መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » የዕለት መና » ለምስጋና ተመለሱ

የትምህርቱ ርዕስ | ለምስጋና ተመለሱ

“ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን ? ዘጠኙስ ወዴት አሉ ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ ።” ሉቃ. 17፡17-18 ።
አንዲት እናት በጣም ችግረኛ ናቸው ። አንድ ቀንም እንጀራ ያስፈልጋቸዋል ብሎ ቁራሽ የሰጣቸው ሰው የለም ። እርሳቸው የባሰባቸው ቢሆኑም ከእርሳቸው የተሻሉ ድሆች ሲረዱ ያያሉ ። ቢሆንም የቀድሞ ጥሩ ኑሮአቸው እንቅፋት ሁኖባቸው መለመን አፍረው ተቀምጠዋል ። ታዲያ አንድ ቀን የአጥሩ ኮሽም ፣ እሾህ ያላቸው አበቦች ተቆርጠው ሳለ ለእኒያ ድሀ ውሰዱላቸው ተባለ ። አሳቡ አድርቀው ማገዶ ያደርጉታል ተብሎ ነው ። እሾሁ ግን አላስደርስ ብሏቸው እጃቸውን ደም በደም አደረገው ። እርሳቸውም በቤታቸው ደጃፍ ላይ ተከምሮ ያዩታል ። በዚህ ጊዜ “በእሾሁ እንዳስታወሳችሁኝ በእንጀራውም አስታውሱኝ” ብለው መልእክት ላኩ ። ይህ በእኔ ላይ የደረሰ ታሪክ ነው ። ይህ ንግግራቸው ሕመም ሁኖ ለረጅም ጊዜ በውስጤ ቆየ ። አሁን ግን እርሳቸውም እየተረዱ በመሆናቸው ደስ ይለኛል ።
በእሾሁ እያስታወሱ በእንጀራው አለማስታወስ የሚገርም ነው ። ለማገዶው ያሰብንለት ሰው የሚጋግረው ግን የሌለው መሆኑ በጣም የሚያስደንቅ ነው ። ከእሳቱ ዱቄቱ ይቀድማል ። ዱቄት በሌለበት ማገዶ ምንም አይጠቅምም ። አብዛኛዎቻችን እግዚአብሔርን የምናስታውሰው በእሾሁ ነው ። ስንወጋ ፣ ስንደማ ፣ ስንቆስል እናስበዋለን ። ጸልዩልኝ ብለን እንማጸናለን ። በእንጀራው ግን አናስበውም ። እግዚአብሔርን እሾህ ጎታች ፣ ዓለምን ግን የእንጀራ ወዳጅ አድርገናልና ሊያመን ያስፈልጋል ። ትላንት ራሳቸውን ሊያጠፉ ብለው ቤተ ክርስቲያን የመጡ ሰዎች ያ ጭንቀት ሲያልፍ አገልጋዮቹን በገመድ ካላነቅን ብለው ሲጋበዙ አይተናል ። ትላንት በመራራ ሕይወት ሁሉም ነገር ጨልሞባቸው የነበሩ ያ ቀን ሲያልፍ በእግዚአብሔር ቤት ደጃፍ ለማለፍ እንኳ ተጸይፈዋል ። ትላንት እግዚአብሔርን ብቻ ፈልገው ከዚህ ጉድ ልውጣ ይሉ የነበሩ ዛሬ ሰዎችን እያየን ተሰናከልን ይላሉ ። ሊሄድ ያሰበ ሰበቡ ብዙ ነው ። ለምስጋና ከተመለሰ ቀምቶ የሮጠ ይበዛል ። የዛሬው እርካታ የሁልጊዜ አይሆንምና አሁንም በሌላ እሾህ እግዚአብሔርን ማስታወስ አይቀርም ። እርሱ ግን ማንንም ሳይታዘብ ይቀበላል ።
የለምጽ በሽታ እንደ ዛሬው ያለ የቆዳ በሽታ አልነበረም ። የመጀመሪያ ተላላፊ በሽታ ነው ። ሁለተኛ ከርኩሰት ጋር የተያያዘ ነው ። ለምጽ ያለበት ሰው በካህኑ አዋጅ ራሱን ከሕዝቡ ለይቶ በምድረ በዳ ይኖራል ። ከተፈወሰ ሲመለስ ፣ ካልተፈወሰ በዚያው ይሞታል ። የሚወዳቸው ቤተሰቦቹም ቤዛ ሊሆኑለት አይችሉም ። “ርኩስ ነኝ” ብሎ በራሱ ላይ ያውጃል ፣ ሰው ከቀረበውም እየሮጠ ይሸሻል ። ከባድ ጭንቅ ነው ። ጌታችን በሰማርያ ሲያልፍ አሥር ለምጻሞችን በምድረ በዳ አገኘ ። እነዚህ ለምጻሞች ያገናኛቸው ኑሮ ሳይሆን ችግር ፣ ከተማ ሳይሆን ምድረ በዳ ነው ። ሐኪም ቤትና ጠበል ደግሞም ስደት ያፋቅራል ። ችግሩ ያ ሲያልፍ መረሳሳት ይመጣ ይሆናል ። የችግር ቦታዎች ጥላቻና ራስ ወዳድነት የሚገረዝባቸው የግርዛት ኮረብታዎች ናቸው ። ጌታችንን ባገኙት ጊዜ አልሮጡም ፣ እንደውም እየጮኹ ቀረቡት ። እርሱ የሚያነጻ ነውና ርኩሶችን አይሸሽም ። የሰው ቅድስና ግን ከራሱ አልተርፍ ስትል መሸሽ ይጀምራል ። “ኢየሱስ ሆይ አቤቱ ማረን አሉት ። ማረን ቢበድሉም ባይበድሉም ትልቅና የመጨረሻ ጸሎት ነው ። ቢታመሙም ባይታመሙም ሐኪም ጋ መሄድ መልካም ነው ። ስለ መፈወስ ቢለምኑ አንድ ልመና ነው ። እርሱ ከማራቸው ግን ሁሉም ጸጋ የእነርሱ ነው ። ማረኝ የጸሎት አባ ጠቅል ነው ። ምሕረት ያለውን ጌታ ማረኝ አሉት ። ማረኝ የሚባልም እርሱ ብቻ ነው ። ሰው ይቅር ይላል ፣ መማር ግን የአንድ አምላክ ግብር ነው ። ሰው ይተዉልናል ፣ እግዚአብሔር ግን እንዳልበደለ አድርጎ ይቀበለናል ።
ጌታችን “ራሳችሁን ለካህን አሳዩ” አላቸው ። ለምጻም ናችሁ ብሎ ያረጋገጠውና በአዋጅ የለያቸው ካህኑ ነውና የሚመልሳቸውም ካህኑ ነው ። ፈውሱን ጌታ አደረገና አዋጁን ግን ለባለሥልጣኑ ካህን ተወለት ። እግዚአብሔር ራሱ የሠራውን ሥርዓት ራሱ አያፈርስም ። “እነሆም ሲሄዱ ነጹ” ይላል ። በጣም ድንቅ ነገር ነው ። ከእነርሱም አንዱ እንደ ተፈወሰ ባየ ጊዜ ጌታችንን ሊያመሰግን ወደ ኋላ ተመለሰ ። ሌሎቹ ግን ቤተሰቦቻቸውንና የተለዩትን መንደር ለማግኘት ገሰገሱ ። አንገታቸው ወደፊት እንጂ ወደኋላ ዞር ብሎ የሚያይ አልነበረም ። ይህ አንዱ ሰው በጌታ እግር ላይ ወድቆ ማመስገን ጀመረ ። ያ ሰው ግን የተናቀ ሳምራዊ ነበረ ። ከተናቀው ሰው የከበረ ምስጋናና ውለታ አክባሪነት ወጣ ። በማይጠበቅ ቦታ የማይጠበቅ ግብር ይገኛል ። ዝናብ የሌላቸው ደመናዎች ብዙ አሉ ፣ ይህ ሰው ግን በቀትር የዘነበ ምስጋና አለው ። ድብልቅ ከሚባል ሕዝብ የጠራ ምስጋና ወጣ ። ወገኑ ሳምራዊ ሳለ እንዴት አብሯቸው ከረመ ብንል የከፋ ችግር የሚያንሰውን ዘረኝነት አስረስቷቸው ነው ። በዘረኝነት የሰከሩ የባሰ ችግር ሲመጣ ይረሱታል ። “እዬዬ ሲዳላ ነው” ይባላል ። ሰው በጦርነት መሐል ልቅሶ አይቀመጥም ። ተደላድሎ ሲቀመጥ ግን ስለሞተው ወንድሙ ማልቀስ ይጀምራል ። ካልበሉ እንባም አይመጣም ።
“ኢየሱስም መልሶ፦ አሥሩ አልነጹምን ? ዘጠኙስ ወዴት አሉ ? ከዚህ ከልዩ ወገን በቀር እግዚአብሔርን ሊያከብሩ የተመለሱ አልተገኙም አለ ።” ለምስጋና የሚመለስ ከአሥር አንድ መሆኑ ይገርማል ። ዘጠኙ ተፈውሰዋል ውለታው የነካው ግን አንዱ ነው ። ዛሬም ከአሥሩ አንዱ ብቻ ለምስጋና ይመለሳል ። እነዚያ ዘጠኙ የገሰገሱት ግን ወደሚያልፉት ወዳጆቻቸው ነው ።ደግሞም ርኩስ ብላ ወደ ገፋቻቸው ዓለም ነው ። ዛሬም ሰዎች ሲፈወሱ ወዳወገዘቻቸው ዓለም ይመለሳሉ ። ለምስጋና የሚመለሱ ጥቂቶች ናቸው ። የሚበዛው የምስጋና ዕዳ ያለበት ነው ። ወዳጆቼ ትልቁ በደል የእግዚአብሔርን ውለታ መርሳት ነው ።
መቃብራችሁ የተደፈነላችሁ ፣ ከጫካ ሕይወት ወጥታችሁ ከሰው ቊጥር የተደመራችሁ ፣ የክረምትን ያህል በእንባ የታጠባችሁ ፣ ከሩቅ አገር ወደ ክርስቶስ የመጣችሁ ፣ … ለምስጋና ተመለሱ ። ፈውስም ማግኘትም ዘላለማዊ አይደሉም ። ዘላለማዊ እግዚአብሔር ብቻ ነው ።
እግዚአብሔር ጌታዬ ሆይ አመሰግንሃለሁ ። ለጸሎት ብዙ ቃል አለኝ ለምስጋና ግን ምንም ቃል የለኝም ። እያደረግህልኝ የምታደርግልኝ ሌላ ነገር ይታየኛል ። ለምስጋና ቆም እንድል እባክህ እርዳኝ ። ለማያጠግብ እንጀራ ስንት ዘመን መለስ ቀለስ አልኩኝ ። ላይሞላ ኑሮ ጀርባዬን ሰጠሁህ ። በበረከትህ ተመዝኜ እንዳልወድቅ እባክህ እርዳኝ ። ሌላውስ አጥቶ ካደህ ፣ እኔ አግኝቼ እንዳልክድህ ፣ እግዚአብሔር ማነው ? እንዳልልህ ልቡናዬን ጠብቅልኝ ። ፈጥሮ በማይጥለው አባትነትህ ለዘላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና 12
ግንቦት 11 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ ተጻፈ አዲስ አበባ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ