የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ግብ የሌለው መንገድ ፣ ቅንነት የሌለው ብርታት

“አካሄዳቸው ክፉ ነው ፥ ብርታታቸውም ቅን አይደለም ።” ኤር. 23፡10።

ነቢዩ ኤርምያስ ገና በለጋነቱ ዕድሜ ለነቢይነት አገልግሎት ወጥቶ ከማይሰማ ሕዝብ ጋር ሲታገል የኖረ ነው ። ያ ሕዝብ ደግ ሳይኖር ደግ መስማት የሚፈልግ ፣ በሚደልሉ ነቢያት ማደንዘዣ ወስዶ የተኛ ስለነበር የኤርምያስ ተግሣጽ እየቀሰቀሰው ይበሳጭ ነበር ። ሰላም ፣ ሰላም በሉ ሰላም ይሆናል በሚል ምኞት የጠፋ ወገን ነበር ። ሕይወት ያልዘሩባትን የማታበቅል ማሳ መሆኗን አላወቀም አላስተዋለም ነበር ። ዝሙትን ዘርተው የተባረኩ ልጆችን ፣ ጣዖትን ወድደው ያረፈ ልብን ፣ መግደልን ፈቅደው ሰላምን ይሹ ነበር ። ያ ዘመን የሐሰት ነቢያት የፈሉበት ፣ ከኤርምያስ እውነት የነቢያቱ ውሸት ይግደለን የተባለበት ፤ ሰው በነፍሱ የጨከነበት ወራት ነበር  ። የነገሥታት ልጆች እየተነቀሉ ወደ ባቢሎን በተራ ሲወሰዱ ቀጥሎ እኔ ነኝ ለማለት አእምሮአቸው ተሰውሮባቸው ነበር ። መዓት ደጃቸውን ሲጸፋ ጎረቤቴን እንጂ እኔን አይደለም ብለው ተኝተው ነበር ። ይህ መረጋጋት ከንቱ መረጋጋት ነበር ። ይህ መኝታ ወደ ሞት የሚወስድ መንገድ ነበር ። ኤርያምስ ቀጣዩ ቀን ታይቶታል ፣ እንዳልታየው ለመኖር ግን አልቻለም ። ታይቶት እንዳልታየው ለመኖር መስከር ፣ ማበድ ፣ አብሾ መውሰድ ያስፈልጋል ። የእግዚአብሔር ቍጣ በድለላ ፣ መዓቱም በፉከራ አይርቅም ። የሚርቀው በንስሐና እርስ በርስ በመታረቅ ብቻ ነው ። ካህናት ፣ ነቢያትን ፣ ሹማምንት የጋራ ርእስ ፈጥረው ስለ ኢየሩሳሌም ልዕልና የሚያወሩበት ፣ የድንጋይ ብርድ ልብስ ለብሰው አንዱ ያንዱን ሞት የሚያደንቅበት ነበር ። ከተሜው በነውር ፣ ገጠሬው በጭካኔ የሚወዳደሩበት ዘመን ነበር ። የድሀ ልጅ ተገፋ ፣ ምስኪኑ ተቃባይ አጣ ። አገር ቅርጫ ሁኖ ጥቂቶች ተካፈሉት ። ዘመናዊ ባርነት በወገን ልጅ ሰፈነ ። ድሀውና ባለጠጋው የሚገናኙበት ድልድይ እስኪሰበር ደሀው በጣም ደኸየ ፣ ባለጠጋውም ልክ አጥቶ ፋነነ ። ይህ ሁሉ ከፍታ በምርኮ ፣ ብልጥግናውም በባቢሎናውያን እሳት እንደሚጠፋ ያስተዋለ አንድ ሰው ነበር ። እርሱም በዛሬ ያልተዋጠው ነገ የታየው ኤርምያስ ነበር ።

ልጆች ዛሬ ዛሬን ሲያዩ ፣ አላዋቆች ለአሁን መሻታቸው ሲገዙ ፣ ሞኞች ቀኑን ሲያመልኩ የእግዚአብሔር ሰዎች ግን በመንፈስ ቅዱስ መነጽር አሻግረው ያያሉ ። ቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት የሚሄዱበት ካርታ ጠፍቷቸው ፣ አንዱ ላንዱ ደረቅ ዜማ ያዜምለት ነበር ። ኤርምያስም ካህኑን ቢገስጽ ካህኑ እንደ መስፍን በእንጨት ጠርቆ የሚቀጣው ፣ ገዥው በጉድጓድ ከትቶ የሚያሰቃየው ፣ ዝም በል እያለ የሚያስጨንቀው ነበር ። የሚያዩ እንዳያዩ ፣ የሚሰሙ እንዳይሰሙ የሐሰት ነቢያት ዓይንን አሳውረው ፣ ጆሮን አደንቁረው ነበር ። ሰው የሚወደውን እንደ ምግብ ዝርዝር እያቀረቡ ፣ ሰውም መርጦ እየሰማ ራሱን የሚያታልልበት ዘመን ነበር ። ጠንቋይ ቤት እንዳይሄድ ዘመናዊነቱ እያሳቀቀው ያለ መጋረጃ የሚጠነቁሉ ፣ ራሳቸውን አዋቆችና ብእሴ እግዚአብሔር ፣ ፈዋሴ ዱያን እያሉ የሚጠሩትን ይከተል ነበር ። ጥፋት የተቀጠረባት ከተማ ነጋሪት ቢጎስሙባት አትሰማም እንዲሉ ሰሚ ጠፍቶ ፣ እውነተኛው የእግዚአብሔር ቃል ጆሮ ተነፍጎ ነበር ። ኤርምያስ ብቻውን የሚጮህ ፣ የእግዚአብሔርን ድምፅ የሚያስተጋባ ነበር ። ያንን ትውልድ ልትሸከም የከበዳት ምድር ብቻ ትሰማው ነበር ። ያች ምድር ሰባ ዓመት የተሸከመቻቸውን ተገላግላ ማረፍ ፈልጋ ነበር ።

ነቢዩ ኤርምያስ ብቻውን በመቅረቱ እኔ ነኝ ወይ የተሳሳትኩት? የሚል ግርታ ባይገጥመውም እግዚአብሔርን ግን ወደማይሰማ ሕዝብ ለምን ላክኸኝ? እያለ ይሞግት ነበር ። የእውነት ቃል አገልጋዮች መስቀላቸው እልከኛ ሕዝብን መቻል ነው ። ነቢዩ ኤርምያስ ሕዝቡን ከገሰጸበት ቃል አንዱ፡- “አካሄዳቸው ክፉ ነው ፥ ብርታታቸውም ቅን አይደለም” የሚል ነው ። ኤር. 23 ፡ 10 ።

ዓይናቸው በምሕረት የማታይ ፣ የወደቀን ለመርገጥ ፣ የሞተን ለመደብደብ የምታይ ክፉ ነበረች ። የድሆች ጩኸት የማይሰማቸው ፣ ምስኪኖችን እንደ ጎመን የሚቀረድዱ ነበሩ ። ጠላታቸውን ያልለዩ ፣ አይጎዱንም የሚሏቸውን ሕፃናትና ሴቶች የሚሰይፉ ነበሩ ። የሚናገሩት መርዝ የተቀላቀለ ፈሳሽ ነበር ። ሰው እንዲህ ያስባል ወይ ? እስኪባል ራሳቸውን ያከፉ ነበሩ ። አዎ አካሄዳቸው ክፉ ነበረ ። እጆቻቸው በንጥቂያና በገዳይነት ፣ እግራቸውም ወደ ጥፋት ሥፍራ በመሮጥ ተጠምደው ነበር ። አዎ ያ ሕዝብ በርትቶ ነበር ። በቀትር ዕረፍት ፣ በሌሊት እንቅልፍ አልነበረውም ። ያ ሕዝብ ከፊቱ ላለው ሩጫ ጊዜውን ሳይሆን ነፍሱን መድቦ ነበር ። ያ ወገን ተሰባስቦ በአንድነት አንድ ዓይነት ነገር ያዜም ነበር ። ትጋቱና ብርታቱ ግን ለቅን ነገር አልነበረም ። ለጥፋትና ለመፍረስ ነበር ። እርስ በርሱ ሲጋደል በደንብ የሚገድሉ ባቢሎናውያን መጡበት ፤ የሕዝቡ ርስት ኢየሩሳሌም ፣ የካህናት ርስት የሰሎሞን መቅደስ በፍጹም መደምሰስ ተደመሰሱ ። የወንድማማቾች መጠላለፍ የባዕድ አጥፊን ለመጥራት ነው ።

ካለፉት ዘመናት ይልቅ ዛሬ ሁለትና ሦስት ሥራ የሚሠራበት የሩጫ ዘመን ነው ። ሰዎች የተወሰነ የሥራ ሰዓት ሳይኖራቸው ሃያ አራት ሰዓት የሚሮጡበት ጊዜ ነው ። በአገር ፣ በአህጉር ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕብረት በዝቷል ። የጋራ ትብብር የሚባሉ ነገሮች ብዙ ነው ። ለአንድ ሰው አንድ ነገር ለመናገር ቀርፋፋ የነበረው ዘመን አልፎ ለሚሊየኖች በአንድ ጊዜ መናገር የሚቻልበት የመረጃ ፈረሰኛ ያለበት ዘመን ነው ። በዚህች ቅጽበት በማኅበራዊ መገናኛ ሺህ ጓደኞችን መመልመል ይቻላል ። ይህ ሁሉ ብርታት ግን ለቅን ነገር አይደለምና እግዚአብሔር ያዝናል ። የእግዚአብሔር ቃልን ዞር ብሎ የሚያየው የለም ፣ የዓመጽ ወሬን ግን ሰው ደጋግሞ ያነባል ። የሰላምን ቃል የሚደግፋት የለም ፣ በለው የሚለውን ግን የሚያስፋፋው እልፍ ነው ። ቀኑን በሙሉ የሚያጠፋ ቃልን ሲሰሙ የሚውሉ ለአሥር ደቂቃ ቃለ እግዚአብሔር ለመስማት አይሹም ። ብዙ መጻፍ የሚችሉ ስለ ሰማያዊ ነገር ለመጻፍ አይፈቅዱም ። እየሄድን ስለሆነ ጎበዝ አንባልም ። የት እንደምንሄድ መናገር ካልቻልን ከርታታ ነን ። ብርቱ ስለሆንን አንደነቅም ። “የበረታነው ለምንድነው ?” የሚለውን ጥያቄ መመለስ መቻል አለብን ።

የተቀመጠ ሰው የለም ፣ ሁሉም እየሄደ ነው ። ዝም ያለ ሰው የለም ፣ ሁሉም እየተናገረ ነው ። የታጠፈ እጅ የለም ፣ ሁሉም እየሰነዘረ ነው ። መንገዱ ግን የሚያደርስ ፣ ብርታቱም ኋላ የሚያኮራ አይደለም ። ዘመኑ ብርታታችን ነው ። ክፋትን እንዳፈጠንበት ደግ ነገርን ብናፈጥንበት ይቻል ነበር ። ብርታታችን የሥላሴ ሕንፃ የሆነውን ሰውን ለማፈረስ ፣ የሰውን ቅስም ለመስበር ነውና ፈጥነን መመለስ ያስፈልገናል ።

በእኛ አገርና በእኛ ዘመን ያልተቋሰለ ማነው ? ያለ ርኅራኄ ስንወጋጋ ከርመናል ። አንድ ሰው ሲነካ ዝም ብለን ነበርና ሕዝብ መነካት ጀመረ ። ስም ማጥፋትን ቸል ብለን ነበረ ፣ አሁን ሐሰተኛ ታሪክ መፈጠርና መነገር ጀመረ ። ከፊታችን ያለው ወንድም ላይ ድንጋይ ሲወረወር ምን ቸገረኝ ? ብለን ነበር ። የቀደሙትን አባቶች ጭምር የሚጠራርግ ተሳዳቢ መጣ ። አካሄዳችን የሚያደርስ አይደለም ፣ ዋናው መሄዳችን ሳይሆን ወዴት እንደምንሄድ ማወቃችን ነው ። ብርታታችን የሚያስመካ አይደለም ። መሪ የሌለው ኃይል መድረሻው ገደል ነው ። የመኪናው ኃይል ያለው ሞተሩ ላይ ነው ። ለመድረስ ግን ትንሽዋ መሪ ታስፈልጋለች ። ያጠፍናቸው ጉባዔዎች ፣ የበተንነው ሕዝብ ይኸው ጦርና እሳት ይዞ መጣ ። ክፉ ሆኖ የተፈጠረ የለም ፣ ክፉዎችን የምንፈጥር እኛው ነን ። ያለን መፍትሔ ከበደልናቸው ሰዎች ጋር መታረቅ ፣ ከእግዚአብሔር ጋር በንስሐ መስማማት ነው ።

ስለ አካሄድህ ሳይሆን ስለመድረሻ ፣ ስለ ብርታትህ ሳይሆን ስለ ቅንነትህ አስብ።

አቤቱ ዘመናችንን አድስ !

ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ሐምሌ 20 ቀን 2012 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ