የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጥምቀት እውነት ነው !

እጅግ ኃጢአት በበዛባት ናዝሬት በጽድቅ የኖረውን ክርስቶስን ፣ ራሱም ጽድቅ የሆነውን መሢሕ ለማግኘት ዮሐንስ መጥምቅ ጓጉቷል ። በዓለም ላይ እውነተኞች ይኖራሉ ፣ እውነት ግን አይደሉም። ክርስቶስ ግን ራሱ ጽድቅ ወይም እውነት ነው ። ውኃ ሲያዩ ጥማታቸው እንደሚያይልባቸው ሰዎች ክርስቶስን ባየ ጊዜ ዮሐንስ ዕረፍትን ናፈቀ ። እርሱ በስድስት ወር አገልግሎቱ የሰው ልጆች የወደቁበት አረንቋ ፣ ከገዛ አንደበታቸው በሚሰማው የጸጸት ድምፅ ጻድቅ ነፍሱ ትጨነቅ ነበር ። እኔ ለጥቂት ወራት የከበደኝን የዓለሙ ጌታ ለዘላለም ሳይጥል የሚሸከም ነው እያለ ይገረም ነበር ። ሰውን ለማዳን መፍትሔው ሰው መሆን ነው ብሎ ፣ ባሕርየ ሰብእን ገንዘቡ አድርጎ ፣ ባዕድነትን ሽሮ የመጣው ልዑል ፣ የዮሐንስ መጥምቅ የዝማሬ ርእስ ነበረ ። አዎ ዛሬም ልንታደጋቸው የምንፈልጋቸውን ሰዎች ፣ ሰው በመሆን ልንቀርባቸው ይገባል ። ደግሞም እውነተኛ ወዳጅ መሆን ያሻል ። ካልተወዳጀነው በቀር ቍስሉን የሚያሳየን ማንም የለም ። ክርስቶስ ሰው ብቻ ሁኖ ሳይሆን አምላክም በመሆኑ ድኅነትን ፈጸመ ። ለሰውነትማ ዮሐንስ መጥምቅ ቀድሞ መጥቶ ነበር ። እኛም በራሳችን ፍቅር ብቻ ሰውን ማዳን አንችልም ፣ አምላካዊ ኃይል ያስፈልገናል ።

ማዶና ማዶ ፣ ናዝሬትና ዮርዳኖስ ሆኖ ሠላሳ ዓመት አለመተያየት ይደንቃል ። ቅንድብና ዓይን ጎረቤት ቢሆኑም ተያይተው አያውቁም ። ባሻገር ያለውን የምታየው ዓይን የጎረቤቷን ማየት አለመቻልዋ ይደንቃል ። የገዛ ቤተሰባችን ያለበትን ሁኔታ መገንዘብ አቅቶን ዓለም አቀፍ የእርዳታ ተቋም ልንመሠርት እንችላለን ። ሥራ የሚጀመረው ግን ከቅርቡ ነው ። ነቢዩ በእግዚአብሔር ቤት የመኖር መስፈርትን ሲያወጣ እንዲህ አለ፡- “ዘመዶቹንም የማይሰድብ” (መዝ. 14 ፡ 3)። ለደጅ ሰው ክብር ያለው ብዙ ይገኛል ፣ የገዛ ዘመዶቹን የሚያከብር ግን ይፈለጋል ። ቤተሰብን ማክበር ራስን ማክበር ነው ። በአንዳንድ አገራት የአገር መሪ ለመሆን መልካም የቤተሰብ መሪ መሆን መስፈርት ነው ። ነቢዩ ኢሳይያስም ስለ ተወደደው ጾም ሲናገር፡- “እንጀራህንስ ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፥ ስደተኞቹን ድሆች ወደ ቤትህ ታገባ ዘንድ፥ የተራቈተውንስ ብታይ ታለብሰው ዘንድ፥ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሽግ አይደለምን?” ይላል ። (ኢሳ. 58 ፡ 7) ። ለቅርብ ሰው ክብርና አሳቢነት ሊኖረን ይገባል ። ጌታና ዮሐንስ ግን ቅርብ ቢሆኑም ሠላሳ ዓመት አልተያዩም ። ጌታ በዓይን ያየዋል ፣ ዮሐንስ በእምነት ያስተውለዋል ።

ዮሐንስ እጅግ ወንጀለኞችን አይቷል ፣ የብዙዎችንም ንስሐ ሰምቷል ። ሰው ሁሉ በልብስ ተሸፍኖ እንጂ ያልወደቀ ማግኘት ከባድ ነው ። ያልታወቀበት ኃጢአተኛ በተጋለጠው ኃጢአተኛ ይስቃል ። አንዳችን ስለ አንዳችን ከምናወራ እግዚአብሔር ስለ ሁላችን ቢናገር ምድር የትሑታን መንደር ትሆን ነበር ። ወደር የሌላቸውን ኃጢአተኞች ባየ ዓይኑ ወደር የሌለውን ቅዱስ አገኘ ። ጽድቅ የጥምቀት ወይም የዮርዳኖስ ርእስ ነው ። ራሱ ጽድቅ ነኝ ያለው ጌታ ሥጋ ለብሶ በማዕከለ ዮርዳኖስ ቆሟል ። “እግዚአብሔር ጻድቅ ነው” የተባለለት አብ በደመና ይመሰክራል ። መንፈሰ ጽድቅ ጰራቅሊጦስ በአምሳለ ርግብ ወርዷል ። ተነሣሕያንም ጻድቃን እውነተኞች ነበሩ ፤ ስለ እውነት የሚመሰክረው የግንባር ሥጋ የሆነው ዮሐንስ መጥምቅም ጻድቅ ነው ። ዮርዳኖስ በጽድቅ ተሞልቶ ነበር ።

ጌታችን ዮሐንስ አላጠምቅህም ቢለው፡- “አሁንስ ፍቀድልኝ ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው ።” (ማቴ. 3 ፡ 15 ) ። ጥምቀት ጽድቅ ፣ እውነት ፣ ፍትሕ ፣ ርትዕ ፣ ሚዛናዊነት የሰፈነበት ነው ። ሰው ከሕገ አራዊት ከመገዳደል ፣ ያሸነፈ ይኑር ከሚል የቃየን ሥርዓት በኦሪት ሕግ ወጣ ። ኦሪትም ያቆሰለ ይቍሰል በማለት ቍስልን በቍስል የምትከፍል ምድራዊ ሕግ ሆነች ። የገደለ ይግደል ስለምትልም ሁለት ሟች አመረተች ። ጌታችን በዮርዳኖስ የክርስትናውን ጽድቅ መሠረተ ። ስለ እውነት መቆም ፣ ለሌሎች ጥቅም ራስን መሥዋዕት ማድረግ ፣ አቅመ ደካሞች የሚኖሩበትን ዓለም መፍጠር ፣ የበደሉ ሰዎችን በይቅርታ መፍታት ይህ በዮርዳኖስ የተገለጠው ጽድቅ ነው ። እስከ ዛሬ የኖረው ጽድቅ አብርሃም በሚበልጠው በመልከ ጼዴቅ መባረኩ ፣ እስራኤል በትልቁ አሮን እጅ መናዘዛቸው ነው ። አሁን ግን በሚያንሰው ባሪያ በዮሐንስ እጅ በመጠመቅ ፣ ጽድቅ የሚያንሱንን ማክበር መሆኑን ገለጠ ።

ይህ ጽድቅ በጥምቀቱ ሊያበራ ይገባዋል ። የሃይማኖት መሪዎች ሥርዓቱን ለመፈጸም ብቻ ሳይሆን ትኩስ ቍስልን ለመሻር ፣ የበደለን በርግጥ በድለሃል ለማለት ጥምቀትን መድረክ ሊያደርጉት ፣ ሊያስታርቁበት ይገባል ። የገደለውን ኃይለኛ ፈርተው ገዳይን የሚያባብሉ ፣ መታገሥ አለብህ ብለው ካባ የሚደርቡ መሆን አይገባቸውም ። መታገሥማ የቆሰለው ፣ የሞተው ድርሻ ነው ። ሕገ አራዊት ላሸነፈ ማቀንቀን ነው ። ይህን ጽድቅ ሊፈጽሙ ይገባል ። እስካሁን በብዙ መመሳሰል ፣ ለሥጋ በማድላት ፣ የተቀየሙት ሲጎዳ በመደሰት አሳልፈው ይሆናል ። “አሁንስ” የምትለዋ ቀስቃሽ ቃል ግን እንደ መርፌ መውጋት አለባት ። “አሁንስ ፍቀድልኝ ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው ።” (ማቴ. 3 ፡ 15 ) ። አዎ “አሁንስ” ማለት ይገባናል ። ዕድሜአችን ሸምግሏል ። ዓለም በቃኝ ብለን መንነናል ። ቤተ ክርስቲያን ቀለብ ሰፍራ እያኖረችን ነው ። “አሁንስ” ብለን የተጠቃውን ልንታደግ ፣ አጥቂውን ለንስሐ ልንጋብዝ ግድ ይለናል ። ጥምቀት ጽድቅ ነው ። አሜን !

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 24 ቀን 2016 ዓ. ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ