የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሆሳዕና

                               የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ…….  ዓርብ መጋቢት ፳፭/ ፳፻፯ ዓ.ም.
ሆሳዕና በአርያም
የዐቢይ ጾም ስምንተኛው እሑድ ሆሳዕና ተብሎ ይጠራል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአህያና    በውርንጭዋ ተቀምጦ በታላቅ ክብር ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ መቅደሱ መግባቱን የምናስብበት ቀን ነው፡፡ ጌታችን ወደ ኢየሩሳሌም ገባው ከደብረ ዘይት ተራራ ወርዶ ነው፡፡ የደብረ ዘይት ተራራ እጅግ ከፍ ያለ ተራራ ነው፡፡ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ቆሞ ዮርዳኖስንና የሙት ባሕርን/ባሕረ ሎጥን/ አሞንና ሞዓብን እንዲሁም መላዋን ኢየሩሳሌም ማየት ይቻላል፡፡ ጌታችን ከዚህ ተራራ ወርዶ ወደ ኢየሩሳሌም የገባው ለመሞት ነው፡፡ እንደሚሞት እያወቀ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፡፡ ጌታችን ጀግንነቱ ብርታቱ ሊነገር ይገባዋል፡፡ ጌታችን ታላላቅ ነገሮችን የገለጠባቸው ሦስት ተራሮች አሉ፡፡ አራተኛው ግን ለሁሉ ይልቃል፡፡ የመጀመሪያው መንፈሳዊውን ከፍታ የገለጠበት የአንቀጸ ብፁዓን ተራራ፣ ሁለተኛው ግርማ መለኮቱን ክብረ መንግሥቱን የገለጠበት የደብረ ታቦር ተራራ፣ ሦስተኛው የዳግም ምጽአቱን ምልክት ያስረዳበት የደብረ ዘይት ተራራ ሲሆን አራተኛው ግን ዘላለማዊ ፍቅሩን የገለጠበት የቀራንዮ ተራራ ነው፡፡ ይህም ከሁሉ ይበልጣል፡፡

 

ጌታችን ከዚህ በፊትም ሆነ ከዚህ በኋላ በዘመነ ሥጋዌው ከሰዎች ያልተቀበለውን ክብር በሆሳዕና ዕለት ተቀብሏል፡፡ ይህም ሞቱን የሚያፋፍም፣ የሰቃዮቹን ልብ ይበልጥ የሚያነሣሣ ነበር፡፡ ከደብረ ዘይት ሲወርድ ኢየሩሳሌም፣ መቅደሱና ቀራንዮ ይጠብቁታል፡፡ ኢየሩሳሌም የስሟ ትርጉም ሀገረ ሰላም ማለት ሲሆን ሰላምን ግን ዓይታ አታውቅም፡፡ ይልቁንም ለሰላሟ የሚበጃትን ክርስቶስን በመግፋቷ ይኸው ስትታወክ ትኖራለች፡፡ የሰላም ስም ይዛ በሁከት ወደምትኖረው ኢየሩሳሌም ጌታ ገባ፡፡ ዛሬም ትዳር፣ ቤተ ክርስቲያን፣ ተራድኦ የሚሉ ስም ይዘው ነገር ግን ሰላም ያጡ በግልግል የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ከፍ ያሉት ሰዎች እነዚህን ወገኖች ከማስማማት በር ዘግተው ተቀምጠዋል፡፡ ከደብረ ዘይታቸው ወርደው ሰላምን ለመስበክ ክብሬ የሚሉት ነገር ያስጨንቃቸዋል፡፡ ትልቁ ክብር ሁሉ እያላቸው መኖር ያቃታቸውን ሕዝቦች መታደግ መሆኑን አልተገነዘቡም፡፡ ጌታ ግን ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም ንጉሠ ሰላም ወፍቅር ሆኖ ገባ፡፡

መቅደሱ በእግዚአብሔር ስም ቢሰየምም እግዚአብሔር ደባል ሰዎች ቤተኛ ሆነውበት ነበር፡፡ መቅደሱም የንግድ እንጂ የሃይማኖት ቦታነቱን ስቶ ነበር፡፡ ጌታ ይህንን ጉድ ለማጽዳት ወረደ፡፡ እግዚአብሔር በቤታችን ይገፋ እንጂ በገዛ ቤቱ መገፋቱ ዛሬም ሊቆጨን፣ ቤተ ጸሎት ቤተ ነጋድያን መሆኑ ሊያቃጥለን ይገባል፡፡ ይህን ቁጭት ይዘን ስንነሣ ግን በቀላሉ በሕዝቡ የሚሰሙ ካህናትና ጻፎች ከምንገምተው በላይ ስደት ሊያስነሡብን ይችላሉ፡፡ እነርሱ ሲነኩ እግዚአብሔር እንደ ተነካ፣ የእነርሱ ግፍ ሲገሠጽ የእግዚአብሔር ቅድስና እንደ ተነቀፈ የሚቆጥሩ ብዙዎች ናቸው፡፡ ጌታ ከደብረ ዘይት የወረደው ቤቱን ሊያፀዳ ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ቤዛ ኩሉ ዓለም ሆኖ ለመሞት ነው፡፡ የማይገባውን የእኛን ሞት ካልሞተ የማይገባንን የእርሱን ሕይወት ማግኘት አንችልም፡፡ ክብርንና ከፍታን ንቆ ለታወኩት ሰላም፣ ለአገልጋይ አጥፊዎች ተግሣጽ፣ በዘላለም ሞት ለተያዙ ሕይወት ለመስጠት ጌታችን ወረደ፡፡
 
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣው መሞትን ዓላማ አድርጎ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ወደ ዓለም የሚመጣው መኖርን ዓላማ አድርጎ ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ መሞትን ዓላማ አድርጎ ወደዚህ ዓለም መጥቷል፡፡ ሕይወቱንም ለእኛ ቤዛ ለማድረግ ተጠንቅቆለታል፡፡ ምንም እንኳ ለመሞት ቢመጣም ያለጊዜው ላለመሞት ተጠንቅቋል፡፡ ሄሮድስ ሊገድለው በፈለገ ጊዜ ወደ ግብፅ መሰደዱ፣ ሰይጣን ራስን ወርውር ሲለው እምቢ ማለቱ፣ አይሁድ ሊገድሉት ሲሉ ከመሐላቸው ተሰውሮ መሄዱ ያለ ጊዜው ላለመሞት ነው (ማቴ. 2፡13፤4፡6፤ሉቃ.4፡29-30)፡፡ ምንም እንኳ ለመሞት ቢመጣም ያለ እግዚአብሔር ጊዜ እንዳይሞት ተጠነቀቀ፡፡ ጌታችን ይጠነቀቅ የነበረው እንደ አባቱ ፈቃድ ለመኖር ብቻ ሳይሆን እንደ አባቱ ፈቃድም ለመሞት ነው (ማቴ. 26፡39)፡፡  
 
ጌታችን በጉዞው ሁሉ መስቀሉን ያስብ ነበር፡፡ ምንም እንኳ በመስቀል ላይ የዋለው በዕለተ ዓርብ ቢሆንም ኑሮው ሁሉ የመስቀል ጐዳና ያለበት ነበር፡፡ መስቀል በዕድሜአችን መጨረሻ ላይ የሚገጥመን ነፍሳችን ከሥጋችን የምትለይበት ሳይሆን ዕለት ዕለት የምንቀበለው፣ ሥጋችን ከዓለም የምትለይበት የሕይወት ሥርዓት ነው፡፡ ነቢዩ፡- ‹‹ስለ አንተ ሁልጊዜ ተገድለናል››እንዳለ (መዝ. 43፡22)፡- መስቀል ዕለታዊ ነው፡፡ ጌታችን ልዩ ምልክቱ መስቀል ነው የእርሱ ምልክት ዘውድ ሳይሆን የእሾህ አክሊል፣ ሕለተ ወርቅ /ንጉሣዊ ዘንግ/ ሳይሆን የመስቀል በትር ነበር፡፡ ዛሬ ሰዎች እየፈለጉ ያሉት መስቀል አልባውን ክርስቶስን ነው፡፡ ስለዚህ ሐሳዊ መሢሕ ላይ መውደቃቸው አይቀርም፡፡ ክርስቶስ ነን ብለው የሚመጡ የሌላቸው አንድ ነገር ቢኖር የችንካር ምልክት ነው፡፡ የዛሬ ክርስቲያኖች ምቾት አምላኪ ናቸውና እዚህ ሐሰተኛ ክርስቶስ ላይ እንዳይወድቁ ያስፈራል፡፡ ጌታችን ኑሮው መስቀል ያለበት ነበር፡፡ መስቀለኛ መንገድን ብናይ አደጋ ይበዛበታል፡፡ በመንገዶቹ ሁሉ አይኬድም፤ ሦስቱን ትቶ ባንዱ የመሄድ ውሳኔ ያለበት ነው፡፡ 
 
መስቀል ብዙ ትግሎች አሉት፣ መስቀል መግደል ሳይሆን መሞት፣ ወደ መቃብር መውረድ ሳይሆን ሥጋዊ ፍላጎትን መናቅ በመሆኑ ለብዙ ምድራውያን ሰዎች ተስማሚ አይደለም፡፡ መስቀል ውሳኔም ነው፡፡ በመንገዶች ሁሉ አይኬድም፡፡ የምንሄደው ወደ ራእያችን ግብ በሚያደርሰው መንገድ ነው፡፡ ብዙዎች በመስቀለኛ መንገድ ላይ ይንገላታሉ፡፡ ሁሉን ለመምረጥ ስለሚፈልጉ ሁሉንም ሳይዙ ይቀራሉ፡፡ ሁሉንም የሚፈልግ ሁሉንም ያጣል፡፡ መስቀል ውሳኔ ነው፡፡ ስለ ክርስቶስና ስለ ራእያችን አጣሁ የምንለው ነገር ሁሉ ቁጥሩ ከጉዳት ሳይሆን ከትርፍ ነው (ፊልጵ. 3፡7-11)፡፡ የመስቀሉ መንገድ ውጤቱ አንድ ከአራት እየሆነባቸው፣ መስቀል አልባው ክርስትና ደግሞ ውጤቱ ሦስት ከአራት እየሆነባቸው በአሳብ የሚንገላቱ በዝተዋል፡፡ ሦስቱ መንገዶች ገንዘብ፣ ዘመናዊነትና የሥጋ ፈቃድ ናቸው፡፡ እየፈለጉ ያሉት ክርስትና እነርሱ የፈጠሩትን ክርስትና እንጂ ክርስቶስ የመሠረተውን መስቀል ያለበትን ክርስትና አይደለም፡፡ የዛሬም ሰባኪዎች መንግሥተ ሰማያትን ሳይሆን ጌጠኛ ከተሞችን የሚሰብኩ የክርስቶስን መምጣት ሳይሆን የገንዘብን ምጽአት የሚተርኩ መንፈሳዊውን ነገር ሳይሆን ሳይኮሎጂን የሚተነትኑ ናቸው፡፡ ‹‹ይኸው ከሆነ ባልሽ አዘንኩልሽ›› እንደሚለው የሠርግ ዘፈን የኢትዮጵያ አብያተ ክርስቲያናት ባሎች እነዚህ ከሆኑ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሳዝናለች፡፡
 
መስቀል ምሥጢሩ ረቂቅ ነው በዓይን ከምናየው ይልቅ በልባችን ዋጋውን የምናስበው ነው፡፡ ትምህርተ ኅቡአት በተባለው የእምነት መዝገብ፡-
‹‹ተሰቅለ በእንቲአነ ወበመስቀሉ ኮነ ሕይወትን ፅንዕነ ቤዛነ ዘውእቱ ምሥጢር ኅቡዕ ፍሥሐ ዘኢይትዌዳዕ ዘቦቱ ኲሎ ነፍሰ ፍትወተ ሰብእ ያርኅቅ እም እግዚአብሔር ኢይክል፤ ኪያሃ እንዘ ትፀውር ወትረ ዛ ይእቲ ስብሐተ ፍቅር እምእግዚብሔር ኢታሴስል፤ ወበእላ ከናፍር ጾታ ነጊር ኢይትከሀል ጥንቁቀ፣ ዘእምትካት ኅቡዓ ኮነ ይእዜሰ ክሡተ ምሥጢረ ኮነ ለምእመናን፤ አኮ ከመ ይትርአይ አላ ከመ ይትሐለይ ውእቱ ዝንቱ መስቀል ወቦቱ ንትመካህ ከመ ንሰብሖ ወቦቱ እለ ይጠመቁሂ ምእመናን ፍጹማን››
 
ትርጓሜ፡- “ጌታችን ስለ እኛ ተሰቅለ፤ በመስቀሉም ሕይወት ሆነልን፡፡ ብርታታችንና ቤዛ የሆነልን ይህ ጥልቅ ምሥጢር፣ የማያልቅ ደስታ ያለበትና የሰው የነፍሱ ፍላጎት ከእግዚአብሔር ለማራቅ የማያስችል ነው፡፡ እርስዋን አዘውትረህ ስትሸከም ፍቅረ እግዚአብሔርን የማታስለይ ምስጋና ይህች ናት፡፡ በእነዚያም ከንፈሮች ጠንቅቆ የመናገር ስልት ሁሉ የማይቻል ነው፡፡ ዱሮ ተሠውሮ የነበረው ዛሬ ለምእመናን ሁሉ የተገለጠ ሆኖአል፡፡ ዳሩ ግን ይኸው መስቀል እንዲታይ ሳይሆን በልብ የሚታሰብ እንዲሆን ነው፡፡ በእርሱም እናመሰግነው ዘንድ እንመካለን፡፡ በእርሱ የሚጠመቁ ምእመናን ፍጹማን ናቸው፡፡›› /ትምህርተ ኅቡዓት/
 
መስቀሉን ማለት የክርስቶስን ቤዛነቱን ተንትነን መፈጸም አይቻልም፤ ከቃላት ብቻ ሳይሆን ከአሳብም ይጠልቃል፡፡ ሙሉና ፍጻሜ የሌለው ደስታ በመስቀሉ ተገኝቷል፡፡ ይህ ፍቅር የገባው ሰው ከእግዚአብሔር ተለይቶ ራሱን ለመምራት በፍጹም አይሻም፡፡ መስቀሉን ባሰብን ጊዜ ይህን ሁሉ ያደርግህልኝ ኧረ እኔ ማን ነኝ? የሚል የፍቅር ዕዳ ይሰማናል፡፡ በፍቅር የታመቀ ምስጋናም በነፍሳችን ላይ ይመነጫል፡፡ የመናገር አቅም ያላቸው ሁሉ የክርስቶስን የቤዛነቱን ፍቅር መግለጥ ይሳናቸዋል፡፡ ፍቅሩ የመጣው በመስቀል ላይ ሳይሆን ዘላለማዊ ነበረ፣ ተሠውሮ ሲኖር ግን በቀራንዮ ተገለጠ፡፡ ይህ መስቀል ወይም ሞተ ክርስቶስ በልብ የሚታሰብ ነው፡፡ መስቀል ከዓይን ይልቅ ለልብ የተብራራ ነው፡፡ በዚህ ፍቅር ስንጠመቅ ያን ጊዜ ፍጹማን እንሆናለን፡፡ የቀደሙት አባቶች እንዲህ በማለት መስቀሉን ያብራራሉ፡፡ የቅርብ ዘመን ዘማሪትም፡-
‹‹እዩት ኢየሱስን መስቀሉ ማማሩ
ለተመራመረው ብዙ ነው ምሥጢሩ››  ብላለች፡፡
ጌታችን ከደብረ ዘይት ወደ ኢየሩሳሌም ወረደ፡፡ ወንጌላዊው ማቴዎስ ይህንን ሲዘግብ፡- “ወደ ኢየሩሳሌምም ቀርበው ወደ ደብረ ዘይት ወደ ቤተ ፋጌ ሲደርሱ& ያን ጊዜ ኢየሱስ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ& እንዲህም አላቸው፡- በፊታችሁ ወዳለችው መንደር ሂዱ& በዚያን ጊዜም የታሰረችን እህያ ውርንጫም ከእርስዋ ጋር ታገኛላችሁ፤ ፈትታችሁ አምጡልኝ፡፡ ማንም አንዳች ቢላችሁ፡- ለጌታ ያስፈልጉታል በሉ፤ ወዲያውም ይሰዳቸዋል” ይላል (ማቴ. 21፡1-3)፡፡
 
ቤተ ፋጌ በደብረ ዘይት ተራራ ላይ ያለች ትንሽ መንደር ናት፡፡ እንኳን ያን ጊዜ ዛሬም አነስተኛ መንደር ናት፡፡ ጌታ ከደቀ መዛሙርቱ ሁለት ላከ፡- ሁለት አድርጎ መላክ የመንግሥቱ የተልእኮ ባሕርይ ነው፡፡ አንዱ ሲደክም አንዱ እንዲያበረታ ሁለት ሁለት አድርጎ ይልካል፡፡ ሁለት ደካሞች አንድ ብርቱ ሲወጣቸው፣ አንድ ብርቱ ግን ብቻውን ብርታቱን ጠብቆ መቆየት አይችልም፡፡ ስለዚህ ሁለት አድርጎ ላካቸው፡፡ ጌታ ስለ ታሠረች አህያ እንኳ ያውቃል፡፡ ከዕውቀቱ የተሠወረ ምንም ነገር የለም፡፡ ስለ ታሠረች አህያ እንኳ ግድ የሚለው ከሆነ ስለ ሰዎችማ እጅግ ይሰማዋል፡፡
 
የታሠሩት አህያና ውርንጫ ናቸው፡፡ እናት ልጅ ሁለቱም ታስረዋል፡፡ ብዙ ሲለፉ ቢውሉም የዕረፍት ጊዜያቸውን በእስር የሚያሳልፉ መከረኞች ናቸው፡፡ ሀብት ለማግኘት፣ ዕውቀት ለመሰብሰብ፣ ከሥልጣን ኮርቻ ላይ ለመፈናጠጥ ብዙ የደከሙ ከባሪያ ያነሰ ሆነው የኖሩ በዕረፍት ጊዜያቸው ወይም አሁን ዕረፍቴ ነው በሚሉበት ዘመን የጭንቀት፣ የፍርሃት፣ የበሽታ እሥራት ይገጥማቸዋል፡፡ ይህ ሁሉ ዘመን ያልገባቸውን አንድ ነገር አሁን ይረዳሉ፡፡ እርሱም ዓለም ዕረፍት እንደሌላት ነው፡፡ ጌታ ግን ለእነዚህም እስረኞች ዓላማ አለው፡፡ እነዚያ አህዮች የተላኩላቸውን ሁለት ደቀ መዛሙርት ቢገፉ አይፈቱም ነበር፡፡ እያሠረ ለሚገዛቸው ጌታ ባሪያ ሆነው ይቀሩ ነበር፡፡ ዛሬም ከብዙ ልፋት በኋላ ራሳቸውን እንደ እስረኛ ለሚያዩ ወገኖች የምናስተላልፈው መልእክት ወደ እነርሱ የተላኩትን የወንጌል አገልጋዮች በፍቅርና በትሕትና መቀበል እንዳለባቸው ነው፡፡ ወንጌል በደረጃ አይሰበክም፡፡ ለሚኒስትሩ ሚኒስትር ሰባኪ አይላክም፡፡ ጳውሎስ የብሉይ ኪዳን አዋቂ፣ ጴጥሮስ ዓሣ አጥማጅ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ እኛ ብናደላድል ጳውሎስን የአይሁድ መምህር፣ ጴጥሮስን የአሕዛብ መምህር እናደርገው ነበር፡፡ እግዚአብሔር ግን ተመኑ እንደ ሰው አይደለምና ጳውሎስን መምህረ አሕዛብ ጴጥሮስን መምህረ አይሁድ አደረገው፡፡ በጸጋው እንጂ በሰው ብርታት ወንጌል አትሰፋም፡፡ ወንጌልን ለመቀበል ትንንሽ አገልጋዮችን አክብሮ መቀበል ያስፈልጋል፡፡ እግዚአብሔር የሚሠራው ምንም የሚመኩበት ከሌላቸው ምስኪኖች ጋር ነው፡፡
 
አህያይቱ ነጻ ስላልወጣች ውርንጭዋም ነጻ አልወጣችም፡፡ በባርነት ሆነን ስንወልድ ልጆቻችንንም ለባርነት እንወልዳለን፡፡ ከልጅ በፊት ነጻነት ይቀድማል፡፡ ዛሬም በኃጢአት፣ በሱስ፣ በሁከት ባርነት ውስጥ ሳሉ የሚወልዱ ልጆቻቸውን ለባርነት ይወልዳሉ፡፡ ልጆች የወላጆቻቸውን ሁሉም ነገር ወራሽ ናቸው፡፡ ባልና ሚስት ሳይግባቡ፣ በቤቱ ሰላም ሳይኖር ልጅን መጋበዝ አይገባም፡፡ ልጆቹ በሕይወት ላይ እርግጠኝነት እያጡ ፈሪና ተጨናቂ ሆነው ያድጋሉ፡፡ ከወላጆቻቸው ያጡትን ፍቅር የትም የማያገኙት ስለሚመስላቸው ግንኙነታቸው ሁሉ ፍርሃት ያጠላበት ይሆናል፡፡ ከመውለድ በፊት መፈታት ያስፈልጋል፡፡ ነጻ የወጣ ነጻነት ያላቸውን ትውልዶች ያወጣል፡፡
ጌታ ፈትታችሁ አምጡልኝ አለ፡፡ ማንም አንዳች ቢላችሁ፡- ለጌታ ያስፈልጉታል ብሎ አላቸው፡፡ በአህዮቹ ላይ ሕጋዊ ጌታቸው ያሰራቸው ገዥ ሳይሆን የፈጠራቸው ክርስቶስ ነበር፡፡ አህዮቹ ከጌታቸው በላይ ጌታ ያለ መስሎ አይሰማቸውም ነበር፡፡ የጌቶቹ ጌታ ግን በሥልጣን ጠራቸው፡፡ አህዮቹ ለምንና እንዴት ማለት አይችሉም፡፡ ስለ እነርሱ ነጻነት የሚከራከር ካለ ግን ጌታ መልሱን ልኮላቸዋል፡፡ የሚፈታን ብቻ ሳይሆን በጠላት ፊት አንደበት የሚሆነን ጌታ ነው፡፡ ዛሬም ከሚገዛን ኃጢትና ሱስ በላይ የሆነ ኃይል ያለ አይመስለንም፡፡ ነገር ግን የገዥዎች ገዥ ክርስቶስ የመልካምም ሆነ የክፉ ጌቶች የበላይ ጌታ ነው፡፡ እርሱ ከጠራን ማነው የሚያስረን፣ እርሱ ቃላችን ሆኖ የሚረታልን፣ ኃይላችን ሆኖ የሚያሸንፍልን ነው፡፡ የአገራችን ባለቅኔ ይህን ጌታ ሲያወድስ እንዲህ ብሏል፡-
 
ስምህ ያንተ ካባትህ
ወልደ ማርያም በላይ ነህ
 
ለጌታ ያስፈልጉታል ሲባል ጠያቂዎቹ ሁሉ ዝም ይላሉ፡፡ የክርስቶስ ስም ሲጠራ አሣሪ ሁሉ ዱዳ ይሆናል፡፡ በራሱ ስም ነጻ ለመውጣት የሚፈልግ የእስራቱ ገመድ ይጠብቅበታል፡፡ በክርስቶስ ስም ነጻ ለመውጣት ለሚሹ ግን ነጻነታቸው እንደ ቀትር ይፈካል፡፡ የታሠሩትን የሚፈልግ ጌታ ብቻ ነው፡፡ ሁሉም ሰው የሚፈልገው የተፈቱትን፣ ከልዩ ልዩ ወንጀልና አመል የፀዱትን፣ ራሳቸውን የሚጠብቁትን፣ ኩራት ሊሆኑ የሚችሉትን ነው፡፡ የታሠሩትን ፈትቶ ለክብሩ ማረፊያ በማድረግ የታወቀው ጌታ እነዚህን የኃጢአት ባሮች ይፈልጋቸዋል፡፡ ከነማንነታችን የሚቀበለን ቀጥሎ ማንነቱን የሚያለብሰን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆሳዕና ለእርሱ ይሁንለት!!
 
አህያ የተናቀች ናት፡፡ ለፍታም የምትደበደብ፣ ድካሟን ማንም የማያውቅላት ናት፡፡ የሜዳ አህያን ሁሉም ሰው በዱር በገደል ባዝኖ ፎቶ ያነሣታል፡፡ ሸክሙን የምትጋራለትን አህያ ግን ማንም ፎቶ አያነሣትም፡፡ ፎቶ በቀረና አህያ ብሎ መሳደብ ገደብ ቢያገኝ አህያም ትመኝ ነበር፡፡ የብዙ ሰዎች ብስጭት ራሴን ዝቅ አድርጌ የምሠራ፣ ለሚወዱኝ ባሪያ መሆን የሚያረካኝ ሰው ነኝ፡፡ ትሕትናዬ መናቅን፣ ፍቅሬ መገፋትን አመጣብኝ ይላሉ፡፡ ውለታን የሚያስብ ጌታ ግን ኑ ወደ እኔ ይላችኋል፡፡ እርሱ የአንድ ብርጭቆን ዋጋ እንኳ የማይንቅ፣ ለመልካምነታችን ለትንሹም እምነታችን ትልቅ ዋጋ የሚከፍል ነው፡፡ ከሰው ምላሽ የሚጠብቅ ኀዘነተኛ ነው፡፡ ምክንያቱም ከሰው ደመወዝ አይገኝምና፡፡ ደመወዝ ያለው ከእግዚብሔር እጅ ነው፡፡ ሰዎች እንኳን ውለታችንን ሊመልሱ ያደረግነውን መልካም ነገር መልካም ብለው ቢቀበሉ እንኳን በቂ ነበር፡፡ ጌታ ይህን ሁሉ ያያል፤ የተናቅን ብንሆን ይፈልገናል፡፡ ትሕትናችንና ፍቅራችን ዋጋ ያጣ ቢመስል እርሱ ዋጋ ይሰጠዋል፡፡
 
ምንም በብዙ ነገሮች የታሠርን መስሎ ቢሰማን ለጌታ እናስፈልገዋለን፡፡ በምድር ላይ የምንኖረው ሥራ ስላለን ነው፡፡ ዓላማ ባይኖረን እንኳ እግዚአብሔር በእኛ ላይ ዓላማ አለው፡፡ ጌታ የሚፈልገን ለዓላማ ነው፡፡ ለዚህ ባለ ዓላማ ጌታ ሆሳዕና መድኃኒት መባል ይሁንለት!
 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ