የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጥበብ

ጃፓናውያን፡- “ጥበብ የራቀው እውቀት ልክ በአህያ ላይ እንደ ተጫነ መጽሐፍ ነው” ይላሉ ።

እውቀትን የምናስተላልፍበት ሕጋዊ መንገድ አንደኛው ማስተማር ነው ። ማስተማር ደግሞ የንግግር ችሎታን የሚጠይቅ ነው ። ማስተማር ከሌለበት ምንም ቢማሩ የጋን ውስጥ መብራት ተብሎ ከመጠራት ውጭ ጥቅም የለውም ። እውቀት ተግባርና ማስተላለፍ ወይም ልግስና ይፈልጋል ። ከእውቀት ዓላማ ውጭ እውቀትን መያዝ ወንጀለኛ ያደርጋል ። ንግግርም የልምምድና የትምህርት ውጤት ነው ። በልምምድ አፍ እንደ ፈታን በልምምድም መልካም ተናጋሪ እንሆናለን ። ከዚያ ባሻገር እግዚአብሔር አንደበትን በጸጋ ይፈታል ። በመከራ ዘመን ቃልም ይሰወራልና፡- “ወደረኞቻችሁ ሁሉ ሊቃወሙና ሊከራከሩ የማይችሉትን አፍና ጥበብ እሰጣችኋለሁና” ብሎ ተስፋ ሰጥቶናል ። ሉቃ . 21፡15 ። ይህን ለዘወትር የማስተማርና የግንኙነት ዘይቤ ብንናፍቀው ላናገኘው እንችላለን ። የመከራ ዘመን ረድኤት ለሰላም ዘመን አይመጣም ። እስራኤል መናን በምድር በዳ እንጂ በከነዓን አልበሉም ። ባለ መናውም ፣ መናውም ፣ ሕዝቡም አሉ ። ያለ ጊዜውና ያለ ቦታው ጸጋ አይመጣም ። እውቀትን የምናስተላልፍበት የንግግር ችሎታ ከእውቀት ትምህርታችን ጋር አብሮ መጓዝ ይኖርበታል ። ምክንያቱም መኪና መንዳት የሚለማመድ ሾፌር ለመሆን እንጂ ወረቀቱን ለመያዝ አይደለም ። በተፈለገ ሰዓት አለሁ ለማለት መኪና ይለማመዳል ። መኪና ካልገዛሁ አልለማመድም የሚል የለም ። አዋቂም የሚፈለግበት ብርሃናዊ ዘመን ይመጣል ። በሕፃንነትና በብልግና ባሕል የተያዘው ዘመናዊ ትውልድ ግራ የገባው ቀን አዋቂዎችን ይፈልጋል ። ሰይጣናዊ እውቀቶች አሉ ፣ ጥይትን የሠራ እውቀት ቢሆንም ለሰው መድኅን የማይሆን እውቀት አጋንንታዊ ነው ። መድኃኒትን የሚሠራ እውቀት ደግሞ ከእግዚአብሔር ነው ።

የሚማር የኋላ ዕዳው ማስተማር ነውና የንግግር ችሎታን ማዳበር አለበት ። በማስተማር ውስጥ የሰው እውቀቱ ሕያው እየሆነ ይመጣል ። “ማስተማር እንደገና መማር ነው” ይላሉ ። የበታቾቹን የሚያስጠና ተማሪ እየተማረ ያልገባው ትምህርት ሲያስተምር ይገለጥለታል ። ንግግር የማናደርግ ከሆነ ለመርሳት በሽታ እንጋለጣለን ። ጭንቀትም እያጠቃን ይመጣል ። መንደር ውስጥ ችግር እንጂ ጭንቀት የለም ። ሲለፈልፉ አእምሮአቸው ነጻ እየሆነ ይመጣል ። ባለመናገር ቃላት እየተረሱ ይመጣሉ ። ቋንቋ ኋላ የመጣ ነውና በየዕለቱ ካልተጠቀምንበት ወደ አገሩ ይመለሳል ። የንግግር ችሎታ የሌላቸው አዋቂዎች ወይ ዝምታን ይመርጣሉ ካልሆነ ግን ቃላትን የማይመርጥ ተራ ተናጋሪ ይሆናሉ ። “ሞኝ ባያፍር ዘመዱ ያፍራል” እንዲሉ በንግግራቸው ወዳጆቻቸው ሳይቀር ይሳቀቃሉ ። ከሃያ አምስት ዓመት በፊት አንድ የገጠር ከተማ ለአገልግሎት ሄድሁ ። በዚያች ከተማ የነበረው ትልቅ ምግብ ቤት ምሳ ተጋበዝሁ ። ምሳው ግን የቀረበው በአዲስ ፖፖ ነው ። የዚያ አገር ሥጋ እንደ ጥጥ ያለ ፣ ጣዕሙ ልዩ ነው ። አሁንም ግን ከሥጋው ማቅረቢያውን ሳስብ እስቃለሁ ። ቃላት ወይም ንግግር እውቀትን ማቅረቢያ ሰሐን ነውና ልንጠነቀቅለት ይገባል ።

ጃፓናውያን፡- “ጥበብ የራቀው እውቀት ልክ በአህያ ላይ እንደ ተጫነ መጽሐፍ ነው” ይላሉ ። ጥበብ የንግግር ችሎታ ነው ። ጥበብ ጊዜን ፣ ቦታንና ሁኔታን መመዘን ነው ። እውቀትን የእጅ ስልካችንም ተሸክሞታል ። ኮምፒዩተርም አህያ ልትሸከመው የማትችለውን ሺህ መጽሐፍ ተጭኗል ። የመቅጃ መሣሪያም ብዙ እውቀትን ሰምቶ ያሰማል ። ሰውን ግን ከእነዚህ ቁሳቁሶች ልዩ የሚያደርገው ጥበብ ነው ። የምንጠቅሳቸው ጥቅሶች ከእግዚአብሔር ቃል ቢሆኑም ጊዜውን የማይመጥኑ ከሆነ ጥበብ ከድቶናል ማለት ነው ። ለፈውስ የተሰጠውን ቃል ሰው ለማቍሰል የምንጠቅሰው ከሆነ የበቀል መሣሪያ አድርገነዋል ፤ እግዚብሔርንም የዓመፃችን ተባባሪ አድርገነዋልና ቅጣት አለው ።

ማስታረቅ ሰው እግዚአብሔርን የሚመስልበት ትልቅ ግብር ነው ። እግዚአብሔር ራሱ ሰው ሁኖ ዓለምን ከራሱ ጋር አስታርቋል ። ማስታረቅ የእግዚአብሔር ልጆች የምንባልበት ትልቅ ተግባር ነው ። የእግዚአብሔር ልጅ የዲያብሎስን ሥራ በደሙ አፍርሷል ። እኛም የእግዚአብሔርን ልጅ መስለን የዲያብሎስን ሥራ ለማፍረስ ሰውን በንስሐ ከፈጣሪው ጋር ፣ በይቅርታ ከጎረቤቱ ማስታረቅ ይገባናል ። ማስታረቅ ግን ጥበብ ይፈልጋል ። በእውቀት ብቻ ማስታረቅ የበለጠ ማጣላትን ይወልዳል ። በማስታረቅ ውስጥ ያዩትንና የሰሙትን በልብ መያዝ ፣ መታዘብን ማራቅ ፣ ታረቁልኝ ብሎ ደግ ደጉን ብቻ ማውራት ይገባል ። ማስታረቅ አንድ ሳለ በስብራት ሁለት የሆነውን አጥንት መጠገን ነውና ጥንቃቄና ጥበብ ይፈልጋል ።

ማጽናናት ሰውን ከሲኦል ጨለማ ወደ ገነት ብርሃን ማምጣት ነው ። ሰይጣን በትካዜያችን ተጠቃሚ ነው ። ሰው ሲተክዝ ችግሩን ያያል ፣ ሲጽናና ግን እግዚአብሔርን ያያል ። ያልተጽናና ሰው ልበ ዕውር ነውና ያለውን ነገር ማየት አይችልም ። ማጽናናት ጥበብ ይፈልጋል ። ጻድቁ ኢዮብ ባልንጀሮቹ ምሁራንና ፈላስፎች ነበሩ ። ጥበብ በማጣታቸው ግን በቍስል ላይ ጥዝጣዜ ጨመሩበት ። አጉል አጽናኝ ኀዘነተኛን ያደክማል ፣ ከፈጣሪው እንዲጣላ ያደርገዋል  ። ዘመናዊ ፈሪሳውያን የሆኑ ሰዎችም ሰው የሚታመመውና የሚያጣው ስላላመነ ፣ የተሰወረ ኃጢአት ስላለበት ነው እያሉ ይናገራሉ ። ይህ የአጽናኝ አቁሳይ የሚወለድበት አስተሳሰብ ነው ። ገና የሚሞት ሥጋ ተሸክመው ስለ መታመም ይደነቃሉ ፣ ዕርቃናቸውን መቃብር ሊወርዱ ተራ እየጠበቁ ስለ ዕለት እጦት ይገረማሉ ። ብቻ ማጽናናት በእውቀት ብቻ ሳይሆን በጥበብም ነው ።

የሰውን የስሜት ሕዋሳት በመግዛት ዓለም ትውልድን ይዛለች ። ስብከት ብቻውን አያስተምርምና ቤተ ክርስቲያን የስሜት ሕዋሳትን ሁሉ የሚገዙ ማስተማሪዎችን አድርጋለች ። ይህ ጥበብ ነው ። ዓይን ቅዱሳን ሥዕላትን ያያል ፣ ጆሮ ዝማሬ ያደምጣል ፣ አፍንጫ ዕጣን ያሸታል … ። ጥበብ ለወንጌል ሥራ አስፈላጊ ነው ። መዳናችንም በጥበብ ነው ። “እግዚአብሔር ዓለምን ከፈጠረበት ጥበቡ ፣ ሰው ሁኖ ዓለምን ያዳነበት ጥበቡ ይበልጣል” እንዲሉ ።

ጌታ ሆይ እውቀትን ከጥበብ ጋር አድለን!

የብርሃን ጠብታ 5

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ነሐሴ 30 ቀን 2013 ዓ.ም.

ያጋሩ