፀንሽ ስለተቀበልሽው ፣ በአንቺ ድልድይነት ሰውና እግዚአብሔር ቤተ ዘመድ ስለሆኑ ፣ ዘላለማዊ አምላክ ደኃራዊ ሥጋን ተዋሕዶ አንቺ የወልድ መቅደሱ ፣ ማኅፀንሽ መንበረ ፀባዖት ፣ የንጉሡ የክብር ዙፋን ስለሆነ ማርያም ሆይ ደስ ይበልሽ !ሰማይ የሰማያት ሰማይ የማይወስኑት በማኅፀንሽ ስላደረ ፣ ከሰፊው ዓለም ይልቅ ያንቺን ጠባብ ማኅፀን ስለመረጠ ፣ ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነሥቶ አማኑኤል ስለተባለ አንቺን የመረጠ ቡሩክ ነውና ሰላም እለዋለሁ ! ኪሩቤል ቢሸከሙት አያዩትም ፣ አንቺ ግን በዓይኖችሽ ያየሽው ነሽና ከኪሩቤል ትበልጫለሽ ! ድንግል ሆይ ደስ ይበልሽ ! የዘላለም አምላክ በማኅፀንሽ የዕለት ፅንስ ሆነ ። ዘላለምና ዕለት በአንድ ላይ የተገናኙት ባንቺ ማኅፀን ነው ። ዘመን ካለ ዘላለም ፣ ዘላለም ካለ ዘመን የለም ። ሰውና እግዚአብሔር የታረቁብሽ የምሕረት አደባባይ ነሽ ። የልጅሽ ጌትነት የታየው ያንቺ ክብረት ይታየዋል ። ልጅሽን የሚወድ ይወድሻል ። ለምንና እንዴት የሚሉ ጥያቄዎች የተገዙልሽ ፣ “በበረት እንድወልድ ለምን ወሰነ ?” ብለሽ ያላዘንሽ ፣ እንዴት ይሆናልን “ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም” በሚል ቃለ አሚን የረታሽ አንቺ ነሽ ። እመ ኢየሱስ ፣ እኅተ ኢየሱስ ሁነሽ ባሕረ እሳት ሲከፈል “ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች” ብለሽ የዘመርሽ ሐዲስ ማርያም ሰላምታ ይገባሻል ! ዛሬም እንደ ጥንቱ ችግራችን አንቺ በሥጋ ከነበርሽበት ዘመን ጋር ተመሳስሏል ። የምልጃሽ በረከት አብሳሪ መልአክን ይላክልን ። ፍልሰትሽ ትንሣኤያችንን ፣ ዕርገትሽ የምእመናንን መነጠቅ ያስታውሳል ። የሆነልሽ ግን ከሆነልን በላይ ነውና ክብር ይገባሻል ! ድንግል ሆይ …..

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ