የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጥምቀት

ዘመነ አስተርእዮ     
        ጥር 11   2004 ዓ/ም
ኤጲፋንያ በማለት በግሪክ ቋንቋ የሚጠራው በግዕዝ ቋንቋችን አስተርእዮ ተብሎ ተተርጉሟል። ትርጓሜውም መገለጥ ማለት ነው። ይህ የያዝነው ወር ዘመነ አስተርእዮ ወይም የመገለጥ ዘመን በመባል ይጠራል። ዘመነ አስተርእዮ የተባለውም፡-

1. አምላክ ሰው ሆኖ ከድንግል በመወለዱ
2. በዮሐንስ እጅ በዮርዳኖስ ወንዝ በመጠመቁ
3. የመጀመሪያውን ተአምር በቃና ዘገሊላ ፈጽሞ ሥራውን በመጀመሩ ነው።

እግዚአብሔር አምላክ ከጥንት ጀምሮ ራሱን በብዙ ዓይነትና መንገድ ሲገልጥ ነበረ። በአረጋዊ አምሳል ለአብርሃም፣ በንጉሥ አምሳል ለኢሳይያስ ተገልጧል(ዘፍ. 18፡1፤ ኢሳ. 6፡1)። እነዚህ ሁሉ መገለጦች እግዚአብሔር ወዳጆቹን ያበረታበትና ያስተማረበት ነበሩ። በጌታችን ሰው መሆን የተገለጠበት መገለጥ ግን አቻ የሌለው ነው። (ዕብ. 1፡1-3) ይኸውም የእኛን ሥጋ ለብሶ ከእኛ ጋር የተዛመደበት፣ የመለኮትና የሥጋ ተዋሕዶ ዘላለማዊ በሆነ መጠን የእኛና የእግዚአብሔርም ኅብረት ዘላለማዊ የሆነበት ትልቅ መገለጥ ነው። ስለዚህ ጌታችን የተወለደበት ዘመን የመገለጥ ዘመን ተብሎ መጠራቱ ተገቢ ነው። አማኑኤል እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ተብሎ የተጠራው በመወለዱ ነው (ማቴ. 1፡23)። በብሉይ ኪዳን እግዚአብሔር ከሕዝቡ ጋር እንደነበረ ራሱ ብዙ ጊዜ ተናግሯል። በልደቱ አማኑኤል መባሉ ግን የተለየ ነው። ይኸውም እርሱ በብሉይ ኪዳን ከሕዝቡ ጋር የነበረው በረድኤት፣ በተአምራት ነበረ። አሁን ግን ከሥጋችን ሥጋ፣ ከነፍሳችን ነፍስ ነሥቶ በማይፈታ ዝምድና እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ሆነ። ለዚህ ነው የአገራችን ባለ ቅኔ በመጓደድ ስሜት እንዲህ ያለው፡-

                   አብ ካልሰጠኝ ብዬ ምነው መናደዴ
                   ለወልድ አልነግርም ወይ ለሥጋ ዘመዴ

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እስከ ሠላሳ ዘመኑ ተሰውሮ እንደ ኖረ እናነባለን። በሠላሳ ዓመቱ ግን በጥምቀት አማካይነት ተገለጠ። እስከ ሠላሳ ዓመቱ የት ነበረ? ስንል በሥጋ የወለደችውን እናቱን ድንግል ማርያምን ሲያገለግል ነበረ። ከሠላሳ ዓመቱ በኋላ ደግሞ ሰማያዊ አባቱን ሊያገለግል ተገለጠ። ምድራውያን ወላጆቻችንን እንዲሁም በመንፈሱ የወለደንን ሰማያዊ አምላክን እንዴት ማገልገል እንደሚገባን ጌታችን በሕይወቱ አስተምሮናል። ጌታችን ራሱን የገለጠበት ጥምቀቱ አስተርእዮ ወይም መገለጥ መባሉ እውነት ነው።

ጌታችን ዐርባ ቀንና ዐርባ ሌሊት ጾሞ ከተመለሰ በኋላ በቃና ዘገሊላ የመጀመሪያውን ተአምር በማድረግ ራሱን ገልጧል። ይህ ቀን የታላቅ አገልግሎት መክፈቻ ብቻ ሳይሆን የታላቅ መከራም መክፈቻ ቀን ነው። ስለዚህ ይህ ተአምርም አስተርእዮ ወይም መገለጥ ተብሎ ይጠራል። ቃና ዘገሊላም ጥር 12 ቀን ይታሰባል፡፡

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተጠመቀው በሠላሳ ዓመቱ ሲሆን የተጠመቀውም በባሪያው በዮሐንስ እጅ ነው። ሠላሳ ዓመት የታላላቅ ውሳኔዎች ዘመን ነው። የልጅነት ዘመን አልፎ፣ የወጣትነት ጭፍንነትም በርቶ ሰከን የሚባልበት ሠላሳ ዓመት የፍሬ ዘመን ብለን የምንጠራው ነው። እስከዚህ ዓመት ድረስ የነበሩት ሩጫዎች ሁሉ ዘር ናቸው። አሁን ግን የመኸወይም የፍሬ ዘመን ነው። ዕውቀትን፣ ወዳጆችን፣ ልምዶችን ሁሉ እስከ አሁን እንሰበስባለን። ከሠላሳ ዓመት በኋላ ግን ዕውቀታችንን በጥበብ፣ ወዳጆቻችንን በቃል ኪዳን፣ ልምዳችንን በማስተዋል የምንተገብርበት ነው። ዕውቀቴ ለአገር ጥቅም፣ ለእግዚአብሔር ክብር ሊሆን ይገባዋል፣ ለትዳር ከመረጥኳት ወይም ከመረጥኩት ጋር አብሬአቸው እኖራለሁ፣ እስከ ዛሬ ካልተለዩኝ ወዳጆቼ ጋር እስከ ሞት እቀጥላለሁ፣ ልምዴን እያካፈልኩ የሌሎችን ልምድ እቀስማለሁ የምንልበት ዕድሜ ነው። አገር ለመምራት፣ ለጋብቻ፣ ለምንኩስና ከሠላሳ ዓመት በላይ መሆን ይገባል። ጌታችን በሠላሳ ዓመቱ ተጠመቀ።

ጌታችን በሠላሳ ዓመቱ ብቻ ሳይሆን በባሪያው እጅ ተጠመቀ። እኛ የምንጠመቀው በጸጋና በመንፈሳዊ መዐርግ በሚበልጡን አገልጋዮች እጅ ነው። ጌታችን ግን በባሪያ እጅ ተጠመቀ። ምሁራን፣ ነገሥታት፣ ባለጠጎች ብንሆን የእግዚአብሔርን አገልጋዮች እንዳንንቅ ሊያስጠነቅቀን ጌታችን በባሪያው እጅ ተጠመቀ። ከምድራዊ ሥልጣንና ኃይል የአገልጋዮች ጸጋ ይበልጣልና!

«ያን ጊዜ ኢየሱስ በዮሐንስ ሊጠመቅ ከገሊላ ወደ ዮርዳኖስ መጣ። ዮሐንስ ግን፡- እኔ በአንተ ልጠመቅ ያስፈልገኛል አንተም ወደ እኔ ትመጣለህን? ብሎ ይከለክለው ነበር። ኢየሱስም መልሶ፡-አሁንስ ፍቀድልኝ፤ እንዲህ ጽድቅን ሁሉ መፈጸም ይገባናልና አለው። ያን ጊዜ ፈቀደለት። ኢየሱስም ከተጠመቀ በኋላ ወዲያው ከውኃ ወጣ፤ እነሆም ሰማያት ተከፈቱ የእግዚአብሔርም መንፈስ እንደ ርግብ ሲወርድ በእርሱ ላይም ሲመጣ አየ፤ እነሆም፡- ድምጽ ከሰማያት መጥቶ፡- በእርሱ ደስ የሚለኝ የምወደው ልጄ ይህ ነው አለ»  (ማቴ 3፡13-17)፡፡
ይቀጥላል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤ/ክ ጥምቀት በየዓመቱ ጥር 11 ቀን ይከበራል። ዋዜማው ወደ ወንዝ የሚወረድበት የሚፈሱ ወንዞች ለጥምቀቱ የሚከተሩበት ስለሆነ «ከተራ» ይባላል። ከተራ ማለት ውኃን መገደብ ወይም በቁሙ መከተር ማለት ነው። የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በጥንታውያን አብያተ ክርስቲያናት የሚከበር ትልቅ በዓል ነው። ጌታችን ወደ ባሕረ ጥምቀት ወርዶ የእኛን ጥምቀት የቀደሰበትን የሮም ካቶሊክ ታከብራለች። የግሪክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንም ወደ ወንዝ በመውረድ ውኃውን ባርከው መስቀሉን በባሕሩ ላይ በመጣል ወጣቶች መስቀሉን ዋኝተው ለጳጳሱ በመስጠት ያከብሩታል። እኛም ጥምቀትን ከባሕል ይልቅ በሃይማኖታዊ ምሥጢሩ ልናስበው ይገባናል፡ ደስታችንንም በመንፈሳዊ ዝማሬና አምልኮ ልንገልጥ ይገባናል። የበረከት በዓል ያድርግልን!
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ