የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጌታ ነው

“ከክርስቶስ ኢየሱስ ከጌታችን” 1ጢሞ. 1፡2 ።
ስለ አንድ አምላክ በአይሁድ ምኩራብ ፣ በእስላም መስጊድ ይነገራል ። ቤተ ክርስቲያንን ልዩ የሚያደርጋት አንዱ አምላክ በሦስት አካላት የተገለጠ እንደሆነ በማስተማሯ ነው ። አንድ አምላክ ስትል እንደ አይሁድ አንድ አካል ማለቷ አይደለም ፤ ሦስት አካላት ስትልም እንደ አሕዛብ ብዙ አማልክት ማለቷ አይደለም ። ልዩ ሦስትነትን የምታምንና የምታስተምር እርስዋ የክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን ናት ። ቤተ ክርስቲያንን ልዩ የሚያደርጋት ስለ ክርስቶስ አዳኝነት የምትናገር መሆኗ ነው ። የቤተ ክርስቲያን መሠረት የክርስቶስ ደም ነውና ያለ ክርስቶስ ቤተ ክርስቲያን የለችም ። ሰባኪው ሁሉ ወንጌል ሰበከ የሚባለው መስቀሉን ማዕከል አድርጎ ፣ ድኅነተ ዓለም በክርስቶስ እንደ ተፈጸመ ሲያስተምር ነው ። መስቀሉ ማዕከል ፣ የክርስቶስ አዳኝነት ግብ ያልሆነበት ስብከት ወንጌል ተብሎ አይጠራም ። ወንጌል ዜና ክርስቶስ ፣ ወንጌል የመዳን ወሬ ነውና ። /የሐዋ. 8፡35 ፤ ሮሜ. 1፡1-3/

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስና ሌሎቹም ሐዋርያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በማለት ይጠራሉ ። ኢየሱስ ብለን ብንጠራም ስሙ ነው ። አይሁድም ኢየሱስ ብለው ለመጥራት አልተቸገሩም ። ኢየሱስ እርሱ ክርስቶስ ወይም አዳኝ መሆኑን ማመን ግን አልቻሉም ። ዓለምም ኢየሱስ ክርስቶስ እያለ ይጠራዋል ። ጌታችን ግን አይለውም ። ክርስቲያኖችን ልዩ የሚያደርጋቸው እንደ አይሁድ ኢየሱስ ብቻ ፣ እንደ ዓለምም ኢየሱስ ክርስቶስ በማለታቸው ሳይሆን “ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ” ብለው እርሱን በመጥራታቸው ነው ።
ክርስቶስ የሚለው የግሪክ ቃል ሲሆን በዕብራይስጡ መሢሕ ማለት ነው ። በእኛ ቋንቋ ደግሞ የተቀባ የከበረ ማለት ነው ። በብሉይ ኪዳን ነቢያት ፣ ካህናትና ነገሥታት በቅብዐት ይከብሩ ነበር ። እነዚህ ሁሉ በፍጡር ተቀብተው ክብርን የሚያገኙ ናቸው ። ጌታችን ግን ራሱ ፈጣሪ ነውና ውጫዊ ቅባትና የፍጡር ክብረት አላስፈለገውም ። የማዳን ሥራውን ለመፈጸም ግን ነቢይነትን ፣ ካህንነትንና ንጉሥነትን ገንዘብ አድርጓል ። በነቢይነቱ ሕዝብን ለንስሐ ጋብዟል ፤ በክህነቱ ራሱን መሥዋዕት አድርጎ አቅርቧል ፤ በንጉሥነቱ ከሰይጣን ባርነት ነጻ አውጥቶን የራሱ አድርጎናል። እነዚህ መዐርጋት ለቀደመው ሰው ለአዳም ተሰጥተው የነበሩ አዳምም በበደል ምክንያት ያጣቸው ክብረቶች ናቸው ። አዳም ነቢይ በመሆኑ ከእግዚአብሔር ጋር ይነጋገር ነበር ፤ ካህን በመሆኑ ለፍጥረቱ በእግዚአብሔር ፊት ወኪል ነበረ ። ንጉሥ በመሆኑም ከፀሐይ በታች ያለውን ያስተዳድር ነበር ። በበደል በወደቀ ጊዜ ግን አዳም እነዚህን ሦስት መዐርጋት አጥቷል ። ነቢይነቱን ቢያጣ ምሪት የሌለው ሆነ ፣ ካህንነቱን ቢያጣ በእግዚአብሔር ፊት ስደተኛ ሆነ ፣ ንጉሥነቱን ቢያጣ ፍጥረት አመጸበት ። ጌታችን ዳግማዊ አዳም ርስት አስመላሽ ሁኖ መጥቷልና ሥጋ በለበሰ ጊዜ እነዚህን መዐርጋት ገንዘቡ አድርጓልና የተቀባ ወይም የከበረ ይባላል ። /ኢሳ 61፡1 ፤ የሐዋ. 10፡38/ ክብረቱ ግን የራሱ እንጂ እንደ ቀደሙት ተቀቢዎች ከውጭ የተገኘ ቅባት ፣ ከፍጡርም የተቀበለው አይደለም ። ክርስቶስ የሚለው ስም መለኮትና ትስብእት በተዋሐዱ ጊዜ የወጣ የተዋሕዶ ስም ነው ። ይህንንም ስም ጌታችን በተወለደ ሌሊት መልአኩ ለእረኞች ገልጦአል ። ዛሬ በዳዊት ከተማ መድኃኒት እርሱም ክርስቶስ ጌታ የሆነ ተወልዶላችኋልና ።” ሉቃ. 2፡11 ።
ኢየሱስ ማለት መድኃኒት ማለት ነው ። ከሙሴ ቀጥሎ እስራኤልን የመራውና ርስተ ከነዓንን ያወረሰው ኢያሱ የስሙ ትርጓሜ ከኢየሱስ ጋር ተመሳሳይ ነው ። ጌታችንም ርስተ መንግሥተ ሰማያትን ያወረሰን ነውና ኢየሱስ ተብሏል ። ኢየሱስ ማለት ከኃጢአት የሚያድን ማለት ነው ። ከኃጢአት የሚያድን መድኃኒት በዓለም ላይ የለም ፣ ኃጢአትንም የሚያክም ሐኪም አልተነሣም ። እርሱ ግን ብቸኛው የኃጢአት ሐኪምና መድኃኒት ነው ። ሐኪም መድኃኒት ቢያዝዝ እንጂ መድኃኒት አይሆንም ። ጌታችን ግን ከኃጢአት የሚያድን ብቸኛው መድኃኒት ነው ። ኢየሱስ ስመ ተዋሕዶ ፣ የተጸውዖ ስም ነው ። ይህ ስም በምድር ላይ የተሰየመ ሳይሆን ከዘላለም በፊት በመንግሥተ ሥላሴ ተሰይሞ ፣ በኋላ በዘመኑ መጨረሻ በቅዱስ ገብርኤል አብሣሪነት ፣ ለእመቤታችን ለቅድስት ድንግል ማርያም የተገለጠ ነው ። /ሉቃ. 1፡31 ፤ ማቴ. 1፡ 21/
ጌታ ወይም እግዚእ – ጌታችን ወይም እግዚእነ የሚለው ስያሜ ለኢየሱስ ክርስቶስ የተሰጠ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ብዙ ጌቶች አሉ ቢባልም የክርስቲያኖች ጌታ ግን አንድ ነው ።/1ቆሮ. 8፡6/ እርሱም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። አይሁድ እንደ ጥፋተኛ ፣ እስላሞች እንደ ነቢይ ፣ አርዮሳውያን እንደ ቀዳሜ ፍጡር ፣ ዓለማውያን እንደ ሞራል መምህር ቢያዩትም እኛ ግን ክርስቶስ ኢየሱስ ጌታችን  እንደሆነ እናምናለን ። እናስተምራለን ። ጸሎተ ሃይማኖታችንም፡- “ወነአምን በአሐዱ እግዚእ ኢየሱስ ክርስቶስ ወልደ አብ ዋሕድ ፣ ዘህልው ምስሌሁ እምቅድመ ይትፈጠር ዓለም” ይላል ። ትርጓሜው፡- “ዓለም ሳይፈጠር ከእርሱ ጋር በነበረ የአብ አንድ ልጅ በሚሆን በአንድ ጌታ በኢየሱስ ክርስቶስ እናምናለን” ማለት ነው ። ይህ የዘወትር ጸሎታችን ነው ።
ክርስትና በተሰበከበት ዘመን የሮማ ቄሣሮች ራሳቸውን ከሰማይ እንደ ወረዱ አማልክት የሚያዩ ፣ ምስላቸውን በመናገሻ ከተማዎች አቁመው ስግደት በመንፈስ የሚቀበሉ ነበሩ ። “ቄሣር ጌታ ነው” ብሎ ያልሰገደውንም በእሳት አንድደው ፣ በሰይፍ ቆርጠው ይቀጡት ነበር ። በዚህ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን “ኢየሱስ ጌታ ነው” በማለት ማወጅ ጀመረች ።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም፡- “ከክርስቶስ ኢየሱስ ከጌታችን ጸጋና ምሕረት ሰላምም ይሁን” በማለት መልእክቱን ይጀምራል ።
እኛስ ማን እንለዋለን ?
1ጢሞቴዎስ /6/
ኅዳር 6 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲአመ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ