የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጌታ ሆይ እኛ ማን ነን ?

 ስማችንን እያወቅን ሥራችንን የማንመዝን ፣ ለምንባለው እንጂ ለምንሆነው የማይገደን ፣ እግዚአብሔርን በመንደራችን አስረን ለሌሎች የት አባታችሁ የምንል ፣ ጠዋት አመስግነን ማታ የምንራገም ፣ ዝም ስትለን እኛን አይነካንም የምንል ፣ ስትነካን የጻድቃን መከራቸው ብዙ ነው ለማለት የምንደፍር ፣ አውቀን ተመርቀን ገና ፊደል የምንቆጥር ፣ ሰማይ ጠቀስ ፎቅ ላይ እየኖርን ጭቃ የምናላቁጥ ፣ ስለ ጨረቃ እያወራን መቃብር የምንቆፍር ፣ ጽርሐ አርያምን እየናፈቅን እንጦሮጦስ የምንወርድ ፣ ወደ ላይ መሄድ ቢያቅተን ወደ ታች ማደግ ማንም አይከለክለንም የምንል ፣ ተማርን ብለን ያልተማረን በማንጫጫት የምንደሰት ፣ የማንበላውን እንጀራ ለድሀ ሰጥተን የምንኮፈስ እኛ ማን ነን ? የእህል ግፍ አለው እያልን ሰው ግን የምንጥል ፣ የውኃ ጡር አለው እያለን ደም የምናፈስስ ፣ ጭቃ ላይ ተቀምጠን እጠበኝ  ተቀያይመን ማረኝ የምንል ፣ የአንገት ንስሐ እንጂ የአንጀት ጸጸት የጎደለን ፣ እንደ ጦጣ ታስረን የምንዘፍን ፣ በምስኪኖች እንባ እንደ ተጠፈርን የረሳን እኛ ማን ነን ?

አምላክ ሆይ መታወቂያችንን የጣልን ፣ መልካችን በእሳት የተቃጠለብን ፣ ጾታችን እንጂ ማንነታችን የማይታወቅ ፣ እየተራብን የምናመነዝር ፣ እየቀጣኸን የምንቀጣጣ ፣ የመጣው ሳያንሰን ሌላ ጉድ የምናፈላ ፣ ዘመንን ማሽተት ፣ ጊዜን ማወቅ የራቀን ፣ በቅጽበት የምንረሳ ፣ አቤት አቤት ብለን በለው በለው የምንል ጸሎትና አድማ የተቀላቀለብን እኛ ማን ነን ? ጤነኛ ሁነን ውለን የትዳር ጓዳችን ሲመጣ አመመኝ የምንም ፣ የተሰጠንን መድኃኒት ንቀን ሌላ መድኃኒት የምንፈልግ ፣ በሞታችንም ተውኔት የምንሻ ፣ እየሰረቅን ዝክር የምናወጣ ፣ የጣር ኑሮ እየኖርን የባለጠጋ ጽዋ የምንጠጣ እኛ ማን ነን ? ሲረዱን በማንኪያ ሰጥተው ባካፋ ሊወስዱት ነው የምንል ፣ የማንኪያውን መልሰን የአካፋውን የማንጠቀም ፣ የሽባ ሩጫ የዕውር ግልምጫ ተብለን የተናቅን ፣ ከተነሣን ማንም አይችለንም እያልን ተቀምጠን የቀረን ፣ የመኖር ሳይሆን የመጋደል ሙያ ያዳበርን ፣ መልካችንን አፍርሰን የሰኞ ገዳይ የማክሰኞ እያልን በአዝማሪ የምንወደስ ፣ የክፉ ባለ አደራ ሁነን ሌላው ሲድን ክፋትን የምንከባከብ እኮ እኛ ማን ነን ? ጌታ ሆይ ንገረን ። አይሁድ ጥቂት ቢታገሡ የምንሰቅልህ እኛ ነበርን ። ቸኩለው ሰቅለውህ ስም ሆነባቸው ። እኛ ግን እንዳልሰቀለ ሆነን ሰቃዮችን የምንረግም ፣ ወንድምን መጥላት ፣ አማኝን ማውገዝ ጌታን መስቀል መሆኑን የረሳን እኛ ማን ነን ? ብትነግረንም አይገባንም ወልድ ሆይ እባክህ ንገረን ። ዓለም ከአንደኛና ከሁለተኛ ጦርነት ተማረ እንላለን ። እኛ ግን ከየትኛውም ጦርነት ፣ ከየትኛውም ስብከት የማንማር ፣ እግዜር እንኳ ያልቻለን ጎበዞች ነን ። እኮ እኛ ማን ነን ? አማኑኤል ሆይ ባንሰማህም ፣ ሰምተን ብንረሳውም እባክህ ንገረን ።
ስንያዝ ጭብጥ የማንሞላ ፣ ስንለቀቅ ዓለም የማይበቃን ፣ ስንታመም አባን ጥሩ የምንል ፣ ሊሻለን ሲል የለም በሉ የምንል ፣ የእግዚአብሔርን ካህናት በጥምጥም የምንደልል ፣ አገልጋዮችህ ሲራቡ ጽድቅ ነው እያልን የምናላግጥ ፣ ርስት የላቸውም እያልን መጠጊያ ግን የማንሰጥ ፣ ካህናትህ ጽድቅ ይልበሱ ሳይሆን አፈር ይልበሱ የምንል እኛ ማን ነን ? ሬሳችንን እንዲመሩ ቀሳውስትን አደራ የምንል ፣ የሞትኩ ቀን አሳምሩልኝ እያልን ለጣፋጭ ሽኝት የመረረ ኑሮ የምንኖር ፣ ለመቃብራችን እንጂ ለሕይወታችን የማንጨነቅ ፣ እሞታለሁ ብለን ዕድር እየገባን እሞታለሁ ብለን ንስሐ የማንገባ እኛ ማን ነን ? ሞትን ባንዴ አስበን ባንዴ የምንረሳ ፣ በየሳምንቱ ዕድር እየከፈልን በየሳምንቱ የማንቆርብ ፣ ቤተ ክርስቲያን ሲዘጋ መሄድ የሚያምረን ሲከፈት የምንጠፋ እኛ ማን ነን ? መለኪያ ጨብጠን በሃይማኖቴ ቀልድ የለም የምንል ፣ አብረውን የሚጠጡ የስም አገልጋዮች ከሃይማኖት ሕፀፅ የምግባር ሕፀፅ ይሻላል እያሉ ስካራቸውን ሕጋዊ የሚያደርጉብን ፣ አምነን ሳይሆን ተደልለን የተኛን ፣ ሆዳችን እያወቀ ዶሮ ማታ የተባልን ፣ በሌለ ዶሮ ኮሶ የጠጣን ፣ መተሬ የተጋትን እኮ እኛ ማን ነን ?  በተስፋ ዳቦ ቦርጭ ያወጣን ፣ በምኞት ጽዋ ጠጥተን የሰከርን ፣ እየተንገዳገድን ሰውን ማለፊያ ያሳጣን እኛ ማን ነን ? አብ ሆይ እባክህ ንገረን ። አባቶቻችን መሐረነ አብ አሉህ ፣ እኛ ደግሞ እግዜርን ተቀይመነዋል አልን ። አባቶቻችን ካንተ ምሕረት ፈለጉ እኛ ደግሞ ምሕረትን እንሰጥሃለን እያልንህ ነው ። ከተቀየምንህ ይቅርታ መጠየቅ አለብህ ። ልጆች ሳንሆን አባቶቻችን የምንል እኛ ማን ነን ? መሪዎቻችን በአደባባይ ከሁሉ ሃይማኖት ጋር ይጨባበጣሉ ፣ ሰፈር ስንመጣ እኛ እሳት አንጫጫርም ፣ ላዩ ልቡን እያሰፋ የሥሩ የሚጠብብን እኛ ማን ነን ? የምንፈልገውን የምንሰማ የማንፈልገን የማንሰማ እኛ ማን ነን ? ሬሳ የሚያቃጥሉ ሕዝቦችን የምንረግም ፣ በቁሙ ግን አቃጥለን የምንገድል ፣ ስንከስሰው የነበርነውን ቀብሩ ላይ ጥሩ ሰው ነበረ የምንም ፣ የሬሳ ክፉ የሌለብን የሰው ክፉ ግን የሞላብን እኛ ማን ነን ?
ጌታ ሆይ በበሽታችን አማረን ፣ በጤናችን የማናመሰግንህ ፣ የምስጋና ባሕል የተነጠቅን ያንተን የእኛ ፣ የእኛን የእኛ የምንል ሁሉን አዋቂውን ለማታለል የምንፈልግ ፣ ጨካኙን እየረገምን ደጉን የማንመርቅ እኛ ማን ነን ? ግብር እየከፈልን አሥራት የማናወጣ ፣ ምድራዊውን መንግሥት አክብረን ሰማያዊውን መንግሥት የናቅን ፣ የምንፈልገውን ባለማወቅ ማግኘት ያቃተን ፣ የማይማታ ባል ፣ የማትጨቃጨቅ ሚስት ፣ የማይገድል ንጉሥ ፣ የማይቆጣ መምህር እውነተኛ የማይመስለን ፣ ያንተን ጸጋ አምጣ የእኛን አሥራት እንቢ የምንል ፣ እኔ ከሞትሁ ማንም አይኑር ያልን ፣ መልካችን ጠፍቶን መስተዋት ላይ የምንውል ፣ ያየነውን መልክ ወዲያው ረስተን ደግመን የምናይ ፣ ከራሳችን ጋር እየኖርን ራሳችን የጠፋን ፣ ስለ ሰው እያወቅን ስለ እኛ የደነቆርን እኛ ማን ነን ? ጌታ ሆይ አንተ ንገረን ። ዋናው ጸሎት ነው እያልን ስናወራ የምንውል ፣ መስቀልህን እየሳምን አንተን የምንሰቅል ፣ ከምህላ በኋላ ምነው በተደባለቀ የምንል ፣ ልባችንን ቤት አስቀምጠን በእግራችን ቤትህ የምንመጣ ፣ አፈር ስሆን ብለን ያበላነውን ቀጥሎ አፈር የምናበላ ፣ በምን ሰዓት እንደምንለወጥ የማናውቅ ፣ አንዴ አፈር አንዴ ሰው ፣ አንዴ መናኝ አንዴ አስመናኝ የሆንን ፣ የማናውቀው ማንነት ድንገት የሚባርቅብን ፣ ጋብዘን የምናኮርፍ ፣ ጸልየን የምንበድል እኛ ማን ነን ? ያረፈደው ደስታ የማይውልልን ፣ ለመርገፍ የምንቸኩል እኛ ማን ነን ?
ጌታ ሆይ የዓለም መፍትሔ ከእኛ ነው እያልን ዓለምን እህል የምንለምን ፣ እኛን የነካ ይጠፋል እያልን እርስ በርስ የምንጠፋፋ ፣ እኛ ማለት ፍቅር ነን እያልን ለዓይን ለመተያየት የተጠላላን ፣ በደብተራ ቅኔ ፣ በአዝማሪ ውዳሴ ፣ በአሚና ማሽሞንሞን ውስጥ የተደበቅን ፣ ትንሽ ባለን ዘመን ሁሉን የምንሰጥ ፣ ብዙ ስናገኝ ምንም የማንሰጥ ፣ ዛሬ ከድቶን በትላንት የምንኮፈስ ፣ የምንለብሰው አጥተን መጋረጃ የምንጋርድ ፣ የታቹን አራቁተን የምንከናነብ ፣ ሽሮ በልተን ዶሮ የምናገሣ ፣ ትንሽ ሰጥተን ብዙ የምናወራ ፣ በቁሙ ሰውን አቃጥለን ሲሞት የማይበላውን በሬ የምንጥል ፣ አበሻ ክፉ ነው እያልን አበሻነቱንም ክፉነቱንም ለማን ሰጥተን እየተናገርን እንደሆነ የማናውቅ ፣ እኛው ገርፈን እኛው የምንጮህ ጅራፍ ፣ ወኔ ክርስትና ፣ ወንድነት እምነት የመሰለን ፣ በስምህ የምናፍር ፣ ራሳችንን በመልካችን በአምሳላችን ፣ በቅንዓት በምቀኝነት የሠራን ፣ አንተ የሠራኸውን መልክ ያፈረስን እኛ ማን ነን ?
ጌታ ሆይ ወይ ቃልህ ወይ ዘመኑ ያልገባን ፣ ከሰማዩም ከምድሩም ያልሆንን ፣ ምድርን ግዙ ተብለን ድሆችን የምገዛ ፣  አመላችንን ትተን ትዳራችንን የምናባርር ፣ በትክክለኛነት ስሜት የሰከርን ፣ የማንሳሳት መልአክ ፣ የማስቀደሻና የሱስ ልብስ ያለን ፣ ስንሰግድ መላእክትን ፣ ስናጫጭስ አጋንንትን የምንመስል ፣ በሙሉ ቀን ሳይሆን በግማሽ ቀን ሺህ ዓይነት ሰዎች የምንሆን ፣ ሰፈሩን አውከን ቤተ ክርስቲያን እንደ ጨዋ የምንቆም ፣ ተበደልሁ እንጂ በደልሁ የማንል እኮ እኛ ማን ነን ?
ጌታ ሆይ ራስን ከመሸንገል ፣ ፈጥኖ ከመርሳት ፣ ልብን አስቀምጦ በአፍ ከመጨዋወት አድነን ። በዚህ ቀን የመሻገር ጉልበት ሁነን ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብርና ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና 22
ሚያዝያ 1 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ