በዚህ ዓለም ላይ ሳይሠሩ ለመብላት፣ ሳይዘምቱ ለማሸነፍ፣ ሳይዘሩ ለማጨድ፣ ሳይወዱ ለመወደድ፣ ሳይሰጡ ለመቀበል፣ ሳያከብሩ ለመከበር የሚፈልጉ ሰዎች አሉ። ወልደው ካላሳደጉት ልጅ ጡረታን የሚጠብቁ፣ በነበራቸው ቀን የረሱትን ወዳጅ ባጡ ቀን አምጣ ለማለት የሚደፍሩ ፣ ሲኖራቸው የሚጠፉ ያጡ ቀን የሚመለሱ፣ ስልካቸውን እነርሱ ይደውሉበታል እንጂ ቢደወልላቸው የማያነሡ፣ ሆዳቸውን የሚወዱ፣ ራሳቸውን የሚያፈቅሩ፣ ካስደሰታቸው ሁሉን የሚያደርጉ፣ እገሌ ያስባል ብለው ለሚጨነቁላቸው የማይጨነቁ ፣ እጅግ ግዴለሽ ፣ ራሳቸውን ሰዎች ላይ ጥለው የሚኖሩ፣ ንዝህላል ሰዎች አሉ። ሰዎች ካላስታወሷቸው መታጠብን ይረሳሉ፣ ካልተጎተጎቱ የወዳጃቸውን ልቅሶ አይደርሱም። መላው ወገን ይንከባከባቸዋል፣ በእጃቸው ላይ ገንዘብ ታይቶ ስለማያውቅ ዘመድ አዝማድ ያዘንብላቸዋል። ሁሉም ሰው ግዴታ ያለበት ይመስላቸዋል፣ በእምነት ሳይሆን በድንዛዜ አርፈዋል ። ስለ ነገ ጭንቀት ስለ ትላንት ፀፀት የላቸውም። ተፈልገው ይገኛሉ፣ ከመጠጥ ቤት በግድ ግቡ ይባላሉ።ማሰብ ያቆሙ ይመስላሉ፣ ራሳቸውን በሚመለከት፣ የሚጠግን ምግብ በመመራመር ደግሞ ሳይንቲስት ናቸው። መብታቸውን ጨርሰው የሌሎችን መብት የሚጠቀሙ፣ የራሳቸውን ወስደው ሰው የተወውን የሚያስሱ ሰዎች የዚህን ዓለም አንድ ጠርዝ ይዘዋል።
በሌላኛው ጠርዝ ደግሞ ድንብር፣ ደንባራ፣ ድንብርብር፣ የያዙትን የሚጥሉ፣ ሰው አየኝ ብለው ያለ እንቅፋት የሚወድቁ ሰዎች ይታያሉ። ስማቸው ገና ሳይጠራ አቤት የሚሉ፣ ዕቃ ሲንኳኳ በልቻለሁ የሚሉ፣ ከእንቅልፉ ገና የተነሣ ሰው አልሳቀልኝም ብለው የሚዋትቱ፣ ስልክ ካላነሡላቸው መኖራቸውን የሚጠሉ ደንባራ ሰዎች አሉ። ለሁሉ የመሳቅ፣ ለሁሉ የመሮጥ፣ ለሁሉ የመስገድ ግዳጅ ያለባቸው የሚመስላቸው፣ ፍርሃት ቤቱን የሠራባቸው ደንባሪዎች አሉ። ፈሪውን የሚፈሩ፣ የሞተ ውሻ ለእኔ ሲሆን ይነሣል ብለው የሚያምኑ ፣ ብርቱ ድምፅን መቋቋም የማይችሉ፣ የሰሙትን በሽታ ወደ ራሳቸው ስበው ሲታመሙ የሚያድሩ፣ ቆመው የሚኖሩ ምስኪን ሰዎች አሉ። እንኳን ዛቻን ቀዝቃዛ ሰላምታን መቋቋም የማይችሉ ፣ የወደድኩት ቢሞት፣ ያየሁት ቢጠፋ እያሉ የሚሰጉ ነፍሳቸውን የሚያሽብሩ ሰዎች አሉ። በከተማው ላይ ዝናብ እየዘነበ ከተማው ቢጠፋስ እያሉ እንቅልፍ የሚያጡ፣ ኒውክለር ቢተኮስስ ብለው መላውን ዓለም ተሸክመው የሚኖሩ ደካማ እምነት ያላቸው ሰዎች አሉ። በሩን ዘግተው ሦስት ጊዜ እየተመላለሱ የሚያረጋግጡ፣ የበሉት ምግብ ይጣፍጥ ነበረ ወይ? ብለው ከአንድ ሰዓት በኋላ የሚጠይቁ፣ የሌለ አደጋ እየፈጠሩ የሚዋትቱ መከረኛ ሰዎች አሉ። የመጣውን መከራ መቋቋም ይቻላል። ከሰማይ የወረደ ለምድር አይከብደውም ይባላል። ፈጥረው የሚጨነቁ ፣ በሌለ ነገር ፣ እንዲህ ቢሆንስ እያሉ ዋጋ የሚከፍሉ ብዙዎች ናቸው ። አየር መጎሰም ድል አያመጣም፣ በሌለ ነገር መጨነቅ ትርጉም አይሰጥም። ደንባራ ሰዎች ግን ስቃይ ባይመጣም ራሳቸውን በማሰቃየት ይደሰታሉ። ነገሮችን ቀለል አድርገው አያዩም። የድርሰት መምህር እስኪመስሉ ንግግሩ ሰዋሰዉ አልጠበቀም፣ ቃላት አልጠነቀቀም ብለው ጠብ ይፈጥራሉ።
ጴጥሮስ እየፈራች የጠየቀችውን ሴት እርሱ ፈራት፣ ደንባሪዎችም ፈሪዎችን ሳይቀር ይፈራሉ። ተጨንቀው ያስጨንቃሉ። ቅድም ሰላምታዬ ቀዝቀዝ ብሎ ነበር መሰለኝ ብለው እንደገና ሰላም ለማለት ይሄዳሉ። ያላቸውን ነገር ካላሳወቁ የሚከሰሱ ይመስላቸዋል። የራሳቸው ኑሮ የራሳቸው ምሥጢር የላቸውም። ለራሳቸው ጊዜ ሰጥተው አያውቁም። ነፍሳቸውን በነፍሳቸው ለማየት ፋታ አላገኙም ። ባልመጡ ቀኖች ላይ በግምት ያልቃሉ። ወጣ ሲሉ ወጥቶ የቀረውን ሲያዩ ለካ ይህም አለ ብለው ሁሉን ይተዋሉ፣ ደንባራ ናቸውና መልሰው ይጨነቃሉ። አረማመዳቸው መሬት እንዳያምማት ተጠንቅቀው ነው፣ እጅግ ጥንቃቄያቸው ስህተት ይወልድባቸዋል። ተጨንቀው ተጠበው ሲናገሩ የፈሩት ነገር ይቀጣጠላል። በላያቸው ላይ ብዙ አለቃ ሾመዋል፣ ትልቅ ትንሹ ያዝዛቸዋል፣ ያላደረጉ እንደሆነ ሁሉ ይቆጣቸዋል። በሕይወታቸው እምቢ ፣ አልችልም፣ ዛሬ አይሆንም ማለት አይችሉም ። ሁሉን እሺ በማለት ይጎብጣሉ። የሰሙት ችግር ሁሉ እነርሱ እንዲፈቱት የተነገራቸው ይመስላቸዋል። ሰውን ማዳመጥ ራሱ እርዳታ መሆኑን አያውቁም። የሰዎችን ትንሽ ስጦታ አክብደው ሲያዩ የራሳቸውን ራእይ ግን ያሳንሱታል።
ደንባሪነት የዚህች ዓለም ባለቤት እግዚአብሔር መሆኑን አለማመን ነው። ደንባሪነት የምንኖረው ለእግዚአብሔር ክብር እንጂ ሁሉን ለማስደስት አለመሆኑን መረዳት አለመቻል ነው። ደንባራነት ጥይት ሳይተኮስ ለምርኮ እጅን መዘርጋት ፣ በተሸነፈ ሕሊና መኖር ነው። ማድረግ እየቻሉ አለማድረግ ደንባራነት የሚያመጣው ነው። እኔ በጌታዬ ሙሉ ሰው ነኝ፣ የራሴን ግዴታ የሰውን መብት እስካወቅሁ ድረስ የሚያስፈራኝ ነገር የለም ብሎ በመተማመን መኖር ይገባል። ደንባሪዎች ያመኑበትን ተናግረው መከራ ሲመጣ ወዲያው ይቅርታ ይጠይቃሉ፣ ላላመኑበት ነገር ዋጋ እየከፈሉ ላመኑበት ዋጋ አይከፍሉም። ሰዎች እንዲያዝኑላቸው በመፈለግ አመመኝ ደከመኝ ማለትን ይወዳሉ። የፈጠራቸውን ትተው ላልፈጠራቸው ይርበተበታሉ። ሞት ላይቀር ሞትን ይፈራሉ። የመጣውን ላይመልሱት በፍርሃት አቅማቸውን ይጨርሳሉ። ፍርሃት የበላው አቅም የመጣውን ችግር ለመመለስ በቂ ነበር። ደንባራነት የሚፈራርሰው በእግዚአብሔር በማመን ነው። የሚያኖር እርሱ ብቻ ነው። እንደ ሰው እንጂ እንደ ውሻ መኖር በቃኝ ማለት ያለበት ራሱ ባለቤቱ ነው። ባልበደለው ይቅርታ መጠየቅም ባለጌዎችን ማንገሥ ነው። ፈርቶ ከመኖር ደፍሮ ማለፍ የጀግና፣ የሰማዕት ጠባይ ነው።
ሳይቆጡህ ራስህን እየተቆጣህ ፣ ሳይቀየሙህ ይቅርታ እየጠየቅህ፣ አምነህ በተናገርከው አስተያየት እያሰባሰብህ መኖር ይብቃህ። አንዱ ነዋሪ፣ አንዱ አኗኗሪ ሆኖ አልተፈጠረም። ዓለም የጋራ ነው። በቃህ!
ይህች ዓለም ማሰብ ያቆሙ ፣ ስለማይጠነቀቁ ሌላው የሚጠነቀቃቸው ግዴለሾች ያሉባት ሲሆን በሌላኛው አንጻር ደግሞ እግዚአብሔር ያላሽከማቸውን ሸክም ተሸክመው የሚኖሩ ሰዎች የሞሉባት ናት ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 5 ቀን 2017 ዓ.ም.