የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 18

የስህተት ትምህርት መነሻ

የስህተት ትምህርት ያለ መሪ መጽሐፍ ቅዱስን ከማጥናት ሊከስት ይችላል ። መጽሐፍ ቅዱስን አለ ማንበብ የስህተት ምንጭ ሲሆን ያለ ዓላማው ፣ ያለ ዐውዱ ፣ ያለ መምህር ማጥናትም ለስህተት ይደርጋል ። የነገረ መለኮት እውቀት ፣ የዓለም አቀፍ የቤተ ክርስቲያን ጉባዔያት ድንጋጌ ፣ የታሪክና የዘመን ስፍር መጽሐፉን ለመረዳት በጣም ያግዘናል ። ብሉይ በሐዲስ ፣ ሐዲስ በሊቃውንት ፣ ሊቃውንት በመነኮሳት ሕይወትና ምክር ተተርጉሟል ። ብሉይ የጸነነበት ሰው ሐዲስን ይመልከት ። ሐዲስ የከበደው ሊቃውንት ያብራሩትን ይይ ። የሊቃውንትን ትርጉም ያልተረዳው አባቶች ይህን ቃል “እንዴት ኖሩት ” በማለት የሕይወት ትርጉም ይፈልግለት። ለብዙ ዶክትሪን መመሥረት ምክንያቱ መሪ የሌለበት የእርስ በርስ የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት ነው ። በጓዳ ያጠኑትን ወደ አደባባይ ይዘው ሲወጡ ብዙ የስህተት ትምህርቶች ይስተዋላሉ ።

የስህተት ትምህርት አንዱ መነሻ ያለ አስተማሪ መንቀሳቀስ እንደሆነ ሁሉ ፣ ሁሉም አስተማሪ ሲሆንም ስህተት ይወለዳል ። ሁሉም አስተማሪ ሊሆን አይችልም ። አስተማሪነት ጸጋ ፣ ለማስተማር መማር ፣ የአስተማሪነት ሥነ-ሥርዓት ፣ ራስን ለዓላማ መስጠት ይጠይቃል ። መናገር መቻል ፣ ማስተጋባት መቻል ማስተማር አይደለም ። ምስክርነትም አስተማሪነት ማለት አይደለም ። አስተማሪዎች በምእመን ምስክርነት ፣ በሰባኪው እንግዳ ተቀባይነት ፣ ምእመኑን በቤተ ክርስቲያን ይተክላሉ ። ምእመን በጓደኝነት ነፍሶችን ያመጣል ። ሰባኪ ደግሞ የዕለት ምግብ ሰጥቶ ያስተናግዳል ። አስተማሪው ደግሞ ዘላቂ ሕይወትን በማካፈል ምእመኑን ለክብር ያበቃዋል ። ሁሉ አስተማሪ ሲሆን ስህተቶች ይወለዳሉ ። መለኪያም እየጠፋ ይመጣል ። ትልቅ የሆነው ፣ ሰማይና ምድር የማይችሉት የሃይማኖት ርእስ ወርዶ የነጠላ ቁጨት ውስጥ ይገባል ።

ሌላው የስህተት ትምህርት መነሻ ቃሉን ከፍልስፍና አንጻር መተርጎም ነው ። መጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈበት የራሱ ዓላማ አለው ። መጽሐፉ የሊቃውንት ሳይሆን የአማንያን መጽሐፍ ነው ። ግን የሚመራ ሰው ይፈልጋል (የሐዋ. 8፡31)። ባይተረጎም እንኳ መነበብ ያለበት ፣ በመነበብም ብፅዕና የሚያስገኝ መጽሐፍ ነው (ራእ. 1፡3)። ቃሉ በምን ዓላማ ፣ ለእነማን ፣ መቼ ፣ በማን ተጻፈ ? የመጀመሪያዎቹ አንባቢዎች እንዴት ሰሙት ? የሚለውን ማሰላሰል ይገባል ። ቍጥሩ አልገባ ሲል ፣ አንቀጹን ፣ አንቀጹ አልገባ ሲል ምዕራፉን ፣ ምዕራፉ አልገባ ሲል ሙሉ ክፍሉን ፣ ክፍሉ አልገባ ሲል የመላውን መጽሐፍ ቅዱስና የእግዚአብሔርን ዘላለማዊ አሳብ በማስተዋል መተርጎም ይገባናል። ፍልስፍና የራሱ መንገድ ያለው ሲሆን ቃሉን ለመረዳት ግን እምነትና ጸሎት ይፈልጋል። በሥጋዊ አሰሳ ትርጓሜውን መፈለግ ለስህተትና ለመንፈሳዊ ድርቀት ይዳርጋል ።

ቃሉን ከዘመኑ ጋር ለማስታረቅ መሞከር ሌላው የስህተት ምንጭ ነው ። ዘመኑ ያጸደቀውን የእኩልነት ፣ የመብት ፣ የሳይንስ ጉዳዮችን ከቃሉ ጋር የማስታረቅ ተልእኮ አልተሰጠንም ። ሳይንሱ መሬት ትዞራለች ስላለ ያንን ለማስታረቅ ቃሉን መፈነካከት አያስፈልገንም ። በተንኮላቸው ያዞሩብን ሰዎች መሬት ትዞራለች ብለውናል ። የሴቶች መብት የተፈጥሮ እንጂ አብዮተኛ የሚሰጣቸው አይደለም ። ሴቶችን ካህናት አድርጎ መሾም ግን መጽሐፋዊ አይደለም ። የተለያዩ የመብት ጥያቄዎች ኃጢአትን ለማጽድቅ እየሞከሩ ነው ። አገልጋይ ግን ዘመኑ ምን ይላል? ሳይሆን እግዚአብሔር ምን ይላል ? ማለት አለበት ።

የሥልጣንና የገንዘብ ጥማት ይህን የስህተት ትምህርት ይወልዳል ። ፖለቲከኞች ሕዝብን የሚለያዩት አንድ የሆነ እንደሁ የምሾምበት ስፍራ የለም ብለው ይሰጉና በነጠሉት ሕዝብ ላይ አለቃ ይሆናሉ ። የስህተት ትምህርት አስተማሪዎችም በሥልጣን ጥም አንድነትን ያፈራርሳሉ ።

የስህተት ትምህርት ጠባያት እግዚአብሔርን ያለ መልኩ ማቅረብ የመጀመሪያው ነው ። የአካል ሦስትነት፣ የመለኮት አንድነት ያለውን እግዚአብሔር የአካል አንድነት ፣ የመለኮት ብዙህነትን ይሰጡታል። ክርስትናችን እግዚአብሔር ሦስት ነው ሲል እንደ አሕዛብ ስለ ብዙ አማልክት እያወራ አይደለም ። እግዚአብሔር አንድ ነው ሲልም እንደ አይሁድ ስለ አንድ ገጽ እየተረከ አይደለም። ፍልስፍና መነሻው የሆነ ግኖስቲካዊው ስህተት የክርስቶስን ሰው መሆን አይቀበልም። ረቂቅ አምላክ ከግዙፍ ሰው ጋር ኅብረት አያደርግም ብለው ያምናሉ ። ይህ ኋላ ለሚነሣው አምላክ አይወልድም ፣ አይወለድም ለሚል ትምህርት መነሻው ነው ። መልካም የሆኑ ነገሮችን እንደ ርኵስ መቍጠር የስህተት ትምህርት ነው ። ጴጥሮስ ተመርጧልና ጋብቻን ርኵስ ነው ማለት ስህተት ነው ። ጳውሎስ ተመርጧልና የድንግልናዊ ሕይወትን መንቀፍ ስህተት ነው ።

እግዚአብሔር የሚገኘው ሥጋን በማጎሳቆል ፣ ራስን በመቅጣት አይደለም ። በዚህ የስህተት ትምህርት የተጠመዱ ራሳቸውን በራብ መግደል እንደ ሰማዕትነት አድርገው ይቆጥሩታል ። ነገር ግን ራስን በራብ መግደል ኃጢአት ነው ። ሥጋን መጎሰም ፣ ራስን መካድ ፣ ጾም የሚሉ ቃላት ፍቺአቸው ሌላ ነው።

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 18
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ግንቦት 23 ቀን 2016 ዓ.ም.

አስተያየት ይስጡ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።