የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጸሎተ ምሕላ

በቤትህ የተከልከን ታላቅ ገበሬ ሆይ ይቅር በለን ።
ለሰማይ ክብር የጠራኸን ክቡር ሙሽራ ሆይ ማረን ።
ሥራህን ካንተ በቀር የሚያደንቀው የሌለ ባለሙያ ሆይ አድነን  ።
ሀብትህ ጉድለት የማያሳይ ወደር የለሽ ባለጠጋ ሆይ ይቅር በለን ።
ሰማይ መንበርህ ፣ ምድር መከዳህ የሆነች ሙሉ ሆይ ማረን ።
የአማኞችን መሥዋዕት የምትቀበል ተለማኝ ጌታ ሆይ አድነን ።
በረድኤት የወረድከው በሥጋም የተገልጥከው ታላቅ መልስ ሆይ ይቅር በለን።የደካሞችን ሸክም ያቀለልህ ፣ ለተከሳሾች የተከሰስህ ቤዛ ሆይ ማረን ።
ምስጋናን የምትወድ የመላእክት ፈጣሪ ሆይ አድነን ።
ርቀው የማይርቁህ ፣ የሙከራ ሁሉ መደምደሚያው ጉልላት እግዚአብሔር ሆይ ይቅር በለን ።
የፊትህ መልክ የማይጠገብ ታላቅ ውበት ሆይ ማረን ።
የዘረጋኸው ክንድህ የማይታጠፍ አሻጋሪ አምላክ ሆይ አድነን ።
ቀኑን ሌት ፣ ሌቱንም ቀን ስታደርግ የማይቸግርህ መጋቢ ሆይ ይቅር በለን።የሚችለው ያጣውን አመለኛ የምትችል የእግዚአብሔር ክንድ ሆይ አትጣለን።እውቀትህ የማይፈተን የማትመረመር ብርሃን ሆይ አድነን ።
ወደ ኋላ ለመመለስ ያፈረውን ፣ ወደፊት ለመጓዝ የፈራውን የምታበረታ መጽናናት ሆይ ይቅር በለን ።
የማትፈርሰው የድሆች አዳራሽ ሆይ በመልካም አስበን ።
ዓለማት ያልቻሉህ በድንግል ማኅፀን ራስህን የወሰንህ ሆይ አድነን ።
እኛን ከራሳችን ጋር ያስማማኸን ጠብ ገዳዩ ኃያል ሆይ ይቅር በለን ።
ለኃጢአት የተጉትን ለጽድቅ የምታነቃ የሕይወት አለቃ ሆይ ማረን ።
የተወረወረን ጦር አጥፈህ የምትጥል የአብርሃም ጋሻ ሆይ አድነን ።
ያላወቁህንና የማይወዱህን የምትታገሥ ታላቅ ፍቅር ሆይ ይቅር በለን ።
የድሆች ጩኸት ፣ የባልቴቶች መፈናቀል የሚገድህ ሆይ እባክህ ተነሥ ።
ራሱን በራሱ በጦር የወጋውን የምትፈውስ መድኅን ሆይ ዛሬ ድረስ ።
ማዕበልና ነፋሳት የሚታዘዙህ የፀጥታው ወደብ አቤቱ ይቅር በለን።
ችለው የማይርቁህ ፣ ደፍረው የማይቀርቡህ እሳት ሆይ አቤቱ ማረን ።
የሞት ነጋሪትን በእልልታ የምትለውጥ የእነ አስቴር የነ መርዶክዮስ አምላክ አድነን ።
የልባችንን ድንዳኔ ይቅር በለን ።
ያልተገራውን ሥጋችንን ይቅር በለን ።
የማያባራውን ምላሳችንን ይቅር በለን ።
ገፍተን ስለጣልነው ወንድም ይቅር በለን ።
ገድለን ስለቀበርነው አቤል ይቅር በለን ።
ያለ በደሉ ስለፈረድንበት ምስኪን ይቅር በለን ።
ከክፉ ቀን ጥፋቶች አድነን ።
ከተመዘዘ ሰይፍ አድነን ።
ከታላቅ ዝንጋዔ አድነን ።
ከልብ ኩራት አድነን ።
ከዝሙት ፆር አድነን ።
በምትመጣው መንግሥትህ አስበን ።
ለአብ ለወልድ ለመንፈስ ቅዱስ ክብርና ምስጋና ይሁን ዛሬም ዘወትርም ለዘላለሙ አሜን ።
የነግህ ምስጋና/16
መጋቢት 17 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
/ይህን ጸሎተ ምሕላ በኅብረት ሲደርስ በቅብብሎሽ ማለት ይቻላል/ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ