መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ለእኔ ነው ! ?

የትምህርቱ ርዕስ | ለእኔ ነው ! ?

እህል በማይበቅልበት በረሃ፣ ማብሰያ በሌለበት ምድረ በዳ፣ እንኳን ሊኖሩበት ለማቋረጥ በሚያሳስበው ቆላ የበሰለ ምግብ ያቀረብከው ለእኔ ነው !? አንተ የመናው ባለበት፣ አንተ የፍጥረት ጌታ እኔን ስታገለግለኝ ክብርህን አላሰብህም ወይ? አድጓል ብለው ወላጆች ሸኝተውኛል፣ አውቋል ብለው መምህራን መልቀቂያ ሰጥተውኛል፣ አሁን እኛ ጋ አይሠራም ብለው የቀድሞ መሥሪያ ቤቴ የማጠናቀቂያ ደብዳቤ አስጨብጠውኛል። የእስራኤል አምላክ አድጓል ብለህ ያልተውከኝ አባት እናቴ፣ ተምሮ ጨርሷል ብለህ ያልመረቅኸኝ የዘላለም መምህሬ ፣ “የቀድሞ አገልጋዬ ነው” ብለህ በነበር ያልጻፍከኝ ጌታዬ አንተ ነህ።

ለአባት አባትነትን በጸጋ ትሰጣለህ፣ እውነተኛውና የዘላለም አባት ግን አንተ ነህ። አገልግሎት ጡረታ የለውም ብለህ እስከ ሞት ታሰማራለህ። አገልጋይ በሰማዕትነት እንጂ ምርኩዝ በመያዝ ከጥሪው አይሰናበትም። ባዘቀዘቀ ጀምበር ትሠራለህ፣ ለዚህም ጻድቁ  አብርሃም እኔ አለሁ ብሎ ይመሰክራል፣ በሬሳ መካከልም በሕይወት ታኖራለህ፣ ኖኅ ምስክር ነኝ ይላል። ታውቀህ አትፈጸምምና ተምሮ የሚመረቅ ባንተ ዘንድ የለም።

ለእኔ ነው ጌታዬ ደረቁን ምድር ያለመለምከው ? ሸለቆውን በውኃ የሞላኸው ለእኔ ነው ? ከገዳዩ ጣፋጭ ማርን፣ ከሰባሪው መኖሪያን የሰጠኸው ፣ ጨለማውን ብርሃን፣ ሌሊቱን ቀን፣ ውድቅቱን ቀትር ያደረግኸው ለእኔ ነው ? አውሬን ለማዳ ፣ ሽፍታን ባሕታዊ፣ ጨካኝን እናት ያደረግኸው ለእኔ ነው ? ቁመናዬን ስጠራጠረው ፣ እንኳን ርቦኝ ጠግቤ ስፈራ ፣ ዛሬን ስላጣጥም ነገን ሰስጋ እኔ አለሁ ያልከኝ እኔን ነው ? እጄ ሲነጥፍ፣ ጓዳዬ ሲጎድል ፣ ገበያን ስፈራ፣ ይህ ምን ይሆናል ? ብዬ በደመወዜ ስጨነቅ በረከትህን የላከው ለእኔ ነው ? በደኅናው ቀን የራበው፣ በክፉ ቀን እንዴት ይብስበት ይሆን ? አንተ ግን የክፉ ቀን ወዳጅ ሆንከኝ ፣ በምችልበት ጊዜ ያላገኘሁትን በማልችልበት ዘመን ሰጠኸኝ፣ ጉልበት የከዳኝን ደገፍከኝ፣ ታዲያ ይህ ሁሉ ለእኔ ነው ?

ሳልዋሸ እናገራለሁ ፣ ራሴን ያለ ማቋረጥ በፊትህ እወቅሳለሁ፣ ስላሳለፍኳቸው ዕድሎች እቆጫለሁ፣ ትላንት ዛሬ ላይሆን ምን ዋጋ አለው  እላለሁ ፤ አንተ ግን ሁሉም በእጄ ነው፣ እንደ ቆመ ሰዓት ጊዜን የምሞላው እኔ ነኝ ትለኛለህ። ብዙ አጥፍቶ፣ በዕድሉ ቀልዶ ለመጣ ሰው፣ ምክርን ንቆ ሃይማኖትን አቃሎ ለተመለሰ ሰው ይህ ሁሉ እንክብካቤ የጸጋህ ብዛት ነው። በእውነት ራሴንና አንተን ፣ ግብሬንና ግብርህን ባሰብሁ ጊዜ ይህ ሁሉ ለእኔ ነው ? እላለሁ።

ሳጣ ብዙ እንጉርጉሮ አለኝ፣ ሳገኝ ምስጋናዬ ትንሽ ነው። እንደ ብቸኛ ልጅህ ቆጥረህ ሁሉን ታወርሰኛለህ፣ ያላስቀመጥኩትን አምጣ ስልህ ደስ ብሎህ ትሰጠኛለህ። አባትና እናትም ይሰለቻል፣ ለራሴ ለማድረግም እኔው እሰስታለሁ፣ ያንተን ግን በገፍ ስወስድ ከእኔ ይልቅ የእኔ መስሎ ይሰማኛል። ምነው አይቼህ በጠገብኩህ፣ ምነው እንደ ወዳጄ በሳምኩህ! ምነው ሮጬ በተጠመጠምኩብህ፣ አለቅህም ብዬ ምነው በተጣበኩህ !

ይህ ሁሉ ለእኔ ነው ? ፀሐይን የምታበራው ፣ ጨረቃን የምታወጣው፣ በጋ ክረምትን የምታፈራርቀው፣ አድሮ ለመገኘት የምበቃው ይህ ሁሉ ለእኔ ነው ? ጌታ ሆይ ኧረ አይገባኝም፣ ተወዉ እንዳልልህ አልኖርም፣ ልቀቀኝ እንዳልልህ መጨረሻዬ ገደል ነው። የምኖረው ጠላት ስለ ሌለ አይደለም፣ ባንተ ጥበቃ ነው። የምበላው ቀማኛ ስለሌለ አይደለም፣ ባንተ መግቦት ነው። የማገለግለው ስላልደከምኩ አይደለም፣ በሰባራ ገል ስለምትጠቀም ነው። እባክህ ሰው አይስማና አገርህ የት ነው ? አሁን ብመጣ የማገኝህን ቦታ ንገረኝ፣ ሰው እንዳያስቸግርህ ተደብቄ እመጣለሁ። የልቤን እንፍዋሎት አንተ ጋ አወጣዋለሁ። አንተም እንደ እኔ ቅን ሰው፣ ጤነኛ አገር ናፍቆህ ይሆን ? አንተስ እንደገና መፍጠር ትችላለህ። እኔ ግን ክፉ ሆኜ ደግ ዘመንን እናፍቃለሁ። የቤቴ ቆሻሻ በክሎት ከተማው ንጹሕ አይደለም እላለሁ።

መቼም ዋጋ ይመልሳል ብለህ እንዳላደረግህልኝ አውቃለሁ። አምጣስ ብባል ምን እሰጣለሁ። በዚህ ሁሉ መጠላትና መገፋት፣ በዚህ ሁሉ ዘመነ ጦጣ የምኖረው ባንተ ቸርነት ነው። ሃይማኖት የሌላቸው የሃይማኖት መስፈርት በሚያወጡበት ፣ አንተን እንወድሃለን እያሉ እናትህን በሚጠሉበት፣ ተፈታኞች ተፈትነው ያለፉትን ቅዱሳን በሚሳደቡበት ዘመን መኖር ከባድ ነው። ዛሬም በቤትህ ያለሁት ባንተ ቸርነት ነው። መሸ ብለህ ደጅህን አልዘጋኸውም፣ ስንቱ ሰብሳቢ ያጣ ይጠለልብሃል።

እስክመጣ እንዳትሰለቸኝ ፣ ሞቅ በረድ ነኝና እንዳትንቀኝ አደራ እልሃለሁ። ራሴን እፈራዋለሁ ከራሴ አድነኝ እልሃለሁ !

ይህ ሁሉ ለእኔ ነው!?

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 16 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ