የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ፍቅር መሄድ ነው

ያለፉት ወራት እግዚአብሔር የምሕረት ፊቱን እየመለሰልን ነው የሚያሰኝ ነገር በዓለም ላይ ሲከናወን እያየን ነው ፡፡ በሰሜን ኮሪያና በደቡብ ኮሪያ መካከል የነበረውን ድንበር ጥሰው መሪዎች ሲገናኙ ፤ ለኒውክለር ጦርነት እየተዘጋጁ የሚመስሉት የአሜሪካና የሰሜን ኮሪያ መሪዎች ተገናኝተው ሲፈራረሙ ፣ በደቡብ ሱዳን የነበረውና ያለው ችግር እንዲቋጭ ሱዳን አደራዳሪ ሁና የተኩስ አቁም ስምምነት ሲያደርጉ ፣ ላለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የነበረው ውጥረት ረግቦ ፣ በአየሩ ላይ አውሮፕላን ሲያልፍበት ፣ መሪዎች በፍቅር ሲገናኙ እያየን ነው ፡፡ በውን ይሁን በሕልም መገመት የሚያዳግት ነገር እያየን ነው ፡፡ ከእግዚአብሔር እንጂ ከሰው ነው ብሎ ማሰብ አይቻልም ፡፡ ደቡብ ሱዳን ነጻ አገር ለመሆን ለዐሥርተ ዓመታት ታግላለች ፡፡ ነገር ግን ነጻ መንግሥት ከሆነች በኋላ ሁለት ዓመት ብቻ በሰላም ቆይታለች ፡፡ እንደገና በሁለት መሪዎች ለሁለት ተከፍላ መዋጋት ጀመረች ፡፡ መከፋፈል መቆሚያ ከሌለው እየቀጠለ ይሄዳል ፡፡ በዚህም ጦስ የደቡብ ሱዳን ዜጎች በዐሥር ሺህዎች ሲሞቱ አራት ሚሊየን ሕዝብ ተፈናቅሏል ፡፡ የአፍሪካ ሶሪያም ሁናለች ፡፡ ኢትዮጵያና ኤርትራም ዕድላቸው ተመሳሳይ ነው ፡፡ ኤርትራን ነጻ አገር ለማድረግ ሠላሳ ዓመት የፈጀ ጦርነት ተካሂዷል ፡፡ ብዙ ትውልድም አልቋል ፡፡ ኤርትራ ነጻ መንግሥት ከሆነች በኋላ በሰላም የቆየችው ለአምስት ዓመታት ብቻ ነው፡፡ በ1990 ዓ.ም ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት ተጀመረ ፡፡ በዚህም “የክፍለ ዘመኑ ኋላ ቀር ጦርነት” ተብሎ የተሰየመው እልቂት ተፈጸመ ፡፡
መለያየት ጥፋት እንጂ ልማት እንደሌለው ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል ፡፡ የእስራኤል መንግሥት ለሁለት የተከፈለው በሰሎሞን ልጅ በሮብዓም ዘመን ነው ፡፡ የእስራኤልና የይሁዳ መንግሥት ተብለው ለሁለት ተከፈሉ ፣ የሁለት መንግሥታት ባለቤትም ሆኑ ፡፡ ነገር ግን የሰሜኑ ግዛት በአሦራውያን በ722 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ተደመሰሰ ፡፡ የደቡቡ የይሁዳ መንግሥትም በ586 ዓመት ቅድመ ልደተ ክርስቶስ ተደመሰሰ ፡፡ እስከ ክርስቶስ መምጣት ብቻ እንዳይመስላችሁ እስከ 1948 ዓ.ም የእስራኤል መንግሥት ፈርሶ ኖረ ፡፡  በመለያየት የተባረከ አገርና ሕዝብ የለም ፡፡ ከሁሉ በላይ የልብ ስብራት የሚያመጣ ነው ፡፡ አንካሳ ትውልድን የሚያተርፍም ነው ፡፡ ስንለያይ ሁሉ ይንቀናል ፡፡
የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝብ በምንም ልንለየው የማንችለው ሕዝብ ነው ፡፡ የኤርትራ ሕዝብ ቋንቋህ ምንድነው ስንለው ትግርኛ ይለናል ፡፡ በመልክ ፣ በቋንቋ ፣ በሃይማኖት ፣ በባሕል ፣ በአመጋገብ ፣ በጀግንነት አንድ ዓይነት ሕዝብ ነው ፡፡ አንድ ሕዝብ መሆኑን ለማወቅም መከራው አንድ ዓይነት መሆኑን ማየት ነው ፡፡ ስደት ሲመጣ በባሕርና በበረሃ የሚሞቱት እነዚህ ወንድማማቾች ናቸው ፡፡ በአንዲት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንም አንድ ናቸው ፡፡ በኤርትራ ያለውና በኢትዮጵያ ያለው ሙስሊም ባሕሉና ጨዋነቱ አንድ ዓይነት ነው ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ተከፍላ የአገር ውስጥና የውጭ ሲኖዶስ ሲባል በኤርትራም እንዲሁ ነው የሆነው ፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆርዮስ በስደት ከእስር ያላነሰ ኑሮ ይገፋሉ ፡፡ የኤርትራ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ እንጦንስ በቁም እስር ላይ ይገኛሉ ፡፡ የውጩን ሲኖዶስ የኢትዮጵያው የሚሰጠውን ስም በኤርትራም እንዲሁ ይሰጠዋል ፡፡ በመወጋገዝም አንድ ነን፡፡ መልካችን ብቻ ሳይሆን መከራችንም አንድ ዓይነት ነው ፡፡ በሊብያ የታረዱት ሰማዕታትን እስቲ እናስባቸው ፡፡ ኢትዮጵያውያንና ኤርትራውያን ናቸው ፡፡ የአይሲስ ዒላማዎች ሁለቱም ሕዝቦች ናቸው ፡፡ ምክንያቱም ጠላት የሚያውቃቸው በአንድነት ነውና ፡፡ ወደ ሞያሌ አካባቢ የአትዮ ኤርትራ ጦርነት እንደ ተጀመረ ኤርትራውያን ይውጡ ሲባል የትግራይ ሰዎችንም አስተዳዳሪው መለየት ስላቃተው አብሮ አስወጣቸው ፡፡ “እንዴት እኛ እንወጣለን” ቢሉት “እኔ አላውቅም አዲስ አበባ ሂዱና መለስ ይለያችሁ” አለ ይባላል ፡፡ አንድ ሕዝብ ነው ፡፡ እኔም እናንተም መለየት እስኪያቅተን አንድ ነን ፡፡ በተፈጥሮና በታላላቅ ጉዳዮች አንድ የሆንነውን የለየን መታወቂያ ብቻ ነው ፡፡ ከእግዚአብሔር ማኅተም የሰው ወረቀት በልጦ ይኸው ተለያይተናል፡፡
በትላንትነው ዕለት በኤርትራ የነበረውን አቀባበል ፣ ለጠቅላይ ሚስትር ክቡር ዐቢይ የተሰማው የዘፈን ድምፅ ፣ ከእንባ ጋር የተቀላቀለው የፍቅር ዜማ ላየው ለሰማው ያስደስታል ፣ ደግሞም የማይለያይ ሕዝብ ተለያይቶ እንደ ኖረ ያሳብቃል ፡፡ ዘፈኑ ፣ ጋሻው ፣ ጦሩ ፣ የእናቶች አለባበስ ፣ እናታዊ ጨዋነት ይኸው ኢትዮጵያ ያለው ነው በኤርትራ ያለው ፡፡ ታዲያ ለምን ተለያዩ ያሰኛል ፡፡ እንዲህ እንደ ተነፋፈቅን አናውቅም ነበር ፡፡ ፖለቲከኞችን ላለማስቀየም የታፈነው ፍቅራችን የወጣ ይመስላል ፡፡ ፖለቲከኞችም የፍቅር ሠራዊት ሁኑ ፡፡ የሚናገሩት የጳጳስ እንጂ የንጉሥ ንግግር አይመስልም ፡፡ ለዚህ ፍቅር  መለምለም ፣ ለሁለቱ አገሮች አንድነት ዘወትር መጸለይ ይገባናል ፡፡ እግዚአብሔር የኢትዮጵያንና የኤርትራን ሕዝብ ይባርክ ፡፡ እናቶች ሲመርቁ የዋለውን ሳቅ ያስመሽልን ይላሉ ፡፡ እግዚአብሔር የሰላም አዋጅ ነጋሪ ያደረገውን መሪያችንን ይባርክልን ፡፡ ይጠብቅልን ፡፡
ተጻፈ አዲስ አበባ
ሐምሌ 2/2010 ዓ.ም.
ዲአመ   
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ