መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ለአንተም ያስፈልግሃል

የትምህርቱ ርዕስ | ለአንተም ያስፈልግሃል

ብትሠራ ነው የበላሁት፣ ብትለፋ ነው ያገኘሁት ፤ ላንተም የሚደክምልህ ያስፈልግሃል ፤ ላንተም ለደጉ ደግ  ያሻሃል። ለአባቱ አባት ያስፈልግሃል። አባ መስጠት ላንተም እጅ ሊፈታልህ፣ አባ መላ ምነው ከፋህ ? ሊሉህ ይገባሃል። የሰውን ልጅ ሁሉ ልጄ ትላለህ እንጂ አታልፋቸውም፣ ላንተም ልጆች ወገን ማግኘት ይገባቸዋል። የሰውን ትዳር በምክርህ አቁመሃል ፣ ያንተም ትዳር ሲናጋ ምክር ያስፈልግሃል። ሸክላ ሠሪ በገል ይበላል ሆኖ ለሌላው መፍትሔ ስትሆን አንተ ግራ ገብቶሃል።

ሐኪም ለራሱ አያውቅምና ስንቱን ስትጠግን፣ ለአንተ ቍስል ማጠቢያ ወይን ፣ ማለዘቢና ዘይት ጠፍቷል ። አባት እናትህን ጦረሃል ፣ ላንተም ማረፍ  ይገባሃል። ባለ ታሪኮችን አስታውሰሃል፣ አንተም እውቅና ይገባሃል። ለልጅህ ፣ ለትዳርህ ፣ ለአገርህ ክብር ዘምተሃል፣ አንተ ስትመጣ ወንበር ሊለቁልህ ይገባሃል።

የዛሬው ባርኔጣ የትላንት አፍሮ ፀጉር ነበረበት። የዛሬው የሚንቀጠቀጥ እጅ ዓለት አገላባጭ ነበረ፣ የዛሬው ምርኩዝ የትላንቱን ሯጭ ደግፎታል። መልክህ ለራስህ ጠፎቶሃል፣ የትላንቱን አንተነትህን ሊያስታውሱህ ይገባሃል። እጆችህ ዘርዛራ እንጂ ድፍን አይደሉም፣ አንድ ለጠየቀህ አሥር ትሰጥ ነበር፣ አለሁ መባል በእውነት ይገባሃል።

ዛሬ መንገድ ቢጠፋህ ስንቱን ሰው መንገድ አሳይተሃል። የማያውቁህ ሕፃናት ቢሰድቡህ፣ የትላንት የመኳንንት አማካሪ ነበርህ። ከቢጤዬ ጋር  ልዋል ያላልህ ፣ ሁሉ በዓይንህ ፊት እኩል ነበረ፣ ብድርን ከሰው ሳትጠብቅ የተገፋን ትደግፍ ነበር፣ ላንተ ውለታ ምላሽ ባይሆንም ወንድም ጋሻ መባል ይገባሃል። ለስንቱ መልክ ለመስጠት መልክ ያጣኸው ፣ ብዙዎች እንዲፈወሱ እንደ ጌታህ የቆሰልኸው፣ ስም እንዲያገኙ ስምህ የጠፋው አንተ አገልጋዩ ክብር ይገባሃል።

ዱዳ በሚያደርግ ባሕል ዝም ብለሽ የኖርሽው፣ መታፈን ጨዋነት ነው የተባልሽው፣ ልጆችሽን ለማስፈታት ታስረሽ ያሳለፍሽው ፣ ያልተዘመረልሽ የጓዳ ጀግና አንቺ ሆይ አድናቆት ይገባሻል።

የተራራቀውን ያቀራረባችሁ፣ የሰው መለያየት ያስጨነቃችሁ ሽማግሌነታችሁ ያልተከበረላችሁ ፣ በነጻ ይህን ሁሉ ምክር የሰጣችሁ እናንተ አዋቂዎች ክብር ይገባችኋል ።

ለዝምታችሁ ሌላ ጭነት የተጫነባችሁ፣ ምንም ብትሠሩ አመስጋኝ ያጣችሁ ፣ የዘመድ ተጋፊ ስፍራ ያሳጣችሁ፣ በወገን መካከል ብቸኛ የሆናችሁ እናንተ ግፉአን ክብር ይገባችኋል።

ለእኔ ማወቅ የቀለጣችሁ መቅረዝ መምህራን፣
እኔን ለማብላት የተራባችሁ መናኝ ሊቃውንት ፣
እኔን ለመጠበቅ ዘብ የቆማችሁ የጸሎት ሠራዊት ፣
እኔን ለመጠየቅ የለፋችሁ ባለ አደራ ካህናት ፣
ለእናቴ ልጅ የደበቅሁትን ንስሐ ለሰማችሁኝ  ላዕካነ  ወንጌል ( የወንጌል መልእክተኞች) ክብር ይገባችኋል::

አቤቱ ለእኛ መልካም የሆኑትን ፣ ሠናይ ያደረጉትን አትርሳ!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 20 ቀን 2017 ዓ.ም .

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ