የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለእኔ መልካም ያደረጉትን አትርሳ

ሲገፉህ ፍቅር ላይ እንጂ ጥላቻ ላይ አትውደቅ ፡፡ ወደ ላይ መውጣት ያቃተውን ይገፉታል ፡፡ መገፋት ለዕድገት ነው ፡፡ የገፉህ ታች ሁነው ፣ አንተ ግን ከላይ ትሆናለህ ፡፡ የተገፋ ወተት ቅቤ ይወጣዋል ፣ የተገፋ ዓለት ቤት ይወጣዋል ፣ የተገፋ አፈር ወርቅ ይወጣዋል ፡፡ የተገፋ ሰውም ክብር ይጫንለታል ፡፡ በጎልጎታ ለመነሣት በሩ ቀራንዮ ነው ፡፡ አማራጭ የለም ቀራንዮን ካላዩ ወደ ጲላጦስ አደባባይ መመለስ እንጂ የጎልጎታን ድል ማየት አይቻልም ፡፡ ላንተ የፈሰሰ ቃለ እግዚአብሔር ቤትህን ባርኮ አንተ ግን ሳትባረክ እንዳትቀር እባክህ ተጠንቀቅ ፡፡ በእግዚአብሔር ከብረህ እግዚአብሔርን እንዳትንቅ ደግመህ አስብ ፡፡ ከሙሉ ፍቅር ጎዶሎ ጥላቻ ሊታወስህ አይገባም ፡፡ በሚጠሉህ መሐል የሚወድህን ካገኘኸው የሚጠሉህን እርሳቸው ፡፡ ጤፍን የቆጠረ ፣ ሰማይን የለካ ፣ አሸዋን የደመረ ፣ ውቅያኖስን የሰበሰበ ማንም የለም ፡፡ እግዚአብሔርም ታውቆ የማይጨረስ ነው ፡፡
ንስሐህ የኅሊናን ድምፅ ፀጥ ለማሰኘት ሳይሆን አባትህን ለመታረቅ ይሁን ፡፡ ኃጢአት ስትሠራ ለሰይጣን ተላልፈህ የተሰጠህ መስሎህ ትፈራለህ ፣ ተላልፈህ የተሰጠኸው ግን ለምኞትህ ነውና ምኞትህን ፍራው ፡፡ ስትጸልይ ከራሴ አድነኝ በል ፡፡ ትዕግሥትህን ለካው ፡፡ ሰዎች ሲናገሩ ስንት ደቂቃ መስማት ትችላለህ ? መጓጓዣው እስኪመጣ በደስታ እስከ ስንት ደቂቃ ትጠብቃለህ ? የትራፊክ መብራት እስኪለቅህ ምን ያህል ትረጋጋለህ ? ከአፍህ ይህን ጸሎት አትለየው ፡- “የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ እባክህ ትዕግሥት ስጠኝ፡፡” ትዕግሥት ያስፈለገህ መከራን ብቻ ሳይሆን ጥጋብንም እንድትችል ነው ፡፡
ከራስ ወዳዶች ጋር ስትኖር ተጠንቀቅ ፡፡ ለራሳቸው እንጂ ላንተ ስሜት አይጨነቁምና ፡፡ ራስ ወዳዶች ሁልጊዜ ተበዳይነት ይሰማቸዋል እንጂ እነርሱ እንደሚበድሉ አያስቡም ፡፡ ራስ ወዳዶች ጫካ ይፈልጋሉና ብዙዎቹ የተደበቁት መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ነው ፡፡ በእግዚአብሔር ቤት ያለ ሽፍታን ፣ በዓለም ያለ ባሕታዊን አምላክ ብቻ ይወቀው ፡፡ ፀጥታህ ሌላውን የሚያውክ አይሁን ፡፡ ፍቅርህ አያስጨንቅ ፡፡ ሰላምህ ሌላውን አይረብሽ ፡፡ ኑዛዜህ ሌላውን አይፈትን ፡፡ ግልጽነትህ መራቆት አይሁን ፡፡ ድብቅነትህ ድፍን ቅል አይምሰል ፡፡ መሽቀርቀርህ ጭንቀት የወለደው አይሁን ፡፡ ለባዕድ ካባ ልበስ ፣ ለወዳጅህ ግን ተገለጥ ፡፡ የሌላው መጨቆን ያንተ መሆኑን አስብ ፡፡ እኔ ሳይሆን እኛ በል ፡፡ የሚመክር ወዳጅ ፣ የሚቀጣ አባት ከሌለህ አልቅሰህ እግዚአብሔርን ለምን ፡፡ አገልግሎትህን ሰዎችን አገኝበታለሁ ብለህ አታድርገው ፡፡ በእግዚአብሔር ከረካህ ሌላ አያምርህም ፡፡ የረካን ማርካት አይቻልምና ፡፡ ትንሽ ሱቅ ትልቅ ሙዚቃ ይለቀቅባታል ፡፡ ትንሽ ጉዳይ ትልቅ ጠብ ይታወጅባታል ፡፡ ጉዳዩ ሲያንስ ጠቡ ትልቅ ይሆናልና የሚጮኹ ጠቦችን ናቃቸው ፡፡ መልካም አጋጣሚ ለማታውቀውና ውለታ ለማይመልስ ሰው ዛሬ የምታደርገው ደግነት ነው ፡፡ ሰው መሆን ሰውን ለመደገፍ ነው ፡፡ እያንዳንዱ ሰዓት የብዙ መልካም ተግባሮች አጋጣሚ ነው ፡፡ ባዶ ቤት ይጮኻል ፣ ብዙ አውቃለሁ ማለትም የባዶነት ምልክት ነው ፡፡
ጥሩ ድምፅ ሲኖርህ ጥሩ እውቀት ጨምርበት ፡፡ አሊያ “ድምፅና ቁንጫ ባዶ ቤት ይወዳል” እያሉ ይሰድቡሃል ፡፡ ሌላውን የማያስተምር እውቀት የጋን ውስጥ መብራት ነው ፡፡ የተዳፈነ እሳት አይሞቅም ፣ ያልተገለጠ ፍቅርም አያስደስትም ፡፡ መብትህን ሳታውቀው ከመልቀቅ አውቀህ መልቀቅ ጠቢብነት ነው ፡፡ ለባለጌ ከሮጡለት ፣ ለውሻ ከደነገጡለት አይሆንም ፡፡ ያለ ምክንያት አትቆጣ ፡፡ ካንተ ቢያንሱም ልጆችህንና ሠራተኞችህን አታሸብር፡፡ አምላካቸው ያዝንብሃል ፡፡ ዋጋ በማይሰጡ ሰዎች ፊት ደግነት ፍርሃት ነው፡፡ ተቀብሎ የማያመሰግን ሰውን አስተምረው ፡፡ በዘመኑ ድሀ ይሆናልና ፡፡ ሰው መቼ እንደሚወድቅ ማወቅ ከፈለግህ ቀላል ነው ፡፡ ትዕቢት የውድቀት ዋዜማ ነው ፡፡ ሁሉን ልያዝ የሚል ሁሉን ያጣል ፡፡ ማሊያ እየለወጠ የሚጫወት መክኖ የሚቀር ነው ፡፡ በራሱ ከፍ ያለ የወደቀ ቀን ትንሣኤ የለውም ፡፡ እግዚአብሔር ያነሣው ቢገፉት ተመልሶ ይቆማል ፡፡ እግዚአብሔር ከሾመው ጋር መታገል ከእግዚአብሔር ጋር መታገል ነው ፡፡
ወሰን ሳትሰጠው ወሰን አላወቀም ብለህ አትውቀሰው ፡፡ እንዲወዱህ ብለህ አትጎዝጎዝ ፣ እንዲያከብሩህ ብለህ አትበጥ ፡፡ የሰው ፍቅር ከሞት አያድንም ፣ ክብሩም ከንቱ ነው ፡፡ ችሎ የቀረብህን ሳይችል ከቀረው ጋር አትደምረው ፡፡ ምክንያቱን ሳትሰማ ማንንም አትውቀስ ፡፡ በወዳጅህ ቅር ካለህ መጀመሪያ ሰላም በለው ፡፡ ለመወቃቀስም መኖር ያስፈልጋልና ፡፡ ቀጥሎ ምክንያቱን ጠይቀው ፡፡ ግምትህ ሊያሳስትህ ይችላልና ፡፡ በመጨረሻ እውነተኛ ሁኖ ካገኘኸው ቅሬታህን ግለጠው ፡፡ ያሰቡት ሁሉ አይወራም ፡፡ ግምትም ከአደጋ ይጥላል ፡፡ ክፉ ልብ ይዘህ ከሰው ጋር እንጀራ አትቁረስ ፡፡ አብሮ መብላት አብሮ የመቁረብ ያህል ነውና ፡፡ ሥራህን በብልሃት እንጂ በጉልበት አትሥራው ፡፡ ይህ ዓለም ከጉልበት ይልቅ ለዘዴ የተሠራ ዓለም ነውና ፡፡ ሃይማኖት በመጀመሪያ ነጻነትን ማወቅና ማክበር አለበት ፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር የነጻነት አምላክ ነውና ፡፡ በሚያሰለች ስብከት ሰውን ዕረፍት አትንሣ ፡፡ ድኛለሁ እያልህ ከምታወራ ድነህ አሳይ ፡፡ ብዙ ስለ ራሳቸው የሚያወሩ ምንም ያልሠሩ ናቸው ፡፡ ደጋግ ነገሥታት ነጻነትን አይሰጡም ፣ ያስመልሳሉ እንጂ ፡፡ ነጻነት በተፈጥሮ ለሰው የተሰጠ ገንዘቡ ነውና ፡፡ የሰውን ነጻነት መግፈፍ እግዚአብሔርን ማዋረድ ነው ፡፡ በምድር ያሉ ነገሥታት በቅዱስ መጽሐፍ አራዊት የሚል ስያሜ ተሰጥቷዋል ፡፡ ንጉሥ ሁኖ በግ የተባለው የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ብቻ ነው ፡፡
የምግብ ለነገ ይጠቅማል ፣ የሥራ ለነገ አይጠቅምም ፡፡ ብዙ ከሠራህ ብዙ ትወገራለህ ፡፡ ካልሠራህ ትወደሳለህ ፡፡ ምክንያቱም ሰነፎች ይጽኑብሃልና ፡፡ የተቀመጡ ሰዎች የቆሙ ሰዎችን አይወዱም ፡፡
ይቅርታ የማያውቅ ሕዝብ አይከብርም ፡፡ በዘመኔ እንስሳ ተቀይመው ላም ያሳረዱ ፣ ውሻ ያስገደሉ አውቃለሁ ፡፡ ቂማችን እስከ መቃብር ነው ፡፡ ከሰው አልፈን እንስሳ የምንቀየም ነን ፡፡ ራሳችንን ደግሞ እንደ እኛ ይቅር የሚል ሕዝብ የለም ፡፡ አንተ ግን ይቅርታ እንዲሰጥህ ለምን ፡፡ ይቅር ማለት ሲያቅትህ ያስቀየሙህን ሰዎች ስም ጠርተህ ጸልይላቸው ፡፡ እግዚአብሔር ልብህን ጥሩ ውኃ ሲረጭበት ታያለህ ፡፡ መልካም ምክር ከእግዚአብሔር ነው፡፡ ሰው የሞተው መልካም ምክርን የናቀ ቀን ነው ፡፡ “ለእኔ መልካም ያደረጉትን አትርሳ” ብለህ ጸልይ ፡፡ እግዚአብሔር ዘመንህን ይባርክ !!
የደስታ ቋጠሮ /19/
ሐምሌ 23/2010 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ