“በተጠራችሁበት መጠራታችሁ እንደሚገባ ትመላለሱ ዘንድ እለምናችኋለሁ፤” ኤፌ. 4፡1 ።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እለምናችኋለሁ” በሚለው ንግግሩ የሚገልጣቸው አራት ነገሮች አሉ ። የራሱን ትሑት ሰብእና ፣ የሰዎችን ነጻ ፈቃድ ፣ የንግግር ጥበብን ፣ የወንጌል ጠባይን ይገልጣል ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እጅግ ትሑት ነበረ ። ትሕትናውን በማየት በዚህ ዘመን ያለነው ክርስቲያኖች ራሳችንን መመዘን እንችላለን ። ቅዱስ ጳውሎስ የክርስቶስ ባሪያ ነኝ ይላል ፣ እኛ ደግሞ የንጉሥ ልጆች ነን እንላለን ። እርሱ ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል ? ይላል ፣ እኛ ደግሞ እምቅ ኃይል አለኝ እንላለን ። እርሱ ድንኳን እየሰፋ ለድሆች ይሰጥ ነበር ፣ እኛ ድንኳን ከሚሰፉት እንዘርፋለን ። እርሱ ደመወዙን ትቷል ፣ እኛ ስለ ቦነስ እንጣላለን ። እርሱ በድንግልና ሕይወት ኖሯል ፣ እኛ በአንድ መርጋት አቅቶናል ። እርሱ ስለ ምእመናን መጽናት ምጥ ይዞታል ፣ እኛ ስለምናገኘው ጥቅም አሳብ ይዞናል ። እርሱ ጸልዩልኝ ይላል ፣ እኛ ሁሉን ጨብጫለሁ ብለን እናስባለን ። እርሱ በሰንሰለቱ ይኮራል ፣ እኛ በወርቅ ቀለበት እንደሰታለን ። እርሱ እለምናችኋለሁ ይላል ፣ እኛ ደግሞ “እነግርሃለሁ ስማ” እንላለን ። ጸጋ እንዳለን ምልክቱ ፣ ጸጋ ካነሰንም እንዲበዛልን መስፈርቱ ትሕትና ነው ። ሐዋርያው እስረኛ ነውና ብስጩ ቢሆን ያምርበታል ፣ እርሱ ግን በትሕትና “እለምናችኋለሁ” ይላል ።
“እለምናችኋለሁ” የሚለው ንግግሩ የሰዎችን ነጻ ፈቃድ ያከብራል ። ሰው እንደ ኮምፒዩተር ፕሮግራም የሚጫንበት ፍጡር አይደለም ። ነጻ ፈቃድን ስናከብር ለሰው ነጻ ፈቃድ የሰጠውን እግዚአብሔር እየሰበክን ነው ። ነጻ ፈቃድን ማወቅ የሰዎችን ክብር እንድንጠብቅ ያደርገናል ። በእልህና በቍጣ ፣ ሌሎች የሚያምኑትን በመንቀፍ ሳይሆን በማዳን ስሜት እንድንናገር ያደርገናል ። በሰው ሃይማኖትና አስተሳሰብ ዘው እያልን መግባት ፣ የእኔ ትክክል ነው ለማለት እገሌ ተሳስቷል ብሎ መጀመር ነጻ ፈቃድን አለማወቅ ነው ። የሰው ቍጣ የእግዚአብሔርን ጽድቅ እንደማይሠራ ዘንግተን በእልህ እየተንጨረጨሩ መስበክ አላዋቂነት ነው ። ሰውን እስከ ዛሬ ያመንከው ዋጋ የለውም በማለት እናስቆጣው ይሆናል እንጂ አናለዝበውም ። የምታምነው ምንድነው ? ብሎ እስኪጠይቀን ሕይወታችን ካልገዛው ቃላችን አይገዛውም ። “እለምናችኋለሁ” የሚለው የሐዋርያው የተለመደ ንግግሩ ነው ። ምን ያህል ከሐዋርያት የስብከት ዘዴ እንደ ወጣን ይህ ክፍል ይነግረናል ።
“እለምናችኋለሁ” በማለቱ የንግግር ጥበብን እያሳየን ነው ። ንግግር ሰዎችን ባለ ድርሻና ተሳታፊ ሲያደርግ ተቀባይነት ያገኛል ፣ ተቃውሞን ያርቃል ። የሚለምንን ሰው የሚሳደብ ማንም የለም ። መለመን መለማመጥ አይደለም ፣ በእግዚአብሔር ስም የሰውን ልብ ማራራት ነው ። ሰው ካልታመመ በቀር ምግብ እንቢ አይለውም ፣ ምግብ እንቢ ያለውን ሰው በጉርሻ ሳይሆን በማንኪያ ፣ በቍጣ ሳይሆን በመለመን ይመግቡታል ። አሊያ ወደ ሞት ይሄዳል ። ክርስቶስ መድኃኒት ነው የምትል ወንጌልም በማዘን መንፈስ መሰበክ አለባት ። የለዘበች ምላስ ቍጣን ማብረድ ትችላለች ፣ አለቃንም ትማርካለች ። “ካነጋገር ይፈረዳል ፣ ካያያዝ ይቀደዳል” እንዲሉ ። ንግግር በተፈጥሮ የምንካነው ብቻ ሳይሆን ልምምድና ትምህርት የሚፈልግ ነው ። ያልቦካ ጭቃ እየለጠፉ ለጽድቅ ቀንቼ ነው ብሎ መቀባባት ተገቢ አይደለም ። በኃይል ንግግርም አሳምናለሁ ብሎ ማሰብ መጠላትን እንጂ መወደድን አያተርፍም ። ሁሉም ሰው የራሱን ጥቅም ሊለቅ ይችላል ፣ የራሱን ክብር የሚለቅ ግን በጥቂት እንኳ ላይገኝ ይችላል ። ደረቅ ንግግር ይሰብራል ፣ የሚልመጠመጥም መልእክቱን የግሉ ያደርገዋል ። በጥበብ የለዘበ ንግግር ለአንድ ልከኛ አገልጋይ አስፈላጊው ነው ።
“እለምናችኋለሁ” የሚለው ንግግር የወንጌልን ጠባይ ይገልጣል ። ወንጌል የምሥራች ናት ። የምሥራች አያሸብርም ። የምሥራች ብለን ስንናገር ሰዎች የሚሰጡት መልስ “ምስር ብላ” የሚል ነው ። ዝም ስንል “ምንድነው ንገረኝ?” ይሉናል ። ወንጌልን እስከዚህ ድረስ የደስታ መልእክት ማድረግ ይገባናል ። ወንጌሉና ወንጌላችን ይለያያል ። ወንጌል ከጌታችን ጽንሰት እስከ ዕርገቱ ያለው ዜና ክርስቶስ ነው ። ከዚህ የወጣ ስድብ ፣ ዘራፍና ፉከራ ወንጌል አይደለም ። ወንጌል የማንንም ክብር ነክቶ አያውቅም ። እንደውም ክብር ለሚገባው ክብር ስጡ ይላል ። ሽቅብ ተንጠራርቶም ከቅዱሳን ጋር እኩል ነኝ ፣ እኔ ከመልአክ እበልጣለሁ አይልም ። ከሁሉ የማንስ ነኝ የሚል ነው ።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “እለምናችኋለሁ” በማለቱ ታላቅ አባት መሆኑን ገለጠ ። ሸለቆ ውስጥ የወደቀ ሰው ልታደግህ ተብሎ አይለመንም ። እርሱ ራሱ አውጡኝ እያለ ይለምናል ። ሐዋርያው ግን “እለምናችኋለሁ” በማለት ሳያበሩ እንዳይሞቱ ይማጸናል ። “ብርሃን ናችሁ” ተብለዋልና ። ብርሃን የማዕረግ ስም ሳይሆን የተግባር ስም ነው ። ወንበሩን ይዘው ሥራ ሳይሠሩበት እንዳያልፉ እየተማጸናቸው ነው ። ዕድልና ጊዜ እኩል ገጥመው አይገኙምና እባካችሁ ተጠቀሙበት እያለ ነው ። ምንም ከሌለው ሰው ይልቅ እያለው የማይጠቀምና የማይጠቅም ያሳዝናል ።
ንግግራችን እልህ ያለበት ከሆነ የበለጠ እልኸኛ እናመርታለንና ዝም እንበል ።
ንግግራችን ጥበብ የሌለው ከሆነ ሰውን እናስከፋለንና ዝም እንበል ።
ንግግራችን የሰውን ነጻ ፈቃድ የማያከብር ከሆነ ሰውን እንደ ዕቃ ቆጥረነዋልና ዝም እንበል ።
ንግግራችን ወንጌሉን ሳይሆን ወንጌላችንን የሚያወራ ከሆነ ከእኛ የበለጠ ዓመፀኛ ያፈራልና ዝም እንበል ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 11 ቀን 2013 ዓ.ም