የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 9

ሕሊና ያጡ ሰዎች

የወጣት አገልጋይ ፈተና

ወደ ሐዋርያው ጳውሎስ እየተጓዝሁ ሳለ ለእኔ የነበረውን አባታዊ ፍቅር በልቤ አስብ ነበር ። እንደ ልጁ እያየ ይወደኝ ፣ ነገን በብሩህ ይመለከትልኝ ነበር ። እውነተኛ አባት ልጁን እየገሠጸ በልቡ የሚያመሰግን ፣ እየተቆጣ በልቡ የሚስቅ ነው ። አባትነት ከውስጥ የሚሰማ ስሜት ነው ። ልጁም ያ ስሜት ይሰማዋል ። አባት ብሎ ለመጥራት አያፍርም ። አይጥለኝም ብሎ ይተማመናል ። ከአባት ብርና ወርቅ ሳይሆን ፍቅር ፣ ምክርና ጥንካሬ ይወረሳል ። እንኳን የሚወደን ሰው አሁን መኖሩ አይደለም ፣ ይወዱን የነበሩ ሰዎች እንደ ነበሩ ማሰብ በራሱ ሕያውነትን ያላብሰናል ። አንድ ቀን ተወድጄ ነበር ብሎ ማሰብ የልብ ሙቀትን ይጨምራል ። ብርና ወርቅ ያልቃል ፣ የምክር ሀብት ግን አያልቅም ። ምክር ለትላንት ወይም ለዛሬ ሳይሆን የነገ ስንቅ ነው ። ነገ ላይ ስላልደረስን ምክር ቀላልና ተራ ነገር ይመስለናል ። የመከሩን ሰዎች ትዝ የሚሉን ካለፉ በኋላ ነው ። ለማመስገን አሁን ጊዜው አልፏል ። ሰው ማለት ትላንት የሚባል ኃላፊ ቀን ያለው ፣ ነገ የሚባል መጪ ቀንን በተስፋ የሚጠብቅ ነው ። እንስሳት የትላንት ትዝታ ፣ የነገ ተስፋ የላቸውም ። ሰው ግን ትላንትን በይቅርታ ፣ ነገን በራእይ ውብ ማድረግ የሚችል ፍጡር ነው ።

አባት ጠንካራ ነው ። በዚህ ዓለም ላይ ቅዱስ ጭካኔ አለ ። ግንቡን ጥሶ ለማለፍ ፣ በጦርነቱ መሐል በጀግንነት ለመመላለስ ፣ በሰው ሳይሆን በራስ ፍላጎት ላይ እንቢ ለማለት የሚያስችል ቅዱስ ጭካኔ ከአባቶች ይወረሳል ። ይህች ዓለም በርኅራኄና በጭካኔ ሚዛን ተደግፋ የምትኖር ናት ።

በአገልግሎት ውስጥ ሕሊና የሌላቸው ሰዎች ይገጥማሉ ። ሰው እምነትና በጎ ሕሊና እንዲኖረው ይመከራል ። እምነት ካለው በጎ ሕሊና አለው ። በጎ ሕሊና ካለውም እምነት እንዳለው ምስክር ነው (1ጢሞ. 1፡19) ። በአገልግሎት ላይ የሚቧደኑ ሁለት ሰዎች ይገጥሙናል ፣ አንደኛው ተንኮለኛ ፣ ሁለተኛው ጅል ናቸው ። ተንኮለኛው ረቂቅ መንገድን ሲጠቀም ፣ ጅሉን ግንብ መደርመሻ አድርጎ ይጠቀምበታል ። ተንኮሉን ተንኮለኛው ሲያረቅቅ ፣ ጅሉ ድምፅ ማጉያ ሁኖ ያገለግላል ። እኔም ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ የሚባሉ የተመረገ ሕሊና የያዙ ሰዎች አስጨንቀውኝ ነበር ። በእምነት ቤት የተቀመጡ ነገር ግን እምነት የሌላቸው ፣ ፍላጎታቸውን እንደ ሕገ እግዚአብሔር የሚመለከቱ ደንዳና ሰዎች በእግዚአብሔር ይከሰታሉ ። እነዚህ ሰዎች የሃይማኖት እውቀትም መገዛትም የላቸውም ። ነገር ግን እውቀቱ መገዛቱ ካለው በላይ ቤተኛነት ይሰማቸዋል ። አይሰብኩም ፣ ሰባኪ ይተቻሉ ፤ መገዛት የላቸውም/አይገዙም የሚገዙትን ምእመናን ለራሳቸው የክፋት ሥራ ይመለምላሉ ። ስለ ሰዎች ሁሉ ያላቸው አመለካከት ክፉ ነው ። እንደ አፍኒንና ፊንሐስ ወደ እግዚአብሔር ቤት የሚመጡ ደናግልን የሚያስነውሩ ፣ ራሳቸውን ግን እንደ ቅዱስ የሚያዩ ናቸው ። ሕሊና ስለሌላቸው የሌላውን ሕሊና አይጠብቁም ። ምእመናንን በክፉ ወሬ ይበክላሉ ። አገልጋዮችን በማማት ሥራ ይጠመዳሉ ። በእግዚአብሔር አያምኑም ፣ ግን ለእግዚአብሔር ተቆርቋሪ መስለው ይታያሉ ።

በእግዚአብሔር ቤት በይገባኛል ስሜት የሚኖሩ ፣ ራሳቸውን የቀቡ ፣ ሌላውን እያባረሩና እያስመረሩ ለመኖር ጥሪ እንዳላቸው የሚቆጥሩ በየዘመናቱ አሉ ። እነዚህ ሰዎች የተንኮል ሊቃውንት ናቸው ። ግን የተንኮል ሊቅነት ሰይጣንን ፣ ሰይጣን እንጂ ሌላ ስም እንዲያገኝ አላደረገውም ። ዕድሜአቸውን በሙሉ በተንኮል ቢኖሩም የምስክር ወረቀት ግን አልተሰጣቸውም። ክፋት እውቅና አግኝቶ አያውቅም ። ሁልጊዜ የሚያወሩት መነኵሴው ረከሰ ፣ የቤተ ክርስቲያን ገንዘብ ተሰረቀ እያሉ ነው ። ሰው ረከሰ እያለ የሚያወራ ራሱ እየረከሰ መሆኑን አያውቅም ። በቤተ እግዚአብሔር ከእውቀቱም ፣ ከመዋቅሩም ፣ ከአገልግሎቱም የሌሉ ግን አዋቂዎችን ፣ መዋቅሩን ፣ አገልግሎቱን የሚያውኩ ሰዎች አሉ ። እነዚህ ሰዎች ቤታቸውን/ትዳራቸውን ትተው በቤተ ክርስቲያን ድንኳን ተክለው የሚኖሩ ፣ እገሌ ገባ እገሌ ወጣ እያሉ ሪፖርት የሚያዘጋጁ ናቸው ። ራሳቸውን የሚያረጋጉት ደመወዝተኛ አይደለሁም ብለው ነው ። የእነርሱ ደመወዛቸው ግን ርኵስ ዋጋ የሆነው ሰውን ማሳደድ ነው ። በምእመኑና በእረኛው መካከል ገደል ይፈጥራሉ ። ለሚናገሩት ልጓም ስለሌላቸው ያመነው እንዲክድ ምክንያት ይሆናሉ ።

መነሻና መድረሻ የሌላቸው ግብ አልባ ሰዎች አገልጋዩን ፣ ወጣቱን ጳጳስ በብርቱ ያውኩታል ። ከእነዚህ ሰዎች ጋር መጋጨት የብዙ ምእመናንን ሕሊና ያውካል ተብሎ ስለሚታሰብ አይነኩም ። “ስለ ምጣዱ አይጧ ትለፍ” በሚለው ርኅራኄ ተጠቃሚ ሆነው ይኖራሉ ። ሁልጊዜ ከመታመም አንድ ጊዜ መወሰን የአገልጋዩ የአመራር ጥበብ ነው ። በቆዩ ቍጥር ካንሰር የመሆን ዕድላቸው ሰፊ ስለሆነ በዕጢነታቸው መሸኘት ያስፈልጋቸዋል ። እነዚህ ሰዎች ለንስሐ ማብቃት ከባድ ነው ። ስለ ስህተታቸው ሲነገራቸው የያዙትን የአገልጋዮች የክስ ፋይል መዘርጋት ይጀምራሉ ። በእግዚአብሔር ምሕረት ሳይሆን በድለዋል በሚሏቸው ሰዎች ስህተት የሚጽናኑ ናቸው ። ከተሸኙ በኋላ ብዙ የበቀል መንገድ ይጀምራሉ ። ስም የለኝም ስሜ ራሱ ክርስቶስ ነው ብሎ የሚያምን ይንቃቸዋል ። ቀላል ማንነት ያላቸውን ሰዎች ሊያነሣሡ ይችላሉ ። ርስታቸውን ስላጡ ብዙ ይተኩሳሉ ። በመጨረሻው ግን የሚያሸንፈው ጸጋ ነው ። ።

ሐዋርያው ጳውሎስም እነዚህ ሰዎች በሚመለከት እንዲህ አለ፡- “እምነትና በጎ ሕሊና ይኑርህ፥ አንዳንዶች ሕሊናን ጥለው፥ መርከብ አለ መሪ እንደሚጠፋ፥ በእምነት ነገር ጠፍተዋልና፤ ከእነዚያም፥ እንዳይሳደቡ ይማሩ ዘንድ ለሰይጣን አሳልፌ የሰጠኋቸው፥ ሄሜኔዎስና እስክንድሮስ ናቸው።” (1ጢሞ. 1፡19-20።)

ለሰይጣን አሳልፎ መስጠት ከቤተ ክርስቲያን እንዲለዩ ማድረግ ነው ። በቤተ ክርስቲያን መኖር ከመላእክት ጋር መዘመር ነው ። ከቤተ ክርስቲያን መውጣትም ከድኅነት መውጣት ነው ። ሐዋርያው ይህን ያደረገው ተቀጥተው እንዲመለሱ ነው ።

ይህን እያሰብሁ “ጢሞቴዎስ ነኝ” ብዬ መልስ ስሰጥ ራሴን አገኘሁት ። የጳውሎስ ቤት በሩ ሊከፈት ተቃርቧል ።

የማያገለግሉ ሰዎች የሚያገለግለውን ሰው እንዴት ያውካሉ?

ይቀጥላል

ጢሞቴዎስ ነኝ ክፍል 9

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 9 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ