የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ፍቅርን የጣሉ፣ ፍቅርን የተራቆቱ የፍቅር ቀን አክባሪዎች፡-

ዓርብ፣ የካቲት 9/2004 ዓ.ም.
አዲስ አበባችን በቫለንታይን መታሰቢያ የፍቅረኞች ቀን ቀይ በቀይ ሆና ነበር የዋለችው፣ እንደታዘብነው በከተማችን የነበረው የተለየ ትዕይንት እለቱን የከተማችን ኮረዶችና ጉብሎች በብዙ ናፍቆት እንዲጠበቅ ያደረገው ይመስላል፡፡ ለዚሁም ይመስላል የመዝናኛ ስፍራዎችና ካፌዎች በቀይ አልባሳትና በቀይ አበቦች ገና ከዋዜማው ጀምረው መድመቅ የጀመሩት፡፡ የስጦታ ካርድና የአበባ መሸጫ መደብሮችም ሞቅ ያለ ገበያ ላይ ነበር የዋሉት፡፡ የኤፍ ኤም ሬዲዮኖቻችንም እለቱን ለማዘከር ቀኑን ሙሉ ለስለስ ያሉ የፍቅር ዜማዎችንና ጭውውቶችን ሲያስተላልፉና በአድማጮች የስልክ መልእክት ተጨናንቀው የዋሉበት እለት እንደነበረ ነው ያስተዋልነው፡፡ በዋዜማው፣ በእለቱም ሆነ በዛች ምሽት የሆነው ነገርና የታዘብነው ሁሉ አስገርሞናል፤ ወጣቱ ትውልድስ ወደየት ነው እየሄደ ያለው ብለን ራሳችንን እንድንጠይቅም አስገድዶናል፡፡
ትውልዳችን በተውሶ ባህል እንዲህ ጭልጥ ብሎ በጠፋበትና የምዕራባውያኑ የመንፈስ ቅኝ ግዛት ስር ወዶና ፈቅዶ ከተጋዘበት፣ ከማንነቱን፣ ከታሪኩና ከባህሉ በተነጣጠለበት በዚህ ዘመን ቤተክርስቲያንና አገልጋዮቿ ትውልዱን የቀናውን መንገድ ለማሳየትና ከገባበት የማንነት ቀውስ ለመታደግ መጫወት ያለብንን ታላቅ መንፈሳዊ ሚና የዘነጋን ይመስላል፡፡ ከመንፈሳዊነትና ከክርስቲያናዊ አኗኗር ጨዋነት የራቅንበትና በስልጣኔ ስም የተጫነብን የምዕራቡ ዓለም የኑሮ ዘይቤያችን በሂደት ያመጣብንና ወደፊትም ሊያመጣብን የሚችለውን የሞራል ውድቀትና ክስረት ከወዲሁ ቢታሰበን የቫለንታይን ቀን ትዝብታችንን ከእውነተኛ ፍቅር አንፃርና ከቅዱስ ወንጌል እውነት በመነሳት ጥቂት ነገሮችን ለማለት ወደድን፡፡  

በእውነት እንነጋገር ከተባለ የቫለንታይን ቀን ለእኛ ሀገር ወጣት ዝምድናው ምኑ ላይ ነው፣ የእኛ ባልሆነና በተውሶ ባመጣነው ባዕድ የባህል ድሪቶ ይህን ያህል ግርግርና ውካታስ አስፈላጊ ነበር…፡፡  እሺ ፍቅርን ማሰብ፣ ፍቅርን መዘከር ጉዳቱ ምኑ ላይ ነው ብለን የመከራከሪያ ሐሳብ ብናነሳ እንኳን በቫለንታይን ቀን ፍቅርን ለመዘከር ፍቅረኞች በዚህ አኳኃን ነበር ቀኑን ማክበር፣ ቀኑን መዘከር የነበረባቸው?!  በዝሙት ጠንቅ የነገይቱ የሀገራችን ተሰፋ የሆነው ወጣቱ ትውልድ በኤች አይ ቪ ኤድስ እንደ ቅጠል እየረገፈበት ባለበትና በዚህም የተነሳ ከገጠመን ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ለማገገም ጉልበቴ በርታ በርታ በምንልበት ጊዜ ላይ እንደገና ትውልዱን ሌላ ጥፋት የሚዳርግ የዝሙት ርኩሰት ባህር ውስጥ የሚደፍቅ እንዲህ ዓይነቱ የጥፋት ድግስ በእርግጥ ለእኛ የሚገባንና የሚገባን ነገር ነው…፡፡
ፍቅረኞችስ ፍቅራቸውን መግለጽ ቢገባቸው በዚህ ዓይነት መንገድ መሆን ነበረበት እንዴ!? ፍቅራችንን በሀገሪኛ ወግና ሥርዓት ለመግለጽ የሚያስችሉን ብዙ ልንኮራባቸው የሚገቡን መልካምና አስደሳች የሆኑ ባህሎች አሉን፡፡ የግድ የውጩን ባህል መዋስ አይገባንም፡፡ ፍቅርን መዘከር ከወደድንም በጨዋነት እንጂ በዳንኪራ፣ በስካርና ልቅ በሆነ የስሜት ትኩሳት መሆን የለበትም፡፡ በእለቱ በቫለንታይን /በፍቅረኞች ቀን ስም የታዘብነው ነገር ምን ያህል ትውልዳችን በስልጣኔ ስም ከጽድቅና ሰላም ሕይወት እንደራቀ ትልቅ ማሳያ ነው፡፡
ትውልዱን እየነጎደበት ካለው የጥፋት ጉዞው ይገታ ዘንድ ማስተማር ያለባት ቤተክርስቲያንና እኛም አገልጋዮች መንፈሳዊ ግዴታችንን የዘነጋን ነው የሚመስለው፣ በዘመናችን እየታዘብነው ያለውም እውነት የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርንና ሰላምን ይታወጅበት ዘንድ የሚገባው አውደ ምሕረት የክርክር፣ የተረትና የፌዘኞች መድረክ የሆነበት፣ ሰላምን፣ ምሕረትንና ፍቅርን የሚያድለውን የእውነትን ወንጌል የያዙ የጽድቅ አገልጋዮች ከቤተክርስቲያን መድረክ የተገፉበት፣  በጥፋት መንታ መንገድ ላይ ግራ በመጋባት ቆሞ ላለው ትውልዳችን የመጽናናትን የሕይወት ቃል ለማቅረብ የደከምንበት ወቅት ላይ ነን፡፡ ለስንፍናችንና ለቸልተኝነታችን ንስሐ በመግባት የትውልዱ ተስፋ የሆነውን የወንጌል ቃል እውነት በማወጅ ትውልዳችንን ለመታደግ ጊዜው ዛሬና አሁን ነው፡፡
ፍቅር፣ ተስፋና ሰላም የራቀው ወገናችን ፍቅርን በቃላት ጋጋታ፣ በቀናት ስያሜ፣ በዳንኪራ፣ በስካርና በርኩሰት እውን ለማድረግ እየተጓዘበት ያለው መንገድ ወደሌላ ጥፋት ወደሌላ ሞት የሚጋብዝ መሆኑን ቆም ብሎ ማሰብ ይችል ዘንድ በፍቅርና በትህትና ቀርበን ልንነግረው ያስፈልጋል፡፡ ፍቅር በእውነት እንጂ በአመፃና በርኩሰት ግብዣ ደስ አይለውም፣ ፍቅር ለኃጢአተኞች የሚራራ፣ የተገፉትን የሚታደግ፣ የበደልን ብዛት የሚሸፍን፣ ለንጹሆች የሚሆን ለዘላለም የሚፈልቅ የሕይወት ምንጭ፣ የህልውናችንም መሰረት ነው፡፡ ፍቅር በዘላለም ቃል ኪዳን በደም የታተመ ወደ ዘላለም ሕይወት የምንደርስበት የእውነት ሠረገላ ነው፡፡
በፍቅር ቀን ሊታሰብ፣ ሊመሰገንና ሊዘከር የሚገባውም ፍቅር የሆነው እግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ እርሱ አምላካችን በውስጣችን ከገለጸው ፍቅርም የተነሳ ከሌሎች ጋር ፍቅርን በነፃነት የምንከፋፈል፣ ሌሎችን ያለምንም ገደብ የምንወድ፣ ለሚወዱን ብቻ ሳይሆን ለሚጠሉን እንኳን ፍቅርን ያለመሰሰት የምንሰጥ የፍቅር መዝገብ መሆን የቻልነው የፍቅር አምላክ ከሆነው ከእግዚአብሔር የተነሳ መሆኑ ሲገባን ቀናቶቻችን፣ እድሜያችንና ዘመናችን ሁሉ የፍቅር መታሰቢያ ህያው መገለጫ ይሆናሉ፡፡
ፍቅር የሕይወት መገኛ ምንጭ ብቻ ሳይሆን የሕይወት መድረሻ ግብም ጭምር ነው፣ ፍጥረትን ሁሉ በሕይወት ጠብቆ የሚያንቀሳቅሰው ሕያው ኃይልም ፍቅርና ፍቅር ብቻ ነው፡፡ በዚህ ፍቅር ጥላ ስር የተጠለሉ ሁሉ ከጥማታቸው ረክተው፣ ከድካማቸው አርፈው፣ የሕይወት እንቆቅልሽ ተፈትቶላቸው፣ ከሞት ፍርኃት ከሲዖል ባርነት ነፃ ወጥተው፣ በሰላምና በጸጥታ በዘላለም የሰንበት እረፍት ውስጥ አርፈው አሉ፡፡
የፍቅር ቀን አክባሪዎች ሆይ!፡- ፍቅር በፍቅር እንጂ በከበረ እንቁና በስጦታ ጋጋታ ልናገኘው አንችልምና ከገባንበት የህልም ዓለም እንንቃ፣ ፍቅርን በዳንኪራ፣ ፍቅርን በእንቡጥ ጽጌረዳ ስጦታ ልውውጥ ልናመጣውም ሆነ ልናጸናው አይቻለንም፡፡ ስጦታችን የሚሰምረው የፍቅርም ጽጌረዳ በእኛም ሆነ በሌሎች ልብ ውስጥ መፍካት የሚቻለው ፍቅር የሆነ እግዚአብሔር ሁለተናችንን ሲገዛው ነውና ወደ ሕይወት ራስ ወደ ጌታ ኢየሱስ እንመለስ፡፡
በፍቅር ስም ትውልዳችን ከገባበት የሽንገላ ሕይወት ይወጣ ዘንድ እንደ ክርስቲያንና እንደ ቤተክርስቲያን አገልጋዮች ከፍቅር አምላክ የተቀበልነውን የፍቅርና የእውነትን የወንጌል መልእክት በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ፍቅርና ርኅራኄ ልንነግራችሁ እንወዳለን፡፡ ወገኖቻችን ፍቅር ግን ሕያው እግዚአብሔር ነው፣ በአንድ ልጁ በጌታችንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የኃጢአታችንን ስርየት ወዳገኘንበት ወደ ፍቅሩ ልጅ መንግስት ያፈለሰን!
ክብር፣ ምስጋና ለቅዱስ ስሙ ይሁን! አሜን! 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ