ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 21 2004
ፅድቅ ተጋድሞ
መርገሙ ቆሞ
ነቢያት አዝነው
አጋንንት ስቀው
ጣኦት ተመልኮ
እግዜር ተንቆ
ሞት በእኛ ነግሶ
ምሬታችን ብሶ
ስንኖር ለአዝማናት
ተሰብረን ስብራት
ህፃኑ ሲሰጠን
መጥቶም ሲዛመደን
የፅድቅ ችቦው ፋመ
የሀጢአት ባህር ቆመ
የሰማይ ደጅ ተከፍቶ
ምስጋናው ፍፁም ተመመ
በጎነቱ ለኛ ሰፈነ፡፡
ምድር የጌጥ ልብስ ለብሳ
ዜና መወለዱን ጮኸች አሰምታ
ህይወት ገፅዋ ፈካ
ፍጥረት ከጥም ረካ
ድቅድቅ ዘመን ነጋ
ጽድቅ ፍሬው ረባ
ነቢያት ሣቅ ሣቁ
የተዘጉ ምንጮች ብርሐን አፈለቁ
ጌታችን ሲወለድ ዘመን ተበሰረ
አመተ ምሕረት ይኸው ተቆጠረ
ጌታችን ሲወለድ ፍዳ መርገም ራቀ
ዘረ አብርሐም ሁሉ ይኸው ሣቅን ሣቀ