የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለእኔም አናግርልኝ

 “ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ምንድር ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ” ዘካ. 4፡7
የይሁዳና የብንያም ነገድ ከክርስቶስ ልደት በፊት በ586 ዓመት ወደ ባቢሎን ተማርከው ነበር ። በባቢሎንም ከተወለዱት ልጆች አንዱ ዘሩባቤል ነው ። ዘሩባቤል ማለትም የባቢሎን ዘር ማለት ነው ። ይህ ዘሩባቤል የዳዊት ዘር ሲሆን በክርስቶስ የዘር ሐረግም ውስጥም የተጠቀሰ ነው ። ማቴ. 1፡12 ። ታላቅ ክብር የነበረው የሰሎሞን መቅደስ በባቢሎናውያን ፈርሷል ። ሁለተኛው መቅደስ የተሠራው የሕዝቡ አለቃ በነበረው በዘሩባቤል ነው ። ይህንንም መቅደስ ሲሠራ በኃይሉ ሳይሆን በእግዚአብሔር መንፈስ እንደሆነ ተመስክሮለታል ። የእግዚአብሔር ሥራ ያለ እግዚአብሔር መንፈስ አይሠራምና ። ዘሩባቤል መቅደሱን የሠራው ብቻውን አልነበረም ። ካህኑ ዕዝራ ሕግን በማስተማር ፣ ነቢዩ ሐጌ ሕዝቡን በመቀስቀስ ፣ ነቢዩ ዘካርያስ የእግዚአብሔርን መልእክት በማምጣት ይሳተፉ ነበር ። ዘሩባቤልም ጠቢባንን ይዞ ከመሠረት እስከ ጉልላት ያለውን በልዩ ሙያ ያሳንጽ ነበር ።
የእግዚአብሔርን ቤት ለመሥራት ሰባኪ ፣ አስተማሪና  መንገድ መሪ ነበሩ ። ሐጌ ሰባኪ ነበረ ፣ ካህኑ ዕዝራ አስተማሪ ነበረ ፣ ነቢዩ ዘካርያስ እንደ እረኛ መሪ ነበር ። በአዲስ ኪዳንም ለቤተ ክርስቲያን ሕንጸት የተሰጡ አምስት ክፍሎች አሉ ። ሐዋርያነት ፣ ነቢይነት ፣ ወንጌላዊነት ፣ አስተማሪነትና እረኝነት ናቸው ። ኤፌ. 4፡11 ። ሐዋርያትና ነቢያት መሠረት ናቸው ። ኤፌ. 2፡20 ። መሠረት ሁልጊዜ አይሠራም ፣ አንድ ጊዜ የሚሠራ ነውና ሐዋርያትና ነቢያት ሥራቸውን ፈጽመዋል ። ሕንፃው የሚያድገው በሦስቱ ጸጋዎች ነው ። በወንጌላውያን ወይም በሰባክያን ፣ በአስተማሪዎችና በእረኞች ነው ። ሰባክያን ያነቃቃሉ ፣ በሩቅ ያለውን ይጠራሉ ፣ አስተማሩዎችም የቀረበውን በእውቀት ያንጻሉ ፣ እረኞች ደግሞ የታነጸውን ይከታተላሉ ፣ ያሰማራሉ ። ዘሩባቤል ሁለተኛውን መቅደስ ሲሠራ እነዚህ የሕንጸት ሠራተኞች ነበሩ ። የአዲስ ኪዳን መንፈሳዊ መቅደስ ሲሠራም እነዚህ ሠራተኞች ይኖራሉ ። የዘሩባቤል መቅደስ ለአምስት መቶ ዓመታት ያህል አገልግሎ በ70 ዓ.ም በሮማውያን ፈርሷል ። እስከ አሁንም የመቅደሱ አንድ ግድግዳ እንደ ቆመ ቀርቷል እንጂ ሦስተኛው መቅደስ አልተሠራም ። የአዲስ ኪዳን መቅደስ የሆነው የሰው ልጅ ግን የማይፈርስ መቅደስ ነው ። የተመሠረተው በክርስቶስ ደም ሲሆን በመንፈስ ቅዱስም ወደ ፍጻሜ የሚሄድ በዘመናትና በታሪክ ውስጥ እየተሠራ ያለ ፣ ለዘላለም እግዚአብሔር የሚያድርበት የምእመናን አንድነት ነው ። ከሰሎሞን መቅደስ ይልቅ የሁለተኛው ቤተ መቅደስ ክብር እንደ በለጠ /ሐጌ. 2፡9/ ከዘሩባቤልም መቅደስም የአዲስ ኪዳን መቅደስ ክብሩ ይበልጣል ።
ዘሩባቤል መቅደሱን ሲሠራ ብዙ ፈታኝ ነገሮች ገጥመውታል ። ሥራውን እንዳያቆምም የእግዚአብሔር ቃል መጥቶለታል፡- “ታላቅ ተራራ ሆይ፥ አንተ ምንድር ነህ? በዘሩባቤል ፊት ደልዳላ ሜዳ ትሆናለህ” በማለት አጽናንቶታል   ። ዘሩባቤል በፊቱ የቆመ ትልቅ ተራራ ነበር ። በዚህ ተራራ ፊትም መናገር የቻለ አይመስልም ። አንዳንድ እንቅፋቶች ቋንቋም ያስጠፋሉ ፣ ፍጹም ዲዳ ያደርጋሉ ። ስለዚህ እግዚአብሔር ተራራውን ተናገረው ። ሦስት ወገኖችን እናያለን ። እግዚአብሔር ፣ ዘሩባቤልና ተራራው ። ተራራው ዘሩባቤልን ዝም አሰኝቶታል ። ምክንያቱም በእግዚአብሔር ሥራ ውስጥ የሚመጡ ፈተናዎች ከራሳቸው የእግዚአብሔር ሰዎች ነን ከሚሉ ነውና ለመናገርም ያሳፍራል ። እግዚአብሔርም የተከዘውን ዘሩባቤልን አላናገረውም ። ለዘሩባቤል አንደበት ሁኖ ተራራውን አናገረው ። ተራራው ጆሮ ያለው ባይመስልም እግዚአብሔር ሲናገር ግን ድንጋይም ያደምጣል ።
ተራራ እንኳን ወጥተውት አይተውት የሚያደክም ነው ። ተራራ ትልቅ ችግር መሆኑን ጌታችን ተናግሯል ፡- የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ፥ ይህን ተራራ። ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት ያልፋል፤ የሚሳናችሁም ነገር የለም።” ማቴ. 17፡20 ። በጌታችን አገላለጽ በትንሽ እምነት ፊት ትልቅ ችግር መቆም አይችልም ። ዘሩባቤል ሲወጣው ብቻ ሳይሆን ሲያስበው ያደከመው ተራራ አለ ። አንዳንድ ተራራዎች የሰማይ ጎረቤት ናቸው ። ሰማይን እየቧጠጡ የቆሙ ይመስላሉ ፣ አንዳንድ ችግርም እግዚአብሔር የተወን እስኪመስለን ድረስ የሚያስደነግጥ ነው ። ተራራ ጫካ ሊኖረው ይችላል ፣ ስለዚህ ጨለማ ነው ። ችግርም ቀጣዩን እንዳናይ እንቅፋት ይሆናል ፣ በዚህ ምክንያት ተስፋ መቁረጥ ይመጣል ። ተራራ የአራዊት መፈንጫ ነው ፣ ችግርም ክፉዎች በላያችን ላይ እንዲሳለቁብን የሚያደርግ ነው ።
ዘሩባቤል በገጠመው ነገር ዝም አለ ። እግዚአብሔር ግን አንደበት ሆነለት ።ዘሩባቤልን አይዞህ አላለውም ፣ ተራራውን ንዶ ደልዳላ ሜዳ አደረገለት ። ተራራው ጋርዶት የነበረው መስክ ሁሉ ተገለጠለት ። ብዙ ኃይል ያስፈልገኛል ያለው ነገር ወደፊት የሚሮጥበት መሰማሪያ ሆነለት ። ተራራውን እግዚአብሔር ደለደለለት ።
ዛሬም የእግዚአብሔርን ሥራ ለመሥራት ስንነሣ አላሳልፍ የሚል ተራራ ይገጥመናል ። ተራራው ግን መጨረሻችን አይደለም ። መጨረሻችን ሰማይ ነው ። ዘሩባቤል መስፍን ቢሆንም ፈተና ግን አልቀረለትም ። የእግዚአብሔር ሥራ ትግል አለው ። ትግል ከሌለውም ምናልባት የእግዚአብሔርን ሳይሆን የራሳችንንና የሰዎችን አጀንዳ እያስፈጸምን ይሆናል ። ከተራራው ጋር ግብግብ መግጠም ጥቅም የለውም ፤ እግዚአብሔር ተራራውን እንዲያናግረው መጸለይ በቂ ነው ። እኛስ ተራራ የገጠመን ለኑሮ ስንሮጥ ነው ወይም ለእግዚአብሔር ቤት ?
አምላኬ ሆይ በዘመናት ታማኝ ፣ በዓመታትም ያው ነህ ። ይህ ማጽናናትህ ይድረሰኝ ። ስለ ብዙ ፈተና አወራለሁ ፣ ትልቁ ችግሬ አለማመን ነውና አምንህ ዘንድ እርዳኝ ። በአንድ ፊደል ጀምሬ ይህን ሁሉ ቃል የምናገር የትላንቱ ሕፃን የዛሬ ተናጋሪ ነኝ ። ትንሹ ብዙ እንደሚሆን አስተምረኝ ። አንዴት አልፈዋለሁ የምለውን ችግር ደልዳላ ሜዳ አድርግልኝ ። እኔ ስናገር ተራራው ያፈጣል ፣ አንተ ስትናገር ደልዳላ ሜዳ ይሆናል ። የወገኖቼንም ተራራ በቃልህ ናደው ፣ በጥበብህ ደልድለው ፣ በእረኝነትህ መረማመጃ አድርገው ። ዘለላለሙ አሜን ።
የዕለቱ መና/5/
ግንቦት 4 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ ተጻፈ አዲስ አበባ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ