የጽድቅ ሠራዊት
አገልግሎት ጦርነት ነው ። ነገር ግን በሐዋርያው ጳውሎስ ገለጣ መልካም ጦርነት ነው (1ጢሞ. 1 ፡ 18) ። ሌላውን ለማዳን ራስን መስጠት ነውና ። በዓለም ላይ ክፉ ጦርነቶች አሉ ። በራስ ወዳድነት ፣ በአልጠግብ ባይነት ፣ በትዕቢት ፣ በኩራት ፣ በንቀት ፣ በጭካኔ ፣ በርኵስ መንፈስ አነሣሽነት ፣ በጥላቻ ፣ በዘረኝነት ፣ በሥልጣን ጥማት የሚነሡ ጦርነቶች አሉ ። ሁሉም የሰው ልጅ ወንድማማች ፣ ከአንድ ምንጭ የተቀዳ ፈሳሽ ነውና በዓለም ላይ የሚደረገው ጦርነት ሁሉ ከወንድም ጋር የሚደረግ ክፉ ጦርነት ነው ። የዚህ ጦርነት መነሻው ቃየንና አቤል ሲሆኑ አድጎ ከሁለት ሰው ወደ ሁለት አገር ፣ ከድንጋይ ወደ ኒውክለር ጦርነት ተሸጋግሯል ። ጦርነት በዓለም ላይ እጅግ አክሳሪ ነገር ነው ። ሕይወትን ፣ ንብረትን ፣ ታሪክን ፣ ትውልድን አጥፊ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ የሚቆይ እንጂ የሚቀር ሰው የለምና የሰውን ጥቂት ዘመን በጦርነት መቅጠፍ የጭካኔ ጭካኔ ነው ። መልካም ጦርነት ተብሎ የሚጠራ አለ ። እርሱም ስለ አገልግሎት ከክፉ ሰዎች ጋር ፣ ከስህተት ትምህርት አስተማሪዎች ጋር የሚደረግ ጦርነት አለ ። አጋንንትም አገልጋዮችን በቀጥታ ይዋጋሉ ።
አገልጋይ ያለው ኳስ ሜዳ ሳይሆን ጦር ሜዳ ነው ። ኳስ ሜዳ እንኳ መልካም ፉክክር ቢሆንም ብዙ ስልጠና ፣ ዝግጅትና ዲሲፕሊን ይፈልጋል ። አንድ ስፖርተኛ ከመጠጥ ፣ ከዝሙት ፣ ከመባከን እንዲድን ይመከራል ። ቅድስና ለስፖርት እንኳ አስፈላጊ ነው ። አገልግሎት ጦር ሜዳ ነው ። በጦር ሜዳ ከጠላት ጋር ብቻ ሳይሆን አጠገብ ካለ አስተኳሽ ወይም የጠላት ወኪል ጋር ትግል ያለበት ነው ። በቅጡ ጠላት የሆነው የወዳጅ ያህል የሚያውቁት ነው ። በወዳጅ ሰፈር የተቀመጠው ጠላት ግን ዋናው አዳካሚ ነው ። በጦር ትምህርት የዓለም የጦር ሜዳ ውሎዎች ይጠናሉ ። የታወቁ የጦር መሪዎች ሕይወትና ልምድ ለዛሬው ሰልጣኝ አብነት ይሆናል ። አገልግሎትም ጦርነት ነውና ስለ መንፈሳዊ ሕይወት የተደረጉ ትግሎች ይወሱበታል ። የተጋድሎ አብነቶች ነቢያትና ሐዋርያት ፣ ሊቃውንትና መነኮሳት ይተረኩበታል ። ጦርነት ሕግ ፣ አዋጅ ፣ መርህ ፣ መመሪያ ፣ ትእዛዝ ፣ ግዳጅ አሉት ። ሕጉ መንግሥትና ሕዝብ የሚተባበሩበት ሕገ መንግሥት ነው ። አዋጁ አገርህ ተወሯልና ለነጻነትህ ፣ ለሃይማኖትህ ፣ ለልጅህ ስትል ዝመት የሚል ነው ። መርሁ ለሕዝቤና ለወገኔ ራሴን መሥዋዕት አደርጋለሁ የሚል ነው ። መመሪያው ሰዓቱንና ቦታውን ወስኖ መንቀሳቀስ ፣ የራስን መንገድ አለመከተል ነው ። ትእዛዙ አዝማቹን ለምን ሳይሉ ማዳመጥ ነው ። ግዳጁ የሚከፈለውን ዋጋ ሳይሆን የሚመጣውን ክብር ማየት ነው ፣ ነጻነትንም ለነጻነት መክፈል ነው ።
መንፈሳዊ አገልጋይ የጽድቅ ወታደር ነው ። ሕጉ መጽሐፍ ቅዱስ ነው ። አዋጁ ክርስትናን ሊያጠፋ የመጣውን ረቂቅ ኃይል ተዋጋ የሚል ነው ። መርሁ ርስተ መንግሥተ ሰማያትን ፣ የሰዎችን መዳን ማየት ነው ። መመሪያው በተሰጠው ዘመን እግዚአብሔርን ማገልገል ነው ። ትእዛዙ መንፈሳዊ አባትን እሺ ማለት ነው ። ግዳጁ ለምን ሳይሉ ታዝዞ መሥዋዕትነትን መክፈል ነው ። ከራሱ ሕይወት አብልጦ ክርስቶስን የማይወድድ መንፈሳዊ ወታደር መሆን አይችልም ። ወታደር ሲጠራ በምክንያት አይቀርም ። ቤተሰቤ ናፈቀኝ ብሎም ከግዳጁ አይመለስም ። መንፈሳዊ አገልጋይም በፈቃዱ የክርስቶስ ሠራዊት ነውና በቤተሰብ ፣ በጓደኛ ፍቅር ተጠልፎ ከተጋድሎው ዘወር ማለት የለበትም ።
አዝማች የሌለው እርሱ ወታደር መሆን አይችልም ። እንዲሁም መንፈሳዊ አገልጋይ አባት ፣ መካሪ ፣ አስተማሪ ያስፈልገዋል ። እርሱ ለሚያገለግለው ሕዝብ ሲያስብ ፣ ለአገልጋዩ ደግሞ የሚያስብ የበላይ አባት በግድ ያሻዋል ። ጦርነቱ ብዙ ዓይነት ነው ። የመጀመሪያው ከራስ ሥጋ የሚነሣ ጦርነት ነው ። ሁለተኛው ማባበያና ድለላ ያለው የዓለም ፈተና ነው ። ሦስተኛው ከሰይጣን የሚመጣ ግልጽ ውጊያ ፣ ስም ማጥፋት ፣ አድማ ማስነሣት ፣ መሥዋዕትነት ሊሆን ይችላል ። አንድ የተሟላ የውጊያ ስልት ሦስት ነገሮች ያስፈልጉታል ። የመጀመሪያው ደጀን ፣ ሁለተኛው የጦር ሰፈር ፣ ሦስተኛው የውጊያ ሜዳ ናቸው ። ደጀኑ ሕዝብና መንግሥት ሲሆን ትጥቅ ፣ ስንቅና ሞራል የሚሰጥ ነው ። የጦር ሰፈሩ የጦርነቱ ስልት የሚነደፍበት ፣ የጦር ሳይንስ የተማሩ ያሉበት ነው ። የጦር ሜዳው ከጠላት ጋር ፊት ለፊት የሚጋጠሙበት ነው ። መንፈሳዊ ወታደርም ደጀን ያስፈልገዋል ። እርሱም በማንበብ በመጸለይ ስንቅና ትጥቁን ማሟላት ነው ። ከምድራዊ ወታደር ልዩ የሆነው አገልጋይ ማሰብ ያለበት ነገር አለ ። ይኸውም ሯጭ ሲሮጥ ደጋፊ ፣ ወታደር ሲዋጉ ዘፋኝና ግፋ በል የሚል ሕዝብ አለው ። አገልጋዩ ግን እየሮጠም የማይታይ ፣ እየተዋጋም በርታ የማይባል ነው ። የጽድቅ ወታደር የሆነው አገልጋይ የጦር ሰፈር ያስፈልገዋል ። እርሱም የመንፈስ ቅዱስ ምሪት ፣ በማመን የቀደሙ አባቶችና ወንድሞች ምክር ነው ። ሦስተኛው በቦታው ላይ ፊት ለፊት መዋጋት ፣ እውነት መመስከርና እውነት የሚያስከፍለውን ዋጋ መቀበል አለበት ።
በልቤ ይህን ሁሉ እያሰብሁ ፣ የመርከብና የየብስ ጉዞዬን ፈጽሜ ሐዋርያው ጳውሎስ ደጃፍ ላይ ነኝ ። በሩን ስቆረቁር “ማነው ?” ለሚለው ድምፅ “ጢሞቴዎስ ነኝ” ብዬ መልስ ሰጠሁ ። አንተ አገልጋዩ እግዚአብሔር ያጽናህ ። በአገልግሎትህ የወለደችህ እናትህ ልትቃወምህ ፣ ሁሉን ስትናገር የሚሰሙህ ወዳጆች ፣ ዛሬ ወንጌል ስትናገር ላይሰሙህ ይችላሉና የዘመኑን ፍጻሜ ተገንዝበህ ወደፊት ግፋ ። የእነዚያ የጀግኖች የነቢያትና የሐዋርያት ልጅ ነህና በመንፈስ ቅዱስ ጨክን !
ይቀጥላል
ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 8
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 2 ቀን 2016 ዓ.ም.