የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 
መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ገብር ኄር

የትምህርቱ ርዕስ | ገብር ኄር

                                             ዓርብ፣ መጋቢት 12/ 2007 ዓ.ም.
መኑ ውእቱ ገብር ኄር  –  ታማኝ አገልጋይ ማነው?
(ማቴ. 25፡14-30)
የዐቢይ ጾም ስድስተኛው እሑድ ገብር ኄር ወይም ታማኝ አገልጋይ ተብሎ ተሰይሟል፡፡ አገልጋዮች ለአገልግሎቱ ባለቤት ሳይሆኑ ባለአደራ መሆናቸው የሚዘከርበት፣ ለታማኝ አገልጋዮች ማበረታቻ የሚሰጥበት፣ ሐኬተኛ አገልጋዮች ለንስሐ የሚጋበዙበት ቀን ነው፡፡ በዕለቱ የሚዘመረው መዝሙር ቅዱስ ያሬድ እንደ ደረሰው፡- “መኑ ውእቱ ገብር ኄር – ታማኝ አገልጋይ ማነው?” የሚል ነው፡፡ የዕለቱም የወንጌል ምንባብ በማቴ. 25÷14-30 ያለው ነው፡፡ ይህ መጠይቅ ከትላንቱ ይልቅ የዛሬ አንገብጋቢ ጥያቄ፣ መልስ የሚያሻው እንቆቅልሽ ሆኗል፡፡ ታማኝ አገልጋይ ማነው?
ዛሬ ውድ ነገር ገንዘብ ወይም ዕውቀት አይደለም፣ የዛሬ ውድ ነገር ሥልጣን ወይም ቆንጆነት አይደለም፡፡ ዛሬ የማይገኘው ውድ ነገር ታማኝነት ነው፡፡ ብዙ ነገሥታት ታማኝ ሹም አጥተዋል፣ ብዙ ባለጠጎች ታማኝ መጋቢ ተቸግረዋል፡፡ ሰው፣ ሰው አጥቷል፣ እግዚአብሔርም ሰው አጥቷል፡፡ እንደ ቃሉ የሚኖር፣ ክብር ያለው፣ አደራ የሚከብደው ታማኝ አገልጋይ ማግኘት ጭንቅ ሆኗል፡፡ ልብ አድርጉ! አገልጋይ ሞልቷል፡፡ ታማኝ አገልጋይ፣ ራሱን ለወገኑ መሥዋዕት ማድረግ የሚያረካው በጎ ባሪያ ግን ጠፍቷል፡፡

“የጥበብ አገሯ ወዴት ነው?” እንደ ተባለ የታማኝ አገልጋይ አገሩ ወዴት ነው? በሚያስብል ዘመን ላይ ነን፡፡ በአገልጋዮች እየተሰናከሉ ከቤተ ክርስቲያናቸው የኮበለሉ፣ በዚያም ከተሰደዱበት መልካም አገልጋይ አጥተው ግራ የተጋቡ፣ ከእባብ ጉድጓድ አምልጠው ዘንዶ ጉድጓድ የገቡ ብዙዎች ናቸው፡፡ እነዚህ ሁሉ የዘወትር የፍለጋ ድምፃቸው፡- “የቸር የአገልጋይ አገሩ ወዴት ነው?” የሚል ሆኗል፡፡
የግብፅ ኦርቶዶክስ አባቶች የሚያስቀና እረኝነት እንዳላቸው እንሰማለን፡፡ አንድ ምእመን ለአንድ ሰንበት ከቤተ ክርስቲያኑ ሲቀር ቄሱ ሄዶ ይፈልገዋል፡፡ መክሮት ችግሩን ተካፍሎት በሁለተኛው ሰንበት ካልመጣ ጳጳሱ ፍለጋ ይሄዳል፡፡ ከዚህ በኋላ ፓትርያርኩ እንዳይመጡ ሰግቶ ወደ ቤተ ክርስቲያኑ ይሄዳል፡፡ በእውነት ይህንን ዓይነት እረኝነት እንኳን ልናደርግ ሰምተን የምናውቅ አይመስልም፡፡ በርግጥ ግብፃውያኑ በብዙ ውድቀት አልፈው ዛሬ የአንድ ነፍስን ዋጋ አውቀዋል፡፡ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ምርትና ግርድን ሳትለይ ትክክለኛ አማኟ 12 ሚሊየን ምእመን ነው፡፡ የእኛን 45 ሚሊየን ሕዝብ የሚተካ አማኝ አላቸው፡፡ አንድ የሥነ መለኮት መምህር፡- ‹‹ኢትዮጵያ በቀንድ ከብት ብዛት ከአፍሪካ አንደኛ ናት፤ በጥራት ግን የመጨረሻ ናት፣ እንዲሁም በአማንያን ብዛት ቤተ ክርስቲያንን የሚያህላት የለም፤ ነገር ግን በጥራት መጨረሻ ነን›› ብለዋል፡፡ ምእመኑ ቤተ ክርስቲያንን የሚጎበኛት ክርስትና ሲነሣና በሞቱ ቀን ሲሆን እርሱም ሰው ተሸክሞት ሳያውቀው ነው፡፡ ይህን ያህል ምእመን ሄደ እንላለን፡፡ ለሄደው ስንቆጭ ያለውም የእኛ አለመሆኑን አልተረዳንም፡፡ በዚህ ሁሉ ዘመን ስብከት ስለሃይማኖቱ የሚሞት ሳይሆን ሃይማኖቱን እንደ አክራሪ እስላም በሰይፍ የሚያስከብር ትውልድ ነው ያፈራነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ወንድ እንጂ አማኝ እያጣች ነው፡፡ ወጣቱ ሞቶ አይቀበርም ጴንጤ ነው እየተባለ ክርክር ሲነሣ ንስሐ አባት መጥተው ምስክርነት ሰጡ፡- ‹‹የእኛው ነው ከሦስት ቀን በፊት ጫት ሲቅም ዓይቼዋለሁ›› ብለዋል፡፡ በእውነት እውነትን በትክክል ያወቀ አገልጋይ ማን ይሆን?


አገልጋዮች ሥራ እንደ ጨረሰ ተቀምጠናል፡፡  መኸሩ ግን ብዙ ሆኖ እጨዱኝ፣ ሰብስቡኝ እያለ አዝመራው ላይ ረግፎ ቀርቷል፡፡ ወገናችን ከነጥማቱም ይሞታል፡፡ ሥራ ያጣ መነኲሴ ቆቡን ቀዶ ይሰፋል እንደሚባለው ሥራ ያጡ አገልጋዮች ጉባዔ መሥራት ቢያቅታቸው ጉባዔ ማፍረስ አላቃታቸውም፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ወደኋላ እየጋለቧት መንፈሳዊት ሳይሆን ባሕላዊት እያደረጓት ነው፡፡ ሁልጊዜ የምናስበው ስለጠፉ ምእመናን ነው፣ ስለጠፉ አገልጋዮች የምናስበው መቼ ነው?
ሦስቱ ጠፊዎች
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ጠፉ ሦስት ወገኖች በሉቃስ ወንጌል 15 ላይ ተናግሯል፡-
1.     የጠፋ በግ
2.    የጠፋ ድሪም
3.    የጠፋ ልጅ
በጉ የጠፋው በሞኝነት ነው፡፡ ዛሬም እረኛ አያስፈልገንም ብለው የጠፉ ብዙ ሞኞች አሉ፡፡ አገልጋዩ ለራሳቸው ጥቅም እንደሚፈልጋቸው ያልተረዱ፣ ነገ የአገልጋይን መቃብር ፈልገው እንዲያለቅሱ የተፈረደባቸው ወገኖች አሉ፡፡ አገልግሎት ለእውነተኛ አገልጋዮች ከባድ ሲሆን ለሐሰተኞቹ ግን በጣም ቀላል ነገር ነው፡፡
ሁለተኛው ጠፊ የጠፋው ድሪም/ገንዘብ ነው፡፡ ከቤት እንዳልወጣ እርግጥ ነው፡፡ እንደ በጉ በምድረ በዳ፣ እንደ ጠፋው ልጅ በባዕድ አገር ሳይሆን ሳይርቅ እቤት ውስጥ የጠፋ ነው፡፡ ድሪሙ ባይርቅም እዚህ ነኝ ብሎ ራሱን ማስረዳት የእርዳታ ድምፅ ማሰማት አይሆንለትም፡፡ እነዚህ በእግዚአብሔር ቤት የጠፉ አገልጋዮች ምሳሌ ናቸው፡፡ ጠፍቻለሁ ብለው እንዳያስቡ ቀዳስያን፣ ዘማርያን፣ ሰባኪያን ናቸው፡፡ በገዛ ነፍሳቸው ፈርደው የነፍስ አደራ የተጣለባቸው ናቸው፡፡ “ለአንቱ ማደሪያ የሎት ከነ አህያዎ መጡ” እንዲሉ ለራሳቸው መግቢያ ሳይኖራቸው የመንግሥተ ሰማያትን በር ለሰዎች እንከፍታለን የሚሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ አቋማቸውን የሚመዝኑት በቦታ እንጂ በእውነት አይደለም፡፡ የጠፉ ሰዎች በዓለም ብቻ ሳይሆን በቤተ ክርስቲያን ውስጥም አሉ፡፡ የኖሩበትን ዘመን እየቆጠሩ እኛ ባቀናነው መድረክ ማን ይፈነጭበታል? የሚሉ ድንጋይም ካስቀመጡት ሺህ ዘመን እንደሚቆጥር የዘነጉ ብዙ ድሪሞች አሉ፡፡
ሦስተኛው ጠፊ የጠፋው ልጅ ሲሆን በምርጫ የጠፋ ነው፡፡ ዛሬም በምርጫ የጠፉ አውቀዋለሁ፣  በብዙ ጸጋ አገልግያለሁ ግን … እያሉ የጠፉ ወገኖች አሉ፡፡ ጌታ ግን ሁሉንም ይፈልጋቸዋል፡፡
ውኃ ቢያንቅ
በእውነት ታማኝ አገልጋይ ማነው? ስለ ሐሰተኛ አገልጋዮች ስናዝን ታማኝ አገልጋዮችን እንንከባከብ ይሆን? በምእመናን ተስፋ እየቆረጡ ሐኬተኛ ባሪያ የሆኑ ብዙ አገልጋዮችን አሉ፡፡ ሐኬተኛ አገልጋዮችን የሚያመርቱ ራሳቸው ምእመናንንም ናቸው፡፡ አገልጋዮችን ሆን ብለው በዝሙት የሚያሰናክሉ፣ የእግዚአብሔርን ቤት በጭካኔ የሚያፈርሱ ስንት ምእመናን እንዳሉ እናውቃለን፡፡ ስለ አገልጋዮች ሲተች እሰይ ይበልልኝ የሚሉ ስለራሳቸው ግን “እኔስ ታማኝ በግ ነኝ ወይ?” ብለው የማይጠይቁ ብዙዎች ናቸው፡፡ ወገኖቼ ሁላችንም ጠፍተናል፡፡ እግዚአብሔር ያግኘን!
“ውሃ ቢያንቅ በምን ይውጡታል
ምላጭ ቢያብጥ በምን ይበጡታል”
ያነቀንን ነገር የምናወርደው በውኃ ነው፡፡ ውሃ ራሱ ቢያንቀን ግን በምን እናወርደዋለን፡፡ መፍትሔ የሚሰጡ አገልጋዮች ችግሮች ከሆኑ መፍትሔ የት ይገኛል? ያበጠውን የምንበጣው በምላጭ ነው፡፡ ምላጭ ራሱ ካበጠ ግን በምን መግሉንና የተበከለውን ደም እናፈሰዋለን? ወንጌሉን የወንጀል መሥሪያ ካደረግነው ወንጀልን በምን እናርቃለን? ዘመናችን ጸሎት ያስፈልገዋል፡፡ እንደ ዮናስ ኮብላይ አገልጋዮች በመርከቡ ተሳፍረው ይኸው እንናወጣለን፡፡ እነዚህ ኮብላይ አገልጋዮች፣ እግዚአብሔርን እንደ አሳቡ ሳይሆን እንደ አሳባቸው ማገልገል የሚሹ ትዕቢተኞች ማረኝ ብለው በትሕትና ካልወደቁ በቀር ነውጡ ይቀጥላል፡፡
ወደ ልዩ ልዩ አብያተ ክርስቲያናት የሚነጉደው ወጣት ቁጥር የለውም፡፡ ወጣቱ የነፍስ ዕረፍት ናፍቆት የሄደ ይመስላል፡፡ ነገር ግን ሁሉም እርስ በርሱ ሆኖ ሰባኪው ወጣት ተከታዩ ወጣት ሆኖ በጭብጨባ የአገልጋዩን ስሜትና ፉከራ አድንቆ በሚችለው ጌታ ሳይሆን እችላለሁ በሚል በራሱ ጉልበት ታምኖ ይወጣል፡፡ ብዙ አብያተ ክርስቲያናት የክርስቲያን ሥነ ልቡና ተቋማት እየሆኑ ስለ ኃያል አምላክ ሳይሆን ስለ ኃያል አገልጋይ የሚሰበክባቸው ሆነዋል፡፡ በእውነት ቸር አገልጋይ ማነው?
የአፍሪካ ወንጌል ተብሎ ስለሚጠራው ምን ያህል ታውቃላችሁ ድሀውን የአፍሪካ ሕዝብ የሚያታልሉ ሰባክያን፡- ጌታን ብትቀበል ታገኛለህ፣ ይሳካልሃል፣ ትበለጽጋለህ፣ አትታመምም፣ ያለ ችግር ትኖራለህ ይላሉ፡፡ እግዚአብሔር ይሰጣል፣ እንደሚባርክም እናምናለን፡፡ ጌታችን ግን ወደዚህ ዓለም የመጣው በነፍሳችን ሊያበለጽገን ነው፡፡ ቃሉም፡- “ በክርስቶስ በሰማያዊ ስፍራ በመንፈሳዊ በረከት የባረከን የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ አባት ይባረክ” ነው የሚለን (ኤፌ. 1÷3)፡፡ የብሉይ ኪዳን በረከቱ ምድራዊ ነበር፣ የአዲስ ኪዳን በረከቱ ግን መንፈሳዊ ነው፡፡ እግዚአብሔር በሥጋም ሊባርከን ይችላል ግን ክርስቶስን የማመናችን እርግጠኛ ምልክቱ ምድራዊ ብልጽግና አይደለም፡፡ ክርስትና ከመስቀል ጋር መሆኑንም መዘንጋት አይገባንም፤ ደግሞም እግዚአብሔር የእጃችንን ፍሬ ይባርካልና መሥራትን ልንዘነጋ አይገባም፡፡
በቴሌቪዥን ሲተላለፍ የሰማሁትን ሰባኪ ሁላችሁም ሰምታችሁት ሊሆን ይችላል፡፡ በፕሮቴስታንት ተቋማት የአንዱ ቸርች መሥራች ይመስለኛል፡፡ እንዲህ አለ፡- “  እኔ ሕመም እስከ ዛሬ በአጠገቤ ደርሶ አያውቅም፣ ክርስቲያን አይታመም እዚህ መካከል የታመማችሁ ካላችሁ ክርስቲያን አይደላችሁም፣ ኢየሱስ ታመመ የሚል ስላላነበብን አያመንም፡፡ ክርስቲያን ድሀ አይሆንም፡፡ ክርስቲያን ባለጠጋ ነው፡፡ እኔ ያማረ መኪና አለኝ፣ ዘርፌ የገዛሁት ሳይሆን ክርስቲያን ድሀ መሆን ስለሌለበት ነው፡፡ እግዚአብሔር ተናግሮኛል ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ወደዚህ ቸርች ስትመጡ ባስ እየጠበቃችሁ አትመጡም፣ መኪና ትገዛላችሁ” ሲል የወጣቶቹ ዝላይ አሁንም በዓይኔ አለ፡፡ መኪና የክርስቲያንነት መለኪያ ከሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚነዳው የመገልገያም ሆነ የቅንጦት መኪና ዐረብ ሰልቾቶት የጣለው መኪና ነው፡፡ ታዲያ ዐረቦቹ ክርስቲያኖች ሆነው ይሆን? ሕዝባችን ተሰድዶም አልደላውምና እዘኑለት፡፡ በሥጋ ስለሚጨቁኑን ፖለቲከኞች እናዝናለን፡፡ በነፍሳችን የሚቀልዱ አገልጋዮች ግን በጣም ያሳዝናሉ፡፡ ይህን ባየሁ ጊዜ ኢትዮጵያ እግዚአብሔር ያጥናሽ አልኩ፡፡
በምዕራቡ ዓለም ከወንጌል ይልቅ የሥጋዊ ተድላ ስብከት በመጧጧፉ ዛሬ እየጠፋ ነው፡፡ በየቴሌቪዥን ጣቢያው አገልጋዩ እግዚአብሔር የለም ይላል፣ ሕዝቡም አብሮ እየካደ ቸርቾቹ ይዘጋሉ፡፡ ይህ የምዕራቡ ዓለም የክርስትናው ውድቀት ነው፡፡ ሥሩ ከደረቀ ቅርንጫፉ መድረቁ አይቀርም፡፡ አብያተ ክርስቲያናት ሊያስቡበት ይገባል፡፡ መኑ ውእቱ ገብር ኄር – ቸር አገልጋይ ማነው?  ቁመናውን ሳይሆን መልክአ ኢየሱስን፣ የቤቱን ቁሳቁስ ሳይሆን የመንግሥተ ሰማያትን ምሥጢር የሚያሳየን አገልጋይ ማን ይሆን?
ዛሬ በዓለም አቀፍ ደረጃ ባሉ አብያተ ክርስቲያናት ማቴሪያሊስቶችና ሞደርኒስቶች ቤተ ክርስቲያንን አጥለቅልቀዋታል፡፡ ስብከቱ ሁሉ ቁሳዊነት ነው፡፡ ምእመኑም እንዳሳዩት ነውና በቁሳቁስ ይወዳደራል፡፡ ዘመናዊነትም ከመንፈስ ቅዱስ በላይ ቤተ ክርስቲያንን እየገዛት ነው፡፡ እነዚህ ሁለት ነገሮች የቤተ ክርስቲያን ፈተና እንደሆኑ በዓለም ዓቀፍ ደረጃ እያየን ነው፡፡ ማን ይሆን ቸር አገልጋይ? የምድሩን ሳይሆን የሰማዩን የሚያሳይ፣ ዓለምን በኑሮው የኰነነ ማን ይሆን ገብር ኄር?  
ሕዝቡ የሚያለቅሰው በምን
የሚያጨበጭበው ለማን ይሆን?
    ሰባኪው ዘመናዊ ነው፡፡ ለጢሙ አቆራረጥ በጣም የሚጨነቅ ጢሙ በኦ(0) ቅርጽ ይጀምርና አገጩ ጋ ሲደርስ በረጅሙ ወደ ታች ይወርዳል፡፡ ዞማ ጢም መሆኑ ነው፡፡ ታዲያ ከሰሜን የአገራችን ክፍል በአንድ ገጠር ለማስተማር ይጠራል፡፡ እርሱም ትምህርቱን ከጀመረ ሰዓት እንሥቶ አንዲት ፊት ለፊት የተቀመጡ እናት ያለቅሳሉ፡፡ እርሱም በትምህርቱ የተነካ ሰው በማግኘቱ በደስታና በመገረም ስሜት ይጨምርበታል፡፡ ትምህርቱን እንደ ጨረሰ እኚህን እናት ማናገር አለብኝ ብሎ ወሰነ፡፡ ወደ እኒህ እናት በመሄድም፡- ‹‹እናቴ ከትምህርቱ መጀመሪያ ጀምሮ በዕንባ እየሰሙ ነበር፣ ለመሆኑ በየትኛው ቃል ነው እንዲህ የተነኩት›› አላቸው፡፡ እርሳቸውም፡- ‹‹ልጄ በትምህርቱ አይደለም›› አሉት፡፡ እርሱም፡- ‹‹ታዲያ በምንድነው ያለቅሱ የነበረው?›› ቢላቸው፡- ‹‹እንደው ገና ስትቆም ይህን የጢምህን አወራረድ ሳየው እንደ ሰው የሚቀበለኝና የጠፋብኝ ፍየሌ ትዝ ብሎኝ ነው የማለቅሰው›› አሉት ይባላል፡፡
ምእመኑ እንኳን በሚሰማው በሚያለቅሰውም መተማመን ከባድ ነው፡፡ ስለ ጠፋች ነፍሱ ከሚያለቅሰው ስለ ጠፋች ፍየሉ የሚያለቅሰው ይበዛል፡፡ በአደባባይ ስንንጎራደድ የምንውለው እንደዚህ ለመደመጥም መሆኑን ማሰብ አለብን፡፡ አገልጋይ ይህን ሁሉ ማስተዋል ያስፈልገዋል፡፡ አስተዋይ አገልጋይ ማነው?
የሰማሁትን አንድ ታሪክ ልንገራችሁ፡- ሰውዬው ለረጅም ዓመታት ያገለገለውና የኖረው በፕሮቴስታንት እምነት ውስጥ ነው፡፡ ዕለት ዕለት እየተባባሰ ባለው የሥነ መለኮትና የሥነ ምግባር ችግር እንደ ሌሎቹ ሽማግሌዎች እያዘነ እቤቱ ተቀምጧል፡፡ ታዲያ ከገባበት አዲሱ ቤት አጠገብ በየሰንበቱ የስብከት ድምፅ ይሰማና አላስችል ብሎት የአጥቢያው ሙሉ ወንጌል ቤተ ክርስቲያን ይሄዳል፡፡ ይህ ሰው ሲናገር እንዲህ አለ፡-
‹‹በዕለቱ የሚያስተምረው ተጋባዥ መምህር የክርስቶስን መለኮታዊነት እየገፈፈ፣ ትንሣኤ ሙታንን እያፈረሰ ሲያስተምር ስቅጥጥ አለኝ፡፡ ሕዝቡ ግን አሜን እያለ ያጨበጭባልና በሕዝቡ መሳት በጣም ተሰማኝ፡፡ በሳምንቱም ዛሬስ ምን እሰማ ይሆን ብዬ ሄድኩኝ፡፡ የዛሬው መምህር ደግሞ የሳምንቱ ትምህርት የተነገረው ይመስል የሳምንቱን ስህተት የሚያርም ትምህርት ሲሰጥ በጣም ደስ አለኝ፡፡ ነገር ግን አንድ ነገር ግር አለኝ፡፡ ሕዝቡ በጣም ያጨበጭብ ነበር፡፡ በዚህ ጊዜ ሐሰተኛ መምህራን ስለመቆጣጠርና ስለ ሕዝቡ ሁኔታ ለማወቅ የቤተ ክርስቲያኑን መጋቢ ማናገር አለብኝ ብዬ ወሰንኩ፡፡ ከፕሮግራሙ በኋላ ጠጋ ብዬ አገልጋይነቴን ሰውሬ ወንድሜ የሣምንቱ ትምህርት ብዬ ገና ስጀምር፡- ‹ተወው ተጫወተብን› አለኝ፡፡ ሣምንት ዝም በማለቱ ገርሞኛል፡፡ የዛሬው ግን … ብዬ ልናገር ስል ‹አይገርምም የሰማ እስኪመስል ነው ያፈራረሰው› አለኝ፡፡ አይ መጋቢው ነገሩ ገብቶታል ብዬ የሕዝቡን ሁኔታ ለመጠየቅ ፈለግሁ፡፡ ሕዝቡ ሣምንት ላስተማረው አስተማሪ አጨበጨበ፣ ዛሬም ላስተማረው አስተማሪ አጨበጨበ ስለው ያጨበጨበው ለሳምንቱ አስተማሪ ለዛሬውም ሰባኪ አይደለም አለኝ፡፡ ታዲያ ለማን ነው ያጨበጨበው? ስለው ለራሱ ነው ያጨበጨበው አለኝ፡፡ እኔም ስደነግጥ መጋቢው መልሶ፡- ‹‹ሕዝቡ የሚያጨበጭበው ከሚያስበው አሳብ ጋር የሚመሳሰል ቃል ሲሰማ እንጂ ለሰባኪው አይደለም፤ የሚያጨበጭበው ለራሱ አሳብ ነውና አትጨነቅ›› አለኝ በማለት ተናግሯል፡፡
ሕዝቡ ያጨበጨበው ለሳምንቱ ስህተት፣ ለዛሬውም እርምት አይደለም፡፡ ሁለቱንም አይሰማም፣ የሚሰማው የሚያስበውን ብቻ ነው፡፡ ከሚያስበው ጋር ሲገጣጠምለት ለራሱ አሳብ ያጨበጭባል፡፡ በሕዝብ ጭብጨባ አቅላቸውን የሳቱ ሰባኪያን ዛሬስ ምን ይሉ ይሆን?
አንድ አገልጋይ የሆነ ወዳጄን ሕዝቡ ይልቁንም በወጣቱ ወደ ቤተ ክርስቲያን መምጣት ደስታዬን ስገልጽለት፡- ‹‹ሕዝቡ የትምህርቱ ርዕስ ምን ነበር ስትለው አይመልስልህም፡፡ አፌ ላይ አለ ተሰወረኝ ይላል፡፡ ሰባኪው ስለ ቁማር፣ ስለ ሰካራም የሚቀልደውን ቀልድ ግን አይረሳም፡፡ ስለዚህ በአብዛኛው የሚመጣው ሰባኪው በዱርዬነት ከእኔ ምን ያህል ይበልጣል?›› የሚለውን ለማወቅ ነው ሲለኝ ለጊዜው አላመንኩም ነበር፡፡ አዎ ሰባኪው ዓለምን ላራቁታት ብሎ ወይም በቀሚስ ብንያዝም ሁሉን እናውቃለን በሚል ስሜት የሚናገረው ዓለምን ከማራቆት ዓለምን እያስተዋወቀ እንደሆነ አልተረዳም፡፡ ዘመኑን የሚዋጅ አገልጋይ ማን ይሆን? መኑ ውእቱ ገብር ኄር፣ ታማኝ አገልጋይ ማን ይሆን? የማቴዎስ ወንጌል 25፡14-30 ስናነብ ሦስት ነገሮችን እንረዳለን፡-
1.     በብዙ ለማትረፍ የሚሮጥ አገልጋይ ማን ይሆን?
2.    ትንሽ ጸጋ ነው ያለኝ ብሎ አፍሮ የማይቀመጥ በተሰጠው የሚታመን አገልጋይ ማን ይሆን?
3.    ፈተናና መከራ ቢመጣብኝስ ብሎ አንድ መክሊቱን ያልቀበረ ቸር አገልጋይ ማን ይሆን?
ዛሬ ደጋፊ ሳይሆን እውነት የምትመሰክርለት አገልጋይ ያስፈልጋል፡፡ በማስታወቂያ ኃይል ሳይሆን በክርስቶስ ጸጋ የቆመ አገልጋይ ያሻናል፡፡ በቁሳቁስ የሚወዳደር ሳይሆን በቅድስና የበለጠ አገልጋይ ያስፈልገናል፡፡ መኑ ውእቱ ገብር ኄር . . .፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም