ወጣቶችና ወጣቱ አገልጋይ
(የወጣት አገልጋይ ፈተና)
ወጣት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ከእኩዮቹ ጋር ያለው ግንኙነት ብዙ ዓይነት መልክ አለው ። የመጀመሪያው ወጣቶች ይህን ዓለም ገና እየተዋወቁ ያሉ ፣ ለሚያዩትን ነገር ሁሉ መደነቅ መልሳቸው የሆኑ የዕድሜ ለጋዎች ናቸው ። ብስለት ስለሌላቸው እዚህ ሲወደዱ የሚያስቡት ከዚህ የበለጠ ፍቅር ሌላ ጋ አገኛለሁ ብለው ነው ። የመወደዳቸው ምሥጢር ወጣትነታቸውና ደም ግባታቸው ይመስላቸዋል ። በዚህ ምክንያት ታላላቅ ዕድሎችን ያሳልፋሉ ። “ገንዘብ በሃያ ዓመት ፣ ልብ በአርባ ዓመት” እንዲሉ ። ወደ ቤተ ክርስቲያን የሚመጡ ወጣቶች ቢያንስ ላለፉት ሃያ ዓመታት በሌላ ዓለም ቆይተው የመጡ በመሆናቸው ቶሎ ለመተከል ያስቸግራሉ ። በየስፍራው ሲተከልና ሲነቀል የሚኖር ዛፍ በቶሎ ይደርቃል ። እነዚህ ወጣቶችም እንደ ቅምሻ ትምህርቶችን ፣ ጉባዔያትን ፣ መምህራንን ሲቀምሱ ስለሚኖሩ ለአገልጋዩ የመደናገር ስሜት ይፈጥራሉ ። የሚጀመሩ እንጂ የሚፈጸሙ ፍቅሮችን የሚያጣው አገልጋይ ግር እያለው ይመጣል ። ሕዝብ ቢያብድም አይከሰስም ። ሕዝብ አቅሙ መሪውን ከምድረ በዳ የማስቀረት አቅም አለው። ለዚህም ሙሴ የመቶ ሃያ ዓመት ዕድሜው ልምድ ፣ የአርባ ዓመት አገልግሎቱ አልረዳውም ። ባገለገለው ሕዝብ ተሰናክሎ መንገድ ቀርቷል ። በሕዝቡ ምክንያት መቃብሩ እንኳ የማይታወቅ ሁኗል ። በየዘመኑ ባገለገለው ሕዝብ ተበልቶ የሚጠፋው አገልጋይ ብዙ ነው ። ካህን ነፍሱን ባገለገለው ሕዝብ እንዴት ነፍሱን ያጣል ?
ወጣቶች አዲስ እንደ መሆናቸው መማር አለባቸው እንጂ የኃላፊነት ቦታን በቅልጥፍናቸው ሲይዙ ካልገለበጥሁ ብለው ያስባሉ ። ዙፋን የሚያጸዳ ሰው ዙፋን ያምረዋል ። ያልተረዳው ነገር ወንበሩ ንጉሥ እንደማያደርግ ነው ። በየቤቱ የንጉሥ ዙፋን አሠርተው የሚቀመጡ አሉ ። ስጦታን በትግል ማግኘት አይቻልም ። ባለስጦታውን በመግፋት ስጦታውን መውረስ አይቻልም ። በቤተ ክርስቲያን በኃላፊነት ላይ ሊቀመጡ የሚገባቸው ፣ አስተዳደርን በሚመለከት የሚታጩ ከአርባ ዓመት ዘለል ቢሉ ይመረጣል ። ጸጋ ያለው ግን በጸጋው በለጋ ዕድሜው ይገለጣል ። ለዚህም ገና ከማኅፀን የተጠራው ነቢዩ ኤርምያስና ዮሐንስ መጥምቅ ምስክር ናቸው ። ወጣቶች በከረሙ ተንኮለኞች ወጥመድ ይጠለፋሉ ። በዚህ ምክንያት አገልጋዩ ላይ በጠላትነት ይነሣሉ ። የሚያስቡት በአእምሮአቸው ሳይሆን በጉልበታቸው በመሆኑ እንደ እነርሱ ወጣት የሆነውን አገልጋይ ፈንግለው መጣል እንደሚችሉ ይሰማቸዋል ። በተንኮለኞች ሴራ የሚወድቁ ወጣቶች ሦስት ዓይነት ምድብ አላቸው ። የመጀመሪያዎቹ ትክክለኛ ጠላቶች ፣ ሁለተኛዎቹ ወላዋዮች ፣ ሦስተኛዎቹ በወዳጅነት የሚጸኑ ትዕግሥተኞች ናቸው ።
አገልጋዩም በወጣቶች በኩል ለሚነሣው ተቃውሞ ማስተዋል አለበት ። ፈረሰኛውን ትቶ ከፈረሱ ጋር መጣላት የለበትም ። ከኋላቸው የሚጋልቡአቸውን ልቡሰ ሥጋ ጋኔን የሆኑትን አካላት ማየት አለበት ። ሁለተኛ ለሕይወቱ ጥንቃቄ ማድረግ አለበት ። ጉልበት እንጂ እውቀት የሚያንሳቸው ለጋዎች አደጋ እንዳያደርሱበት ጥንቃቄ ያስፈልገዋል ። አእምሮ የሌላቸው ሰዎች አእምሮ የመጉዳት አቅም አላቸውና መጠንቀቅ አለበት ። በተንኮለኞች የተጠለፉ የወጣት ሴቶች ተሳትፎ በዚህ ግብግብ ውስጥ ምናልባት “ደፈረኝ ፣ ከእርሱ ወለድኩ” የሚል ይሆናል ። አገልጋዩ ብዙ ሥነ ልቡናዊና አካላዊ ጥቃት ይደረግበታል ። የሚሆነው ሁሉ ሲሆን የነበረ ነው ። አዲስ ነገር የለምና መጽናት ለወጣቱ አገልጋይ የውዴታ ግዴታ ነው ። ስለ ወዳጅ እሬት ይላሳል ። ስለ እግዚአብሔር ሲሉ ይህን መከራና ፈተና መታገሥ ያስፈልጋል ።
ቤተ ክርስቲያንን በጉልበታችን እናገለግላለን ብለው የሚያስቡ ብዙ ወጣቶች አሉ ። ይህ ጉልበት የሥራ ሳይሆን የመደባደብ ነው ። እኔ ጢሞቴዎስም እነዚህን ወጣቶች አስተናግድ ነበር ። ለቤተ ክርስቲያን ትልቁ ጠላትዋ የገዛ ኃጢአታችን እንጂ የውጭው ተጋፊ አይደለም ። የውጭው ጠላት ነፍሳችንን ከሥጋችን ይለይ ይሆናል ። ኃጢአታችን ግን ከእግዚአብሔር ይለየናል ። በዚህ ሁሉ ማመንታት ውስጥ ሳለሁ ከመንፈሳዊ አባቴ ከጳውሎስ መልእክት ደረሰኝ፡- “እንግዲህ ወንዶች በስፍራ ሁሉ አለ ቍጣና አለ ክፉ አሳብ የተቀደሱትን እጆች እያነሱ እንዲጸልዩ እፈቅዳለሁ።” (2ጢሞ. 2 ፡ 8) ። ወጣቶችን የጸሎት ሰዎች እንዲሆኑ ማበረታታት ይጠቅማል ። ምሁራን ቢሆኑ መከራከር ፣ ሰባኪ ቢሆኑ መፎካከር ፣ ዘማሪ ቢሆኑ ቆንጆ መኮልኮል ይቀናቸዋል ። የጸሎት ሰው ሲሆኑ ግን እግዚአብሔርን ያዩታልና ትሑታን ይሆናሉ ። በተንኮለኞች ተጠልፋችሁ ፣ የሌሎችን አእምሮ ተከራይታችሁ በጸጋው የሚያገለግለውን አገልጋይ መንገዱን ብትዘጉበት የምትጣሉት ከማትችሉት እግዚአብሔር ጋር ነው ። ደግሞም በወጣትነታቸው ተሳስተው አገልጋዮችን የወጉ ብዙዎች ዘመናቸውን በጸጸት ሲያሳልፉ ፣ ጸጸታቸውም ፍጹም ዓለማዊ ሲያደርጋቸው አይቻለሁ ። ለአገልጋዮች ዋጋ ክፈሉ እንጂ ዋጋ አታስከፍሉ ። እኔ ጢሞቴዎስ ነኝ ።
ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 11
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 20 ቀን 2016 ዓ.ም.