የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 17

የስህተት ትምህርት

(የወጣት አገልጋይ ፈተና)

ከኣላውያን ነገሥታት ሰይፍ በላይ ቤተ ክርስቲያንን የጎዳት የስህተት ትምህርትና አስተማሪዎቹ ናቸው ። የስህተት ትምህርት ሙሉ ውሸት ሳይሆን ከፊል እውነት ነው ። የስህተት ትምህርት የሚያስክድ ሳይሆን የሚያጠራጥር ነው ። በጥርጥር የሚኖር ሰው በገደል አፋፍ ላይ የሚራመድ ነው ። በስህተት ትምህርት የተወጋ ሰው የድንበር ነዋሪ ነውና የሁለት ወገኖች የትግል ሜዳ ነው ። የጋራ ወዳጅ የጋራ ጠላት የሌለው የሁልጊዜ ተጠቂ ነው ። የስህተት ትምህርት የምግባር ሳይሆን የሃይማኖት ሕፀፅ ነው ። የስህተት ትምህርት የነካው ሰው ጣዖት አያመልክ ይሆናል ፣ ነገር ግን እግዚአብሔርን በፈላስፎች መነጽር ያየዋል ። የስህተት ትምህርት የበከለው ሰው ለተቀረጹ ምስሎች አይሰግድ ይሆናል ፣ ራሱ የስህተት ትምህርት ግን ረቂቅ ጣዖት ነው ። የስህተት ትምህርት የበከለው ሰው የእግዚአብሔርን ስም ይጠራ ይሆናል ፣ ነገር ግን በአስተርእዮ ራሱን የገለጠውን አምላክ ሳይሆን በራሱ ግምት “እግዚአብሔር ይህ ነው” ያለውን የሚጠራ ነው ። እግዚአብሔር ስሙ ከህልውናው ፣ ጠባዩ ከባሕርዩ ፣ አካሉ ከግብሩ የማይለይ አምላክ ነው ። የስህተት ትምህርት የያዘው ሰው በክርስቶስ ስም ይመጣል ፣ አንዳንድ ድንቅ ተአምራትን ያደርጋል ። እንኳን በክርስቶስ ስም መምጣት ይቅርና “እኔ ክርስቶስ ነኝ” እያለ የሚመጣ ሐሳዊ እንደሚኖር አስቀድሞ ተነግሯል ።

የስህተት ትምህርት ያጠመደው ሰው ሰንበትን ሊያከብር ይችላል ። በሰንበት ግን ምቾቱን ፍለጋ የራሱን አስተማሪ ይመርጣል እንጂ በልዕልናው ያለውን እግዚአብሔርን አይሻም ። በስህተት ትምህርት ገደል የወደቀ ሰው አባትና እናቱን ሊያከብር ይችላል ። አባትና እናት የሰጠውን ሥላሴን ግን በአንድነቱና በሦስትነቱ ማመን ይቸገራል ። የስህተት ትምህርት ያጠመደው ሰው አልገደልኩም ብሎ ጥይት ባለመተኮሱ ይኮራ ይሆናል ፣ ነገር ግን በተመረዘ ትምህርት የሰውን ነፍስ ይገድላል ። አላመነዘርኩም ብሎ ሊታበይ ይችላል ። ሰይጣን በትዳር ላይ ከማመንዘር በላይ የሃይማኖት ዘማ መሆን የበለጠ ያስደስተዋል ። በሐሰት ሰው ላይ አልመሰከረ ይሆናል ፣ ነገር ግን በእግዚአብሔር ላይ የሐሰት ምስክር የሚያሰማ ነው ። ሰይጣን በምግባር ቆንጆ እያደረገ በሃይማኖት የሚያጠወልጋቸው ሰዎች ብዙ ናቸው ። በሁሉ ከከፉማ ምን እየሆንሁ ነው ? ብለው ቶሎ ይነቃሉ ። የባልንጀራውን ሀብት አይመኝ ይሆናል ፣ ነገር ግን የስህተት ትምህርት የነካው ሰው ሀብትና ሥልጣንን ሲያስስ ይኖራል ። በእግዚአብሔር ታገኛለህ እንጂ እግዚአብሔርን ታገኛለህ የሚል ስብከት አይወድም ። ጾምን ፣ ጸሎትንና ምጽዋትን እንደ መጎሳቆል ያየዋል ። ሃይማኖታዊ ተጋድሎንም ያጣጥላል ። “አለሁ በጌታ” ከማለት “አለኝ በጌታ” ብሎ መታበይ ይፈልጋል ። የስህተት ትምህርት መጀመሪያ ሃይማኖትን ቀጥሎ ጠባይን እያጎሳቆለ ይመጣል ።

የስህተት ትምህርት እግዚአብሔርን አሳንሶ ፍጡራንን ከሆኑትና ከተሰጣቸው በላይ አተልቆ ማየት ነው ። የስህተት ትምህርት የተነሣው በዓለመ መላእክት ሲሆን አስነሺውም ራሱ ዲያብሎስ ነው ። እግዚአብሔርን አሳነሰ ፣ ራሱን እግዚአብሔር አከል አደረገ ። በዚህም ሳጥናኤል ሰይጣን ሆነ ፣ አሳች ተባለ ። ጎዳናውን የተከተሉ ማለትም እግዚአብሔርን አሳንሰው መልአክ የሆነውን ሳጥናኤልን አስበልጠው ያመኑ አጋንንት ተባሉ ። የስህተት ትምህርት መነሻው ትዕቢት ሲሆን ከሆኑት በላይ በጉልበት ለመሆን መሞከር ነው ። ሰይጣን በዝሙት ፣ ጾም በመግደፍ ተፈትኖ አያውቅም ፣ ነገር ግን በጥርጣሬ ሲፈተንና ሲፈትን ይኖራል ።

የስህተት ትምህርት ሌላኛው መነሻ ፍልስፍና ነው ። ፍልስፍና ሰው አእምሮውን ማዕከል የሚያደርግበት ሲሆን ሃይማኖት ግን መገለጥ ላይ የሚመሠረት ነው ። ፍልስፍና ቁሳዊ ነገርን መሠረት ሲያደርግ ፣ ሃይማኖት ግን በማይዳሰሰው ነገር ላይ ይመሠረታል ። የሚታየው ዓለም መሠረትም የማይታየው እግዚአብሔርና ቃሉ ነው ብሎ ያምናል ። ፍልስፍና ሞትን መጨረሻ ሲያደርግ ፣ ሃይማኖት ግን ተስፋ የሚያደርግና በትንሣኤ እንዲሁም በሚመጣው ሕይወት ላይ የሚተነትን ነው ። ፍልስፍና በምድር ጀምሮ በምድር የሚፈጽም ሲሆን ሃይማኖት ግን በሰማይ ጀምሮ በሰማይ የሚፈጽም ነው ። ፍልስፍና ነገሮችን ከንቱ ነው ሲል ተስፋ በመቍረጥ ሲሆን ሃይማኖት ግን ዓለምን በዓለም ለውጦ ወይም ንቆ ነው ። ፍልስፍና በከንቱንት ስሜት ራስን መጣል ያለበት ሲሆን ሃይማኖት ግን በተስፋ ግለት መመነን ነው ። ፍልስፍና በእውቀት ላይ ሲመሠረት ሃይማኖት ግን በቀራንዮ ፍቅር ላይ ይመሠረታል ። ፍልስፍና ራስን ያስጥላል ፣ ሃይማኖት ግን ራስን መካድ ያለማምዳል ። ራስን መጣል መቆሸሽ ሲሆን ራስን መካድ መቀደስ ነው ።

የሮም ጎዳናዎች በውበታቸው አልማረኩኝም ። የጳውሎስን የብራና መጻሕፍት ተሸክሜ ስጓዝ ቤተ ክርስቲያንን ስለሚያውኩ የስህተት አስተማሪዎች አስብ ነበር ። አሳቤን አልገታሁትም ። በዋርካው አጠገብ ትንሽ ልረፍና መጓዝም ማሰብም እቀጥላለሁ ። ከተጓዝሁ አስቤ ነበር ፣ ካሰብሁ በግድ እጓዛለሁ ! ጢሞቴዎስ ነኝ ።

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 17
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 21 ቀን 2016 ዓ.ም.

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።