የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጌታ ሆይ ለምን እንዲህ ሆነ !?

ስብከት ያንተን መልክ ማሳያ መሆኑ ቀርቶ የሰው ጆሮ ማጫወቻ ሆነ ፤ ርካሹ ከብሮ ፣ ትልቁ ተዋረደ ፤ የምናየው አርአያ ፣ የምናፍረው ሽማግሌ ጠፋ ፤ ጌታ ሆይ ለምን እንዲህ ሆነ !? አገልጋዮች ብቻቸውን እየጮኹ ፣ ክርስቲያን ነኝ የሚል ወገን ዘፈን ሊሰማ ሄደ ። ካህናት የምድራውያን ካድሬ ፣ የኃያላን ቃል አቀባይ ሆኑ ፤ ቃለ እግዚአብሔር እንደ አባባል ተወሰደ ፣ መቅደስ በክፋት ረከሰ ፣ እውነት ተወግዞ ከእውነት አደባባይ ተባረረ ፣ ሐሰት ካባ ለብሶ ተንጎማለለ ። ጌታ ሆይ ለምን እንዲህ ሆነ !?

አምልኮት አክብሮትን ፣ መሥዋዕት ትኩስነትን አጣ ፤ በመንደር እሳት በዘመን ቄንጥ ስግደት ላንተ ቀረበ ፤ ሥራችንን ለማጻፍ የሰውን ሥራ አፈረስን ፤ የሁሉም ነገር ጀማሪ እኔ ነኝ ባይ በዛ ። ትላንት የሌላት ፣ ነገ የማይኖራት ዛሬ ተፈጠረች ። ጌታ ሆይ ለምን እንዲህ ሆነ !? ዘመኑን ተሻገሩ ያልናቸው ተመልሰው በደሉ ፤ በፍቅር ገመዳቸው የሳቡን በስለት ቆረጡን ። ሊቅ ጠፍቶ ጥያቄ መጠየቅ ስህተት ሆነ ፤ አፍ ተከፍቶ ጆሮ ተደፈነ ፤ ተመልከቱኝ እንጂ ልመልከታችሁ የሚል ጠፋ ። ጌታ ሆይ ለምን እንዲህ ሆነ !?

አባቶቻችን ጥቂት ዘርተው ብዙ እንዳጨዱ ሰምተን ነበር ፣ ብዙ ዘርተን ጥቂት ማጨድ አቃተን ፤ የደከምንለት ትዳር ፈራረሰ ፣ ልጆች በጭንቀት እንድንሞት ድራማ ሠሩብን ፣ በመልካም ቃልና በክፉ ልብ ጓደኞች ቀረቡን ፤ ከአደባባይ ተበታትነን በጎሣ ዋሻ ተደበቅን ። ጌታ ሆይ ለምን እንዲህ ሆነብን !? ብዙ የወደዱህ ላንተ ፍቅራቸውን ቀነሱ ፣ በሕይወት ጀምረው በኑሮ ጨረሱ ፣ ፍርድ ዘገየ ብለው ከቤትህ ፈለሱ ፤ የትላንት ቁመታቸው በዛሬ ውድቀታቸው ተለካ ። ያነሡት ሰው ጣላቸው ፣ የመሰከሩለት ከሰሳቸው ። ጌታ ሆይ ለምን እንዲህ ሆነ !?

ትልቅ ጠልተን ፣ ሊቅ አሳድደን ፣ መንፈሳውያንን ተጸይፈን ፣ የዋሉልንን ረግጠን ፣ ያሳደግናቸውን ልጆች በልተን ይህ ሁሉ ሆነብን ። በስብሰባ የዘራነውን ክፋት ፣ በስብሰባ መንቀል አቃተን ። የገፋነው ገፊ ሁኖ ሲመጣ ያስተማርነውን መቀበል ተሳነን ። ጌታ ሆይ ይህ ሁሉ ለምን እንደሆነብን አንተ ታውቃለህ ። ወልድ ሆይ በእውቀትህ ይቅር በለን ። አሜን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ተጻፈ ሐምሌ 6 ቀን 2015 ዓ.ም

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ