“እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤…የማይጨቃጨቅ ነገር ግን ገር የሆነ” 1ጢሞ. 3፡2-3 ።
ማር ብቻ አትሁኑ ልሰው እንዳይጨርሷችሁ ፣ እሬትም አትሁኑ እንዳይተፏችሁ ይባላል ። ሚዛናዊ መሆን የምድር ኑሮን ቀላል ያደርጋል ። የሚጨቃጨቅ ሰው የሚኮሰኩስ ነው ። ማቅ ቢሞቅም ይኮሰኩሳልና ምቾት አይሰጥም ። ተጨቃጫቂም ሰው ቢያበላ ቢያጠጣ ያሳቅቃልና ዕረፍት አይሰጥም ። ተጨቃጫቂ ፋታ የማይሰጥ ነው ፣ ገራም ለጊዜና ለእግዚአብሔር እየተወ በሰው መለወጥ የሚያምን ነው ። ተጨቃጫቂ ትላንት ላይ የሚቆም ሲሆን ገራም ነገን የሚያይ ነው ። ተጨቃጫቂ ስህተትን ፈላጊ ሲሆን ገራም ስህተትን የሚሸፍን ፣ እግዜር በምድር ነው ። ተጨቃጫቂ እንደ ምዕራብ የፀሐይ መጥለቂያ ነውና ልብን ያሳዝናል ፣ ገራም እንደ ምሥራቅ የፀሐይ መውጫ ነውና ልብን ያስደስታል ።
መጨቃጨቅ አትኩሮ ማየት ነው ፣ ገራምነት ማለፍ ነው ። መጨቃጨቅ አለማለፍ ነው ፣ ገራምነት ይቅርታ መስጠት ነው ። መጨቃጨቅ ይቅርታ ሲባሉም አለማወቅ ነው ፣ ገራምነት ለሰው ሁሉ ይቅርታ ሰጥቶ መኖር ነው ።መጨቃጨቅ እኔ ብቻ ተጎዳሁ ባይነት ነው ፣ ገራምነት ላስቀይም እችላለሁ ማለት ነው ። ተጨቃጫቂነት ሕመምን አለመርሳት ነው ፣ ገራምነት የበለጠውን እያሰቡ ማመስገን ነው ። ተጨቃጫቂነት ሰው ሁሉ ችግር አለበት ብሎ ማሰብ የሚወልደው ነው ፣ ገራምነት ሰው ከነክፋቱ ጥሩ ነው ብሎ መቀበል ነው ። ተጨቃጫቂነት ነገር መቆርጠም ፣ ቃላት መሰንጠቅ ነው ፣ ገራምነት አርሞ መስማት ነው ። ተጨቃጫቂነት ወዶ መታወክ ነው ፣ ገራምነት የልብ ዕረፍት ነው ። ተጨቃጫቂነት የያዙትን አለመልቀቅ ነው ፣ ገራምነት መንገድ አጋምሶ መቀበል ፣ ሌሎችን ከነአስተሳሰባቸው ማስተናገድ መቻል ነው ። ተጨቃጫቂነት ሆዳምነት ነው ፣ ገራምነት በመጠን መኖር ነው ። ተጨቃጫቂነት በብዛት ማመን ነው ፣ ገራምነት በበረከት ማመን ነው ።
ተጨቃጫቂነት ሁሉን ነገር አጨልሞ ማየት ነው ፣ ገራምነት የተሻለ ቀን መጠበቅ ነው ። ተጨቃጫቂነት ማሩን አምርሮ ፣ ወተቱን አጥቁሮ ማየት ነው ። ገራምነት ነገርን በልኩ የሚያይ ነው ። ተጨቃጫቂነት ወንድሙ አጉረምራሚነት ነው ፣ የገራምነት ወንድሙ የዋህነት ነው ። ተጨቃጫቂነት ድንበሬ ተነካ ማለት ነው ፣ ገራምነት መነካካት ተፈጥሮ ነው ብሎ የሚያምን ነው ። ተጨቃጫቂነት አይረካምና አመንዝራነት አለው ፣ ገራምነት የከተማ መናኝ መሆን ነው ። ተጨቃጫቂነት ወርቅ አለመጥገብ ነው ፣ ገራምነት በመስጠት መደሰት ነው ። ተጨቃጫቂነት ወገናዊ ነው ፣ ገራምነት ግዛቱ ሰፊ ነው ። ተጨቃጫቂነት ነቃፊነትና ቊጣ የሚባሉ ሁለት ክንፎች አሉት ፣ ገራምነት አመስጋኝነትና ትዕግሥት የሚባሉ ሁለት እግሮች አሉት ። ተጨቃጨቂነት ለመብረር ይሻል ፣ ገራምነት ለመራመድ ይፈልጋል ። ተጨቃጫቂነት በራሱ ይናደዳል ፣ ገራምነት በእግዚአብሔር ይደሰታል ።
ተጨቃጫቂነት አምባገነን ነው ፣ ገራምነት ትሕትና ነው ። ተጨቃጫቂነት ራሱ ወድቆ የልጆቹን መቀደስ የሚሻ ነው ፣ ገራምነት ምሳሌ መሆን ነው ። ተጨቃጫቂነት ያለፈውን ስህተት የሚቆጥር ነው ፣ ገራምነት ያለፈውን ጥሩ ጊዜ የሚያስብ ነው ። ተጨቃጫቂነት የሚያስበው ያጣውን ነው ፣ ገራምነት ያገኘውን የሚቆጥር ነው ።
ገራምነት ስሜት አልባ ሁኖ ስድብና ነቀፋን አይሰማኝም ማለት አይደለም ።ገራምነት እንደ ሞኝ ተቆጥሮ ሞፈር ከደጁ ሲቆረጥ ማየት አይደለም ። ገራምነት እግሬ ላይ ቆማችኋል ብሎ ለመናገር እየታመሙ ዝም ማለት አይደለም ። ገራምነት ልብሱን ጨርሰው ቆዳውን ሲገሸልጡት አይበርደኝም የሚል አይደለም ። ገራምነት ሁልጊዜ ይቅርታ ጠይቅ ተብሎ ያለ ጥፋቱ የሚረገጥ አይደለም ። ገራምነት ሌሎች ያሻቸውን ሲያደርጉ ድንበራቸውን የማያሳውቅ አይደለም ። ገራምነት ስለ እርሱ ሌሎች እንዲናገሩለት የሚፈልግ የውክልና ኑሮ ፈላጊ አይደለም ። ገራምነት እርሱ ተበድሎ ይቅርታ የሚጠይቅ አይደለም ። ገራምነት ሰዎችን ካጣሁ ምን እሆናለሁ ብሎ ቢጭኑበት አህያ ፣ ቢለጉሙት ፈረስ መሆን አይደለም ። ገራምነት ውሻውም ዶሮውም ሲነክሰው የሚስቅ አይደለም ።
መጨቃጨቅን ብቻ መተዉ በቂ አይደለም ፣ ገራም መሆን ይገባል ። ገራምነት ቀጥሎ ያለው ነው፡-
1- ሰውን ዕድሜ እንደሚያስተምረው ፣ እግዚአብሔር እንደሚለውጠው ያምናል ።
2- ነገ የተሻለ እንደሆነ ይቀበላል ።
3- ያየውን ለማሳየት ፣ የሰማውን ለማሰማት የማይሻ ነው ።
4- የጨለመውን ልብ በፈገግታና በመልካም ቃል የሚያበራ ነው ።
5- በሁለት ዓይን ሰዎችን የማያይ ፣ በሁለት ጆሮ ሰዎችን የማይሰማ ነው።
6- ሲበድል ማሩኝ ፣ ሲበደል ይቅርታ ለማለት የማይቸገር ነው ።
7- ይቅርታ ለማድረግ የሚታገል ሳይሆን የይቅርታ ሰው ለመሆን የሚሻ ነው ።
8- ልበድል እችላለሁ ብሎ የሚያስብ ነው ።
9- የደረሰብኝ ሌሎች ከደረሰባቸው ትንሽ ነው ብሎ የሚያመሰግን ነው ።
10- ሰው መልካም ነው የሚያስብ ነው ።
11- የሰዎችን ግድፈት አትኩሮ አለማየትና አጥብቆ አለመስማት ነው።
12- እንደ እርሱ የማያምነውንና የማያስበውን ሰው መውደድ ነው ።
13- ለመብላት የሚያስፈልገው መሰብሰብ ሳይሆን ፈቃደ እግዚአብሔር መሆኑን የሚያምን ነው ።
14- ሰውን መልአክ አድርጎ የማይስል ነው ።
15- ምን ጎደለኝ ? ሳይሆን ምን አለኝ ? የሚል ነው ።
ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል ።
1ጢሞቴዎስ 42
ጥር 23 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.