የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ፍቅረ ንዋይ


“እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ … ገንዘብን የማይወድ” 1ጢሞ. 3፡2-3
ቢል ጌትስ የተባለ ባለጠጋ፡- “ገንዘብ ሲኖርህ ራስህን ትረሳለህ ፣ ገንዘብ ከሌለህ ዓለም ይረሳሃል ፤ ሕይወት እንደዚህ ነው” ብሏል ። ገንዘብ መቀመጫው ከአካላችን በላይ በኪስና በቦርሳችን ነው ። ገንዘብ ከእኛነታችን ውጭ እንጂ የእኛነታችን አካል መሆን አልነበረበትም ። ገንዘብ እውነተኛ መቀመጫው ግን የሰው ልብ ነው ። ገንዘብ በግዙፍ በኪሳችን ፣ በረቂቅ በልባችን ይቀመጣል ። ገንዘብ በልብ ሲቀመጥ መመዘኛ ሚዛናችን እርሱ ይሆናል ። አለን የምንለው ገንዘብ ሲኖረን ብቻ ነው ፤ ገንዘብ ከሌለን የማንኖር መስሎ ይሰማናል ። ገንዘብ ግን ዛሬ በእኛ እጅ የምናየው ነገ በሰዎች እጅ ላይ የምናየው ወረት ነው ። የጥንት ጠቢባን ገንዘብን የናቁ መናንያን ነበሩ ። ቤተ መንግሥት እንዲኖሩ ሲለመኑ የወንዝ ፈፋ ውስጥ ያደሩ ፣ ከነገሥታት ግብር/ማዕድ ይልቅ የድሆችን ቁራሽ የናፈቁ ነበሩ ። እውቀት ከገንዘብ ከሥልጣን በላይ ነው ብለው ያምኑ ነበር ። ዛሬ ግን የምንማረው ለገንዘብ ነው ፣ ገንዘብ ካገኘሁ እውቀት አያስፈልገኝም የሚል ትውልድ እያተረፍን ነው ። ባለሥልጣናት ሥልጣን ከሁሉ በላይ ነው ብለው የባለጠጎች ታዛዥ ላለ መሆን ይጥሩ ነበር ። ዛሬ ግን የሚበዙት ገንዘብ ካገኙ ክብራቸውንና አገራቸውን ለመሸጥ የማይሳሱ ሁነዋል ። ባለጠጎች በአዋቂዎች እየቀኑ ባለሥልጣናትን እያከበሩ ለዘመናት ኑረዋል ። ዛሬ ግን በገንዘባቸው አዋቂዎችንና ባለሥልጣናትን ገዝተዋል ። ከገንዘብ ክብር ፣ ከንብረትም መልካም ስም ይሻላል የሚለው ነገር ጊዜ ያለፈበት ይመስላል ።

ሰዎች ለመስረቅ ሲያስቡ ይህን ያህል ዓመት ብታሰር ነው ፣ ከዚያ ወጥቼ እበላዋለሁ እያሉ ነው ። ገንዘብ ለሰው ባይሞትም ሰው ግን ለገንዘብ እየሞተ ነው ። ለሚገድለን ገንዘብ ያለን ፍቅር ለሞተልን ክርስቶስ ካለን ፍቅር ይበልጣል ። የብዙ ሰዎች መልካም ጠባያቸው በገንዘብ ተሰርቋል ። ትሕትናቸው በትዕቢት ፣ ፍቅራቸው በጥርጣሬ ተለውጧል ። ገንዘብ ራስን ያሳጣል ፣ ማጣትም በሰው ፊት ያቆማል ። እግዚአብሔርን መፍራት ሁሉን ይለውጣል ። ራቁቱን የተወለደ የሰው ልጅ ከሀብት ይልቅ ድህነትን ቶሎ ይለምዳል የተባለው ለዚህ ነው ።
ገንዘብ ከኋላ ስናስከትለው መልካም እናደርግበታለን ፣ ከፊት ስናስቀድመው ግን ገደል እንገባበታለን ። “ገንዘብ ለሚያዝዘው ታማኝ ሎሌ ፣ ለሚታዘዝለት ግን ክፉ ጌታ/አሳዳሪ ነው” ይባላል ። ገንዘብ የሰውን ክብር ዝቅ እንድናደርግ ይገፋፋናል ። ገንዘብ ካለኝ ቆንጆ ማግባት እችላለሁ ፣ ሰዎችን ማሰገድ ቀላል ነው ብለን ካሰብን ገንዘብ የሰውን ክብር ዝቅ ስላደረገብን ነው ። በገንዘብ የገዛናቸው የበለጠ ከከፈላቸው ለሌላ ይገዛሉ ። በአዝማሪ ዓለም፡- “የከፈለ ያዛል” ይባላል ። የሚዘፍነው ለከፈለው ነው ። ገንዘብ ራስን የማስረሳት አቅሙ ከፍተኛ ነው ። ብዙ ሰው የሚሄድበት የጠፋው የመጣበት ስለጠፋው ነው ። በመንፈስ ጀምረን በሥጋ የምንጨርስበት አንዱ ምክንያት ገንዘብ ነው ። በየሥፍራው ወንጌል እሰብካለሁ እያለን የምንባላው ፣ በሰላም መልእክት ጦርነት የምንከፍተው የከፈትነው የገንዘብ ቋት እስኪሞላ ነው ። ያወገዝነውን የምናወድሰው ፣ ያሞገስነውን የምናኮስሰው በገንዘብ ነው ። ገንዘብ ሐሰተኛ ስብከትን ፣ በእግዚአብሔር ስም የመነገድ ድፍረትን የሚያመጣ ነው ። በየፍርድ ቤቱ የሐሰት ምስክሮች የፈሉት በገንዘብ ነው ። በየአደባባይ ሰውዬው ከሆነው በላይ የሚያወድሱ የመርሐ ግብር መሪዎች የገንዘብ ምርኮኞች ናቸው ። በድግምት በጥንቆላ ሰው እንፈውሳለን የሚሉ ግባቸው ገንዘብ ብቻ ነው ። እውነተኛ ፈዋሾች ካሉማ ሆስፒታሉን ባዶ አድርገው ቤት ያጣነው ለምን አንከራየውም ?
ገንዘብ ሲመጣ ሁለት ቤት መመሥረት ፣ ሁለት ትዳር ማቋቋም ይጀመራል ። ገንዘብ የቤተሰብን ክብር ይነካል ። ከችግር ቀን ጓዶቹ ጋር ሳይሆን ከዛሬ ወዳጆቹ ጋር እንዲዘል የሚያደርገው የገንዘብ ራስን የማስረሳት አቅም ነው ። መሬት ለመርገጥ የሚጠየፉ ፣ ድሀን እንደ በሽታ የሚሸሹ የድሀ ልጅ የነበሩ ናቸው ። በድህነት ኑረው ያገኙ በድሀ ይጨክናሉ ። እግዚአብሔር ግን ያንን ኑሮ ያሳያቸው ለሌሎች እንዲራሩ ነበር ። አዎ ድሀ ድሀ አይወድም ።
ኢጲስ ቆጶስ ገንዘብን የሚወድ መሆን የለበትም ። ገንዘብን የሚወድ ሲባል ገንዘብን የሚጠላ አለ ወይ ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም ። ያለ አግባብ የመጣንና የሚመጣን ገንዘብ ክርስቲያን መጠየፍ አለበት ። ድሆችን አፈናቅሎ ፣ የሙት ልጆችን አስለቅሶ ፣ ንጹሖችን ለሞት ገብሮ ፣ ሽፍቶችን ነጻ ለቅቆ ፣ ፍርድን አዛብቶ ፣ የእርዳታ እህል ሸጦ ፣ ለድሆች የመጣውን ወደ ራሱ ጎተራ ከትቶ ፣ ባልቴቶችን አሸብሮ ፣ ከምስኪኖች ጉቦ በልቶ የሚመጣውን ገንዘብ መጠየፍ ይገባል ። የክርስትና ዋጋው ይህ ካልሆነ ምን ሊሆን ነው ? ለንስሐ የሚያስከፍሉ ፣ ባለጠጋና ድሀ የሚለዩ ፣ ለሰጣቸው በደንብ የሚሰብኩ አገልጋዮች እንኳን ከአገልጋይነት ከአማኒነትም እየወጡ ነው ። አንድ ኤጲስ ቆጶስ እገሌ ምን ያህል ገንዘብ እንደ ሰጠም ማወቅ የለበትም ። ምክንያቱም እገሌ አሳቢ ፣ ያልሰጡ ድሆች የማያስቡ መስሎት ፍቅሩ ደረጃ እንዳይኖረው ነው ። አንድ ኤጲስ ቆጶስ አስቀድሞ በምርጫው የመነኮሰ ነውና ድህነትን በፈቃዱ መልመድና መቀበል አለበት ። የግል ጥሪት ሊኖረው አይገባም ። እንደ ሥርዓተ ሐዋርያት በኅብረት የሚመገብ መሆን አለበት ። አንድ ኤጲስ ቆጶስ ከበላይ ሁኖ የአስተዳደር ሙያ ያላቸውን ይቆጣጠራል እንጂ ቼክ ላይ የሚፈርም መሆን አይገባውም ። የኤጲስ ቆጶስ ተግባር ማስተማር ፣ መገሠጽ ፣ ቀሳውስትና ዲያቆናትን መሾም ፣ ሕዝብን መባረክ ነው ። አስተዳደሩ በባለሙያ ሊሠራ ይገባዋል ። ቤተ ክርስቲያንም ኤጲስ ቆጶሱ ከሌላው እንዳይከጅል አድርጋ በቂ ገንዘብ መክፈል አለባት ። ይህ ሲሆን እንግዶችን መቀበል ፣ የሚያማክሩትን ድሆች መርዳት ይችላል ። በቂ ደመወዝ ያለው ካህን የአገልግሎት ቀን ባሪያ ነው ፣ በሌላው ቀን ሰው ቤት የማይልከሰከስ ፣ ባለጠጎችን የማያጫውት ጌታ ነው ። አንድ የእግዚአብሔር አገልጋይ አምባሳደር ነውና ስለ መብሉና ስለ መኖሪያው ሊያስብ አይገባውም ። ስለ መብሉና መኖሪያው የሚያስብ የምድር አምባሳደር እንኳ የለምና ። ለዚህ ተጠያቂ የሚሆኑት ምእመናን ናቸው ። ደግሜ እላለሁ ምእመናን ስለ አገልጋዮች እግዚአብሔር ይጠይቃችኋል ። በበቂ ስለማትይዙአቸው ዛሬ የፖለቲካ መጠቀሚያ ፣ የዓለም ድምፅ ፣ የዲያብሎስ መሣሪያ ፣ የጦርነት ቀስቃሽ ሁነዋል ። የተራበ ጆሮ የለውም ።
ከሦስቱ አርእስተ ኃጣውዕ አንዱ ፍቅረ ንዋይ ነው ። ፍቅረ ንዋይ መኖሪያህ የዘላለም አምላክ ነው ሳይሆን መኖሪያህ ያጠራቀምከው ሀብት ነው የሚል መመሪያ ያለው ነው ። ብዙ ሰው በአፉ ባይናገርም እግዜርን ካንገት ፣ ገንዘብን ካንጀት ይወዳል ። የተቆለፉ በሮች ሁሉ በገንዘብ ይከፈታሉ ተብሎ ስለሚታሰብ ሰው ሌሊትና ቀን ሚሊየነር ወደ መሆን እየተጓዘ ነው ። የሚያስፈልገውን ሳይሆን የሚፈልገውን ብቻ እየተከተለ ነው ። ራበኝ ማለት ሕጋዊ ጥያቄ ሲሆን አልረካሁም ማለት ግን መልስ የለሽ ጥያቄ ነው ። አዳም መርካት ያቃተው የዓለሙ ንጉሥ እርሱ ብቻ ሁኖ ሳለ ነው ። በመላው ዓለም ያለው ሀብት ለስስቱ ጥጋብ ሊሆነው አልቻለም ። በገነት ካልረካ እሾህና አሜኬላ ይብቀልብሽ ተብላ በተረገመች ምድር ሊረካ በፍጹም አይችልም ። በገንዘብና በንብረት ባለ መርካታችን እግዚአብሔር ይመስገን ። እነርሱ ቢያረኩን ኑሮ ወደ ክርስቶስ አንመጣም ነበር ። ፍቅረ ንዋይ የሚፈልገው ቦታ የፍቅረ ቢጽን ነው ። ወንድምን የመውደድ ጫማ ውስጥ ካልጠለቀ ፍቅረ ንዋይ እርካታ የለውም ። በአንድ ጊዜ ሁለት ነገሮችን በእኩልነት መውደድ አይቻልምና ፍቅረ ንዋይ ሲመጣ ወንድምን መጥላት ይመጣል ።
ፍቅረ ንዋይ ስስትን ፣ በመጠን አለመኖርን ፣ አለመርካትን ያመጣል ። ፍቅረ ንዋይ ባዕድ አምልኮን ያመጣል ። ገንዘብ ለማግኘት ልጆቻቸውን ለአጋንንት የገበሩ ብዙ አሉ ። ፍቅረ ንዋይ ከልጅ ፍቅር በላይም ሊሆን ይችላል ። ፍቅረ ንዋይ ቀናተኛ ስለሆነ ሌላ እንወድድ ዘንድ ነጻነት አይሰጠንም ። አዳም በገነት ብዙ የሚበላ እያለ በመብል ወደቀ ። ጌታችን ምንም አማራጭ በሌለበት በገዳመ ቆሮንቶስ ስስትን አሸነፈ ። የመነኮሳት ፈተናቸው ስስት ነውና በገዳም በመኖሪያቸው ስስትን አሸነፈላቸው ። የሚጦረኝ ልጅ ፣ የሚደግፈኝ ዘመድ የለም ብለው መነኮሳት ይሰስታሉና ጌታችን እኔ አለሁላችሁ ብሎ ስስትን ድል ነሣላቸው ። ኤጲስ ቆጶስ ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ ያመነ ሁሉ ፍቅረ ንዋይን ድል መንሣት አለበት ። ወደ ቤተ ክርስቲያን የመጣነው አገልጋይ ሁነን ሳይሆን ምእመን ሁነን ነው ። ወደ መንግሥተ ሰማያትም የምንገባው በአማኝነት ነውና ፍቅረ ንዋይ ከሁላችንም መራቅ ይገባዋል ። አሥራት በኩራት ለማውጣት የምንቸገረው ፣ ከእግዚአብሔር ለመስረቅ የምንደፍረው በፍቅረ ንዋይ ነው ። ፍቅረ ንዋይ ለድሆች እንዳንሰጥ ብቻ ሳይሆን ለራሳችንም እንድንሰስት ያደርገናል ።
ሄቲ ግሪን የተባለች አሜሪካዊት በ1916 ስትሞት ከመቶ ሚሊየን ዶላር በላይ ሀብት ጥላ አልፋለች ። ይህች ሴት ግን ምግቧን የምትበላው ቀዝቃዛውን ነበር ፣ ምክንያቱም ካሞቀች ገንዘብ አወጣለሁ ብላ ትሰጋ ስለ ነበረ ነው ። ልጇ በእግር በሽታ ተይዞ ፈውስ ወደሌለው ጉዳት የደረሰው የነጻ ሕክምና ስታፈላልግ ነበር ። ፍቅረ ንዋይ ለራስና ለሚወዱት ልጅ ሳይቀር ጨካኝ ያደርጋል ። ራቁታችንን እንደ መጣንና ራቁታችንን እንደምንሄድ ሲገባን ፍቅረ ንዋይን እየጣልን እንመጣለን ። ከሁሉ በላይ የማያልፍ መንግሥትን አዘጋጅቶ የሚጠብቀንን መድኃኔ ዓለምን ስናምን ከፍቅረ ንዋይ እንድናለን ።
“እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ … ገንዘብን የማይወድ” 1ጢሞ. 3፡2-3
1ጢሞቴዎስ 44
ጥር 28 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ውድ አንባብያን የአንደኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ መልእክት ቀጣዩን ወደፊት በሚወጣ መጽሐፍ ጠብቁ ። ለጊዜው ፈጸምን ።
የረዳኸን አምላክ አንተ ቡሩክ ነህ ፣ ምንጭህም ቡሩክ ነው ።
ክብር ለሥላሴ !!!
የሚወዱህ ያመስግኑህ ።

ያጋሩ