September 29, 2021 by ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ሁላችንም
“ሁላችን የእግዚአብሔርን ልጅ በማመንና በማወቅ ወደሚገኝ አንድነት ፥ ሙሉ ሰውም ወደ መሆን ፥ የክርስቶስም ሙላቱ ወደሚሆን ወደ ሙላቱ ልክ እስክንደርስ ድረስ ፥ ቅዱሳን አገልግሎትን ለመሥራትና ለክርስቶስ አካል ሕንጻ ፍጹማን ይሆኑ ዘንድ ።” ኤፌ. 4 ፡ 12-13 ።
ጳጳሱ እንዲህ እያደረጉ ካልን ጳጳስ መሆን ያለበትን እናውቃለንና እውቀታችን ከጳጳሱ በላይ ነው ። ጳጳሱ እንዲህ እያደረጉ የምንለው ራሳችንን ነጻ ለማውጣት ነው ። ጳጳስ ምን ማድረግ እንዳለበት እናውቃለንና የምንጠየቀው ከጳጳሱ በላይ ነው ። ቅድስናን ከፋፍለን ይህን መነኩሴ ፣ ይህን ምእመን ሊያደርገው ይገባል እንላለን ። ቅድስና ግን ለምእመናን ሁሉ የተሰጠ እንጂ ለጥቂቶች የተጣለ ግዴታ አይደለም ። እግዚአብሔር ቅድስናን ሲሰጠን ተጨንቀን እንድንፈጽመው ሳይሆን ለምድራዊ ደስታችንም አስቦ ነው ። ሐሰተኛ ደስታ በምድር ላይ አለ ፣ እውነተኛውን ደስታ የምናገኘው ግን በቅድስና ነው ። በድሎ ያረፈ ፣ ተቀድሶ የተጨነቀ የለም ። ወንጌላውያን ሰባኪ ሊሆኑ ይችላሉ ፣ ምእመናን ሁሉ ግን እንደ መግደላዊት ማርያም የትንሣኤው ምስክር ናቸው ። ክርስቶስ ተነሣ ብቻ ሳይሆን በክርስቶስ ተነሣሁ ብለው መመስከር የምእመናን ግዳጅ ነው ። ወደ መንሥተ ሰማያት የምንገባው በአማኝነት እንጂ በካህንነት አይደለምና ለምእመንነት ዋጋ መስጠት ይገባናል ። የክህነትም መነሻው አማኝነት ነው ። የመንግሥት ባለሥልጣናት አገር እየዘረፉ እንላለን ፣ እኛ ግን የአገራችንን ሀብትና ጊዜ ጭምር መስረቃችንን እንደ ቀላል እናየዋለን ። በየመሥሪያ ቤቱ ሰውን የሚያስለቅሱ ሠራተኞች አብዛኛዎቹ ሃይማኖት አለን ብለው የሚናገሩ ናቸው ። ሃይማኖት የሌላቸው ሕዝቦች ስለሚከፈላቸው በትጋት እየሠሩ እኛ ግን በሃይማኖትም በደመወዝም ሁነን ሰው እናሰቃያለን ።
እርስዋ ቤቱን ጥላ እየዞረች ነው የሚለው ምሽት ስድስት ሰዓት የሚገባው ባል ነው ። ካህኑ ይህን ግፍ እያዩ ለምን አያወግዙም እንላለን ፣ ግፍን ለማውገዝ ሁሉም ካህን መሆኑን አናስተውልም ። የመጣውን ዕዳና የሚመጣውን መከራ ለጥቂት ሰዎች ማሸከም እንፈልጋለን ። ለምትናወጥ መርከብ ጥፋቱ የካፒቴኑ ነው የሠራተኞቹ ብንል ማዕበሉ ጸጥ አይልም ። ሰበብና እገሌ ነው እያሉ መጠቆም የመጨረሻው ዘመን ምልክት ነው ። ማቴ. 24፡10 ።
ሐዋርያው ግን “ሁላችን” በማለት ይናገራል ። ሁላችን የሚጠበቅብን ነገር አለ ። ማመን ፣ ማወቅ ፣ አንድነት ፣ ሙሉ ሰውነት ፣ እስከታቀደልን ድረስ ማደግ ፣ የተቀደሰ አገልግሎት ፣ የጠፉትን የክርስቶስ አካል ማድረግ ከሁላችን ይጠበቃል ። ትንሽ ለመዘርዘር እንሞክር ። ሁላችን ማመን ይገባናል ። እግዚአብሔር ፀሐይን ለሁሉ እንደ ሰጠ ፣ የሰው ልጆችም ሁሉ የፀሐይን ጌታ ማመን ይገባቸዋል ። ስጦታውን ወዶ ሰጪውን ጠልቶ የትም መድረስ አይቻልም ። እውቀትና ፍልስፍና የማይመልሳቸው የሕይወት ጉዳዮች አሉ ። ማን ፈጠረኝ ? ለምን እኖራለሁ ? ወዴት እሄዳለሁ ? የሚሉት የሕይወት ጥያቄዎች በእምነት ብቻ መልስ ያገኛሉ ። እምነት ከእኔ የበረታ ኃይል አለ ብሎ “ደካማው ብርቱ ነኝ” በማለት የሚፎክርበት ምሥጢር ነው ። ኢዩ. 3 ፡ 10 ፤ ሚክ. 7 ፡ 8 ። እምነት ከተፈጥሮ በላይ የሆኑ ተአምራቶች የሚደረጉበት ብርሃናዊ ዘንግ ነው ። እምነት የማይቻለው የሚቻልበት ነው ። እያንዳንዱ ኑሮአችን ከእምነት ጋር የተያያዘ ነው ። ባናምን ኖሮ አንተኛም ነበር ። ባናምን ኖሮ ከቤት አንወጣም ነበር ። ባናምን ኖሮ የቅድሙን ምግብ አንበላውም ነበር ። እምነት ለምድርም ለሰማይም አስፈላጊ ነው ። ማመን የሚገባን ሁላችንም ነን ።
ማወቅ ሁላችንም ይገባናል ። እያወቅን እናምናለን ፣ እያመንን እናውቃለን ። እግዚአብሔርን ጠንቅቆ ያወቀው ሰውም መልአክም የለም ። ማወቅ ያሳስተናል የሚሉ ሰዎች አሉ ። መጽሐፉ ደግሞ “ሕዝቤ እውቀት ከማጣቱ የተነሣ ጠፍቷል” ይላል ። ሆሴ. 4፡6 ። እያንዳንዱ ክርስቲያን የነገረ መለኮት ተማሪ ነው ። ቅዳሴው ፣ ስብከቱ ሁሉ ነገረ መለኮት ነው ። ሁላችን አንድነት ያስፈልገናል ። የአንድነት ነገር “ቁጭ ብለው የሰቀሉትን ቁመው ማውረድ ይቸግራል” ዓይነት ሁኖብናል ። ግንብን መገንባት መለያየትን መፍጠር እውቀት አይጠይቅም ፣ ድልድይ መዘርጋት አንድነትን መፍጠር ግን ብስለት ይጠይቃል ። አንድ ፀሐይ እየሞቅን መለያየታችን ይገርማል ። ከእንስሳት ጋር እንኳ በሥጋ ዘመድ ነን ። ከመላእክት ጋርም በነፍስ ዘመድ ነን ። እኛን ከሚመስል ሰው ጋር ደግሞ የበለጠ ዘመድ ነን ።
ሙሉ ሰውነት ይጠበቅብናል ። ሙሉ ሰው ራሱንና ያዳነውን በትክክል የሚያውቅ ነው ። ላመነበት ነገር መልስ መስጠት የሚችል ነው ። አዩኝ አላዩኝ እያለ የሚኖር ሳይሆን ለቃል ኪዳኑ ታማኝ የሆነ ነው ። ይህን ካወቅሁ ይህን ካደረግሁ በቃኝ ማለት ሳይሆን እስከታቀደልን ድረስ ማደግ ከሁላችን ይጠበቃል ። የዓለም ታሪክ የጥቂት ሰዎች ታሪክ ነው የሚባለው ጥቂቶች ሠርተው ወይም ጎልተው ስለሚወጡ ነው ። ለሥራ እንጂ ለተመልካችነት የተፈጠረ የለም ።
ሁላችንም የተቀደሰ አገልግሎት ይጠበቅብናል ። ብራብ አብልታችሁኛል የሚለው የተቀደሰ አገልግሎት ነው ። ታመው በቤት የቀሩ ፣ ረሀብ በሽታ ሆኖ የሚያሰቃያቸው ፣ ልብስ በማጣት አፍረው ከቤት የማይወጡ ፣ በግፍ ታስረው በወኅኒ ያሉ ብዙ ወገኖች አሉ ። ይህን የተቀደሰ ተግባር ለእርዳታ ተቋማት መስጠት ተገቢ አይደለም ። በጎ ነገር ለሰው ልጅ እንጂ ለድርጅት አልተሰጠም ። ከአካሉ ርቀው የሚኖሩትን በሚመለከት እገሌ ሰባኪ ባገኛቸው ማለት ሳይሆን ሁላችንም ወደ መንፈሳዊው ኅብረት ልናቀርባቸው ይገባል ። ሁላችንም የሚለውን እናስተውል ። እገሌ ይሥራው ፣ እገሌ ነው ጥፋተኛው ማለት የትም አያደርሰንም ። ሁላችን ብንነሣ በዓለም ላይ ያለው ጉድለት ሞልቶ ያድር ነበር ።
ጌታ ሆይ አግዘን ። ሥራችንን ሌሎች ሲሠሩልን የሚያፍር ልብ ስጠን ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መስከረም 19 ቀን 2014 ዓ.ም.