የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጀምበር ሳለ ሩጥ

  

ዩክሬናውያን፡- “የስኳርን ጣዕም የምታደንቀው ሎሚን ስትቀምስ ብቻ ነው” ይላሉ ። 

 

“ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኸ” ይባላል ። ጅቡ አጥር ጥሶ ፣ በረት ሰብሮ ፣ ጠቦት ሰርቆ ከሄደ በኋላ ውሻ ይጮኻል ። ሁሉም ውሻ ሳይሆን ፈሪ ውሻ ይህን ያደርጋል ። መጀመሪያ ቢጮህ ረዳትም ምስጋናም ፣ ጉርሻም ያገኝ ነበር ። ካለቀ በኋላ በመጮኹ ግን ረዳትም ፣ ምስጋናም ፣ ጉርሻም አያገኝም ። በኩራት ከመንጎማለል በውሻነቱ ቅልስልስነት ለመኖር ይገደዳል ። በመጮኹና ባለመጮኹ መካከል ልዩነት የለም ። ሁሉም ነገር አልቋል ። ውሻው ጅቡ ሲመጣ ያልጮኸው ብቻዬን ብጋፈጥስ ? ብሎ ስለፈራ ነው ። ጅቡም ውሻውን ያልነካው ስለፈራ ነው ። ደግሞም ለጅቡ ረሀብ ከውሻው ጠቦቱ ይሻለዋል ። ጅቡ አጥር ጥሷል ፣ በረት ሰብሯል ፣ ንብረት ሰርቋል ። በጥንቱ የመጽሐፍ ቅዱስ ትርጉም “ገንዘብ አትውደዱ” የሚለውን “ከብት አትውደዱ” ይለዋል ። ከብት ጥንታዊ የሀብት መለኪያ ነው ። ውሻ ጅቡን ፈራ ፣ ጅቡም ውሻን ፈራ ። የላይ ፈሪና የታች ፈሪ ፣ ሁለቱም ፈሪዎች ፣ ሁለቱም ራሳቸውን የፈሩ ናቸው ። ውሻ ፈርቼ ነው ከማለት አንድ ቀን ባለቤቱ አርዶት የሚበላውን ከብት ዛሬ ጅብ በላው ብዬ ለምን ጠላት አተርፋለሁ? ሁለቱም ሞት ነው ብሎ ይሆናል ። ብቻ ውሻ የሚጮኸው ስለፈራም ነው ። 

 

የመጀመሪያ ጩኸት የፍርሃት ቢሆን እንኳ የድፍረት ያህል ነው ። ለንብረቱ አለሁ የሚል ባለቤቱ ይወጣለታልና ። መጀመሪያ የጮኸ ገላጋይ አያጣም ። ሁሉም ነገር ካለቀ በኋላ ጩኸት ከወቀሳና ከከሰሳ ለመዳን ይመስላል ። ውሻው አሁን ባይጮህም ሲነጋ ከብት እንደ ተሰረቀ ይታወቃል ። የመጀመሪያ ጩኸት የንቁ ሲሆን የመጨረሻ ጩኸት ግን ሪፖርት ነው ። ውሻ ግን ሥራውን አክብሮ ሳይሆን ሐሜት ፈርቶ መጨረሻ ላይ ይጮኻል ። ለመልካም ነገር አይረፍድም ቢባልም ላለፈ ሕይወት ግን ይረፍዳል ። አልረፈደም የሚባለው ከዚህ በኋላ ለውሻው ሳይሆን ለባለቤቱ ነው ። አጥሩን ማጥበቅ ፣ በረቱን መግጠም ፣ እረኛውን መሾም አለበት ። 

 

ውሻን ካነሣን ዘንድ ውሻ የሰውን ስሜት ይጋራል ። ከቅርብ ዘመናት ወዲህ ካንጀት የሚጮህ ውሻ እየጠፋ ነው ። የባለቤቱን ስሜት ይጋራልና ሰውዬው ምን ቸገረኝ ? ሲል ውሻውም ምን ቸገረኝ ? ይላል ። ጮኬ ነበር ለማለት መጮኽ እየበዛ ነው ። “ካንጀት ካለቀሱ እንባ አይገድም” ይባላል ። ካንጀት ቢሆን ብዙ ነገሮች በተስተካከሉ ነበር ። ምልክቱ እንጂ እውነቱ ጠፍቷል ። ምንደኛ እንጂ እረኛ ተሰውሯል ። ብዙ ያመለጡን ነገሮች አሉ ፣ ካለፉ በኋላ ግን ጩኸት አይጠቅምም ።

 

በኑሮህ ተመርረህ ለማን ልተንፍሰው ብለህ ይሆናል ። ዓለመ ሰብእን ሳይሆን ዓለመ መላእክትን ጠብቀህ አጉረምራሚ ሆነሃል ። አንደኛውን ቤት ጀምረህ ሁለተኛውን መሬት ስላልገዛህ ፈተና በዛ እያልህ ይሆናል ። ኑሮህ ከበቂ በላይ መሆኑ የሚገባህ ጤናህ የታወከ ቀን ነው ። አሁን ጤናን ስጠኝ ለማለት ስለ ጤናህ ያላመሰገንህበት ዘመን ፊትህ ድቅን ይልብሃል ። የራስህን ጫና ልጆችህ ላይ እየጫንህ በረባ ባልረባ ታስጨንቃቸው ይሆናል ። እነርሱም እኛን ካየ ይበልጥ ይበሳጭብናል ብለው ቶሎ ከፊትህ እልም ይሉ ይሆናል ። የሚያጭበረብሩህን ወጣቶች ፣ የሚያዋርዱህን የመንደር ልጆች ስታይ የልጆችህ ቡሩክነት ይታይሃል ። የእግዚአብሔር ትእዛዝ ልጆች ወላጆቻቸውን እንዲያከብሩ ብቻ ሳይሆን ወላጆችም በረባ ባልረባ ነገር ልጆቻቸውን እያንዳይቆጡም ይከለክላል ።  ኤፌ. 5 ፡ 4 ፤ ቈላ . 3 ፡ 21 ። በሥራ የሚራዱህ ላያረኩህ ይችላሉ ። ምክንያቱም ሥራው ላንተ ግማሽ ኑሮህ ነው ። ለእነርሱ ግን እንጀራቸው ብቻ ነው ። ያከራዩት ሙያቸውን ነው ፣ የተሻለ ሲያገኙ ለመሄድ ዝግጁ ናቸው ። አጠገብህ ለነበሩት ሙሉእነትን ፈልገህ ስትሸኛቸው ቀጥለው የሚመጡት እነዚያን የሚያስመሰግኑ ናቸው ። ከዚያ “ትሻልን ትቼ ትብስን አገባሁ” ትላለህ ።

 

ዝቅ ብሎ እግር የሚያጥቡህን አባቶች ፣ በትሕትና የሚቀርቡህን አገልጋዮች እንደ ተራ ሰው ታያቸው ይሆናል ። እነርሱ ግን ሁሉን አይተው ሁሉን ንቀውት ትሑት የሆኑ ናቸው ። በጎነታቸው ላይታይህ ፣ ላንተ መንፈሳዊ ጤንነት የሚጨነቁት ሚዛን ላይደፋልህ ይችላል ። ሥጋህን ለጥጋብ በልተው ፣ ለጥርሳችን ጥንካሬ ደግሞ አጥንቱን እንስበረው የሚሉ ፣ በሥርዓቱ ቆዳህን መግፈፍ ሳይሆን ልገሽልጠው ብለው የሚጨክኑ ሲመጡብህ ያን ጊዜ የገፋሃቸው አባቶችህ ትዝ ይሉሃል ። ዕድል ነውና ዳግም ላታገኛቸው ትችላለህ ። ፍቅርን የሚሰጡህ ቤተሰቦችህ ፣ ወጥተህ እስክትገባ የማያምኑህ ፣ ምነው ሰላም በለን እንጂ እያሉ ድምፅህን የሚናፍቁትን እንደ ዕዳ ታያቸው ይሆናል ። መንገድ ስትወድቅ ልጄን ብለው የሚጮኹ እናቶች ፣ ከብበው አየር እንድታገኝ የሚያራግቡልህ የአገርህ ልጆች ድሮም አበሻ ብለህ ታረክሳቸው ይሆናል ። ገባህ ወጣህ ፣ ተኛህ ሞትህ ትዝ የማይላቸው ፣ ካንተ ይልቅ ለውሻ ክብር የሚሰጡ ፣ አደናቅፎህ ስትወድቅ በሩቅ የሚሸሹ ወገኖች ያሉበት አገር ስትሄድ ወይ አገሬ ብለህ ታመሰግናለህ ። 

 

“ቢመታኝም አልፈታውም ፣ ቃል የገባሁት እስከ ሞት ላልተወዉ ነው” ብላ የቻለችህ ሚስትህ ትሄዳለች ። አንተ ለጉድ ትቀመጣለህ ። ያን ጊዜ “የሞትኩት እርስዋ የሞተች ቀን ነው” እያልህ በኀዘን ትቀመጣለህ ። ልጆችህን እንኳን ለመምታት በሙሉ ዓይንህ ለማየት ትፈራለህ ። መጨረሻህ እንደ ውሻ መባረር መስሎ ይሰማሃል ። የሚስትህን ደግነት ሞት ከነገረህ መካስ አትችልም ። ቃሉ ይንገርህ እንጂ የደጎችን ደግነት ሞት አይንገርህ ። የከፉ ክፉዎችን ስታይ የተሻሉ ክፉዎችን ትናፍቃለህ ። ከክፉም ክፉ ይመረጣል እንዲሉ ። 

 

ብቻ የገጠሙህ መራራ ሰዎችና ነገሮች ያላጣጣምከውን ደግነትና ፍቅር ያስታውሱሃል ። እንደ ቀላል የቆጠርካቸውን እነዚያን ፍቅሮችና ክብሮች የሰጡህ በሕይወት ካሉ ዛሬ አመስግናቸው ። ከሌሉ እነርሱን የሚወክል ጌታ አለና ይቅርታ ጠይቀው ። አሁን ከቀደሙት ቢያንሱም ያሉትን መልካም ሰዎችና ዕድሎች ተንከባከባቸው ። ፀሐይ ብርሃንዋ እየቀነሰ እንደሚሄድ ዕድሜ ሲገፋም ወዳጆችና ዕድሎች እየቀነሱ ይመጣሉ ። ያሉትን መንከባከብ ብልህነት ነው ። 

 

እባክህ ወዳጄ የስኳርን ጣዕም የሚነግርህ የሎሚ ምሬት አይሁን !

 

በደስታ ዋሉ ! 

 

የብርሃን ጠብታ 3 

 

 

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

 

ነሐሴ 29 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ