የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሆሳዕና – ክፍል 2

                                       የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ….. ሰኞ፣ መጋቢት ፳፰/ ፳፻፯ ዓ/ም
ጌታችን በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ ብዙ ምሥጢራትን የያዘ ነው፡፡ በእርሱ ዘንድ በአጋጣሚ ወይም በድንገት የሚሠራ አንዳች ተግባር የለም፡፡ የዘመናት ዕቅዱ የሚፈጸምበት ክንውን ያደርጋል፡፡ ጌታችን በአህያ ውርንጫ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ፡-
1.     ትንቢትን ለመፈጸም
2.    የተናቁትን ለማክበር
3.    ሰላምን ለማብሰር ነው፡፡
ትንቢትን ለመፈጸም
ብሉይ ኪዳን የተስፋ ዘመን ነው፡፡ በትንቢትም ክርስቶስን የሚሰብክ ነው፡፡ የተስፋና የትንቢት እውነተኛነቱ የሚረጋገጠው በፍጻሜው ነው፡፡ ለብሉይ ኪዳንም እውነተኛነት የሰጠው የሕግ ፍጻሜ የሆነው ክርስቶስ ነው(ሮሜ. 10፤4)፡፡ ክርስቶስ ባይመጣ ኖሮ ብሉይ ኪዳን ሐሰተኛ በተባለ ነበር፡፡ የጌታችን እያንዳንዱ እንቅስቃሴው በትንቢት ተነግሮ ነበር፡፡ ነቢዩ ዘካርያስ፡- “ለጽዮን ልጅ፡- እነሆ ንጉሥሽ የዋህ  ሆኖ በአህያ ላይና በአህያይቱ ግልገል በውርንጫይቱ ላይ ተቀምጦ ወደ አንቺ ይመጣል በሉአት” በማለት ትንቢት ተናግሮ ነበር (ዘካ. 9÷9፤ ማቴ.21÷3)፡፡ ጌታችን ይህን ትንቢት ሊፈጽም በአህያና በውርንጫይቱ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ በዚያን ቀን እንዳትገፋው ነቢዩ የጽዮንን ልጅ አስጠንቅቋት ነበር፡፡ ነገር ግን ባለመስማት ለስቅለት አበቃችው፡፡
የሰው ልጅ የሚስተው ዕውቀት አጥቶ፣ መምህርም ተቸግሮ አይደለም፡፡ ዕውቀትንና አስተማሪን ረግጦም ይበድላል፡፡ በደሉ ስህተት ብቻ ሳይሆን ምርጫም የሚሆንበት ጊዜ አለ፡፡ የጽዮን ልጅ ይህን ሁሉ ማስገንዘቢያ አልፋ ክርስቶስን ገፋችው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ለጽዮን ልጅ ብቻ ሳይሆን ለሰው ልጅ ትልቅ እንግዳ ነው፡፡ ለኢየሩሳሌም ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም መፍትሔ ሰጪ ነው፡፡ የምንፈልገው ሳይሆን ፈልጎን የመጣ፣ የከተማችንን እና የልባችንን በር የሚያንኳኳ ነው፡፡ እርሱ በአንዱ አማኒ ደስ የሚለው በብዙዎች መጥፋት ሳያዝን ቀርቶ አይደለም፡፡ ወደ መንግሥቱ የጠራው መላውን ዓለም ነው፡፡ እኛ እንኳ ሺህ ሰው ሠርግ ጋብዘን ድግሱን ደግሰን ሂሳቡን ከፍለን ሁለትና ሦስት ሰዎች ቢመጡ ከማዘን አልፈን እንታመማለን፡፡ ጌታም መንግሥተ ሰማያትን ለሰው ፈጥሮ ሰው ግን ለእርሱ ወዳልተፈጠረ ወደ ዘላለም እሳት ሲሄድ ያዝናል፡፡ የእኛን ሠርግ የቀሩ አይሞቱም፤ የክርስቶስን ሠርግ የቀሩ ግን ወደ እሳት ይጣላሉ፡፡ በእግዚአብሔር ግብዣ አለመገኘት በዲያብሎስ ግብዣ ላይ ራስን እድምተኛ ማድረግ ነው፡፡
ጌታችን ወደ እኛ መቼ መጥቶ ይሆን? ስንት ጊዜስ ሰማነው? በድምፅ ብቻ ሳይሆን በበትር ብዙ ጊዜ መጥቶ ነበር፡፡ ሲናገረን አልሰማነውም፡፡ በአልጋ ሲጥለን፣ ወኅኒ ሲከተን አልሰማነውም፡፡ ዛሬም በመንገዳችን ትክክል ቆሞ ይፈልገናል፡፡ የገዛ ልጆቻችንን አድገው ተመለሱ ሲሉን ልባችንን ያፀናን ወላጆች እግዚአብሔር በወለድኩት ሳይቀር እየተናገረኝ ነው ማለት ያልቻልን ሆነን ይሆን?

ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም በአህያይቱና በውርንጫይቱ ተቀምጦ መግባቱ ትንቢትን ለመፈጸም ነው፡፡ ነቢዩ፡- ንጉሥሽ የዋህ ሆኖ በማለት ይናገራል /ዘካ.9÷ 9/ የዋህ አውቆ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ ነው፡፡ የበታችነት መንፈስ የሚያሰቃየው ወይም ጅል ሁሉ የዋህ ተብሎ አይጠራም፡፡ የሚያደርገውን አውቆ ራሱን ዝቅ የሚያደርግ እርሱ የዋህ ነው፡፡ ጌታ የዋህ ንጉሥ ነው፤ ከነገሥታት የዋሆችን ማግኘት ከባድ ነው፡፡ በየዕለቱ ከሚያዩት አንጻር የዋህ መሆን ይቸገራቸዋል፡፡ ቂማቸውንም የሚያስታውስ ቢሮ አላቸው፡፡ የቂምና የክፋት ደወል ሞልተው ነው የሚተኙት፡፡ ጌታ ግን የዋህ ንጉሥ ነው፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ንጉሥ ተብሎ ከተገለጠባቸው ትንቢቶች የመጀመሪያው የዘካርያስ ትንቢት ነው፡፡ ጌታ ንጉሥ ሆኖ ተወልዷል፡፡ ንጉሥ ሆኖ ይኖራል፡፡ ሰዎች በሌሉበት ንጉሥ አይኖርም፡፡ ንጉሥ የሰዎች አለቃ ነውና፡፡ ጌታችን ግን ዓለም ሳይፈጠር ንጉሥ ነበር፡፡ በምርጫ ካርዳችን የምንሰቅለውና የምናወርደው ንጉሥ አይደለም፡፡ የማያምኑት እንኳ ሳያውቁት የሚገዙለት ንጉሥ ነው፡፡ ክፉ ነገሥታት እየቀጡ ሊረኩ ቢችሉም ቅጣት የሚገባው ሕዝብ ሲኖር እግዚአብሔር እንዳስነሣቸው፣ የመዓቱም ጨንገር /ሰይፍ/ እንዳደረጋቸው አይገነዘቡም፡፡ እርሱ ንጉሥ ነው፡፡
የተናቁትን ለማክበር
ጌታችን ሁሉ የእርሱ ነው፡፡ ሁሉንም ሲለዋውጥ የማይደክመው ነው፡፡ እመቤታችን ማርያም እንደተናገረችው ባለጠጎችን ድሆች ሲያደርግ የማይከሰስ፣ ድሆችን እንጀራ ሲያጠግብ የማይሳነው ነው፡፡ እግዚአብሔር የዚህን ዓለም በረከት እንደ ጽዋ በእጃችን ላይ አስቀምጦታል፡፡ ጽዋ አሁን በእጃችን ቢሆንም ለቀጣዩ ማስረከብ አለብን፡፡ በእጃችን የነበረውን ጽዋ በሰው እጅ ላይ እናየዋለን፡፡ ዓለም ጽዋ ነው፡፡ ዛሬ የእኛ ነገ የሌላ ነው፡፡
በዚህ ዓለም ላይ የሚያስፈራው ከውርደት ይልቅ ከፍታ ነው፡፡ ከውርደት ቀጥሎ ከፍታ አለና ተስፋ አለው፡፡ ከከፍታ ቀጥሎ ውርደት ሊመጣ ይችላልና ጥንቃቄ ያስፈልጋል፡፡ አልቅሱ የተባሉት ባለጠጎችና ትልልቆች ነን የሚሉ ናቸው፡፡ ጌታችን የተናቁትን ያከብራል፡፡
አህያ የተናቀች ናት፡፡ መልክ የላትም፣ ፈጣን አይደለችም፣ ጉልበቷም ብርቱ አይደለም፡፡ ትልልቅ ጆሮ ቢኖራትም ለመስማት፣ ትልልቅ ዓይን ቢኖራትም ለማየት ትቸገራለች፡፡ ሰዎች ሁሉ የንቀት ሸክማቸውን የሚያሸክሙት ለአህያ ነው፡፡ አህያ ተብሎ የተሰደበም እንደከፋው ይኖራል፡፡ ምሥጢሩ ግን የጌታ ማረፊያ ማለት መሆኑ አይገባውም፡፡ ጌታችን በዚህች አህያ ላይ ተቀምጦ ንግሥናውን መግለጡ የተናቁትን የሚያከብር አምላክ መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡
አህያን ለሸክም እንጂ ለሰው መጓጓዣነት አትፈለግም፣ አትሸለምም፡፡ ጌታ ግን ሸላልሞ ተቀመጠባት፡፡ ልብሳቸውን እንዳትነካ የሚሸሿት ሰዎች ዛሬ መሬት ላይ አነጣጠፉላት፡፡ ጌታ ተቀምጦባታልና ስለ ጌታ አከበሯት፡፡ እንዲሁ የተናቅን፣ የተረሳን፣ ጅሎች፣ ነገር የማይገባቸው የተባልን ብንሆን ጌታ ብቻ ይረፍብን፤ ያን ጊዜ እንከብራለን፡፡ ራሳችንን ለማስከበር ለመማርና ለመድከም ጌታን ለመሸከም ማሰብ አለብን፡፡ ከራሳችን የተነሣ ሳይሆን ከጌታ የተነሣ የሆነ ክብር የማይጠፋ ክብር ነው፡፡ የተናቁትን ጌታ ያከብራል፡፡ እግዚአብሔር ላንተም ላንቺም ቀን አለው፡፡ በቀናችሁ እናንተን መግፋት ማንም አይችልም፡፡
ሰላምን ለማብሰር
የጥንት የእስራኤል ነገሥታት በፈረስ ተቀምጠው በሕዝቡ መሐል ሲመላለሱ ጦርነት እንዳለ እየጠቆሙ ሕዝቡን ተነሥ ማለታቸው ነው፡፡ በአገራችን ፋኖ ፋኖ እየተባለ ሲዘፈን ቀጥሎ የሚጠበቅ ነገር አለ፡፡ ኢትዮጵያ አገራችን እየተባለ ሲዘፈን አገርን መጥራት በጦርነት ቀን እስኪመስል ሁሉም አንድ ነገር ያጭርበታል፡፡ በእስራኤልም ነገሥታት ልማድ ፈረስ ላይ ተቀምጦ ጦር ይዞ መታየት ጦርነትን ማወጅ ነውና ሴቱ ለስንቅ፣ ወንዱ ለትጥቅ ይዘጋጅ ነበር፡፡ በአህያ ላይ ተቀምጦ ከታየ ግን አገሩ ሰላም፣ ምድሩ በረከት እንደሆነ መግለጡ በመሆኑ ጎበዝ ሊዳር፣ ቆንጆ ሊኳል ይሰናዳል፡፡
ጌታችን በአህያ ውርንጭላ ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም መግባቱ ንጉሠ ሰላም ወፍቅር መሆኑን ለመግለጥ ነው፡፡ በርግጥም ክርስቶስ ሰላማችን ነው፡፡ ሰው ለሰላሙ ብልጥ የሆነ እየመሰለው አመለኛ ሠራተኛውን ያባርራል፤ ከክፉ ጎረቤት ለመሸሽ ቤቱን ይሸጣል፡፡ ትዳሩን ይፈታል፡፡ ልጁን ውጭ አገር ይልካል፡፡ ሰው ግን ገና ለሰላሙ አላወቀበትም፡፡ የሰላም ምንጩ ክርስቶስን ማመን ነው፡፡ እርሱ ራሱ ወደ ኢየሩሳሌም ሲገባ ከተማይቱን ቁልቁል እያየ በዕንባ፡- ‹‹ለሰላምሽ የሚሆነውን በዚህ ቀን አንቺስ ስንኳ ብታውቂ አሁን ግን ከዓይንሽ ተሰውሯል›› (ሉቃ.19፡43)፡፡
ጌታችን በታላቅ ምስጋና ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፣ ሆሳዕና በአርያም፣ ሆሳዕና ለወልደ ዳዊት እየተባለለት፡፡ ሕጻናት ቋንቋ ሳያውቁ ምስጋና አውቀው ዘመሩለት፡፡ በሕጻናት የከበረውን ጌታ እኛስ አክብረነው ይሆን? እርሱ ሰላማችን ምንጭ ነው፡፡
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ