የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ለይኩን ለይኩን

 ድንጋይ ሳትወቅር ዓለማትን የሠራህ ፣ ወርቅ ሳታቀልጥ ሁሉን ያስጌጥህ ፣ አጋዥ ሳትሻ ሁሉን የፈጸምህ ፣ አማካሪ ሳትፈልግ ሁሉን በጥበብ ያከናወንህ እግዚአብሔር ሆይ ላሠራርህ እንከን ፣ ለግዛትህ ወሰን የለብህምና አንተን እናመሰግናለን ። ፊተኞች አሉኝ ብለህ የኋለኞችን የማትንቅ ፣ አርፍደው መጡ ብለህ በርህን የማትቆልፍ ፣ በጎነታቸው አነሰ ብለህ ገሸሽ የማትል ፣ ኃጢአታቸው በዛ ብለህ የማትጠየፍ የጎስቋሎች ወዳጅ ነህና ምስጋና ይገባሃል ። ከራሱ ለሚሸሸው መጠጊያ ፣ በወኅኒ ላለው በር ከፍተህ የምታወጣ ፣ በስደት ያለውን ለአገሩ የምታበቃ ፣ እናቱ የጨከነችበትን ራርተህ የምታፈቅር አንተ ነህ ። ወዴት ልሂድ ? ለሚል መድረሻው ፣ ምን ልሥራ ? ለሚል ብልሃቱ ፣ ማን አለኝ ? ለሚል አለኝታው አንተ ነህ ። ፍቅሩን ለሚያመልከው ሰው ፍቅሩን የሚያስንቅ ፍቅር ታሳየዋለህ ። ልቡ ደንዳና የሆነውን በመውደድህ ታቀልጠዋለህ ። በእውነት እኛን የተቀበለች እጅህ ትባረክ ።
እንኳን መከራ ብሥራትም የሚያስደነግጠን ደካማ ልጆችህ ነንና አቤቱ ለእኛ ራራ ። ትላንት የተሸከመችን እጅህ ዛሬም ያለ መዛል ትሸከመን ። ዝቅተኞች ብንሆንም ልዑልነትህ ከፍ ያድርገን ። በአስተሳስብ ብንወድቅም በዘላለም ምክርህ አክብረን ። የያዝነውን እየለቀቅን ፣ የለቀቅነውን ብንፈልግም የሚሻለውን ምረጥልን ። ወጥተን ለመግባት ድፍረት ቢያጥረንም በዓይኖችህ ተመልከተን ። ቢያንስብህም ምስጋናችንን ተቀበለው ። አሜን ወአሜን ፣ ለይኩን ለይኩን ፣ ይሁን ለይሁን ።
የነግህ ምስጋና /4
የካቲት 18 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ