የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ጾመ እግዚእ /3/

“ዲያብሎስም፡- የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ፥ ይህን ድንጋይ፡- እንጀራ ሁን ብለህ እዘዝ አለው።” ሉቃ. 4፡3 ።
ጌታችን አርባ ቀንና አርባ ሌሊት ጹሞ ከፈጸመ በኋላ ዲያብሎስ ለፈተና መጣ ። ዲያብሎስ የእግዚአብሔርና የመልካም ነገር ተቃዋሚ ነው ። ሰዎች በእግዚአብሔር ላይ ያላቸውን እምነት እንዲጠራጠሩ ያደርጋል ። ጥርጣሬና ፍርሃትን ካልዘራ ሰዎችን ባሪያ ማድረግ አይችልም ። ሰዎች የተደገፉትን እግዚአብሔር ሲጥሉ እንደሚወድቁ ያውቃል ። ዲያብሎስ መፈተኑ በራሱ የአቅሙን አናሳነት ያሳያል ። ማስገደድ አይችልም ማለት ነው ። ዲያብሎስ በአርባ ቀንና በአርባ ሌሊት ጾም ጸሎት ወደ ጌታ የሚቀርብበት ምክንያት አላገኘም ። ጌታችን እንደ ተራበ ባየ ጊዜ ግን ቀረበ ። ዲያብሎስ ጉድለት እየፈለገ የሚቀርብ ነው ። በጉድለቱ አማካይነት እግዚአብሔርን ለማማት ይሞክራል ። ወደ ሔዋን በቀረበ ጊዜ እንዳይበሉ የተከለከሉትን ነገር በመጠየቅ ንግግሩን ጀመረ ። ጉድለት ላይ ብቻ ስናተኩር የዲያብሎስ ፈተና ውስጥ ገብተናል ማለት ነው ። ያለንን ስንቆጥር ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ እየረዳን ነው ማለት ነው ። መራብ ምኞትን ሊገልጽልን ይችላል ። በምንመኛቸው ነገሮች ላይ ብዙ ፈተናዎች ይነሣሉ ። ምኞት ጥቁሩን ነጭ ፣ ነጩንም ጥቁር አድርጎ ያሳያል ። ምኞት በጊዜ የተለካውን የዓለም ሥርዓት ያፈርሳል ። አሁን ካልሆነ ይላል ። ዲያብሎስ በምኞታችን በኩል በብርቱ ይዋጋናል ። አንድን ነገር በጣም ስንፈልገው በጣም መተው አለብን ። ምክንያቱም ቢመጣም ሰላማችንን ይነሣናል ። እምነታችንን ይወስድብናል ። በዓለም ላይ የሚበረክተው ጣል ፣ ጣል ያደረጉት ነገር ነው ። በአንድ ነገር ላይ ያለን ቅዱስ ጭካኔ የዚያን ነገር ዕድሜ ያረዝመዋል ። “ያለ ምንምና ያለ ማንም እኖራለሁ ፣ ያለ ጌታዬ ግን አልኖርም” ብለን ስናስብ ውስጣችን ይጠገናል ። የፈተናም በር ይዘጋል ።
ጌታችን በተራበ ጊዜ ፈታኝ ቀረበ ። ወደ ሔዋን ግን የቀረበው ባለመርካቷ እንጂ በመራቧ አይደለም ። ሔዋን ሳትራብ ታዘዘች ። ድንጋይን ዳቦ ለማድረግ ሞከረች ። ማለትም ከዕፀ በለስ አምላክነትን ፈለገች ። ከዕፀ በለስ አምላክነትን መፈለግ ድንጋይ ዳቦ ይሁን ማለት ነው ። ሰይጣን በሔዋን የለመደውን ወደ ጌታ ይዞ መጣ ። የሰይጣን ቀላልነት ለክፋቱ ተስፋ የማይቆርጥ ብቻ መሆኑ አይደለም ፤ አንድን ሰው በጣለበት መንገድ ሁሉንም እጥላለሁ ብሎ ማሰቡ ነው ። በመደጋገም አንድ ድምፅ በማሰማት ድምፁን ከባዕድነት ወደ ዘመድነት ያመጣዋል ። በዚህም ብዙዎችን ሲጥል ኑሯል ። ጌታችን ተአምራት በማድረግ ረሀቡን እንዲያስታግሥ እየመከረው ነው ። አዎ ጌታችን አምስት እንጀራና ሁለት ዓሣ አበርክቶ መግቧል ። አሁንም ተአምራትን ለራሱ ረሀብ ቢያውለው ተገቢ አይደለም ወይ ? ብለን እንጠይቅ ይሆናል ። ተአምራት ግን ሌሎችን ለመርዳት እንጂ ለራስ ጥቅም የማይውል መሆኑን ለማስተማር ጌታ እሺ አላለም ። ተአምራት የራስ ዝና መገንቢያ ፣ ገንዘብ መሰብሰቢያ አይደለም ። በከንቱ የተቀበሉትን በከንቱ ለመስጠት ፣ ብዙ ተአምራት ካደረጉ በኋላ “እኔ የማልጠቅም ባሪያ ነኝ” ብሎ መሰወርን የሚጠይቅ ነው ። ዛሬ እንደምናየው ሰይጣንን ቃለ መጠይቅ እያደረጉ በምስል ለዓለም እንደሚያሰራጩ ሰዎች ጌታ አላደረገም ። ተአምራት የማድረግ ጸጋ ቢኖረኝ እኔ ጋ የተቀመጠ ለሰው የማደርሰው አደራ ማለት ነው ። አደራውን በቪድዮ የሚያስቀርጽ ሰው ለአደራ የሚበቃም አይደለም ። ራሱን ተጠራጥሯል ማለት ነው ። እግዚአብሔርን ይህን አደረገ እያሉ ማስታወቂያ የሚሠሩ እንደሚያደርግ ቀድሞም ይጠራጠሩ ነበር ማለት ነው ።ይህች ቀንም ተአምር መሆኗን አላወቁም ።
ጌታችን የዲያብሎስን ምክር ቢሰማና ድንጋይን ዳቦ ቢያደርግ ኑሮ ሰይጣን በእኔ ምክር ነው ይህን ያደረገው ፣ እኔ የአምላክ አማካሪ ነኝ ይል ነበር ። የሰይጣንን አሳቡን አንስተውም የተባለው ለዚህ ነው ። ሰይጣን ክፋቱን የሚፈጽመው በደግነት ድምፅ ውስጥ ነው ። ሔዋንን ሲጠይቃት በአሳቢነት ድምፅ ነው የጠየቃት ። ለጌታችንም በረሀቡ ያዘነ ይመስላል ። ያዘነማ አያማክርም ዳቦ ይዞ ይመጣል ። ሰይጣን አይሰጥም ፣ ግን ይህ የለህም እያለ አእምሮን ይበጠብጣል ።
“ዲያብሎስም፡- የእግዚአብሔር ልጅ ከሆንህ ፥ ይህን ድንጋይ፡- እንጀራ ሁን ብለህ እዘዝ አለው።” ሉቃ. 4፡3 ።
የዲያብሎስን ንግግር ልብ በሉ ። ማር የተቀባ መርዝ ነው ። ሰይጣን ግማሽ ደግ ነው ። ሙሉ ክፉ ቢሆን ኑሮ ሁሉ ያውቅበትና ይርቀው ነበር ። ወደ ሔዋን የመጣው በእባብ ሥጋ ተሰውሮ እንጂ እውነተኛ መልኩን ይዞ አይደለም ። ጌታችንን እያለው ያለው “የእግዚአብሔር ልጅ ሁነህ እንዴት ትራባለህ ?” ነው ። ዛሬም እግዚአብሔርን እያመንሁ ይህ ችግር እንዴት ወደ እኔ መጣ የሚል ፈተና ብዙ ሰውን እየናጠ ነው ። አንዳንዶችም እምነት ማለት ፉከራ መስሏቸው፡- “የንጉሥ ልጅ ምን ይሆናል ?” ይላሉ ። የንጉሥ ልጅ ጳውሎስ ግን በረሀብ ፣ በእርዛት ፣ በእስራት ፣ በግርፋት ፣ በመጨረሻም በሰይፍ ውስጥ አልፏል ። ዛሬ የአፍሪካ ወንጌል ተብለው የሚጠሩ ትምህርቶች “ታገኛለህ” ፣ “ትፈወሳለህ” የሚሉ ናቸው ። ታገኛለህ የሚለው የድሀን ጆሮ እንጂ የባለጠጋ አገሮችን ጆሮ አይከፍትም ። ስለዚህ ይህ ወንጌል የአፍሪካ ወንጌል ነው ። ሰዎች ታገኛላችሁ ተብለው ተሰብከው ሲያጡ በመጨረሻ፡- “እምነት ውሸት” ነው ይላሉ ። ሰይጣን በረጅም አቅዶ እየሠራ ነውና መጠንቀቅ ይገባል ። ይህንን የሚሰብኩ ጤነኞች ናቸው ። ምክንያቱም አመጋገባቸው ፣ ስፖርታቸው የተጠበቀ ነው ። ደግሞም በሰው የሚያላግጥ አይታመምም ። የሚጨነቅ ነው የሚታመመው ።
የእግዚአብሔር ልጅ መሆኑን ሰይጣን እንዴት አወቀ ? በዮርዳኖስ ከአርባ ቀን በፊት እግዚአብሔር አብ፡- “የምወደው ልጄ ይህ ነው” ብሎ ሲመሰክርለት ሰምቷል ። የሰማውን ግን ለጥርጥር ተጠቀመበት ። ሰይጣን የራሱ መጽሐፍ ስለሌለው እውነተኛውን ቃል በማጣመም አሳቡን ያስፈጽማል ። ጌታችን ድንጋይን ዳቦ ማድረግ ይችላል ። ነገር ግን ራሱን ለመርዳት ብሎ ተአምር አድርጎ አያውቅም ። ተአምር ለሰዎች ካደረገ በኋላም ብዙ ጊዜ አትናገሩ ይል ነበር ። በእግዚአብሔር መንግሥት ከተአምራት ይልቅ የእግዚአብሔር ፍቅርና የዘላለም ሕይወት ዋጋ አለው ።
ጌታችን በመራቡ ፍጹም ሰው መሆኑ ታወቀ ። የእግዚአብሔር ልጅ በመባሉ ደግሞ ፍጹም አምላክ መሆኑን ተረዳን ። ሰው ሁኗልና ተራበ ። እርሱ ሰው ሁኖ ከተራበና ከታመመ ፣ እኛም ሰው ስለሆንን በችግር ውስጥ እናልፋለን ። ችግር ሰው የመሆን ጉዳይ እንጂ የመንፈሳዊነት ጉድለት አይደለም ። መንፈሳዊነት ሰውነትን ይቀድሳል እንጂ አያስቀርም ። ያለ ኃጢአት እንድንሆን እንጂ ያለ ችግር እንድንሆን አልተጠራንም ። ችግር ባይኖር ብልሃት አይኖርም ነበር ። በረዶ ባይኖር ፈረንጆቹ ማሞቂያ አይሠሩም ነበር ። ዕድገት ተግዳሮት ዋዜማው ነው ። ያለ ችግር መሆን በራሱ ችግር ነው ። ጌታ በሥጋ ታሞ መታመም አይገባኝም ማለት አስደናቂ ትዕቢት ነው ። ፈውሰኝ ማለት ግን ትሕትና ነው ።
የሰይጣንን አሳቡን እንዳንስተው መንፈሳዊ ዓይናችንን ያብራልን !!
ይቀጥላል
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ