የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ….. ሐሙስ የካቲት 13/2006 ዓ.ም.
ሰዎች ኩሩ የሚሏቸውን ሰዎች በጣም ይከታተላሉ፡፡ የኮሩበትን ምክንያት ለማወቅ በደንብ ያጠኗቸዋል፡፡ ገለልተኛ ሰዎች የሰላዮችን ቀልብ ይስባሉ፡፡ ትልቅ አቅም ያለው መንግሥት እንኳ የተደበቀ ኑሮ ያላቸውን ወገኖች ይከታተላል፡፡ ማስተዋል ያለበት ግንኙነት፣ ጥንቃቄ ያለበት ማኅበራዊነት ከአትኩሮትና ክትትል ከሚያመጣው እንቅፋት ያድናል፡፡ በርምጃችን ሰዎች እያዩን እንደሆነ ስናስብ እግራችን ይተሳሰራል፣ በንግግራችን ሰዎች እየሰሙን እንደሆነ ስናስብ ንግግር ይጠፋብናል፡፡ እንዲሁም ሰዎች እየተከታተሉን እንደሆነ ስናስብ በኑሮ ውስጥ ፍርሃት ይገጥመናል፡፡ የዚህ ሁሉ ችግር ኑሮን በምሥጢር መልክ መኖር ነው፡፡ በዚህ ዓለም ላይ ከዚህ በፊት ያልደረሰ በእኛ ላይ የደረሰና ለእኛ የደረሰ ምንም ነገር የለም፡፡ ድብብቆሽ ስንጫወት ግን ኑሮአችን እየከበደ ሰዎችም ለደካማው አቅማችን ብርቱ መሣሪያ እንዲያዘጋጁ እናደርጋለን፡፡
ብዙ ድብቅ ሰዎች የገዛ ቤተሰባቸው ሳይቀር የሚፈልጋቸው ስለሚወዳቸው ሳይሆን ስለሚፈራቸው ነው፡፡ ድብቆች በምድር ላይ ወዳጅ ማግኘት ይቸገራሉ፡፡ ይህ ዓለም የግንኙነት ዓለም ነው፣ አንደበትም የግንኙነት መሣሪያ ነው፡፡ ድብቆች ግን የገዛ ተፈጥሮአቸውን ተቃውመው ይኖራሉ፡፡ ታዲያ ከራሱ የተጣላ ከሌላው ጋር ሰላም ሊኖረው እንዴት ይችላል? አላዋቂነት ሲጫነን የማይደበቀውን መደበቅ፣ ሁሉንም ነገር በሽፍንፍን መኖር እንጀምራለን፡፡ ከዚህ ሁሉ በላይ ድብቆች የብዙ ተንኮለኛ ዓይኖችን ይስባሉ፡፡ ምክንያቱም የሰዎች ባሕርይ የተደበቀውን ነገር አውቆ ለማዋረድ የሚጓጓ ነውና፡፡ ታዲያ ለማንም እንዳትናገሩ የተባለው ድብቅነትን ለማበረታታት ይሆን?
ሰውዬው ከአማቱ ጋር አስቸጋሪ ኑሮ ይኖራል፡፡ አማቱ ይህን አድርጉ ከተባሉ ያን ያደርጋሉ፡፡ ስለዚህ የሚግባቡት በተቃራኒው ነበር፡፡ ሂዱ ካላቸው ይቀራሉ፡፡ እንዲሄዱ ከፈለገ ቅሩ ይላቸዋል፡፡ “ደሞ አንተ ብለኸኝ ነው የምቀረው?” በማለት ይሄዳሉ፡፡ አንድ ቀንም በመንገድ ሲጓዙ ወንዝ ዳር ደረሱ፡፡ በዚህ ጊዜ ጎርፍ ሞልቶ ነበርና የአማቱን ጠባይ ረስቶ “እንዳይሻገሩ” አላቸው፡፡ እርሳቸውም፡- “እሻገራለሁ” ብለው ወንዙ ውስጥ ቢገቡ ጎርፉ ይዟቸው ሄደ፡፡ በዚህ ጊዜ ቢጮህ አገሬው ተሰበሰበ፡፡ አማቴን ውሃ ወሰዳቸው እርዱኝ አለ፡፡ እነርሱም ወደ ታች ፍለጋ ቢሄዱ ወደ ላይ ፈልጓቸው አለ፡፡ “ውሃ የሚሄደው ቁልቁል አይደለም ወይ?” ቢሉት “ውሃ የሚሄደው ቁልቁል ከሆነ እርሳቸው የሚሄዱት ሽቅብ ነው የአማቴን ጠባይ መች አጣሁትና” አለ ይባላል፡፡ ይህ ጠባያቸው ለቁርጥ ቀን የሚሆን አይደለም፡፡ በዚህ ጠባያቸው መዳን ሲችሉ አማቱ ሞተው ቀሩ፡፡ ሁልጊዜ ተቃራኒውን ነገር የሚከተሉ፣ ከሰው ልዩ ለመሆን የሚፈልጉ መከራቸው ረዳት የለውም፡፡ የደረቆች መጨረሻ ደርቆ መቅረት ነው፡፡
እኛም የእውነት አማች ሳንሆን አንቀርም፡፡ አስቸጋሪ አማቾች ነንና እውነት ሂዱ ስትለን እንቆማለን፣ ቁሙ ስትለን እንሄዳለን፡፡ የዚህ የመጨረሻ ውጤት መዳን እየቻልን ጠፍተን መቅረት ነው፡፡ በሕይወት ውስጥ የመሮጥና የማረፍ፣ የመናገርና የዝምታ፣ የውጊያና የድል፣ የአዝመራና የአጨዳ፣ የብርታትና የድካም …… ዘመን አለ፡፡ ትልቅ ችግርና የጊዜ መተላለፍ የሚፈጠረው በመሮጥ ዘመን ስናርፍ፣ በማረፍ ዘመን ስንሮጥ፣ በመናገር ዘመን ዝም ስንል፣ በዝምታ ዘመን ስንናገር፣ በአዝመራ ዘመን አጨዳ ስንፈልግ፣ በአጨዳ ዘመን ስንዘራ ነው፡፡ አቅም በክንዳችን፣ ዘር በእጃችን፣ ቃል በጉንጫችን ቢሆን ውጤት ያለው በጊዜው ነው፡፡ ጌታ ለማንም እንዳትናገሩ ያለው ስለ ዘላለማዊ ዝምታ ለመናገር ፈልጎ ሳይሆን ጊዜን ስለሚያከብር ዝምታ ለመናገር ነው፡፡ ቃሉ እንዲህ ይላል፡-
“ኢየሱስም ከዚያ ሲያልፍ ሁለት ዕውሮች፡- የዳዊት ልጅ ሆይ÷ ማረን ብለው እየጮሁ ተከተሉት፡፡ ወደ ቤትም በገባ ጊዜ ዕውሮቹ ወደ እርሱ ቀረቡ÷ ኢየሱስም፡- ይህን ማድረግ እንድችል ታምናላችሁን? አላቸው፡፡ አዎን÷ ጌታ ሆይ አሉት፡፡ በዚያን ጊዜ፡- እንደ እምነታችሁ ይሁንላችሁ ብሎ ዓይኖቻቸውን ዳሰሰ፡፡ ዓይኖቻቸውም ተከፈቱ፡፡ ኢየሱስም፡- ማንም እንዳያውቅ ተጠንቀቁ ብሎ በብርቱ አዘዛቸው፡፡ እነርሱ ግን ወጥተው በዚያ አገር ሁሉ ስለ እርሱ አወሩ” /ማቴ. 9÷ 27-31/፡፡
ለእነዚህ ሁለት ዕውሮች የተደረገው ትልቅ ተአምር ነው፡፡ ጌታ ግን በዚህ ተአምር ውስጥ የሚከብረው በዝምታ ነው፡፡ መዳናቸውን በመጀመሪያ ራሳቸው እንዲያጣጥሙት ነገራቸው፡፡ የሰው ባሕርይ ግን ተናገር ሲባል ዱዳ የሚሆን ዝም በል ሲባል ደግሞ የሚናገር ነው፡፡ ዓይኖቻቸው ቢድኑም ጆሮአቸው ግን ይቀረው ነበር፡፡ የጌታን ቃል አልሰሙምና፡፡ ቃሉ፡- “አወሩ” ይላል፡፡ ጌታ ካላዘዘን አወሩ እንጂ መሰከሩ አንባልም፡፡
ጌታችን ብዙ ተአምራቶችን ካደረገ በኋላ እንዳይናገሩ ያዝዝ ነበር፡- ይህን ያደረገው ለምንድነው? ስንል፡-
1. እንዲያጣጥሙት ነው፡- ለሌሎች ለመንገር የሚችኩሉ ለራሳቸው ግን ያልገባቸው ብዙ ሰዎች አሉ፡፡ ሲናገሩም፡- “እኛ አሸንዳ ነን” ይላሉ፡፡ አሸንዳ ግን ውኃው ያልፍበታል እንጂ አያርሰውም፡፡ እኛ ግን የአፈር ቦይ ነን፡፡ የአፈር ቦይ እየራሰ የሚያስተላልፍ ነው፡፡ የረካንበትን ነገር ለሌሎች የምንናገር ነን፡፡ ጌታ አትናገሩ ያለው አስቀድመው እንዲጣጥሙት ነው፡፡ የሰሙትን ነገር በደንብ ሳያስተውሉ ለመናገር የሚሞክሩ አሉ፡፡ ያደነቅነው ሁሉ የገባን ነገር አይደለም፡፡
2. ያለጊዜው መከራ እንዳይቀበሉ፡- የመከራ ዓላማው እኛን ማጽናት ነው፡፡ ለማጽናት ደግሞ መተከል ያስፈልጋል፡፡ በጌታ ፍቅር እንተከላለን፣ በመከራ ደግሞ እናድጋለን፡፡ የመከራው ዓላማ ወርቅነታችን ከተራ አፈር እንዲለይ አንጥሮ የሚያወጣ ነው እንጂ ማጥፊያ አይደለም፡፡ ከተራ ማንነትና አስተሳሰብ ወደ ተመደበልን ከፍታ የምንወጣው በመከራ መንገድ ነው፡፡ መከራ ከሚመጣበት መንገድ አንዱ ስለ ክርስቶስ አዳኝነት መናገር ነው፡፡ ያበሰሉ ሰዎች መከራውን እንደ አደጋ ቆጥረው ሊደነግጡ፣ ሊሸሹ ይችላሉ፡፡ ምስክርነት የሚያስከፍለው ዋጋ አለ፡፡ ምስክርነትን ከነዋጋው የሚይዙበት ደረጃ ላይ እስኪደርሱ አትናገሩ አላቸው፡፡
3. መስቀሉን እንዳያፈጥኑበት፡- ጌታችን በአባቱ ጊዜ ለመሞት ይጠነቀቅ ነበር፡፡ አንዳንድ ምስክርነቶች በእርሱ ላይ መስቀልን ያበዛሉ፡፡ ሞቱን ያፋጥናሉ፡፡ የሚሄድበት መንገድ ላይ የተሰናዳ እሾህ ያስቀምጣሉ፡፡ ስለዚህ ጌታችን እስከ ጊዜው አትናገሩ አለ፡፡
ዛሬም የክርስቶስን ማንነት ልንመሰክር ይገባናል፡፡ ታሪኩ ጥሞን ብቻ ሳይሆን የመሥዋዕትነቱ ፍቅር፣ የትንሣኤው ብርታት ማርኮን ልንናገር ይገባናል፡፡ እንዴት እንደምንናገር ማሰብ አለብን፡፡ ደቀ መዛሙርቱ ዝም በሉ ተባሉ፣ ጌታ ከሞት እስኪነሣ (ማቴ 17÷9)፡፡ እንደ ገና ተናገሩ ተባሉ (ማር 16÷15)፡፡ እነርሱም ከዚህ በኋላ ዝም ማለት እንደማይችሉ ተናገሩ (የሐዋ 4÷20)፡፡ በንግግር ችሎታ ብቻ፣ በመግለጽ ብቃትም ወንጌል አይሰበክም፡፡ ከመንፈስ ቅዱስ ኃይል ጋር የምንናገረው ነው፡፡ እኛ ስንናገር እርሱ ካላጸና ከንቱ ድካም፣ ፃማ ከናፍር (የከንፈር ድካም) ብቻ ነው፡፡ መንፈስ ቅዱስ ከእኛ ጋር የሚሠራው ደግሞ በጽሞናና በጸሎት መቆየትን ስንለማመድ ነው (ሉቃ 24÷49)፡፡
የክርስትናውን ዜና ገና እየሰሙ ያሉ ከሌሎች ጋር ሊከራከሩ፣ ሳይጠነክሩም ባልንጀሮቻቸውን ሊሰብኩ አይገባም፡፡ የሚያላምጡትን ምግብ ሳይውጡ መናገር እንደሌለ ሳያጣጥሙም ሐዋርያዊ ተልዕኮ ሊደረግ አይገባም፡፡ ስለዚህ ለቤተ ክርስቲያንና ለምሥጢሩ እንግዳ የሆናችሁ የሃይማኖት አባቶቻችሁ አትናገሩ ሲሉአችሁ የጌታን ቃል ይዘው ደግሞም እስከ ጊዜው ነውና ደስ ይበላችሁ፡፡ የሞላ ነገር በግድ ይፈሳል፡፡ ዛሬ ተሞሉ፣ ነገ ትፈስሳላችሁ!!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር