“ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል” ሉቃ. 5፡4 ።
ጌታችን ከደቀ መዛሙርቱን አራቱን ጴጥሮስና እንድርያስን ፣ ዮሐንስና ያዕቆብን የጠራበት ድንቅ ምዕራፍ ነው ። እግዚአብሔር ሰውን የሚጠራው ለወዳጅነት ነው ። ወዳጅነት ከዝምድናም ከጓደኝነትም በላይ ነው ። ዝምድና የሥጋ እንጂ የአሳብ ቋጠሮ ላይኖረው ይችላል ። ጓደኝነት እኩል እውቀት ነውና በነጻነት ማጥፋት ሊኖርበት ይችላል ። ወዳጅነት ግን መመካከርና መሸፋፈን ያለበት ፣ ቅን የሆነውን መንገድ የሚከተል ፣ በዘላለማዊ ፍቅር የታሸ ነው ። ጓደኛ ያላቸው ወዳጅ ላይኖራቸው ይችላል ። በፍቅር ዓለም ወዳጅነት እግዚአብሔር ቋንቋ የሆነበት ተግባቦት ነው ። እግዚአብሔር ወዳጅነትን ሲመሠርት በራሱ መለኮታዊ ፍቅር ላይ ተመሥርቶ ነው ። ምንጊዜም በፍቅር ቀዳሚው እግዚአብሔር ነው ። ስለወደደን ወደድነው እንጂ ስለወደድነው አልወደደንም ። እግዚአብሔር ሰውን ሲጠራ አፍኣዊ ሕይወትን አይቶ ሳይሆን ልብን አይቶ ነው ። እግዚአብሔር የጠራቸው ሁሉ ሲጠሩ በሥራ ላይ የነበሩ ናቸው ። የያዝነውን ካላከበርን የምንይዘውን አናከብረውም ። ትንሽዋ ድርሻ ለትልቁ ሹመት የምታበቃ ናት ። ታማኝ የበግ ጠባቂ የነበሩት ሙሴና ዳዊት ለመሪነት ታጭተዋል ። ነገ ለሚሠራው ታላቅ ሥራ እግዚአብሔር ዛሬ በተባለች ቤተ ሙከራ ውስጥ እያሳለፈን ነው ።
እግዚአብሔር ሰውን ሲጠራ እንቢታቸው እንጂ ድካማቸው አላስቸገረውም ። ከሰዎች የሚጠቀመው ባይኖርም ሰዎችን ለመጥቀም ግን በዘመናት ሲጣራ ይኖራል ። ስለ ራሳችን ጥቅም ደጅ የሚጠናን ፣ በራችንን የሚያንኳኳ ፣ በፍቅር የሚለምነን እርሱ ቡሩክ ነው ። ዳዊትን እግዚአብሔር ያነሣው ከወለል በታች ሳለ ነው ። ሸለቆው ተራራ የሚሆነው በእግዚአብሔር ነው ። ያለንበትን ሁኔታ ጌታ እያየ እንዳላየ ፣ እየሰማ እንዳልሰማ አያልፈውም ። እነዚህን ደቀ መዛሙርት ሲያገኛቸው ተስፋ ቆርጠው ሳሉ ነው ። ሐዋርያው ጴጥሮስ እስከ ዛሬ ድረስ ይሠራ የነበረው በሙያና በራስ አስተሳሰብ ነው ። ዛሬ በተአምራት እግዚአብሔር ሲሠራ ያያል ። እውቀቱ እውቀት አልባ ፣ ብልሃቱ ሞኝነት ሲሆንበት ያን ጊዜ ወደ እግዚአብሔር ምክር ዘወር አለ ። እግዚአብሔር ካልረዳን ያለን ነገር እንደሌለን ነው ። ይህች ዓለም እውነተኛ ድሆችንና የባለጠጋ ድሆችን የምታስተናግድ ዓለም ናት ።
ሌሊቱን በሙሉ ዓሣ ለማጥመድ ወጥተው ምንም አላገኙም ነበር ። ሲነጋም ተስፋ ቆርጠው ሳለ በባሕሩ ዳርቻ ጌታ አገኛቸው ። ዓሣ አጥማጆቹ መረባቸውን ያጥቡ ነበር ። ሌሊቱን በሙሉ ሲያጠምዱ ያደሩ ሲነጋ ማጠባቸው እረፍት እንደሌላቸው ያሳያል ። መረብን ማጠብ ግን ያገኙና ያላገኙ የሚያደርጉት ተግባር ነው ። ያገኙ በደስታ ሲያጥቡ ያላገኙ በኀዘን የሚከውኑት ሥራ ነው ። በትልቋ መርከብ ላይ ከፊት የሚቆመው የኋላው ጴጥሮስ ነው ። የመርከቧ ባለቤት ክርስቶስ በጴጥሮስ ታንኳ ላይ ተሳፈረ ። በታንኳዋ ላይ ሁኖ ያስተምር ነበር ። መጀመሪያ የነፍስን ረሀብ አጠገበ ። መድረኩም የጴጥሮስ ታንኳ ነበረች ። ይህ ሁለት ነገር ያሳየናል ። የመጀመሪያው ጴጥሮስ መፈለጉን ፣ ሁለተኛ ጌታችን ሕዝቡን እያስጨነቀ ሳይሆን እያስደሰተ ማስተማሩን ነው ። አሁን ታንኳውን የለቀቀው ጴጥሮስ፣ ቀጥሎ ሕይወቱን ይለቅቃል ። ጌታ ሳይጋብዘውና ሳያስፈቅድ በጴጥሮስ ታንኳ ላይ መሳፈሩ እንኳን ታንኳው ባሕሩም የእርሱ ስለነበረ ነው ። አንድ ቀን ሳያስፈቀደን በሞት ይወስደናል ። ሥልጣን የእርሱ ነውና ።
ጌታችን ትምህርቱን ከጨረሰ በኋላ ጴጥሮስን፡- “ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል መረቦቻችሁንም ለማጥመድ ጣሉ አለው ።” ዳር የወጣው ሰዓቱ አልፏል ብሎ ነው ። ዓሣ የሚገኘው በሌሊት ነው ። ከነጋ በኋላ የሰው ጥላና የፀሐዩ ሙቀት ያሸሻቸዋል ። ጌታ ፈቀቅ በል ሲለው ሰዓቱ አልፏል ፣ ነገር ግን ሰዓት የማያልፍበት አምላክ ነው ። ጴጥሮስ ተስፋ ቆርጦ ነበር ። ባቆመው ነገር ጅማሬ ሊሰጠው ክርስቶስ መጣ ። ሰው ሲጨርስ እግዚአብሔር ይጀምራል ።ትልቅ የሆነብን ጉዳይ ጌታችን ሲመጣ ትንሽ ይሆናል ። ጌታ ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በል ካለው ጴጥሮስ ዳር ወጥቶ ነበር ። ዳር መውጣት ሥራን ለመተው መሰናዳት ነው ። ካለቀው ነገር ላይ ጌታ ሊያስጀምረው ፣ ከዳሩ ወደ ጥልቁ መራው ።
ፈቀቅ በል የሚለው ቃል የሚገርም ነው ። ከራስህ ፈቀቅ በል ማለት ነው ። ከራስህ ማስተዋል ፣ ከስሌትና ከግምትህ ፈቀቅ በል ማለት ነው ። ከተስፋ መቊረጥህና ከልብ ዝለትህ ፈቀቅ በል ማለት ነው ። ወደ ጥልቁ ወደ መካከለኛው ባሕር ፣ ያለፈውን ሰዓት ገና እንደሆነ አድርገህ ሥራህን ጀምር ማለት ነው ። ሌሊቱን በሙሉ ያደከመውን ጥልቅ እርሱም በኃይለ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ እንዲያደክመው አዘዘው ። ዳር ላይ መረብ ከምናጥብበት ፣ ቀቢፀ ተስፋ ፣ ወደ እግዚአብሔር ጥልቅ ፈቀቅ እንድንል ዛሬም ጌታ ይናገረናል ። ራሳችንና ሁኔታዎችን ስናይ ይደክመናል ። የእግዚአብሔርን ጥልቅ ስንመረምር ግን ኃይሉ ያበረታናል ። ሕይወት ጥልቅ ናት ። በሚገኝበት ጊዜ ባዶ ልትሆን በማይገኝበት ጊዜ ሙሉ የምትሆን ናት ። የሕይወትን ጥልቅ ባሕር ያለ ክርስቶስ መቅዘፍ አይቻልም ። ሕይወት ያለ ጌታ አጥምደን አንይዛትም ።
ወደ ጥልቁ ፈቀቅ ለማለት እምነት ፣ ራስን ባዶ ማድረግ /አለመመራመር/ መታዘዝ ያስፈልጋል ። ክርስቶስ የሌለበት ልፋት ሁሉ የዜሮ ድምር ነው ። ጌታ የተናገረው ለሁኔታው የማይመች ነው ። ሰዓቱ አልፏል ፣ ልብም ደክሟል ፣ ሁሉም ነገር ባዶ ሁኗል ። እርሱ ካዘዘ ግን ሁሉም ነገር ቀላል ነው ። በእግዚአብሔር ምክር ውስጥ ኪሣራ የለም ። ሽምግልና በዘይት የሚዋበው በእግዚአብሔር ነው ። ሽምግልና መገርጣት ያለበት ፣ የተፈጥሮ ቅባት የሚባክንበት ነው ። እግዚአብሔር ግን ሽምግልናን በዘይት ያለመልማል ። ያ ባሕር ዓሣ አላጣም ፣ እነ ጴጥሮስ ግን ማግኘት አልቻሉም ። ጌታችን በዚያ ባሕርም ዓሣ አልጨመረም ። እያለ ማየት አልቻሉም ። ጌታ ግን ዓይኖቻቸውን አበራላቸው ። ዛሬም ያለው ችግር አቅርቦት ሳይሆን የዕይታ ነው ። አለ ግን አላገኘነውም ። የጌታ ትእዛዝ ግን ዓይንን ያበራል ።
ጴጥሮስ ለጌታ ታዝዞ መረቡን ሲጥል ሊጎትተው እስኪያቅተው ብዙ ዓሣ አገኘ ። ራሱ መሸከም አቅቶት ከጎረቤት ረዳቶች ጠራ ። እግዚአብሔር ሁሉን የማይሰጠን ስለማንችለው ነው ። ጴጥሮስ በዚህ ጊዜ ልቡ ተነካ ። እግዚአብሔር የሚወደው ሰው ቶሎ ልቡ የሚነካ ሰው ነው ። እንዲህ ያለውን ሰው ለአገልግሎት ይጠራዋል ። ደንዳኖች የእግዚአብሔርን ፍቅር ማየት አይችሉም ። እግዚአብሔርን ለማየት የልብን መስተዋት መወልወል ያስፈልጋል ።
ጌታችን ችግራችንን ያያል ። ተስፋ የቆረጥንበትን ፣ ትተነው ዳር ላይ የቆምንበትን ነገር ይመለከተዋል ። ክብሩን ለማየት ግን መታገሥ ያስፈልጋል ። ጌታችን ሲያዘን እንዴት ብለን የአቅምና የግምት ጥያቄ ማንሣት የለብንም ። መታዘዝና ከራሳችም ሁኔታ መላቀቅ ብቻ ይገባል ። ጥልቅ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር አሳብ ለመጠጋት ብዙ ጊዜ አንፈልግም ። ዳር ዳሩን መዞር እንወዳለን ። ጥልቅ ወደሆነው ክርስትናም መዝለቅ አንሻም ። ወደ ጥልቁ ሕይወት ካልገባን ልናተርፍ አንችልም ። በራሳችን ሞክረን ካልቻልን ጌታን መታዘዝ አለብን ። እንደ ቃሉ ማድረግ ያተርፈናል እንጂ አያከስረንም ። ውለታውና እየበደልነው እንኳ የሚያደርግልን ቸርነት ለንስሐ ሊጋብዘን ይገባል ። በእግዚአብሔር ፍቅር የማይነካ ሰው ጉደኛ ነው ። ክርስቶስን አስተካክለን አንወደውም ፣ አስበልጠን እንጂ ። ስለዚህ ሁሉን ትተን ልንከተለው ይገባናል ።
ዳር የወጣነው በምን ይሆን ? አገሩ ሊለወጥ የማይችል ነው ብለን ዳር ወጥተን ይሆን ? አገልግሎቱ የማይሰምር ነው ብለን ዳር ላይ ቆመን ይሆን? በብዙ ነገሮች ተስፋ ቆርጠን ፣ የራሳችንን ግምት እያዳመጥን ይሆን ? ጌታ ግን ገና ነው ፣ ወደ ጥልቁ ፈቀቅ በሉ ፣ የተዋችሁትን ሥራ ጀምሩ ይላል ። ያ ነገር የሚገኝበት ዕድሜውም ፣ ጉልበቱም ፣ ተፈላጊነቱም ፣ … አብቅቶ ይሆናል ። እግዚአብሔር የሚመቸው የእኛ ነገር ሲያልቅ ነው ። ፈቀቅ ማለት መልካም ነው ። እልፍ ሲሉ እልፍ ይገኛል ።
አምላኬ ረዳቴ ሆይ ፣ ከፍ ከፍ አደርግሃለሁ ። ተስፋ መቊረጥን ሳልጨርሰው እንደገና ትንፋሽህን ዝራብኝ ። ደስ በማያሰኙ ቀኖችም አንተን እንዳይህ እርዳኝ ። በገባዖን ሰማይ ፀሐይን ያቆምህ ለእኔም አድርግልኝ ። ውጊያዬን ሳይሆን ውጊያህን እንድዋጋ እርዳኝ ። አለማመኔን አግዘው ። ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና 23
ግንቦት 23 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ