“ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች፤” ሉቃ. 1 ፡ 47 ።
አባቶች የብሉይ ኪዳኗ ማርያም የንስብሖ ምስጋና ፣ ከእመቤታችን ታዐብዮ ውዳሴ ጋር ትይዩ እንደ ሆነ ያስተምራሉ ። የብሉይ ኪዳኗ ማርያም ባሕረ ኤርትራ ሲከፈል ንሴብሖ – ምስጉን ነው የተመሰገነ ብላ ከበሮ ነጥቃ ፣ ሰልፍ መርታ ፣ ከፊት ወጥታ ፣ ቀዳሚት ሁና አመስግናለች ። ዘጸ . 15፡21 ። እመቤታችንም በጌታ መፀነስ ባሕረ ሞት ሲከፈል ታዐብዮ ነፍስየ – ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች በማለት ቀዳሚት ሁና አመስግናለች ። በማኅፀኗ አምላክ በሥጋ እንግድነት እንደመጣ ከምድራውያን ወገን የምታውቅ እርስዋ ነበረች ። ከሰማይ ቅዱስ ገብርኤል ከምድር ድንግል ማርያም የሥጋዌው ባለ ምሥጢር ሁነዋል ። በቅዱሳን መካከል ሽሽግ የለምና ኤልሳቤጥም በመንፈስ ቅዱስ ተረድታ ድንግል ማርያምን አመስግናለች ። አድንቃለች ። “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ ፥ የማኅፀንሽም ፍሬ የተባረከ ነው” ብላለች ። /ሉቃ. 1፡42 ።/ ይህን ምስጋና መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል አስቀድሞ ለድንግል ማርያም አቅርቦ ነበር ። /ሉቃ. 1፡28 ።/ መልአኩንና ቅድስት ኤልሳቤጥም ያስተባበራቸው መንፈስ ቅዱስ ነው ። መንፈስ ቅዱስ የሞላበት ሰው እግዚአብሔር ያከበረውን ያከብራል ። መንፈስ ቅዱስ የክብር መንፈስ ነውና ። አንድ ሰው መንፈስ ቅዱስ እንዳደረበት ምልክቱ ለእግዚአብሔር ክብር ሲሰጥ እንደ ድንገል ማርያም ፣ እግዚአብሔር ያከበራቸውን ሲያከብር እንደ ኤልሳቤጥ ነው ።
ቅድስት ኤልሳቤጥ፡- “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?” በማለት ጉጉቷን ገልጣለች ። /ሉቃ. 1 ፡ 43 ።/ የእግዚአብሔር ሰዎች የሆኑትን ኤልያስና ኤልሳዕን የተቀበሉ የሰራፕታዋ መበለትና የሱነም ሴት ታላቅ በረከት እንዳገኙ የምታውቀው ኤልሳቤጥ ከሁሉ በላይ የሆነውን አምላክ በማኅፀኗ የተሸከመች ድንግል ማርያምን መቀበል ትልቅ ዕድልና በረከት መሆኑን ተገንዝባለች ። ይህን ሰላምታ ሲለዋወጡ መንገድ ጠራጊው ዮሐንስ የስድስት ወር ጽንስ ሁኖ በኤልሳቤጥ ማኅፀን ፣ የዓለሙ አዳኝ ደግሞ የዕለት ጽንስ ሁኖ በድንግል ማርያም ማኅፀን ነበሩ ። መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልና ቅድስት ኤልሳቤጥ ሳይገናኙና ሳይነጋገሩ አንድ ዓይነት አድናቆት አስተላለፉ ። የእግዚአብሔር ሰዎችን አንድ ልብና ቃል የሚያደርጋቸው የእግዚአብሔር መንፈስ ነው ። ዛሬ ቋንቋችን ሲደባለቅ ፣ የምድሩን ጨርሰን በሰማይ ያሉትን ቅዱሳን ስንሳደብ መንፈሰ እግዚአብሔር እየራቀ መሆኑን ያሳያል ። ቡራኬውም “የመንፈስ ቅዱስ ኅብረት ከሁላችን ጋር ይሁን” የሚል ነው ። 2ቆሮ. 13 ፡ 14 ።
የእመቤታችን ምስጋና ወይም ጸሎተ ማርያም የምንለው በሉቃ. 1፡46-55 ያለው ነው ። ይህ ምስጋና ከነቢይት ሃና ምስጋና ጋር ተመሳሳይ ነው ። እመ ሳሙኤል – የሳሙኤል እናት ሃና ልጅ ባለመውለዷ ምክንያት እንደ ተረገመች ሴት ፣ ስካርና እብደት እንደ ተቀላቀለባት ወይዘሮ ተቆጥራ ሳለ እንደ ሰው በጉድለት የማይሳለቅ ፣ ጉድለት የተባለውን እንደ ችሎታው መጠን የሚሞላ እግዚአብሔር ሳሙኤልን ሰጣት ። የመሳፍንት መጨረሻ መስፍን ፣ የነቢያት መጀመሪያ ነቢይ ፣ የመጀመሪያዎቹን ሁለት ነገሥታት ሳኦልና ዳዊትን ቀብቶ ያነገሠው ሳሙኤል የሃና የጸሎትዋ መልስ ፣ የመናቅዋ ክብረት ነበረ ። ሃና ዘመኗን በሙሉ ያማጠች እንጂ አንድ ቀን ብቻ ያማጠች ሴት አልነበረችም ። የጸሎት ምጥ ሳሙኤልን ይወልዳል ። ሃናም፡- “ልቤ “በእግዚአብሔር ጸና ፥ ቀንዴ በእግዚአብሔር ከፍ ከፍ አለ አፌ በጠላቶቼ ላይ ተከፈተ በማዳንህ ደስ ብሎኛል” በማለት አመሰገነች ። 1ሳሙ. 2፡1 ።
የእመቤታችን የድንግል ማርያም ምስጋና ወይም ጸሎተ እግዝእትነ ማርያም ከብሉይ ኪዳን ብዙ ጸሎቶች ፣ ምስጋናዎች ፣ ቃል ኪዳንና ትንቢቶች ጋር የተስማማ ነው ። በዚህም እመቤታችን የቃለ እግዚአብሔር እውቀቷ ከፍ ያለ መሆኑን ያሳየናል ። ጸሎተ ማርያም፡-
• እውነተኛ አክብሮት የልብ መሆኑን ፣
• እግዚአብሔር ነገርን የሚለውጥ አምላክ መሆኑን ፣
• ትውልድን በብሩህ ዓይን ማየትን ፣
• ብርቱ አምላክ በደካማ ሰው እንደሚገለጥ ፣
• ማዳን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ግብር መሆኑን ፣
• እግዚአብሔር የዘረጋውን የማያጥፍ ፣ የሰጠውን የማይነሣ መሆኑን ፣
• በችሎታው እንጂ በችሮታ የማይኖር ኃያል መሆኑን ፣
• የትሕትና አፍቃሪ እንደሆነ ፣
• ዘመናትን የሚለዋውጥ መሆኑን ፣
• ችግረኛን እንደሚያስብ ፣
• ሲነሣ ወይም ሲነጥቅ የሚወቅሰው እንደሌለ ፣
• ከጥንት ጀምሮ ሲናገር መኖሩን ወይም ነባቢ አምላክ መሆኑን፣
• የቃል ኪዳን አምላክ እንደሆነ ፣
• ምሕረቱ አስታዋሽ መሆኑን ፣
• እስራኤልን በልጅ ወግ መቀበሉን ወይም የሕዝቡ አባት መሆኑን የሚገልጥ ነው ።
የእመቤታችን ምስጋና ታላቅ የነገረ መለኮት ትምህርት ቤት ነው ። በዘመናት ሁሉ የተነሡ ደጋግ አባቶች ክፉውን ከይሲ የቀጠቀጡበት የምስጋና በትር ነው ። ዘወትርም የሚጸለይ ፣ ከጸሎተ ነቢያት ጋርም የሚደርስ ታላቅ ግዳጅ የሚፈጽም ጸሎት ነው ። ስለ ሣራ ፣ ስለ ርብቃ ፣ ስለ ራሔል ፣ ስለ ሃና ፣ ስለ ኤልሳቤጥ ስንናገር ብዙዎች ደስ ይላቸዋል ። ስለ ድንግል ማርያም ሲንናገር ግን ይከፋሉ ። ለምን ይሆን ? ቀዳማዊት እመቤት እየተባለ በሚጠራበት ዘመን እመቤታችን ብለን የአምላክን እናት ስንጠራ ይነቅፉናል ። ተገቢ አይደለም ።
በአማኑኤል ስሙ ፣ በተወጋ ጎኑ ፣ በእንተ ማርያም እሙ ምሬአለሁ ፣ ይቅር ብያለሁ ይበለን ። ዘመኑን በሰላም ያሻግረን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 2 ቀን 2012 ዓ.ም.