የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጥቂት ዕረፉ/ማር 6፡31/

ቤተ ጳውሎስ አርብ ሰኔ 1 2004 ዓ.ም.
ወንጌል ማለት የምሥራች፣ የድኅነት ዜና ማለት ነው፡፡ ወንጌል ስለ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት የሚናገር የነጻነት አዋጅ ነው፡፡ ወንጌል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በሞቱ የኃጢአትን ዋጋ እንደ ከፈለ፣ በትንሣኤው ጽድቃችንን እንዳረጋገጠ፣ ገነት እንደተከፈተች፣ ሕይወት እንደ ተመለሰ፣ ክርስቶስ በድል ነሺ ዙፋኑ እንደ ተቀመጠ፣ ዳግመኛ ያመነውን ሊያሳየን እንደሚመጣ የምትናገር ሰማያዊ ዜና ናት፡፡ ወንጌል ራሱ ክርስቶስ ነው፡፡ ስለ ሌሎች ሃይማኖታዊ ነገሮች ብንናገር አስተማርን ይባላል፡፡ ወንጌል ሰበክን የሚባለው ግን ስለ ክርስቶስ አዳኝነት ስንናገር ብቻ ነው፡፡ ስለ ኢትዮጵያዊ ጃንደረባ በሚናገረው ክፍል ፊልጶስ፡- “ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት” ይላል (የሐዋ. 8÷35)፡፡ ወንጌል ስለ ኢየሱስ የሚናገር ነው፡፡ 
 
ሐዋርያው ጳውሎስም፡- “… ይህም ወንጌል በሥጋ ከዳዊት ዘር ስለ ተወለደ እንደ ቅድስና መንፈስ ግን ከሙታን መነሣት የተነሣ በኃይል የእግዚአብሔር ልጅ ሆኖ ስለ ተገለጠ ስለ ልጁ ነው፣ እርሱም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው” ብሏል (ሮሜ 1÷1-4)፡፡ ወንጌል የሚል ስያሜ የተሰጣቸውም አራቱ የአዲስ ኪዳን መጻሕፍት ናቸው፡፡ ለምን? ወንጌል ተባሉ ስንል ስለ ክርስቶስ ከልደቱ እስከ ዕርገቱ በሙሉነትና በሌጣነት ስለሚዘግቡ ነው፡፡ ወንጌል የክርስቶስ ዜና፣ የመስቀሉ ነገር፣ የአዳኝነቱ ምሥጢር፣ የዘላለም ሕይወት አጀንዳ፣ ብቸኛ የመዳን መፍትሔ፣ የዘላለም ጉዳይ፣ ዘመን የማይሽረው ጥበብ፣ የማይጨረስ ሀብት፣ የማይጎድል ፍቅር ነው፡፡

ብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ የስብከት ዘዴ በተባለውና በ1980 ዓ.ም ባሳተሙት መጽሐፍ ውስጥ እንዲህ ብለዋል፡-
“ምንም የስብከት ምንጩ ቅዱስ መጽሐፍ ቢሆንም ጥቅሱም ከእርሱው ቢወጣም ሐተታውና አገላለጡ ስለ አዳኙ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆን አለበት፡፡ ኢየሱስን ማዕከል ያላደረገ የእርሱንም አዳኝነት የማይገልጥ ስብከት፣ ስብከት ሊሆን አይችልም፡፡ ለምሳሌ የጥበብ መጀመሪያው እግዚአብሔርን መፍራት ነው ብሎ ስለ ጥበብ፣ ስለ ፈሪሃ እግዚአብሔር ቢናገርም ስለ ክርስቶስ የአዳኝነት ሥራ አልመሰከረም ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ስለ 0ቱ ቃላት ቢናገር፣ ይህም ከቅዱስ መጽሐፉ ቢጠቀስም የኢየሱስ ክርስቶስን የሕይወት ታሪክና የአዳኝነቱንም ሥራ አልተመለከተም ማለት ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስ “እኛ ግን በክርስቶስ እናስተምራለን በተሰቀለው” ሲል በክርስቶስ ስም መስበክ መናገርም ተገቢ መሆኑን ገልጦ ተናግሯል (1ቆሮ. 1÷23)፡፡
የኢየሱስን ስም የአዳኝነቱንም ሥራ አይናገሩም እንጂ በጠቅላላው ስለ እግዚአብሔር በአይሁድ ምኩራብ በእስላሞችም መስጊድ ሊነገር ይችላል፡፡ ሲነገርም ይሰማል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ግን መሪያችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለሆነ የእርሱን የሕይወት ታሪክ የማዳኑንም ተግባር መመስከር፣ መስበክ፣ መናገርም አለብን፡፡ … ማንኛውም እውነት ነቢያት የተናገሩት ትንቢት፣ የሰው ልጅ ድኅነት በኢየሱስ ክርስቶስ መፈጸሙን የሁሉም መፈጸሚያ እርሱ መሆኑን በመግለጥ የሚሰበከው እውነተኛው ክርስቲያናዊ ስብከት ነው፡፡ ሰባኪውም እውነተኛ ሰባኪ ነው።” /የስብከት ዘዴ በብፁዕ አቡነ መልከ ጼዴቅ 1980/
ወንጌል የሚሰበከው በምድራውያን ሹማምንት ፈቃድ ሳይሆን የሰማይና የምድር ጌታ በሆነው በኢየሱስ ክርስቶስ ሥልጣን ነው፡፡ ወንጌል ለመስበክ የምናሳየው የፈቃድ ወረቀት፡- “ሥልጣን ሁሉ በሰማይና በምድር ተሰጠኝ፡፡ እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው÷ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም÷ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ” (ማቴ. 28÷19-20) የሚለው አምላካዊ ቃል ነው፡፡
ጌታችን ወደ ሰማይ ከማረጉና ታላቁን ተልእኮ ከመስጠቱ በፊት ደቀ መዛሙርቱን እየላከ ያለማምዳቸው ነበር፡፡ “ሐዋርያትም ወደ ኢየሱስ ተሰብስበው ያደረጉትንና ያስተማሩትን ሁሉ ነገሩት” (ማር. 6÷30)፡፡ ሪፖርቱን ለክርስቶስ ሲያቀርቡ ብዙ ጊዜ ይሰጣቸው የነበረው መልስ አስደናቂ ነው፡፡ በአንድ ወቅት ርኩሳን መናፍስት ስለተገዙላቸው እጅግ ደስ ብሏቸው ወደ ጌታ ሲመጡ፡- “ነገር ግን መናፍስት ስለተገዙላችሁ በዚህ ደስ አይበላችሁ÷ ስማችሁ ግን በሰማያት ስለ ተጻፈ ደስ ይበላችሁ”ብሏቸዋል (ሉቃ. 10÷20)፡፡ የወደቀውን ጠላት ስለረገጣችሁ ሳይሆን በእኔ ቤዛነት ስለዳናችሁ በእግዚአብሔር አባታችሁ ፊት ዕውቅና ስላገኛችሁ ደስ ይበላችሁ ብሏቸዋል፡፡ ከጸጋ ስጦታዎች ይልቅ ደስ የሚያሰኘው መዳናችን ነውና፡፡
በሌላ ጊዜም ደቀ መዛሙርቱ ስለነበራቸው የወንጌል ጉዞ ሪፖርት ሲያቀርቡለት እንዲህ ብሏቸዋል፡- “እናንተ ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ አላቸው፤ የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና÷ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ” (ማር. 6÷31)፡፡
ጌታችን በገጣባ አህያ የሚጭን ሳይሆን አህያዋን ቀድሞ የሚያክም ነው፡፡ እንዲሁም አገልጋዮን ከነ ሕመምህ አገልግለኝ የሚል ሳይሆን ፈውሶ የሚልክ መልካም ጌታ ነው፡፡ እንደ ሻማ እያለቅን እንድናበራ አይፈልግም፣ እንደ መቅረዝ ዘይቱን እየሞላን እንድናበራ ይፈልጋል፡፡ ሕፃኑ የጡት ወተት የሚያገኘው እናቲቱ በትክክል ስትመገብ ነው፡፡ እናቲቱ ካልበላች ልጁ ወተት አያገኝም፡፡ ጌታ ለልጁ የሚያስበው እናቲቱን በመመገብ ነው፡፡ ሞልቶን እንድንፈስ እንጂ እንጥፍጣፊ እንድንሰጥ አይፈልግም፡፡ እኛ ለምናገለግላቸው ብቻ እያሰብን የራሳችንን መንፈሳዊ ምግብ እናጓድላለን፡፡ እግዚአብሔር ግን ለእኛም ያስባል፡፡ እየወደቁ ማንሣት የለም፣ ስንቆም ብቻ የወደቁትን ማንሣት እንችላለን፡፡ ይህ ደግነት ወይም መሥዋዕትነት አይደለም፡፡ ክርስትና ኖሮ የማኖር ሥርዓት ነው፡፡ መሥዋዕት የምናደርገው ምድራዊውን ጥቅም እንጂ ሰማያዊውን ምግብ አይደለም፡፡ ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ስለዚህ እኔ ያለ አሳብ እንደሚሮጥ ሁሉ እንዲሁ አልሮጥም÷ ነፋስን እንደሚጎስም ሁሉ እንዲሁ አልጋደልም። ነገር ግን ለሌሎች ከሰበክሁ በኋላ ራሴ የተጣልሁ እንዳልሆን ሥጋዬን እየጐሰምሁ አስገዛዋለሁ” ብሏል (1ቆሮ. 9÷26-27)፡፡
የጡት ወተትና የጡጦ ወተት ልዩነት አለው፡፡ የጡት ወተት እናቲቱ ለራሷ ከወሰደችው ምግብ ለልጁ የሚተርፈው ሲሆን የጡጦ ወተት ግን ለልጁ ብቻ ተብሎ የሚዘጋጅ ነው፡፡ ለልጁ ግን ጠቃሚነት ያለው ከጡጦው ይልቅ የጡት ወተት ነው፡፡ ዛሬ ያለው አገልግሎት የጡጦ አገልግሎት ነው፡፡ ለሕዝቡ ተብሎ ብቻ የሚዘጋጅ፣ የስብከት ሰዓት ሲደርስ አገላብጦ የሚወጣበት፣ ወይም ተበድሮ የሚሰበክበት ነው፡፡ ስለዚህ የሚወለዱት ልጆች አቅም የለሽ፣ በፈተና የማይፀኑ ሆነዋል፡፡ ለራሳችን ከበላነው፣ ካረፍንበት፣ በጸሎት ሆነን ካጣጣምነው ቃል ብንናገር ኖሮ ብዙዎች ለነጻነት በተወለዱ ነበር፡፡ ስለዚህ የምንወልዳቸው የአጋር ልጆች እየሆኑ መንፈሳዊ ነጻነታቸውን የተገፈፉ ለኃጢአት የተማረኩ ይሆናሉ፡፡ ነጻ ሳይወጡ መውለድ ትውልድን ለባርነት መፈልፈል ነው፡፡
ከትንሹ እስከ ትልቁ ያሉት አገልጋዮች የሚያስቡት ለሕዝቡ ነው፡፡ ለአገልጋይ የሚያስብ አገልጋይ ጠፍቷል፡፡ የእረኞች አለቃ ኢየሱስ ግን ለአገልጋዮች መንፈሳዊ ደኅንነት ያስባል፡፡ ስለ አገልግሎታችን ብዙ ሪፖርት ስናቀርብለት፡- “እናንተ ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ” ይለናል (ማር. 6÷30)፡፡
ዐሥር ሺህ ሜትር በሩጫ ይዘለቃል፣ አንድ ሺህ ኪሎ ሜትር ግን በሩጫ አይዘለቅም፡፡ አገልግሎት ሰፊ ሩጫ ነው፡፡ በዛሬው ግለታችን ብቻ አሸንፈን የጠላትን መንደር አፈራርሰን በጨለማ የተያዙትን ነጻ አውጥተን የምናድርበት አይደለም፡፡ እያዳመጥን የምንናገርበት፣ እያረፍን የምንጓዝበት ነው፡፡ አገልጋዮች በቃሉ ብቻ ሳይሆን በሥጋም ማረፍ አለባቸው፡፡ የፀጥታ ጊዜ፣ ከራሳቸው ጋር የሚሆኑበት ሰዓት፣ ነጻነት የተላበሰ ተፈጥሮ ውስጥ ማረፍ ያስፈልጋቸዋል፡፡ ይህ ቅንጦት አይደለም፡፡ ሕዝባችን ለአገልጋዮች ብዙ መብልና የሚያሰክር መጠጥ ከሚያቀርብላቸው ዕረፍትን ቢያዘጋጅላቸው ተገቢ ነበር፡፡ የሱነም ሴት ያደረገችው ይህንን ነው፡፡ ለኤልሳዕ ማረፊያ ቤት፣ ማንበቢያ ጠረጴዛ፣ … አዘጋጀችለት (2ነገሥ. 4÷8-10)፡፡ አራስ ልጅ እንዲህ ይላል ይላሉ፡- “እናቴ ረሀቤን ስታውቅልኝ ጥማቴን አታውቅልኝም” እናቲቱ ብዙ ጊዜ ሕጻኑ ምግብ እንጂ ውሃ እንደሚያስፈልገው አታውቅም፡፡ ታዲያ በዱዳ አንደበቱ፡- “እናቴ ረሀቤን ስታውቅልኝ ጥማቴን አታውቅልኝም” ይላል ይላሉ። መልእክቱ ለአራሱ ልጅ ውሃም ያስፈልገዋል ማለት ነው። አገልጋዮችም ዛሬ ተናገሩ ቢባሉ ከአራሱ ሕፃን ይልቅ፡- “ወገኔ ረሀቤንም ጥማቴንም አላወቀልኝም” ሳይሉ አይቀሩም፡፡ የአገልጋይ አድናቂ ነኝ ማለት ቋንቋውም መንፈሳዊ አይደለም፡፡ ከማድነቅ መደገፍን መለማመድ ያስፈልጋል፡፡ ብዙ አገልጋዮች እየራባቸው እንደሚያድሩ አውቃለሁ፡፡ ሕዝባችንም በአብዛኛው ሐሰተኞቹን መምህራን ሲቀልብ ለእውነተኞቹ ግን ቁጥብ እንደሆነ አውቃለሁ፡፡
ሩኅሩኁ ጌታ፣ ያስቀመጠውን የማይረሳ አምላክ ለደቀ መዛሙርቱ፡- “እናንተ ራሳችሁ ብቻችሁን ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ” አላቸው (ማር. 6÷30)፡፡ ጌታችን እየተናገረ ያለው የአገልጋዮች ጊዜ እንዲኖር፣ አገልጋዮች በኅብረት ሆነው እንዲያርፉ እየመከረ ነው፡፡ ብዙ አገልጋዮች አገልጋዮችን አያቀርቡም፡፡ አገልግሎታችን ሰማያዊ ጥሪያችን ከሆነ መዋደድ ግድ ነው፡፡ ገበያ ከሆነ ብንራራቅም አይደንቅም፡፡ ባለንበት ዘመን የነጋዴዎች ማኅበር፣ የፖለቲከኞች ማኅበር፣ …. እየተባለ ሁሉም ሲገናኝ የአገልጋዮች ጉባዔ ግን አለመኖሩ ያሳዝናል፡፡ ወንጌሉን ከሚሰብኩት አገልጋዮች ይልቅ ወንጌሉን የሚቃወሙት ሰዎች የተሻለ ድርጅታዊ ኅብረት አላቸው፡፡ ምንም እንኳ የአጋንንት ማኅበርተኞች ባያስቀኑም እኛ ግን ልናውቅበት ይገባል፡፡ ጌታችን፡- “የዚህ ዓለም ልጆች ለትውልዳቸው ከብርሃን ልጆች ይልቅ ልባሞች ናቸውና” ያለውን መመከሪያችን ልናደርገው ይገባል (ሉቃ. 16÷8)፡፡
“ብቻችሁን” የሚለው ቃል ማራኪ ነው፡፡ አገልጋዮች ምእመናን ጣኦት ይሆኑባቸዋል፡፡ የሚኖሩት በእግዚአብሔር እጅ ሳይሆን በምእመናን ይመስላቸዋል፡፡ ምእመናኑ ቢሰጡ ቸርነት አይደለም፡፡ መንፈሳዊ ግዴታቸው ነው፡፡ የማያልቀውን ሀብት አገልጋዩ እየሰጠ የሚጠፋውን ገንዘብ ከምእመናኑ በመቀበሉ ሊሳቀቅ አይገባውም፡፡ ምእመናን በአገልጋዮች ጉባዔ ሊገኙ አይገባም፡፡ በውጭ ነገሮችን ሊያስተካክሉ ይችላሉ፡፡ አገልጋዮች ግን የራሳቸው የጽሞና ጊዜ ያስፈልጋቸዋል፡፡ መንግሥት፣ መንግሥት የሚሆነው የራሱ ምሥጢር ካለው ብቻ ነው፡፡ እንዲሁም የመንግሥቱ ሠራተኞች የሆነ አገልጋዮች የራሳቸው ምሥጢር ያስፈልጋቸዋል፡፡ በእውነት አገልጋዮች ከቸር ምእመናን ይልቅ አገልጋዩ ድካማቸውን እንደሚያውቅላቸው ሊረዱ ይገባል፡፡ ባልና ሚስት የቤቱን ምሥጢር ለልጆቹ በሙሉ አይነግሩም፡፡ ምክንያቱም ልጆቹ የመሸከም አቅማቸው አይፈቅድምና ነው፡፡ እንዲሁም ከአገልጋይ ጋር ሊነገር የሚገባው ምክክር ወደ ምእመናን መምጣት የለበትም፡፡ “በጫጩት ፊት ፈንግል አይወራም” ይባላል፡፡ ለጫጩት አቅም እንኳን በሽታው መጥቶ ድምፁም ይገድላታል።
ወደ ምድረ በዳ ኑና ጥቂት ዕረፉ
ምድረ በዳ እግዚአብሔር ልጆቹን የሚያሰለጥንበት ስፍራ ነው፡፡ በነቢዩ በሆሴዕ ከተነገረው ተስፋ፡- “ስለዚህ እነሆ÷ አባብላታለሁ÷ ወደ ምድረ በዳም አመጣታለሁ÷ ለልብዋም እናገራለሁ” የሚል ነው (ሆሴ. 2÷16)፡፡ ምድረ በዳ እግዚአብሔር ለልብ የሚናገርበት ስፍራ ነው፡፡ በከተማ በጆሮአችን ብዙ ድምፆችን እንሰማለን፡፡ በምድረ በዳ ግን የእግዚአብሔርን ድምፅ በልባችን እንሰማለን፡፡ እግዚአብሔር ለልብ የሚናገር አምላክ ነው፡፡ ወሬኞች ለጆሮአችን፣ ጠቢባን ለአእምሮአችን፣ እግዚአብሔር ግን ለልባችን ይናገራል፡፡ ታዲያ እግዚአብሔር ተናግሮ እንዲያሳርፈን ወደ ምድረ በዳ መምጣት ያስፈልጋል፡፡ ምድረ በዳ ለዓይን የሚታይ ነገር የሌለበት ማለት ነው፡፡ እንዲሁም ከቊሳዊ ዓለምና ዕይታ ወጥተን በገለልተኛ ስፍራ የጌታን ድምፅ መጠባበቅ ያስፈልገናል፡፡ ጥቂት ዕረፉ ነው ያለው፡፡ ጥቂት ማረፍ ለሁለት ሦስት ቀናት በፀጥታ መሆን ለወሩ የሚበቃ ኃይል የምንሞለበት ነው፡፡ ሂሳብ ሳንሞላ የሞባይል ስልካችንን ብንደውል የምንፈልገው ጋ አያገናኘንም፡፡ በባዶ የምንገናኘው ከዋናው ቴሌ መሥሪያ ቤት ጋር ነው፡፡ እንዲሁም መለኮታዊውን ኃይል ሳንሞላ ወገናችንን ማግኘትና ማሳረፍ አንችልም፡፡ በባዶ የምንገናኘው ከዋናው ቤታችን ከክርስቶስ ጋር ብቻ ነው፡፡
“የሚመጡና የሚሄዱ ብዙዎች ነበሩና÷ ለመብላት እንኳ ጊዜ አጡ” (ማር. 6÷31)፡፡ ዛሬ ቀልብ አጥተን የምንባዝንለት ተተክሎ የሚቀር ብቻ አይደለም፡፡ አንዱ ይመጣል፣ ሌላው ይሄዳል፡፡ ሽርሽሩ ብዙ ነው፡፡ ስለዚህ ሁሉም ለመዳን አይመጣምና ጸሎትን ስለረሳንበት፣ ጽሞናን ስለተውንበት ጊዜ ንስሐ እንግባ፡፡ አስተውለን ልናርፍ ካልቻልን እግዚአብሔር የማንፈለግበትን ጊዜ አምጥቶ በግድ ያሳርፈናል፡፡ ያ ደግሞ በነጻ እንደ መማር ቀላል አይሆንም፡፡
አገልጋይ የሚባሉት በመድረክ የሚያገለግሉ ብቻ አይደሉም፡፡ እናት በቤት ውስጥ፣ ሠራተኛ በሥራ ስፍራ አገልጋይ ነው፡፡ የኑሮን ግዴታ ለመሙላት ብዙ መባዘን ያለባቸው እንደ ማርታ ላይ ታች፣ ሽቅብ ቁልቁል የሚሉ ወገኖችም እንደ ማርያም ከጌታ እግር ሥር ቁጭ ብለው ዕረፍትን ሊጠጡ ይገባል/ሉቃ. 10፡42/፡፡ እንቅልፍ አጥተው ቢሮጡም ዓለም ጐዶሎ ነው፡፡ ከጌታ ጋር ስንሮጥ ግን ትንሹ ብዙ ነው፡፡ ለእግዚአብሔር ጊዜ ያጡ፣ በሩጫቸው ብቻ የሚኖሩ የመሰላቸውን እግዚአብሔር በአልጋ አስተኝቶ፣ በወኅኒ ጥሎ አግኝቷቸዋል። እግዚአብሔር ከወከባ ወጣ የምንልበት የጽሞና ሰዓት እንዲኖረን ይፈልጋል። ዕድሜ ልክ መባዘን ምንድነው?
                                    ጥቂት ዕረፉ”

                                                   /ማር 6፡31/።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ