የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 6

ተረት

የስህተት ትምህርት ልዩ ትምህርት ፣ ከፊል እውነት ነው ። ይህን የሚያራምዱ ወገኖች ቤተ ክርስቲያንን ለማፍረስ አሊያም ከፍለው ለመውሰድ ይጠቀሙበታል ። በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን ሁለተኛው ቡድን ተረትና መጨረሻ የሌለው የትውልዶች ታሪክ አፍቃሪ ነበር ። የመጀመሪያይቱ ቤተ ክርስቲያን የትምህርት ነፋስን በተመለከተ ከአይሁድና ከአሕዛብ የተለያየ ውዝግብ መጥቶባት ነበር ። ከአይሁድ የመጣው ሁለት ዓይነት ቅርጽ ነበረው ። የመጀመሪያው ክርስቶስንም ክርስትናንም አንቀበልም የሚለው ቡድን ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ ክርስትናን ተቀብሎ ግዝረት ያለ ጥምቀት ፣ ክርስቶስ ያለ ሙሴ ፣ ወንጌል ያለ ኦሪት ብቻውን ሊያድን አይችልም የሚል አቋም የነበረው ክልስ ማኅበረሰብ ነበር ። ከአይሁድ ሦስተኛው ወገን ግን ቤተ ክርስቲያንን የመሠረቱ መቶ ሃያው ቤተሰብና ስምንት ሺህው ማኅበረ እስጢፋኖስ ተጠቃሽ ናቸው ። አይሁድ ለብሉይም ለሐዲስም ቀዳሚ ናቸው ። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከአይሁድ ተገኝቷል ፣ እመቤታችንም አይሁዳዊት ናት ።

ከአሕዛብ የተነሣው ፈተና መዳን በእምነት ሳይሆን በእውቀት ነው የሚል ፍልስፍና ቀመስ የሆነ ፈተና ነበር ። የዚህም መነሻ የግሪክ ሐተታ አማልክትና ፍልስፍና ነበር ። ፍልስፍና ከክርስትና ጋር የተራራቀ ነው ። ፍልስፍና በምድር ጀምሮ በምድር የሚጨርስ ሲሆን ፣ ሃይማኖት ግን በሰማይ ጀምሮ በሰማይ የሚፈጽም ነው ። የፍልስፍና መገኛው የሰው አእምሮ ሲሆን ሃይማኖት ግን መለኮታዊ መገለጥ ነው ። ፍልስፍና ቁሳዊ ነገር ላይ ሲመሠረት ፣ ሃይማኖት ግን መንፈሳዊ ነገር ላይ ይመሠረታል ። ከአሕዛብ የመጣው ፍልስፍና ለብዙ ስህተቶች መወለድ ምክንያት ሁኗል ። በዋነኛነት የክርስቶስን በሥጋ መምጣት የማይቀበል ነው ። ክርስቶስ በሥጋ ካልመጣ ፣ ቤዛ ኵሉ ዓለም ሁኖ በመስቀል ላይ ካልሞተ ዓለም አልዳነም ማለት ነው ። ይህም የቤተ ክርስቲያንን መሠረትና ተልእኮ የሚያናጋ ነፋስ ነው ። እኔም ወጣት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ብሆንም ይህ ፈተና ገጥሞኝ ነበር ። በአንደኛው እጄ ወደ አይሁድ ኦሪታዊ ገደል ሊገባ ያለውን ልይዝ ስጥር ፤ በሌላው እጄ ደግሞ በአረማውያን ፍልስፍና እየሰመጠ ያለውን ወገን ለማትረፍ እሞክራለሁ ። እያየሁ ብዙዎች በገደሉ ይወድቃሉ ። ሕፃን ልጅ በእጁ የያዘውን ስለት ቢቀሙት ያለቅሳል ፣ የነጠቀውንም ሰው ይጠላዋል ። ምእመናንንም ከስህተት ትምህርት ስንናጠቃቸው ከማመስገን መቀየም ውስጥ ይገባሉ ። የሚበልጠንን ሰው እንደ ጠላን ፣ ለአዲስ ነገር ዝግ እንደሆንን ፣ ጸጋ እግዚአብሔን እንዳሰርን ያስባሉ ። ሕፃን ልጅ እስኪገባው ተብሎ ስለት በእጁ እንደማይተዉለት ፣ ምእመናን እስኪረዱ ተብሎ መንጋውን በአጥፊው ማስበላት ተገቢ አይደለም ። ሥልጣን አብሮ መወሰን ፣ አንዳንድ ጊዜ ወስኖ ማስከተል ነው ።

ልዩ ትምህርት ያመጡ ወገኖች ለማንበብና ለመፈላሰፍ ሲፈልጉ ተረትና መጨረሻ የሌለው የትውልድ ታሪክ ይዘው የሚመጡ ደግሞ ማንበብና ማሰብን ያቆሙ ናቸው ። የእነዚህ ሰዎች መነሻቸው ሁለት ዓይነት አመለካከት ነው ። የመጀመሪያው እነእገሌን ስላዩ ማንበብና ማወቅ ያሳስታል ብለው ያስባሉ ። ሁለተኛው አመለካከታቸው ለማንበብ ሰነፍ ፣ ለወሬ ግን ብርቱ ናቸው ። የእንቁላሉን ቅርፊቱን እንጂ አስኳሉን አይፈልጉትም ። ሰማይና ምድር የማይችሉትን ሃይማኖት አውርደው ተራና ትንሽ ነገር ያደርጉታል ። ሥርዓቱን ከሃይማኖቱ ያምታቱታል ። ሽቅብ መምህራንን ለማረም ይሞክራሉ ፣ ከሳሽ ናቸው ። ደርሰው በመሃይም ቃሌ ገዝቻለሁ ይላሉ ። መሃይም መማር እንጂ መገዘት አይችልም ። ትልልቅ ሃይማኖታዊ ምሥጢራትን ንቀው ሃይማኖትን ጥለትና የዶሮ አንገት ላይ ያሳርፉታል ። ጾምን በምግብ ለውጥነቱ ይወዱታል ። ያለ ፍቅር መጾምን ግን አይጸየፉትም ። እንደ ኪሎ ሜትር ድንጋይ ባሉበት የሚቀሩ ፣ እውቀት እንዳይነካቸው የሚጠነቀቁ ፣ ድንግል አእምሮ የያዙ ናቸው ። አለማወቅ በሰውም በእግዚአብሔርም የተጸየፈ ነው ። ቃሉም፡- “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቶአል አንተም እውቀትን ጠልተሃልና እኔ ካህን እንዳትሆነኝ እጠላሃለሁ” ይላል (ሆሴ. 4፡6 ፤ ዮሐ. 17፡3) ። ከሁሉ በላይ በዚህ አመለካከት ካህን ከሆኑ የድንቁርና ጠባቂ ይሆናሉ ።

ታሪክ ደስ የሚል ነገር ነው ። ለዛሬ ማንነትም መሠረት ነው ። ታሪክን ሲተርኩት ሳይሆን ሲደግሙት ክብር ነው ። በዛሬው ውሳኔው ፣ በእምነትና በኑሮው እንጂ በታሪኩ ብቻ እግዚአብሔርን የሚያገኝ ፣ መንግሥቱን የሚወርስ ማንም የለም ፣ ለዚህ ከጸጋው የወደቁ አይሁድ ምስክር ናቸው ። ተኝተው ሲነቁ አዲስ ተረት የሚፈጥሩ ፣ የምናብ ዓለምን ከመለኮታዊ መገለጥ ጋር የሚያስተካክሉ ፣ ስመ እግዚአብሔር እንዳይነሣ ዘብ የሚቆሙ ፣ መለኪያ የሌላቸው መለኪያቸው ስሜታቸው የሆነ ብዙ ሰዎች አገልግሎትን ያውካሉ ። እነዚህ ሰዎች መናፍቃን የሚባሉ አይደሉም ፣ አላዋቂ የሚባሉ ናቸው ። መናፍቅ የሚባለው ቢያንስ በከፊል የሚያውቅ ፣ የሚያነብ ነው ። ሃይማኖትን የራሳቸው ቤተሰብ የግል ሀብት የሚያደርጉ ፣ በስድብ ብዛትና በዱላ ርስት ይዘው ለመኖር የሚፈልጉ ፣ ለሲኦል የፈረሙ ናቸው ። ቤተ ክርስቲያንን የራሳቸው ጎሣና ወገን መጠቀሚያ ፣ አገልግሎቱንም የገንዘብ ማግኛ ያደርጉታል ። ግብር የማይከፈልበት ንግድ በቤተ እግዚአብሔር ያቋቁማሉ ። ልዩ ትምህርት የሚያስተምሩት የሰውን ነፍስ ሲፈልጉ ፣ እነዚህ ደግሞ ሕዝብን አደንቁሮ በመግዛት ገንዘብ የሚሰበስቡ ናቸው ። የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን በዚህ ጭንቅ ውስጥ ነበረች ። ችግሩ በጊዜው ስላልተወገደ ይህች ቤተ ክርስቲያን ለታላቅ ጉዳት በቅታለች ። አገልጋዩ በዚህ ስበት ውስጥ የተወጠረ ፣ በመስቀል ላይ የተሰቀለውን ክርስቶስን የመሰለ ነው ። ተረት ሕፃናትን ያሳድግ ይሆናል ፣ ጎልማሶችን ግን አያኖርም ። የዘላለም መልእክት የተሰቀለውን መድኃኒት ክርስቶስን ማወቅና ማሳወቅ ነው ።።

አንተ ቸር አገልጋይ ሆይ ! በሁለት ወገን እንደ ተሳለው እንደ ምትሰብከው ቃሉ ፣ ለማንም የማትመች በመሆንህ ሁሉ ይጠላሃል ። ሰማይ ግን ይወድሃልና በርታ ። ጌታ ሆይ ከዚህ መለኪያ ከሌለው ዘመን እባክህ አድነን !

ይቀጥላል

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 6

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 22 ቀን 2016 ዓ.ም.

ያጋሩ

ያግኙን

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ስልክ ፡ +251930006086                             +251911699907

ኢሜል፡ ashumekon@gmail.com

የገጹ ዓላማ

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።

አሸናፊ መኮንን
Ashenafi Mekonnen
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ
Commercial Bank of Ethiopia
1000165078482

አቢሲኒያ ባንክ
Bank of Abyssinia
23202573

ሕብረት ባንክ
Hibret Bank
1030416569497017

ወጋገን ባንክ
Wegagen Bank
0870286030101

አዋሽ ባንክ
Awash Bank
01320034656200

በማህበራዊ ሚዲያ ይወዳጁን።

copyright @ 2021 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

የዚህ ገጽ ዓላማ ኦርቶዶክሳዊ ትምህርቶችን ማስተላለፍ፣ ትውልድን 
በእግዚአብሔር ቃል ማነጽና የተሻለ ዘመንን መናፈቅ ነው።