ሕጋውያን
(የወጣት አገልጋይ ፈተና)
በኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን የነበሩት ልዩ ትምህርት የሚያስተምሩ ፣ ተረትና የታሪክ ትምክሕት ያለባቸው ሰዎች ብቻ አይደሉም ። ሕጋውያንም ነበሩ ። እነዚህ ሕጋውያን የሕጉን አሉታዊ ቅድስና የሚጠብቁ እንጂ አዎንታዊ ቅድስናውን የሚጠብቁ አልነበሩም ። አያመነዝሩም ፣ ለትዳራቸው ግን ፍቅር የላቸውም ። አጠገባቸው ላሉት ሰዎች ቅን ሳይሆን ቅንቅን ናቸው ። አይሰርቁም ፣ ለተቸገረ ለመስጠት ግን ይፈተናሉ ። ባዕድ አምልኮ አያመልኩም ፣ ለእግዚአብሔር ግን በመንፈስ አይሰግዱም ። ለተቀረጸ ምስል አይንበረከኩም ፣ ሰማያዊ መቅደስ ተገኝተው ማምለክ ግን አይችሉም ። ሥርዓትን ያከብራሉ ፣ ለፍቅር ግን ግዴለሾች ናቸው ። ሰዎችን በክብር ቃላት ይጠራሉ ፣ ሲወድቅ ግን አያነሡትም ። ሁሉን ነገር ሂሳብ ውስጥ አስገብተው ሰላምታንም እንደ ውለታ ያያሉ ። አይገድሉም ፣ እነርሱን ካልነካቸው ግን ማንም ቢያልቅ ግድ የላቸውም ። በሰንበት በእግዚአብሔር ቤት ይገኛሉ ፣ የሰንበት ሥራ የሆነውን የተጎዱትን መጠየቅ ግን ይቸገራሉ ። አሥራትን ያወጣሉ ፣ የድሀ መባን ግን ያስቀራሉ ። ውብ ቃላትን ይናገራሉ ፣ ውብ ልብ ግን የላቸውም ።
ክርስትናን የማይገፋ ተራራ አድርገው ይስላሉ ፣ ያስተምራሉ ። የፍቅርን አምላክ በልጅነት ስሜት መጥራት ግን እንደ መዳፈር ይቆጥሩታል ። እግዚአብሔርን በፕሮቶኮል ያወሩታል ፣ በልባቸው ጭካኔ ግን ያስቀይሙታል ። ምስኪን ፊት ያሳያሉ ፣ በዓለም ላይ ካሉ ጨካኞች ጋር በክፋት ይወዳደራሉ ። ስለ ሩቅ አምላክ ያወራሉ ። እግዚአብሔርን ምሕረት እንደሌለው ዳኛ ይስሉታል ። ስለ አስከፊው ፍርድ ይናገራሉ ፣ ነገር ግን አይቀደሱም ። በእንባና በቁጭት ስለ ንጽሕና ሕይወት ያወራሉ ፣ ልባቸው ግን በክርስቶስ ላይ የሸፈተ ነው ። ለእግዚአብሔር የቅድስና ፖሊስ አድርገው ራሳቸውን ሰይመዋል ፣ የወደቀን ሰው ግን በሰበር ዜና ያጣድፉታል ። በንስሐ አያምኑም ፣ ሰው ተመለሰ ቢባልም ማመን ይቸገራሉ ። ወደ እግዚአብሔር ቤት አይገቡም ፣ ለሚገባም በሩን ይዘጋሉ ።
ሕጋውያን አክራሪዎች ናቸው ። አክራሪነት የራስን እምነት በግለት መያዝ አይደለም ። ከእኔ ወገን ውጭ ማንም አይኑር ብሎ ማሳደድ ነው ። ቀኝ ጉንጭህን ለሚመታህ ግራውን አዙርለት የሚለውን እንኳን ለመፈጸም ለማሰብ ይቸገራሉ ። ክርስቶስንም ቢያገኙት የሚጠይቁት ነገር ቢኖር እንዴት እንዲህ ያለ ትምህርት ታስተምራለህ ? የሚል ነው ። የትዳር አጋራቸውን እንደ ዕቃ ይመለከታሉ ። ለራሳቸው ፍላጎት እንጂ ለሌላው ስሜት አይጨነቁም ። በአገር በምድር ያሉት እነርሱ ብቻ መስሎ ይሰማቸዋል ። ለሚሊየኖች የሚያወሩት ነገር ለራስ እንኳ ደግሞ የማያስቡትን ነው ። ኃጢአተኛ ነኝ በማለት ማንም እንዳያያቸው መከላከያ ያበጃሉ ፣ የሌላውን ኃጢአት ግን ሲያውጁ ይውላሉ ። ሕጋውያን የሕይወት ድራማ የሚሠሩ ነው ። የተጠጋቸውን የሚቆርጡ ስለቶች ናቸው ። ልጆቻቸውን በነጻነት ይለቃሉ ፣ የሌሎችን ልጆች በወግ ያስጨንቃሉ ። መለኪያው ስሜታቸው እንጂ መጽሐፍ አይደለም ። የራሳቸው ስህተት ስለሚያስጨንቃቸው በሌሎች ስህተት መደበቅ ይፈልጋሉ ። ሁሉን ማርከስ ይፈልጋሉ ። የራሳቸው ወገን ቢሳሳትም ጽድቅ አድርገው ይደግፉታል ፣ የሌላውን ጽድቅ ኃጢአት ፣ ትምህርቱ ስህተት ይሆንባቸዋል ። ሕጉን እንደ ዜና ያነቡታል ፣ ግን አይፈጽሙትም ። ሕጉን እንደ መዶሻ ሌላውን መምቻ ያደርጉታል ።
ሕጋውያን ከፍቅር የተራቆቱ ናቸው ። በፍቅር ቤት በቤተ ክርስቲያንም ነፍስ በማባረር ፣ ሰዎችን በመክሰስ ፣ ሰላማዊውን ሰው ገፍቶ አውሬ በማድረግ ፣ ለክርስቶስ መንግሥት ጠላት የሚያበዙ ናቸው። ወጣት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ከእነዚህ ሰዎች ጋር ወይ በእልህ አሊያም በሽንገላ ሲመላለስ መንፈሳዊ አደራውን ይጥላል ፣ ሰውን ከክርስቶስ በላይ ያከብራል ። እነዚህ ሰዎች መማርን የጨረሱ ፣ ሳያውቁ የሚያውቁ የሚመስላቸው ናቸው ። ሌላው ሰው በይሉኝታ አይሰድባቸውም ፣ እነርሱ ግን የሚያቆማቸው የሕሊና ክብር ስለሌላቸው ትኩስ ጭቃ ይለጥፋሉ ። “ሞኝ ባያፍር ዘመዱ ያፍራል” እንዲሉ ሌላው ይሳቀቅላቸዋል ፣ የብልግና የምስክር ወረቀት የያዙ ስለሚመስል ተዋቸው ከእነርሱ ጋር አትነካኩ ይባልላቸዋል ። ስለ ሠሩ ሳይሆን እንዳይሳደቡ ደመወዝ ይከፈላቸዋል ። ወጣት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይን እነዚህ ሕጋውያን ያሳድዱታል ፣ ስህተቱን ፍለጋ ረጅም ርቀት ይሄዳሉ ። ሰው ግላዊ ኑሮ እንዳለው ይዘነጋሉ ። አቃቂር ለማውጣት ይማራሉ ። እንከን ለመፈለግ ወደ አግዚአብሔር ቤት ይመጣሉ ።
እነዚህ ሕጋውያን መንፈሳዊ አገልግሎትን ይጎዳሉ ። ሙያ ስለሌላቸው ለማገልገል ስለሚቸገሩ በአክራሪነት አገልግሎትን እንደ መዥገር ይጣበቃሉ ። ለጽድቅ መጥቼ ለምን ኵነኔ እገባለሁ ? የሚለው ሰው በቀላሉ በእነዚህ ሰዎች ምክንያት ከቤተ ክርስቲያን ይርቃል ። አዳዲስ ነፍሶችን የራሳቸው ለማድረግ ይጋደላሉ ፣ የእግዚአብሔር ነኝ ካለ ስም ይሰጡታል ። በዚህ ምክንያት ለብዙዎች መጥፋት ፣ ለመንጋው ሰላም ማጣት በብርቱ ይሠራሉ ። አሁንም ለእግዚአብሔር ቀናዒ እንደ ሆኑ በውሸት እንባ ይገልጻሉ ። በቍጣ ሲናገሩ እውነታቸውን ያስመስላሉ ። ፊትን መቋጠር የቅድስና ምልክት ያደርጋሉ ። ደረጃን ስለሚያበዙ ወንድማማችነትን ያርቃሉ ። ጥርጣሬን ስለሚዘሩ እረኛውንና መንጋውን ይለያያሉ ። ለሰገደላቸው የቅድስና ማዕረግ ሲሰጡ ፣ ተዉ ያላቸውን ከሥሩ ለመንቀል ይታገላሉ ።
የኤፌሶን ቤተ ክርስቲያን በእነዚህ ሕጋውያን ፣ ስርየተ ኃጢአትን ፣ ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ፣ ንጹሕ ፍቅርን ፣ የመንፈስ አምልኮን በማያውቁ ሰዎች ትናጥ ነበር ። እነዚህ የሳጥናኤል የውስጥ ካድሬዎች ሆነው አገልግሎቱን ያውኩ ነበር ። ሐዋርያውም በዚህ አዝኖ ነበርና እንድበረታ ጻፈልኝ ። (1ጢሞ.1 ፡ 5-11) ። እነዚህን ሰዎች በማባበል ሳይሆን አድራሻቸውን እንዲያውቁ መገሠጽና በውሳኔ ወደ ፊት መገስገስ ይገባል ። ሕልም ተፈርቶ ሳይተኛ አይታደርም ፣ ይሉኛልን ፈርቶ አገልግሎት አይኖርም ።
ይቀጥላል
ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 7
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 25 ቀን 2016 ዓ.ም.