ከአገልግሎት በፊት
ሰው ብቻውን አይሆንም ። ወይ ከእግዚአብሔር አሊያም ከራሱ ጋር ያወጋል ። ሰው ካገኘም ከሰው ጋር ያወራል ። ትዝታም እንደ አሁን ትኩስና ወቅታዊ ሁኖ ያነጋግረዋል ። የመምህር ቃልም ከሚኖረው ኑሮ ጋር ሲገጣጠም እንደ ገና አዲስ ፍንዳታ ሁኖ በውስጡ ይጮኻል ። መስፈርት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ቅዱስ ጳውሎስ የነገረኝን ከኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን አስተዳደር ጋር ማነጻጸር የጀመርኩት አሁን ነው ። ቤተ ክርስቲያን በእምነት የምትቀበል ፣ በፈሪሀ እግዚአብሔር መስፈርት የምትሾም ናት ። የአገልግሎት የመጀመሪያው መስፈርት ፍላጎት ነው ። አገልግሎት ጊዜን ሳይሆን ሕይወትን ሰጥተው የሚገቡበት ነው ። አገልግሎት የፍትፍት ሰደቃ ሳይሆን የመስቀል ጉዞ ነው ። ገሀነምን ከሚያህል የእሳት ዓለም ነፍስ ሲያወጡ ወላፈኑ አይንካኝ ማለት ሞኝነት ነው ። የአገልግሎት ጉዞ ራስን መካድ ያለበት ነው ። ራሴን ከዛሬ ጀምሮ ያለ ክርስቶስ አላውቀውም ብሎ መማል ይጠይቃል ። ይልቁንም ኦርቶዶክሳዊው/ቀጥተኛው ጎዳና ብዙ እንግልት ከውስጥና ከውጭ ያለበት ነው ። ከክርስቶስ ጋር ያልሞተ ፣ ገና ውዳሴና ክብርን ነቅዐ ሐሰት ከሆነው ከሰው ልጅ የሚናፍቅ ጉዞው ይከብደዋል ። ኦርቶዶክሳዊው አገልግሎት በመከራ እድናለሁ ሳይሆን በመከራ የድኅነት ጉዞዬን እፈጽማለሁ ብሎ የሚያምን ነው ።
ኦርቶዶክሳዊው አገልግሎት የሀብት ውድድር ያለበት አይደለም ። ኦርቶዶክሳዊው አምልኮ ስሜትን የሚያነቃቃ ሙዚቃና ጭፈራ ሳይሆን ተመሥጦ ያለበት ነው ። ኦርቶዶክሳዊው ክርስትና ስማዕትነት ያለበት ነው ፣ የጥብዐት/ቅዱስ ጭካኔ/ መንገድ ነው ። ራሱን ያልካደ ፣ የብልጽግና ወንጌል ሰባኪ ፣ የስስት ጦር የወጋው ፣ ግለኝነትን አምላኪ ፣ የራሱን ደሴት መሥርቶ ልጄ ሚስቴ እያለ ኗሪ ኦርቶዶክሳዊው መንገድ አይመቸውም ። ሃይማኖት ከሰው ያልተቀበልነው ፣ በሰው የማንጥለው ነው ።
አገልግሎት ሥራ ቢሆንም በሙያ ብቻ ሳይሆን በጸጋው የምንወጣው ሰማያዊ ግዳጅ ነው ። ወታደርበራሱ ትጥቅ እንደማይዋጋ አገልጋይም የመንፈስ ቅዱስ የጦር ዕቃ በሆነው በጸጋ ያገለግላል ። ቢሆንም የአገልግሎት መስፈርቱ ፍላጎት ነው ። አገልጋይ የሚሆነው በርግጥ መቍረጡ ፣ ዓለምን መካዱ መፈተን አለበት ። ይህን የመሰለ ቆንጆ አንድ ደብር ይገባዋል ብሎ አገልግሎትን ማርከስ ቀጥሎ ያረክስናል ። ጳጳሱ መፍራት ያለበት ዲቁና ሲናቅ ነው ። ዲቁና ሲናቅ ቅስና ይናቃል ፤ ቅስና ሲናቅ ጵጵስና ይናቃል ። አገልግሎት መስፈርት ከሌለ ሰላማዊ ሰልፍ ያማረው ሁሉ ወደ ዐውደ ምሕረቱ ይጠጋል ። ቄሣርን ለመዋጋት ቤተ ክርስቲያንን ምሽግ ያደርጋታል ። ቤተ ክርስቶስ ዘእግዚአብሔር መባሏ ቀርቶ ቤተ ክርስቲያን ዘጴጥሮስ ፣ ቤተ ክርስቲያን ዘጢሞቴዎስ ትባላለች ።
ራሱን የመራ ቤቱን ይመራል ። ቤቱን የመራ አገርና ቤተ ክርስቲያንን ይመራል ። አገልጋይ በግል ሕይወቱና በቤቱ መመዘን አለበት ። ንብረት ጠባቂ እንኳ ሥነ ምግባሩ ይታያል ፣ ተያዥም ይጠራል ። ነፍስን የሚጠብቀው አገልጋይማ ኑሮው መገምገም አለበት ። አገልጋይ በንግግሩ ፣ በአመጋገቡ ፣ በመጠጡ ፣ በግንኙነቱ ፣ በአስተያየቱ ልከኛ መሆን አለበት ። በሁለት ክንፍ በቤተ ክርስቲያንና በዓለም ካልበረርኩ ማለት የለበትም ። ቁጥብነት መከራን ባያስቀርም ይቀንሳል ። እጅግ መራራ ከሆኑ መተፋት አለ ፤ እጅግ ጣፋጭ ከሆኑም ማለቅ አለ ። ድንበር የሌለው አገልጋይ ሁሉ ይደፍረዋል ። ሁሉን ላስደስት የሚልም ሁሉ ይከፋበታል ። ሰውን ብናስደስት እግዚአብሔር ሊያዝንብን ይችላል ። እግዚአብሔርን ስናስደስት ግን እግዚአብሔርን የሚያውቅ ይደሰትብናል ።
ራስን መግዛት የአገልግሎት ትልቅ መስፈርት ነው ። በከተማ ላይ የበላይ ከመሆን በራስ ላይ የበላይ መሆን የተሻለ ነው ። ራስን አለመግዛት ለጸጸት ይዳርጋል ። በሕይወት ሰልፍ ውስጥ ታጋሽ ያልሆነ ሰው ራስን ባለመግዛት ይፈተናል ። ራስን መግዛት በሁሉም ነገሮች ውስጥ ያስፈልጋል ። በፍቅር ራሱን ያልገዛ ከመውደድ አልፎ አምልኮ ውስጥ ይገባል ። የወደደውን ሰው ሲያጣ ሞቱን ይመኛል ። በቸርነት ራስን መግዛት ይገባል ። ችግር በተወራበት ፣ መዋጮ በሚጠየቅበት ቦታ ሁሉ በስሜት እሰጣለሁ የሚሉ ሲጨነቁ እናያለን ። በቁጠባም ራስ መግዛት ይገባል ። ለጤናቸው እንኳ ገንዘብ ላለማውጣት የሚሰስቱ ሰዎች አሉ ። የሰበሰብነውን አንድ ቀን የማናውቀው ሰው ይበላዋል ። በቅጡ መጠቀም መልካም ነው ። በእውነት እያንዳንዱ ተልእኮ አገልግሎት ነው ። ሠራተኛ ሁሉ አገልጋይ ነው ። ስለዚህ ራስን መግዛት ይገባቸዋል ። አዳራሹ በስብሰባ ሲግል ራስን ባለ መግዛት ሹሞችን የሚሳደቡ ሲወጡ ይጨነቃሉ ። ያጨበጨበላቸው ሕዝብም የት ደረሱ አይላቸውም ። በርግጥ ነገሥታት የመከራቸውንም ሰደበን እንደሚሉ የታወቀ ነው። ቢሆንም ስንገሥጽም ራስን በመግዛት ሊሆን ይገባዋል ።
አዎ አገልግሎት የተገነባ ሰብእናና ፣ ያጌጠ መንፈሳዊነት መስፈርቱ ነው ።
ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 14
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 14 ቀን 2016 ዓ.ም.